Saturday, 04 October 2014 14:01

‹‹.በቫይረሱ ቢያዙም... ነጻ የሆነ ልጅ መውለድ ይችላሉ

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ ruthebebo@gmail.com
Rate this item
(0 votes)

›› የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ሓል..ማ ኤችአይቪ ኤይድስ ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍ በአገር ደረጃ ከሚደረገው ጥረት ተሳታፊ በመሆኑ ከተለያዩ የግል የህክምና ተቋማት ጋር አብሮ ይሰራል፡፡
በመሆኑም በኦሮሚያ መስተዳድር አዳማ ከተማ በሚገኙ የግል የህክምና ተቋማት ያለውን አሰራር በዚህ እትም ለንባብ አቅርበነዋል፡፡ በዚያ ቆይታ ከቫይረሱ ጋር ከሚኖሩ ሕጻናት እና አዋቂዎች እንዲሁም ከህክምና ባለሙያዎች ጋር ውይይት አድርገናል፡፡
በመጀመሪያ ያገኘናት ህጻን የ13 /አመት እድሜ ያላት ናት፡፡ ‹‹...እኔ ቫይረሱ በደሜ መኖሩ የታወቀው የ8/አመት ልጅ ሆኜ ነው፡፡ ወደዚህ ሆስፒታል የምመጣው መድሀኒት ለመውሰድ ነው፡፡ በእርግጥ እና..ም ከቫይረሱ ጋር ስለምትኖር ሁልጊዜ ይዛኝ ትመጣለች፡፡ ዛሬ ግን እስዋ ስራ ስለረፈደባት በር ላይ ትታኝ ሄደች፡፡እኔ አሁን መድሀኒቱን ሲሰጡኝ ወደትምህርት ቤት እሄዳለሁ፡፡
መድሀኒቱን የምወስደው ማታ ማታ ብቻ ነው፡፡ ሌላ ሕመም እንዳይይዘኝ እራሴን እጠብቃለሁ፡፡››
ብላናለች፡፡
                                                        -------///-----
በአዳማ ጄኔራል ሆስፒታል ያገኘናት ሲስተር አዚዛ አብዱል ሰመድ የአገልግሎት አሰጣጡን በሚመለከት የሚከተለውን ብላለች፡፡
‹‹...እኔ በሙያዬ ክሊኒካል ነርስ ነኝ፡፡ የምሰራውም በእናቶች ክፍል ነው፡፡ በዚህ ሆስፒታል በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እስከ ሀምሳ የሚደርሱ እናቶች የእርግዝና ክትትል ያደርጋሉ፡፡ ከእነዚህ እናቶች መካከል ምናልባት አንድ ወይንም ሁለት የሚሆኑ እናቶች ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ቢገኝ ነው ፡፡ ለምሳሌ እስከአሁን ተመርምረው ቫይረሱ በደማቸው የተገኘ እናቶች ወደ አራት የሚሆኑ ሲሆኑ ለልጆቻቸውም..ሞመ ሰርተንላቸዋል ፡፡ የዚህም ውጤት የሚያሳየው ሁሉም ልጆች ከቫይረሱ ነጻ ሆነው የተወለዱ መሆኑን ነው፡፡ እናቶቹም ቢሆኑ ወደ ኤ አር ቲ ክፍል ተልከው ጤናቸውን ይከታተላሉ፡፡
ጥ፡ አንዲት እናት HIV POSTIVE ነሽ ስትባል ምን አይነት ስሜት ነው የምታዩት?
መ፡ በጣም ያዝናሉ ፡፡ ያለቅሳሉ ፡፡ አንዳንዴም ባለቤቶቻቸው እንዳመጡባቸው ነው የሚነግሩን፡፡
የተለያዩ ምክንያቶች ይነግሩናል ፡፡ ስሜታቸው በጣም ይጎዳል፡፡ ነገር ግን ውለው አድረው በሚደረግላቸው የምክር አገልግሎት ስሜታቸውን አስተካክለው ልጆቻቸው በቫይረሱ እንዳይያዙ ሲሉ ተገቢውን ክትትል ያደርጋሉ፡፡ ከባለሙያዎችም ጋር በጣም ቅርበትን ይፈጥራሉ፡፡
