Monday, 22 September 2014 13:50

ሁለተኛዉ

Written by  ሂሳዊ ንባብ -አብደላ ዕዝራ
Rate this item
(0 votes)

ለምን ትጽፋለህ ? የሚሉኝ አሉ
ስለሚያመኝ ነዉ።
የምጽፈዉም ሲያመኝ ነዉ።
ሲያመኝ ነጩ ወረቀት ላይ ራሴን አክማለሁ
ነጭ ወረቀት ጤና-አዳም ነዉ
ነጭ ወረቀት ዳማ-ከሴ ነዉ።
ነቢይ መኮንን
(ቁጥር ሁለት ስዉር-ስፌት)

በነቢይ ግጥሞች የሚመሰጥ አንባቢ ለኅላዌ ህመም ፈዉሱ፥ ምሱ ቅኔ መበተን መሆኑ ያስደምመዋል። ባህላዊ
ሀገራዊ ጤና-አዳም በወተት በቡና መነከሩ ቀርቶ በግጥም ሲጨመቅና ዳማ-ከሴ ቅጠሉን ሲያሹት ቀይ የመሰለዉ
ፈሳሽ ቅኔ ሆኖ ሲጠል የቃሉ ዜማ ጭምር ጣዕም አግቷል። የገጣሚዉ ህመም አካላዊ ሳይሆን ሥነዉበታዊና
ህይወታዊ መብሰክሰክ ነዉ። ግለሰብ ብቸኝነት፥ እጦት ሆነ ጥጋብ ሲያዋክበዉ፥ ወንድ ለእንስት ሲስገበገብ፥ ሴት
የኑሮ መዳፍ ሲቆረፍዳት ... ሰዉ ሲፈካ ሲጠወልግም “ጊዜም ቀን ይጐድልበታል” ብሎም “አንዱ ያንዱን ጫፍ
ሲጐመጅ” እየተጤነ እንዴት አለመታመም ይቻላል ? በየዕለቱ እየኖርነዉ ለምደነዉ የፈዘዘብን ክስተት ሆነ
ትዕይንት ነቢይን ይኮሰኩሰዋል። ግጥሞቹ አንዳንዴ ጠብታ ቃል፥ ኮሽታ እንቅስቃሴ እየቆሰቆሳቸዉ፣
ከአስተዉሎት ከኑሮ ብዙ ብዙ ይቀጣጠላል። ለመግለጥ ቢያዳግትም አንድ ረጅም ግጥሙን ያሟሸበት ሁለት
ስንኝ ዘግነን አብረን ስዉር-ስፌቱን እንበርብረዉ።

