Saturday, 06 September 2014 11:48

የግጥማችን ችቦ - በበለው ግጥሞች!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(3 votes)

       ጥበብ የጠማው ከንፈር፣ ውበትና እውነት ካረገዘ ሰማይ ስር ተደቅኖ፣ በምኞት ቢባትት ችሎት የሚያቆመው፣ በሀሜት የሚዠልጠው ጨካኝ ያለ አይመሥለኝም፡፡ ሰው በእንጀራ ብቻ እንዳይኖር እግዜር የጥበብ ቋት ውስጡ ሸጉጦ እየጠገበ ይራባል? ምናልባት አንዱን ሆድ ብቻ ከፍቶ መኖር የተጣባው ካልሆነ በቀር፡፡
እኛም ከሀገራችን ሰማይ ሥር ጥበብ እንዲያብብ፣ ጠቢባን ችቦዋቸው እንዲደምቅ፣ በየራሳችን ድምፅ ስንጮህ የዕድሜያችን ቀለም እየቀየረ፣ የነፍሳችን አታሞ እየሳሳ መሄዱን አንዘነጋም፡፡ ይሁን እንጂ የመጥምቁ ዮሐንስን አይነት የምድረ በዳ ድምፅ አይደለም ድምፃችን ፡፡ የቁራ ጨኸት ሆኖም አይቀርም! እመኑኝ የዘራነውን እናጭዳለን፡፡ ምንም እንኳ ከባህላችን ጠማማ ክንፎች አንዱ ተመሳስሎ ማመሳሰል ቢሆንም፣ ይህንን ኬላ ጥሰን ለመሮጥ የሞከርን ሁሉ ደም ያረገዘው ጉዟችን ዳና፣ እንደ አመድ ተበትኖ አይቀርም፡፡ እምባ ያረገዙ ዓይኖቻችን ሳቅ የሚጠግቡበት ቀን ሳይመጣ አይመሽም፡፡
በሀገራችን ሥነ - ፅሑፍ የቅርብ ጊዜ ጉዞ የግጥሞቻችን ያለ ልክ መጉረፍና ግልብ መሆን ቢያናድድም፣ እነዚህ ግልብ ያልናቸው ግጥሞች ያመጡልን አዳዲስ አንባቢ አለ፡፡ አደባባዮቻችን ለግጥም ፌሽታ መኳል መጀመራቸውም አንድ እመርታ ነውና አንዱን ወገን ይዘን መሄድና ማሻሻል እንችላለን፡፡
አሁን አሁን ግን የግጥሙ ሕትመት ቁጥርና ጥራት ያለመመጣጠን እንጂ በቅጡ ካስተዋልነው፣ ከኋላዎቹ የገጣሚያን ቁጥርና የግጥም ልቀት እግር የሚለካኩ የዘመናችን ገጣሚያን እንዳሉ የምንገነዘብ ይመስለኛል፡፡ የዛሬዎቹ ገጣሚያን ሁሉ ቀሽም አይደሉም፤ እንደ አክሱም ሀውልት ቀና ብለን የምናያቸው ግጥሞች የሚጽፉ ከያኒን ብቅ እያሉ ነው፡፡ ለጊዜው በቁጥርና በስም መጥቀስ ባያሻንም፤ ሁለቱንም ዘመን ፊት ለፊት አስቀምጠን የምናይበት ቀን ሩቅ አይደለም፡፡ ፈጣሪ የጥበብ እግሮቻችን በእንጀራ ሽባ እንዳይሆኑ ብቻ ይጠብቅልን፡፡
 በዚህ ዘመን ተስፋ አላቸው የምላቸው ገጣሚያን ቁጥር ብዙም ባይባል፣ የነፍስ ንዝረት ከሚፈጥሩት ውስጥ ገጣሚ በለው ገበየሁ አንዱ ነው፡፡ ሁለት የግጥም መፃሕፍት አሉት፡፡ ግጥሞቹም የኛን ዘመን አጫጭርና የቀደመውን ዘመን ረጃጅም ግጥሞች ጠቅሏል፡፡ እንደ ዲክንሰን በአጫጭር ስንኞች፣ እንደነ ዋልት ዊትማን በረጅም እግሮች መሄድም ይችላል፡፡ ረጃጅም ግጥሞቹ፤ አስደናቂ ሃሳብና ቋንቋ፣ ጥልቅ ምናብ የሚታይባቸው ናቸው፡፡ ጥቂት ቢሆኑም የዶክተር በድሉ ግጥሞች ውስጥ የሚታየው ዓይነት  ብርታት አላቸው፡፡ ይህንን የምለው ታላቁ የሥነ ግጥም መምህር “In making judgments on literature, always be honest” ያሉትን መርህ መሰረት አድርጌ ነው፡፡ ፔረኔ እንዳሉት፤ “Don’t pretend to like what you really do not like! Don’t be afraid to admit a liking for what you do like.” መፍራትም ማስመሰልም ለጥበብ ቤትና ህይወት እንቅፋት ነውና ራሴን ሆኜ  አያለሁ፡፡
