Monday, 06 October 2014 08:30

ትምክህተኛ የባህል ዘፋኞችና ጠንቃቸው

Written by  ናትናኤል ግርማቸው Natipoiem@Gmail.com
Rate this item
(2 votes)

               አንድ የቅርብ የምለው ጓደኛዬ በሰርጉ እለት እንድገኝለት የጋበዘኝ ከሁለት ወር በፊት ነበር፡፡
እኔም ጥሪውን አክብሬ ደስታውን ለመካፈል ከመለስተኛዋ የሠርግ አዳራሽ ውስጥ ተገኘሁ፡፡ ለስለስ ባሉ የሠርግ ዘፈኖች ምሣ ከተበላ በኋላ የመጠጡ፣ ዘፈኑ እና የታዳሚው ስሜት እየጋለ መጣ፡፡ አንድ ቁርጥ እንጀራ ለማንሳት የተጀነነ ትከሻ ሁሉ በጠጁ ብርታት የቅምጥ እስክስታውን ያስነካው ጀምሯል፡፡ ፀጋዬ እሸቱ “ተይሙና ተይሙና” ሲል ሠርገኛውም “አሆሆይ ሙና” እያለ ያጅበዋል፡፡ መቼም የሐበሻ ባህሪ ሀዘንና ደስታን እስከጫፉ እንዲለካ ሆኖ ነው የተፈጠረው፡፡ የሐበሻ ዘፈንም እንደዛው ከሙሾ እስከ ጭፈራ፡፡ ዲጄው በተቀመጠበት ጭፈራ የነሸጠውን ታዳሚ በመመልከት፣ አከታትሎ የባህል ዘፈኖቹን መልቀቅ ጀመረ፡፡ አሸብር በላይ፡- “ለበላይ ቤልጅጉ ለዓባይ ጣና አለለት ለእኔም እሷን ሰጠኝ፣ ጎጃም ዘር ይውጣለት”
በዚህ ግዜ ሙሽራው ጓደኛዬን ጨምሮ ግማሽ የአዳራሹ ሰው ተነስቶ፣ በእስክስታ መርገፍገፍ ጀመረ፡፡ የሚገርመው ነገር ከላይ በሀገር ጀግንነቱ የሚታወቀውን በላይ ዘለቀን አርዓያ አድርጎ የጀመረው ዘፋኝ፤ ለአንዲት ሴት ጠብ-መንጃ ይዞ ሐገር አይብቃኝ ማለቱ ሳያሳፍረው “ጎበዝ ከሠነፉ ፈረስ ከእግረኛ
    እኔ ነኝ ያለ ይሞክረኛ”
እያለ የኔ ያላት ጉብል ላይ ያጎበጎበውን በጥይት እሩምታ ተራራ ለተራራ ሲያዳፋው ክሊፑ በአይኔ መጣ፡፡
ሙሽራው ጓደኛዬ እራሱ አጨፋፈሩ ሙሽሪትን በፍቅር መፈቃቀድ ሳይሆን ነፍጥ አንግቦ በዙሪያዋ ያንዣበበውን ሁሉ… ሠላም የሚላትን ሳይቀር በጥይት እሩምታ አስፈራርቶ ያገባት ነው የሚመስለው፡፡ እኔ የምለው ህግ ባለበት ሐገር፣ ሠው በሠላም ወጥቶ በሠላም ሊገባ በሚገባበት ሃገር፣ ህገ-መንግስቱን ንዶ ህገ-እንስቱን ሊጠብቅ እሳት ጎራሽ ብረት ታጥቆ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚል ዘፋኝ ሀይ ባይ አጥቶ፣ “ኢ-ቲቪን” ጨምሮ ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያውን ሲያጨናንቅ አይገርምም? እውነትም አሸብር! ጥበብስ የህብረተሠቡን ጎጂ ማህበራዊ እሳቤን በሀይሏ መግራት ሲገባት፣ የእብሪተኞች አርማ መሆኗ አያሳዝንም? ይሄ ሲገርመኝ የዚህ ዘፈን መንታ ወንድም የሚመስሉ የባህል ቸብቸቦዎች የታዳሚውን የጭፈራ  እልህ ማስወጣት ጀመሩ፡፡ ሠማኸኝ በለው ቀጠለ፡- “በለው!” የዚህንም ዘፈን ምስል በቴሌቪዥን መመልከቴ ታወሰኝ፡፡ ህግ አላከበርክም ተብሎ ሁለት አመት በእስር ካሳለፈ በኋላ ሠሜ አንድ መቀመጫዋን “ኧረ ምኑን ሠጠሽ” እያለ የሚያደንቅላትን ኮረዳ የተመኘበትን ሠው ካልገደልኩ እያለ የሚፎክርበት ዘፈን ነው፡፡ በዚህ ማን ይነካኛል ብሎ ነው መሠለኝ፡-
“ምን ፈልጎ አጅሎት የሚመላለሰው
በክትክታ ሽመል ግንባሩን ልግመሰው………ጭንጋፍ ነው ጭንጋፍ ነው ጭንጋፍ ነው ሙትቻ
ተውልኝ ብያለሁ ቆይ ብቻ ቆይ ብቻ…….”