አገር የሌለዉ ህዝብ፥ ህዝብ የሌለዉ አገር
ዕንቅቡም አይሞላ፥ ወንዝም አያሻግር

ነቢይ የሆነ ትዕይንት ካደናቀፈዉ፥ የሰዉ ሁኔታ ከጓጐጠዉ፥ ጊዜ እየተንቀረፈፈ ችክ ሲልበት በአንድ ነጠላ ጉዳይ
ሣይሆን የኖረዉ፥ ያነበበዉ፥ <የታመመበት> እየደፈረሰበት እሚዋከብ ይመስለኛል። ይህ ዉስጣዊ ግርግር ሰበቡ
የአያሌ ስብጥሮች ወረራ ነዉ። አገር-ህዝብ ሲል እንደ ዜና ሳይሆን ለተለየ ህሊናዉ ለሚነዝር ትስስር እንጂ።
ምናልባት “ዕንቅብ” ሲያፈተልክበት ከግራምጣ የተበጀ ጐድጓዳና ሰፊ የእህል መስፈሪያ ተረቱንም ይጠራል።
“በዕንቅብ ያሰጣ፥ በሰፌድም ያሰጣ /እኩል ቀን ወጣ” አሻሚነቱ ያዉካል። ወንዝስ ? የሚፈስ ወራጅ ዉሃ ወይስ
ሌላ ያባብሳል ? አለማየሁ ገላጋይ በአንድ ልቦለዱ ከግንፊሌና ቀበና ወንዝ እየቀዘፈ እየዋኘ ያደገን ህፃን እሞጆ
ያሸሸዋል። ኒኮላ የተባለ ጣሊያን የዉሃ ወፍጮ የተከለበት ሥፍራ “ኒኮላ ወንዝ” ተባለ። ህፃኑ በዚህ ወንዝ
ለመንጨቧረቀ ይጓጓል። ቅኔ በሚመጥን ዘይቤ ደራሲዉ “ኒኮላ ወንዝ ዉሃዉን ከየቤቱ በጣሳ የተበደረዉ
ይመስላል” ሲል ወንዝ-አልባዉ ወንዝ ይነካካል። ህዝባዊ ተረትና ምሳሌ ለደራሽ ወንዝ ካደፈጠበት ያፈተልካል።
“ጌታዋን የምታምን ዉሻ ፍሪዳ ሲታረድ ወንዝ ወረደች” ይህ የሰባ የእርድ ከብት ከእምነት አይበልጥም። ወንዝ
እማያሻግር አገር፥ ወንዝ እማያሻግር ህዝብ፥ ዉሻ የታማኝ ሰዉ አለኝታ ሳይነፈግ ጀማዉ ጉድ ሊሆን ? እንግዲህ
ነቢይ ሽራፊ ክስተት ከቧጨረዉ በእንደነዚህ ብዙ ጨረሮች ይወረራል። ብሎም በግሪኮች ሥነተረት ሰዎች
እንደሞቱ የሚነከሩበት ወንዝ አለ፤ ምድራዊ ትዉስታቸዉን እንዲዘነጉ እንደ ጠበል ዉሃዉን ይጠጣሉ።
የሚሰቅቀዉ፥ ነፍስ ሌጣዋን ብትላላጥም የቀዬዋን ትዝታ ለመርሳት በጀ ሳትል በሆነ ልክፍት ትነዝራለች። የነቢይ
በዕዉነታ የተጣደ ሆነ ገሐድ-ዘለል ግጥሞቹን የሚያነብ “የምፅፈዉ...ስለሚያመኝ ነዉ” ሲል ካነበበዉ፥ ከኑሮዉ፥
ከአጤነዉ... በተናደ እሳቦትና ምስሎች መወረሩ ያስጨንቃል። “አገር የሌለዉ ህዝብ”በሌላ ግጥም መች ያለ አገር
ተወሰነ ?