አንዳንዴ በሥነ ጸሑፉም ዓለም ሆነ በሌላኛው ሌጣ ዓለም በጊዜ መተራረም፣ በጊዜ መተያየት መልካም ይመስለኛል፡፡ በለው ገበየሁ “ከሰው በላይ ቅኔ” በሚለው የግጥም መጽሐፉ “የዘገየ እርማት” በሚል ርዕስ እንዲህ ይለናል፡-
የተከልኩት ቀርካ ረዝሞ
ከግቢዬ መሐል ቆሞ
ለከርሞ ጌጥ ያኔ ባጨው
አልሆነ ላይ ጎኑ ጠሞ፤
እንጭጭነት ላዩ ቃግሞ
በለጋነት ጦዞ ዘሞ፤
ወይ የክብር ሳላቀናው ያኔውኑ አስቀድሜ
ጊዜ ስቸር ስመፀውት በመታከት ከራርሜ
ለጋነቱ ነጥፎ ኑሮ ላቃናው ብል ድንገት ዛሬ
ለካ ደረቅ አይታጠፍ አረፍኩታ ሰባብሬ፡፡
በቀርከሀ ተክል የመሰለው የገጣሚው እርማት ተምሳሌት፣ በሰው ልጅ ሁለንተና ውስጥ ተመሳሳይ መልክ አለው፡፡ ዛፍ በልጅነቱ ባይገረዝ፣ ሲያድግ እንደሚያስቸግር፤ በልጅነቱ ቁመናው ባይቃና ለማገዶ እንጂ ለኢንዱስትሪ ወግ እንደማይበቃ ሁሉ የኛም የአዳማዊያን ስህተት በጊዜ ቢታረም፣ ጊዜው ካለፈ በኋላ ተሰባብረን፤ አረቄ መለኪያ ስር እንዳንወዘት ያግዘናል፡፡ እንዲያ ቢሆን ቀዳዳችንን ለመድፈን፣ ስብራታችንን ለመጠገን ሌላ መርፌ መወጋት አያስፈልገንም ነበር፡፡ ገጣሚውም ለነፍሳችን ጆሮ በዜማ ቀምሞ ሹክ የሚላት እውነት ይህችው ናት፡፡
ገጣሚው ከዚህ ቀደም ባነበብኩት መጽሐፉም እንዳየሁት፤ በግጥሞቹ ወደ ውስጣችን ሲመጣ በዱልዱም ቃላት ልባችንን እያናጋና በራችንን እየደበደበ አይደለም፤ ይልቅስ ላውረንስ፤ “Poetry appeals directly to our senses, of course, through its music and rhythm” እንደሚሉት ነው፡፡ በተለይ ድምፅ ከፍ ተደርገው ሲነበቡ፣ … ከሁሉ ይልቅ ደግሞ የእይታ ምናብ በግጥም ውስጥ በአብዛኛው ተከሳች ነው፡፡
“አንደማመጥም” የምትለው የበለው ገበየሁ ግጥም ያዘለችው ቁም ነገር ጤዛ አለ፣ ከርመኖ ላይ ያንጠለጠለችው ጌጥ፡፡
ሀሰት ተኮላሽቶ - ሀቅ እንዳይፈረጥም
የመለወጥ ማጡ - ድጡ እንዳያሰጥም
ሁላችን ተቃጥለን - በወሬ ውሀ ጥም፣
በ’ኛነት አንቀልባ -
ታዝለን ዙሪያ ጥምጥም …
እንናገራለን … አንደማመጥም!፡፡
ይህች ግጥም የኛ ባህል በብሩሽ የቀባት የማንነታችን ሥዕል ትመስለኛለች፡፡ እውነትም ሆነ ውሸት፣ እኛ ያልነው ካልሆነ የሚል ህመም የመጣብን ከጥንት ነው፡፡ ለመላቀቅ ባለመሞከራችን ዙፋኑን ተክሎ፣ ዘውዱን ጭኖ ሰልጥኖብናል፡፡ የራሳችንን ማውራት እንጂ የሌሎችን ባለማድመጣችን፣ ልናሻሽላቸው ይገቡን የነበሩ ነገሮችን በግትርነት ታቅፈን ወደ መቃብር መውረድ እንመርጣለን፡፡ ገጣሚው የሚወቅሰን በዚህ ነው፡፡
ብዙ ጊዜ ስለጥበብ ገጣሚያንና ደራሲያን የሚሉት ነገር አለ፡፡ ወይ ቀና ወይ በብሶት የታመቀ ልቅሶና ምሬት፡፡ ገጣሚ በለው ገበየሁም በመጀመሪያ ገፁ “ከጥበብ ሲጋቡ” ብሎ ስንኞች ቋጥሯል፤ እንዲህ፡-