ጥ፡ እንዴት ነው የምትቀርቢያቸው እንደባለሙያ ነው ?እንደ ቤተሰብ ፣ እንዴት ነው ቅርበቱ ?
መ፡ ጓደኛም እህትም ሁሉም ነገር ሆነው ነው ከእኔ ጋር የሚቀራረቡት ፡፡ ለቤተሰቦቻቸው
የማይነግሩትን ነገር ለእኔ ይነግሩኛል፡፡ እንዲያውም በጣም ከመቀራረባችን የተነሳ ከሕክምናው ውጪ ስለማንኛውም ነገር ይደውላሉ ፡፡
ጥ፡ ባሎች ተመርመሩ ለሚለው ጥያቄ ምላሻቸው ምንድነው?
መ፡ በእርግጥ አንዳንዶቹ እስኪያምኑ ድረስ ያስቸግራሉ፡፡ ግን አንዴ ከጀመሩ ክትትሉን
ይቀጥላሉ እንጂ አያቋርጡም፡፡
ጥ፡ የውጤት ልዩነት ሲገጥም የተጠቃሚዎች ሁኔታ ምን ይመስላል?
መ፡ አንድ ጉዳይ ገጥሞኛል፡፡ ባልየው ኔጌቲቭ ሆኖ ሚስትየው ግን ፖዘቲቭ ነች፡፡ እናም
ምርመራውን እንዲያደርግ ሲጠራም ሆነ ውጤቱ ሲነገረው በጣም የተረጋጋ ነበር፡፡ በውጤቱ ምንም ሳይበሳጭ በጣም ነው የረዳት፡፡ በቃ አብረን እንኖራለን ፡፡ ምንም ችግር የለም ነው የሚላት ፡፡ በጣም ነው ያዘነላት ፡፡ እሷ ይህንኛውን ባሏን ከማግባቷ በፊት ተገዶ የመደፈር ታሪክ ያላት ናት፡፡ ይህ ባልዋ ውጤቱን ከሰማ ጀምሮ ከአጠገብዋ የማይለይ ሲሆን ለምርመራውም በየወሩ ወደሆስፒታሉ ይዞአት ይመጣል ፡፡
-------///---------
ተከታዩ ሀሳብ በአዳማ ሆስፒታል ካገኘናት ታካሚ ያገኘነው ነው ፡፡
ጥ፡ የአዳማ ነዋሪ ነሽ ?
መ፡ እኔ የምኖረው በናዝሬት ከተማ ነው፡፡ በዚህ ከተማ ለረጅም ጊዜ ኖሬአለሁ፡፡ ባለትዳር እና የሁለት ልጆች እናትም ነበርኩ፡፡ ትዳሬን ግን ባለመስማማት ምክንያት የፈታሁ ሲሆን ልጆቼንም አባታቸው አሳድጎአቸዋል፡፡ ተምረዋል፡፡ ትዳር ይዘዋል፡፡ አሁን የልጅ ልጅ አይቻለሁ፡፡
ጥ፡ ከቫይረሱ ጋር መኖርሽን ያወቅሽው መቼ ነው?
መ፡ ከባለቤቴ ጋር ከተጣላሁ በኋላ በተለያዩ ቦታዎች በሰው ቤት ሰርቻለሁ፡፡ በአንድ ወቅት ከአንዳ ወንደላጤ ቤት የሰራሁ ሲሆን በእሱ በገጠመኝ መደፈር ቫይረሱ እንደያዘኝ ያወቅሁት በሁዋላ ነው፡፡ ስራዬን ትቼ አሁን ከምሰራበት ቤት እየሰራሁ ሳለሁ በመታመሜ ሲያስመረምሩኝ የዛሬ አምስት አመት ቫይረሱ በደሜ ውስጥ ተገኘ፡፡ በጣም ነበር ያዘንኩት፡፡ ነገር ግን ምንም ማድረግ ስለማይቻል እራሴን አሳምኜ መድሀኒቱን እየወሰድኩ እገኛለሁ፡፡ አሁን ትንሽ ያስቸገረኝ የምሰራው ስራ ባህርይ ነው፡፡ ልብስ ማጠብ ...የቤት ውስጥ ስራ መስራት...የመሳሰሉት ስለሆኑ ጉልበት የሚጠይቁ ናቸው፡፡
ጥ፡ አሁን ሆስፒታል የመጣሽው መድሀኒት ለመውሰድ ነው... ወይንስ ?
መ፡ አሁን የመጣሁት እያመመኝ ልታከም ነው፡፡ ኧረ እያመመኝ ነው፡፡ እንዲያው ሰውነ..
እራሱ ይንቀጠቀጣል ፡፡ የዛሬ ሳምንትም መጥቻለሁ ባለፈውም መጥቻለሁ፡፡ የምወስደው መድሀኒትማ ጊዜው ገና መስከረም ማብቂያ ላይ ነው፡፡
ጥ፡ መድሀኒት ከመውሰድ ሌላ አራስሽን አንዴት ትጠብቂያለሽ?
መ፡ ያው ሁሉንም ነገር አጠብቃለሁ ፡፡ ምግብ በስርአቱ እመገባለሁ፡፡ የምሰራባቸው ሰዎች
እግዚአብሔር ይስጣቸውና ምንም አይጎድልብኝም፡፡ እኔ አልበላልሽ ካላለኝ በስተቀር በደንብ እበላለሁ፡፡ ጽዳ..ን ፣ጤንነ..ን ሐኪሞቹ በሚነግሩኝ መሰረት በጣም እጠብቃለሁ፡፡ ግን አሁን ...አሁን እያመመኛ እየደከመኝ ተቸግሬአለሁ፡፡