አገሬን አገሬ እምላት
“በል በሩን መለስ አድርገዉ
አባትህ አልገባም አደል ?
ዉሃዉ አልተዘጋም እየዉ፤
ወንድምክን አንዳፍታ እቀፈዉ”፤
ያለች ዕለት ... ልክ እንደ እናት [ገፅ 64 ]
በኑሮ ወከባ እንደ የለሆሳስ ድምፅ የሰለለ የእናት ጭንቀት አገርን ወጥሮ ለመሞገት ጉልበት አለዉ - የገጣሚዉ
ምናብ አደንድኖታል።
ስዉር-ስፌት ቁ.2 የተመረቀዉ ገና ትናንት ስለሆነ በጥሞና ተላልጦ ቢነበብ የተደራሲን ጣዕመ-ፍሰት አንድም
መበረዝ፥ አንድም መገደብ እንዳይሆን አቅማማሁ፤ ከተብላላ ከተዳረሰ በኋላ እመለስበታለሁ። እንደገና የአዲሱ
ስብስብ ርዕስ ስዉር-ስፌት መባሉ በተለይም የሽፋኑ ምስልና ቀለም ለሰባት አመታት ረግቶ መክሰሙ ከነከነኝ።
ጀርባዉ ግን የራስ ምስል በሚመጥን ስዕል እና ለገብረክርስቶስ ደስታ በተበረከተ ግጥም በመወሳሰቡ አንባቢን
ክሶታል፤ ጀርባዉ ፊት በሆነና የስብስቡ ለጋ ርዕስ እምቁ ሀረግ <ሰዉ እያለ አጠገባችን> በወረሰዉና በወረሰን
ያስመኛል። ነቢይ “ጊዜም እኮ እንደ ሰዉ ፊት / ሲያረጅ ይጨማደድና /ገፁን ማድያት ይወረዋል”እያለን ለሰባት
አመት ያረጀዉን የሽፋኑን ርዕስና ምስል ማድያቱን ለምን ቸል አለዉ ? ምናልባት ቁጥር አንድ ድጋሜ ሳይታተም
ተጋርዶ ስለተሰወረ፣ አሁንም ሽፋኑ ገና አልፈዘዘ ይሆናል ከሚል ሲሜት ሊመጣ ይችላል። ቢሆንም ቁ.2
እዉስጡ የሚርመሰመሱት ሰማንያ ያክል ግጥሞች ያዉኩናል፤ እያነበብናቸዉ እንመሰጣለን። በስብስቡ ከሞት
ጋር ግብግብ ገጥሞ “ክብር ስምን” እነሎሬት ፀጋዬን፥ እነጥላሁን ገሠሠን ... ከመንደራችን የተመለሱ
እስኪመስለን ስሲሜቱ እና ዕይታዉ -የገጣሚዉ- ያባንኑናል። የአገር፥ የህይወት፥ የጥበብ ጉዳይ፥ እንደ በኩር
ዉበት በግጥሞቹ አቧራቸዉን አራግፈዉ ሲመጡብን፣ በፍቅርም በፍርሃትም በጥርጣሬም እንሞላለን።
ለየትዉልዳችን መብሰክሰክ ብሎም ዘመን ሲለወጥ፥ በአል ከተፍ ሲል እንደ አዘቦት ቀን ሳይደበዝዝ፣ ከልባችን
ከጭንቀታችን በቋንቋ ቅኝት በሚነዝር ሀቅ ይሁን ሀሰት እንሰወራለን፤ ትዉልድንና እራሳችንን እንታዘባለን።
“የኖርኩት፥ ያየሁት፥ የሰማሁት ነገር፥ የቧጠጥኩት አድማስ / ዉቅያኖስ ነዉ ህይወት፥ ተቀድቶ አይጨረስ”
ቢለንም ነቢይ የነፃነቱን አድማስ ሳይገድብ ከገሐድ ከዕዉነታ እያፈተለከ surrealistic (ዲበዕዉነታ) (ለምሳሌ
<መጻሕፍት ቤት ተዘግቶብኝ> )ግጥሞች ብቻ ሳይሆን እየረቀቀ ወደ አስማታዊ እዉነታዊነት -magical
realism- (ለምሳሌ <ለካ ሞት ግጥም አይችልም>) ዘልቆ ይፈካል። ፀደይ ወንድሙ የስብሐት ገብረ
እግዚአብሔርን <ስምንተኛዉ ጋጋታ> ስታነብ እሷ ሕልማለማዊነት የምትለዉን በsurrealism እና በአስማታዊ
እዉነታዊነት መካከል ያለዉን “ቀጭን ልዩነት” ታብራራለች። የነቢይን ግጥሞች“... ወጣ-ያለ አስተሳሰብ ያጨቁ፥
እብደቴ በፈቀደልኝና መንፈሴ እሺ ባለኝ ጊዜ የከተብኳቸዉ ...” ያላቸዉን በጥሞና ለመረዳት የፀደይን ድንቅ
ትንታኔ ማንበብ የግድ ነዉ:: [መልክአ ስብሐት፥ ገፅ 264-278]።
ዛሬ ብዙም ልነካካዉ አልደፈርኩም እንጂ በጃዝ ግጥም ምሽቶች ለመነበብ፥ በሙዚቃ ለመታጀብ፥ በመጠኑ
ግጥም መለጠጥ ስለአለበት በነቢይ ብዕር አንዳንድ ስንኙን የመበረዝ የማላላት አዝማሚያ ተጋብቶበታል። አስር
ገፅ የፈጀዉ <እነንትና ደሞ>ሳይሰለች ሁለት-ሶስት ገፅ የወጣዉ ግጥም መወጠርን፥ ትርፍ ስንኞችን ማራገፍን
ይጠይቃሉ። እንደ <ከአሮጌ ልደታ እስከ አዲስ ልደታ>የመሰለ ግጥም። የነቢይን ችሎታ የማይመጥኑ በጣም ጥቂት