እግዜር ያሳያችሁ እንግዲህ ይሄ ሠው “ማር ዘነብ” የሚላትን ጉብል ተሳስቶ የነካበት እንደሁ ወይ መንካት! ኧረ ቀና ብሎ ያየበት እንደሆን “ጭንጋፍና ሙትቻ” ተብሎ ሞራላዊ ባልሆነ መንገድ የተሠደበው አፍቃሪ፤ ግንባሩ የክትክታ ሲሳይ መሆኑ ነው፡፡
   ስለዚህ ያሻውን የመውደድ ሠብዓዊ መብት ያለው አፍቃሪ ጉልበተኛን ፈርቶ ዝም ነዋ! ማን ከእብሪተኛ ጋር ይጋፋል፡፡ ጀግና ነኝ ካለ ደግሞ ወይ ብትርን በብትር ወይ ብትርን በጥይት ሊመክት ይነሳል፡፡ ከዚያ ደም ወደ መፋሠስ፡፡ ኢ-ቲቪም ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በኋላ እኚህን አነስተኛ ጦርነቶች እያስተላለፈልን ይገኛል፡፡ በምስል ይስሩ አይስሩ ያላረጋገጥኳቸው፣ በየራዲዮ ጣቢያዎቻችን “ለክቡራን አድማጮቻችን” እየተባለ በግብዣ መልክ ከሚበረክቱልን መሠል ዘፈኖች የታወሱኝን ላስከትል፡- ይሆኔ በላይ /ይሁን የበላይ/ “ገላጋይ”ን እንይ፡-
“ቆይማ ቆይማ ላሳየው ቆይማ
አንቺን ብሎ መጥቷል ነገር የተጠማ
ደሞ ለወንድነት ድሮም ካልታማ
ባንቺ ይፈትኑኝ ይታይ የኔ ግርማ”
ይህም ቀደም ብዬ የጠቀስኳቸው እብሪት የተሞላባቸው ዘፈኖች መንትያ
ነው፡፡ አዝማቹ ላይ እንደሚታየው የአማርኛ ፍቺ ከሆነ፤
ማፍቀር፡- ነገር መጠማት ነገረኝነት
ጀግና፡- አፍቃሪን ድባቅ የመታ /የወደዳትን የተመኘበትን/ ሆኖ ቀርቧል፡፡ የጡንቻ
   መለኪያው የመስዋእትነት ጥግ ለሴት መሞት! ለሴት መግደል! በሆነበት ጥበብ ለሀገር የወደቁ ለሀገር የተሠው አርበኞቻችንን ምን ስም ልናወጣላቸው ይሆን? ይሁኔ ይቀጥላል፡-
“… ቢሻው በማባበል ቢሻው በሽመሉ
   ይመለስ የለም ወይ ሁሉም እንዳመሉ
እንደምናውቅበት በፍቅር ማስከርን
የት እናጣዋለን ጥሎ መፎከርን፡፡”
የመጀመሪያዎቹ ሁለት ስንኞች ሀሳብ ልክ እንደ ውሻ
ሠው የሠጠውን መብት ተቀብሎ የሚኖር ሠው ካልሆነ በቀር፣ ሠብዓዊ መብቴን ተጠቅሜ
ልውደድ፣ ላፍቅር ለሚል ሰው ዘፋኙ ምንም ርህራሄ እንደሌለው፣ በቀጣዮቹ ሁለት ስንኞች
ደግሞ እንደድሮ አንበሳና  ነብር ገድሎ እንኳን መፎከር ወንጀል በሆነበት ዘመን፣ እንኳን
የሠው የእንስሳት መብት ተሟጋቾች በተፈጠሩበት ጊዜ፣ ክቡሩን የሰው ልጅ አንፈራፍሮ
መሬት ጥሎ ጀግና ነኝ ብሎ መፎከር፣ እሰይ አበጀህ የሚያስብል ጀብድ ሆኖ ቀርቧል፡፡
የቀጣዮቹ ስንኞች አንድምታም ከእ አይሻል ዶማ ነው፡፡ ይሄ‘ኮ ሠልጠነናል የምንልበት ዘመን
ነው ጃል፡ ዛፍን ያለ አግባብ መቁረጥ ደሞ ወንጀል እስከመሆን የደረሠበት ጊዜ ላይ ሆነን
እንኳን ለዛፍ ለሠው ግድ የሌለው ዘፋኝ፡-
“ባንድ ድር ይበቅላል በትርና አበባ
በልምምጥ ባይሆን ለምጠኸው ግባ” ይልሃል፡፡
እንግዲህ ያቺን ጉብል ጥሎብህ የወደድክ ሆይ፤ ከዱሩ የፈካ አበባ ቀጥፌ ላበርክትላት ብለህ እንዳታስብ፤ ምክንያቱም አጅሬ ካንተ ቀድሞ ከጫካው በትሩን ቆርጦ መልምሎ፣ ላናትህ ሲሳይ የሚሆን ገፀበረከት ሊያበረክትልህ ተዘጋጅቷልና፡፡ እዚህ ላይ ከነዚህ ዘፈኖች መልእክት ጋር ተያይዞ መነሳት የሚገባው ጉዳይ ደሞ ሴቶች ፍቅር ላይ ያላቸው ተሳትፎ ነው፡፡ ግጥሞቹ ላይ እንደምንመለከተው አንዲት ሴት እንደ ሪሲሊንግ ቀበቶ ፍልሚያውን ለሚያሸንፈው ጡንቸኛ በሽልማት መልክ የምትበረከት ስጦታ እንጂ ቀልቧ የተመኘውን፣
የሕይወቴ መንገድ የምትለውን ሠው የመምረጥ መብት የሌላት ሆና ትታያለች፡፡ ምናልባት እኮ ያቺ ሴት በፍቅር ልቧ የቀለጠለትና ነብሷም የመነነለት ያ በፍልሚያው ተሸንፎ የወደቀው ወጣት ይሆናል፤ ወድቆ ሲፎከርበት ሕይወቱ ቢያልፍ እንኳን ፍቅሯ ከሱ ጋር ተያይዞ መቃብር መውረዱ እኮ ነው፡፡ ከዚያም ከገዳይም ጋር አብራ ልትኖር! አይበለውና ይህ ቢፈጠር፣ ልቧ በፍቅር እጦት የጠለሸባት ሴት እንዲህ የምትል አይመስላችሁም?