ጥ፡ ተመርምሮ እራስን ማወቅ ምን ይጠቅማል ትያለሽ?
መ፡ ተመርምሮ እራስን ማወቅማ እራስንም ሰውንም ይጠቅማል ፡፡ እራስን ማወቅማ ትልቅ ብልህነት ነው፡፡ ለሁሉም ሰው የምመክረው እራሳችሁን ተመርመሩና እወቁ፡፡ ለእራሳችሁም ለቤተሰባችሁም በጠቅላላው አብሮአችሁ ለሚኖረው ሁሉ ይጠቅማል እያልኩ ነው፡፡
                                             ----------///-------
በተከታይ ያነጋገርናት ፓርክሊን ሜዲካል ሴንተር ያገኘናት ሲስተር ቤዛ ዳንኤል ናት፡፡
‹‹...ክሊኒካችን መካከለኛ ክሊኒክ እንደመሆኑ መጠን በደረጃው ለክትትል የሚመጡ እናቶችን ያስተናግዳል፡፡ ከቫይረሱ ጋር ለሚኖሩ እናቶች ARTን ከመስጠት ደረጃ ገና አልደረሰም፡፡ ነገር ግን ምርመራውን እያደረግን አገልግሎቱን ለሚሰጡ ሆስፒታሎች ሪፈር እንላለን፡፡ ፓርክሊን ሜዲካል ሴንተር በሚሰጠው አገልግሎት ግን የምክር አገልግሎቱን በተሟላ መልኩ የሚሰጥ ሲሆን ወደሆስፒታሎች ሪፈር የምንላቸው እናቶችም ክትትል በሚገባ ማድረግ አለማድረጋቸውን የምንከታተልበት መንገድ አለን፡፡
ጥ፡ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ እናቶች ውጤታቸውን ሲያውቁ ምን ስሜት ያድርባቸዋል?
መ፡ በጣም ያዝናሉ፡፡ ግን በተከታታይ በሚሰጣቸው የምክር አገልግሎት ይጽናናሉ፡፡
ጥ፡ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ምን ያህል እናቶች ይተያሉ ?
መ፡ በወር ውስጥ አሁን ለምሳሌ ከ2006 ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ወደ አስራሰባት እናቶች
ታይተዋል፡፡ ውጤተቸው እንደሚያመለክተው ከሆነ ሁሉም NON-REACTIVE ወይም ኤችአይቪ ኤድስ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ የለም ማለት ነው፡
ጥ፡ ART..ሖማ ን መስጠት የሚቻለው መቼ ነው ?
መ፡ PMCT በሰለጠነው መሰረት መድሀኒቱን እንዲጀመር የምናደርገው ውጤቷን ባወቀችበት በዚያው ሰአት ነው እንጂ ሲዲፎሯ ታይቶ ቀንሶ ወይንም ጨምሮ የሚለው PROCESS ውስጥ አንገባም ፡፡ ስለዚህ ወዲያው ባወቀችበት ሰአት የዛኑ እለት ብንችል እንድትጀምር COUNSEL እናደርጋተለን፡፡ አንዳንድ ጊዜ አይቀበሉሽም ቶሎ መድሀኒቱን መጀመር ሰውነታቸውን እንደሚያወፍር የመሳሰለ አንዳንድ የተሳሳተ ግንዛቤ ስላለ እምቢ ሊሉ ስለሚችሉ በሚቀጥለው ቀጠሮ ተረጋግታ ስትመጣ መድሀኒቷን መጀመር እንዳለባት ምንም አይነት ነገር እንደማያስከትልባት አሳምነን ወዲያው እንድትጀምር እናደርጋለን ፡፡ አንዲት እናት በኤችአይቪ ኤድስ ቫይረስ ብትያዝም እን..ን ልጅ መውለድ ትችላለች ፡፡ በቫይረሱ መያዝ ከቫይረሱ ነፃ የሆነ ልጅ ለመውለድ አያግድም፡፡ ነጻ የሆነ ልጅ ለመውለድ እናትየው ማድረግ ያለባት ህይወቷን በጥንቃቄ መምራት እና መድሀኒቷን እንዴት አድርጋ እንደምትወስድ ማወቅ...ከመውለዷ በፊት ፣በወሊድ ጊዜና ከወለደች በኋላ የምታደርገው ጥንቃቄ ተጨምሮ ጤነኛ ልጅ መውለድ እንደምትችል ማወቅ አለባት፡፡

 

Read 2240 times