የኮሚቴ አሞሌ - በቀለሟ ድምቀት
እየተሞሸረ፡-
እንቅልቅል እሳቴ - በወራጅ ውሃዋ እየተገሸረ
ቁርኝት ክራችን - ፈትሉ እየከረረ…
የምናቤ - ፍሬ - በኪን ማህፀኗ                 እየተወሸቀ፣
የኔ - ኩሬ ሲነጥፍ - ምንጩ እየፈለቀ፣
የኔ - አበባ ሲረግፍ - ዘሩ እየፀደቀ
(…እንዲህ ነው ድባቡ…
በጥበብ ክህነት፤ በቀለም ቀለበት …ከጥበብ ሲጋቡ…)
የኔ አካል - ቢጫጭም…
    ከሷ የወለድኳቸው ልጆች እየሰቡ፣
ምላሴ ሲታሰር - በፍት ልሣናቸው እያነበነቡ፣
ህይወት ስኮበልል፣ ወደ ሕይወት ስርፀት፣
ዘልቀው እየገቡ…
(…እንዲህ ነው ድባቡ፤
በቀለም ቀለበት ከጥበብ ሲጋቡ…
ይሄ ነው ሚስጥሩ፤
ቀለም ተሞሽረው - ለጥበብ ሲዳሩ…)
ጥበብና ከያኒው በፍቅር አብደዋል፤ ቁርኝት ክራቸው፣ ፈትሉ ከርሯል፡፡ የምናቡ ፍሬ - ማህፀንዋ ውስጥ ገብቶ፣ ተፀንሷል፤ ግና የከያኒው ኩሬ ሲነጥፍ የኪነት ምንጭ እየፈለቀ ነው፡፡ እያኘከችው ታፈራለች፤ እያጠወለገችው ታብባለች፡፡ የከያኒው አካል ጫጭቶ፣ ከርሷ የወለዳቸው ልጆች ሰብተዋል፡፡ እርሱ መናገር ተስኖታል፡፡
ኪነት ግን በፍትህ ምላሥዋ ታነበንባለች፡፡ እንግዲህ ከያኒና ኪነት ትዳርና ጐጆዋቸው ይህ ነው እያለ ነው ገጣሚው፡፡ መልካችን ዥንጉርጉር ነው፤ ደሜን ሰጥቻት ደመግቡ ሆና አደባባይ ትታያለች - እያለ ነው!!...እንደጧፍ ነድዶ ብርሃን መስጠት እንደሚሉት ዓይነት ነው መሠል!
የመጽሐፉን ርዕስ የያዘው “ከሰው በላይ ቅኔ” የሚለው ግጥሙን - በወፍ በረር ቃኘት ማድረግ ቢያሻኝ ትንሽ እናየው ዘንድ ወድጃለሁ፡፡ ለነገሩ የዘርፉ ጠቢባን በተለይም ሂሊየር እንደሚሉት፤ ግጥም በመመላለስ ንባብ ብዙ መልኮችና ውበቶች ያወጣል፡፡
የ “ፊት ሬት - ታጅሎ
“ማር ልጥ የታሠረ
ልብ ተራራ - ላይ፤
የተቆረቆረ…
የተመነደረ…
ሰው የቅኔ ሀገር ነው፤ የቅኔ ከተማ
ሰም ሲሆን ብርሃን - ወርቅ ሲያይ ጨለማ
ላዩ ስልጣኔ
ውስጡ ስይጣኔ…
አፈ ፍቅሩ ቁንጣን፣ ልበ ፍቅሩ ጠኔ -
ከሰው በላይ ሚስጥር ከሰው በላይ ቅኔ …
መቶ ጊዜ የለም!”
“የለም!” ባይ ነኝ እኔ፡፡
ግጥሙ አንዳች ምሬት፤ አንዳች ቁጣ - በውስጡ የያዘ ፍምነት አለው፡፡ ሰውን በሬት ውስጥ የተቦካ፣ ትንሽ ማር የላሰ፣ ልብ ቁንጮ ላይ የተፈናጠጠ፣ መልኩ የማይታወቅ፣ ወይም ፍልቀቃ የሚያሻ ከተማ አድርጐታል፡፡ በሰምና ወርቅ፣ በብርሃንና ጨለማ የመልኩን ዥንጉርጉርነት ፍተሻ ናፍቆት አርቆታል፡፡ ሥውር ድንበሩን  ኮንኖታል፡፡
አፈ-ፍቅሩ ቁንጣን፤ ልበ - ፍቅሩ ጠኔ - በማለት በልቡና በከንፈሩ መካከል የቆመውን ተራራ ቀና ብለን እንድናስብ አስገድዶናል፡፡ በተለይ ያለንበትን ዘመን የግለኝነት ሕይወት ለማንፀባረቅ የሞከረ ይመስላል፡፡ ስለዚህም የሆሄያትን ጡብ፤ የሀረጋትን ሰንሰለት፣ የአረፍተ ስንኞችን ውህደት ቅኔ አትበሉ፤ ይልቅስ ከዚያ የባሰ ሰምና ወርቅ አለላችሁ ነው የሚለን!

Read 3497 times