Saturday, 04 October 2014 14:02

ኖርዌይ፤ ለአዛውንቶች ጤናማ ህይወት “ተመራጭ አገር” ተባለች

Written by 
Rate this item
(3 votes)

             በዓለም ላይ ከሚገኙ አገራት የትኞቹ ዕድሜያቸው ለገፉ አዛውንቶች ህይወት ምቹ እንደሆኑ ለማወቅ በ96 አገራት ላይ በተካሄደ ጥናት፣ ኖርዌይ ለአዛውንቶች ጤናማ ህይወት ቁጥር 1 ተመራጭ አገር ስትሆን አፍጋኒስታን በመጨረሻ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡ የኸልፕኤጅ ኢንተርናሽናል ግሎባል ኤጅዎች ኢንዴክስ፤ ዕድሜያቸው ከ60 በላይ የሆናቸው አዛውንቶችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ደህንነት (ዋስትና) በመለካት ነው የአገራቱን ደረጃ ያወጣው፡፡ በተባበሩት መንግስታት የአዛውንቶች ቀን መፅሄት ላይ በወጣው መረጃ መሰረት፤ አውስትራሊያ፣ ምዕራብ አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ እድሜያቸው ለገፉ ዜጎች እጅግ ምቹ አገራት መሆናቸው የተረጋገጠ ሲሆን አፍጋኒስታን ግን ለአዛውንቶች ህይወት የማትመች መሆኗ በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡

እ.ኤ.አ በ2050 ከዓለም ህዝብ ውስጥ 21 በመቶ ያህሉ ዕድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ የሆኑ አዛውንቶች እንደሚሆኑ ሪፖርቱ ተንብይዋል፡፡ የኑሮ ምቹነትን የሚጠቁመው ኢንዴክስ፤ አራት ዘርፎችን የሚመዝን ሲሆን እነሱም የገቢ ዋስትና፣ ጤና፣ ግለሰባዊ አቅምና ሰውየው ሴትየዋ የሚኖሩት በ“ምቹ አካባቢ” ነው አይደለም የሚሉት ናቸው፡፡ ለአዛውንቶች ምቹ የመኖርያ ሥፍራ በመሆን በቀዳሚነት ከተጠቀሰችው ኖርዌይ ቀጥሎ ስዊድን፣ ስዊዘርላንድ፣ ካናዳና ጀርመን ይከተላሉ፡፡ በጥናቱ ውስጥ ከተካተቱት አገራት በ40 ያህሉ በ2050 ዓ.ም 30 በመቶ የሚሆነው ህዝብ 60 እና ከዚያ በላይ ዕድሜ ያለው እንደሚሆን ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡ የተባበሩት መንግስታት መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በ2030 ዓ.ም በዓለም ላይ ዕድሜው 60 ወይም ከዚያ በላይ የሚሆነው ህዝብ ቁጥር 1.4 ቢሊዮን ይደርሳል ተብሎ ይገመታል፡፡

Read 2337 times