ግጥሞች አምልጠዉ ተሸሽገዋል። “ነብሰ-ጡር ጊዜ እጅግ ወሩ ገብቷል / እጅግ ሆዱ ገፍቷል”የመሰለ ምስልና
እሳቦት ከግጥሙ በመትረፉ በጀ እንጂ። በደምሳሳዉ ግን የነቢይ ግጥሞች ከሀገር ቤት ጓዳኛ እምነት በታሹ
ቅላትና ሀረጐች፥ ጣዕማቸዉ በማይቸክ ረቂቅነት ከዕዉነታም ከዲበገሐድም በተወሳሰቡና በሚያባንኑ እሳቦትና
ኪነዉበት ሰርክ ይነዝራሉ።
በጥሞና እና በዝርዝር በማንበብ -እኔም ህመሜን በሂስ ልፈወስበት- የምርበተበትላቸዉ ድንቅ ግጥሞች አሉ።
<ለካ ሞት ግጥም አይችልም>፥ <ማቲን አዉቀዋለሁ>፥ <ጫፍ ወራጅ አለ>፥ <አይሳሳም ለሬሳዉ>፥
<ዜማ-አዉራጅ... >፥ <የራስክን እሳት ሙቅ>፥ <እነንትና ደሞ>፥ <ነብሰ ጡሩ ገና>፥ <አንዲት ቢራቢሮ ሆዴ
ዉስጥ ገብታ>፥ እና <ቅቤ የተቀባችዉን ልጅ ለምን ወደድኳት ?> ። እንደ ሞቆያ -ለጊዜዉ- አንድ አጭር አሳሳቢ
ግጥሙን <ያለ እኩያ መቅረት>ን በመጠኑ አብረን እናንበብለት።
ያለ እኩያ መቅረት
ከነገሬ ሁሉ እኔን ደስ የሚለኝ -ከእኩያ መጫወት።
ይሄ ሳይሆን ቢቀር -ሌላዉ ደስ የሚለኝ፥
ከእኩያ መጣላት።
አሁን ያለዉ ግና፥ አለመታደል ነዉ -የመርገምት መርገምት፥
ሁለቱን ፈልጐ፥ ሶስት ነገር ማጣት።
የሚያፈቅሩት ሲያጡ
የሚጣሉት ሲያጡ
ራስን ቢለምኑት፥
<እኩያህን ፈልግ !> ብሎ ራስም ጥፍት !
አያድርስ እንጂ ነዉ፥
እንዲያ ያለ ረሀብ፥ የኑሮ ዉድነት
እኩያን ጨርሶ፥ ያለእኩያ መቅረት !!
[በገዛ እጃቸዉ እኩያ ላጡ] ገፅ 94
ግለሰብ አልያም ግራ የተጋባ ነፍስ ለፍቅርም ለፀብም <እኩያ> ተነፈጐ በአባዜ ተቦረቦረ፤ ባዶነት፥ ለብቻ
መቅረት፥ከጀማዉ መሸሽ ይለመዳል እንዴ? ለኛ የመጨረሻ መጠለያ፥ የክፉ ቀን ምሽግ እራሳችን ነን። በቋጠርነው
ትዝታ፥ በአስተሳሰብ፥ በእድሜ ... ከሚመጥነን (እንደ ብልህ እንደ ጅል) ጊዜን ለማባበል <እኩያ> ያስፈልገናል።
ለብቻ ከመንገዳገድ፥ ለብቻ ከመሳቅ፥ ከራስ ላለመላተም ካባሰበት ሳይሆን ከአቻ ባልንጀራ መጫወትም
መጣላትም ያምረናል። ይህ ንፍገት ባለቅኔዉን እምብዛም አልቆረቆረዉም፤ የተፈታተነዉ ከራስ ጋር ለማዉጋት
ለማበድ ህሊናችን ዉስጠታችን ፊት ነስቶን <እኩያህን ፈልግ!> ተብለን መገፍተራችን ነዉ። ባይተዋርነት እራስን
መጥላት፥ ከራስ ጋር እኩያ የአለመሆን ሥነልቦናዊ ቀዉስ ግለሰብን ያሳድደዋል። በሌላ ግጥሙ ነቢይ እንደ
ተቀኘዉ “ምን ጫፍ አለ? ምንስ ወራጅ / አንዱ ያንዱ ጫፍ ሲጐመጅ // ጫፍ ወራጁን ሲጠብቁ / የራስ
መዉረድ ጣር ነዉ ጭንቁ”ከሌላዉም ከራስም መንገዳችን ላይ “እንደ ጨፈቃ ተሳስረን” ያለ እኩያ እየተጋፋን
መኖር ሰቆቃነቱ በቀልድም በምርም ይመዘምዛል። ሰባ አመቷን የዘለለች ፖላንዳዊት ባለቅኔ - ሽምቦሪስካ -
<ቁጥር ፍለጋ ተራ ከሚጠብቁ ዜሮዎች ይልቅ ብቻቸዉን የቀሩ ነፃ ዜሮዎች እመርጣለሁ:: > ትላለች:: ዜሮና ዜሮ
መደርደር:: ነቢይ ግን ለዜሮ በተመስጦ <እኩያ>ቁጥር እያፈላለገ ነዉ::
ስዉር-ስፌትን (ቁ2.) ስናነብ ልብ ለማንለዉ ክስተት ሆነ ትዕይንት እንነቃቃለን። ስሙን የዘነጋሁት ደራሲ
እንዳለዉ፤ “Each person carries within him the soul of a poet who died young” እንደ አንባቢ
የአንድ ሟች ግጥም መንፈስ እዉስጣችን የሚፀድቀዉና ለዉበት የምንደመመዉ ነቢይ መኮንንን ለመሰሉ
ባለቅኔዎች መመሰጥ ስንችል ነዉ።

 

Read 1981 times Last modified on Monday, 22 September 2014 14:20