“ብትር የለም እንጂ ለሴት የሚቆረጥ
ጀግና የለም እንጂ ከሴት የሚፋለጥ
በክትክታ…. አልቄ
ከመሬት….. ወድቄ
ካንተ ጋር መሞትን ነበር ልቤ ሚመርጥ”
የሷ ይብቃንና የዘፈኑን ማሳረጊያ ግጥም እንይ፡፡
“ወዲህ ወዲያ የለም ቀና ነው ነገሬ፤ ቀልድ መች አውቃለሁ ባንቺና ባገሬ” እኔም እንዲ አልኩ፡- ሀገር ማለት ወንድም፣ ሀገር ማለት እህት፣ ሀገር ማለት ጎረቤት፣ የመንደሩ ሠው፣ ብቻ ሀገር ማለት ሁሉም ሠው ነው፤ ከሁሉም ነገር ሠውና ሠውነት ይቀድማል፡፡ አገር ማለት የሠው ደም የጠጣ መሬት አይደለም! በፍቅር የፀና፣ በሞራላዊ ህግ የተገዛ ማህበረሠብና በሠላም የተሳሠረ ማንነትን በአንድ የሚያኖር ምድር ነው፤ ሀገር ሀገር የሚሸተው፡፡ የራስ ጠላት ከራስ ወገን አበጅቶ፣ በዓመፅ ክንድና ቂም በቀል ቢተላለቁ ለየትኛዋ ሀገር ነው የትኛውን የውጪ ጠላት የሚመክቱላት?! አንድ የመጨረሻ ዘፈን ልመርቅና
ትዝብቴን ላሳርግ፡፡
“የኔአለም አንቺን ያለውን
በሳንጃ ሆዱን…”
የዚህኛው ደሞ ይብሳል፡፡ ከግድያ ወንጀሎች ሁሉ ሠውን በስለት መግደል በአሠቃቂነቱ የሚስተካከለው ያለ አይመስለኝም፡፡ በዚህ ዘፈን ላይ ግን የፍቅር መግለጫ ሆኖ ቀርቧል፡፡ /አያስቅም?/ ሚዲያዎቻችን ግን መሠል ሙዚቃዎችን ለማስተላለፍ ምንም አያግዳቸውም፡፡ “ሼም” የለም እንዴ? ከዚህ አንፃር እኮ ፖሊስና ህብረተሰብ ፕሮግራም ላይ የሚቀርቡ የዝርፊያ፣ የድብድብና የጥይት ግድያዎች ሚዛናቸው ይቀላል፡፡ ቲቪያችን ግን በመዝናኛ ፕሮግራም ላይ ሳይቀር ለመልቀቅ እፍረት የለውም፡፡ እንዲህ አይነት ሙዚቃዎች  ለመዝናኛ የሚሆኑ ከሆነ ፖሊስ ፕሮግራም ላይ የሚቀርቡ ወንጀሎችንም እሁድ መዝናኛ ላይ ያቅርብልን፡፡ ሕዝቤም እየተነሳ ይጨፍርባቸው፡፡ በርግጥ እንዲህ አይነት እብሪት የተሞላባቸው ዘፈኖች ዛሬ ላይ አይደለም መሠራት የጀመሩት፡፡ ከድሮ ጀምሮ ሙዚቀኞቹ ከበቀሉበት ማህበራዊ እሳቤ እየተነሱ ይሠራሉ፡፡ ነገር ግን ጥያቄው እንደ ጥበብ ምንድነው ማድረግ ያለብን ነው፡፡ የሕብረተሰቡ ማህበራዊ የአኗኗር ዘይቤና ፍልስፍና ቢሆን እንኳን ይሄን ጎጂ ባህል ማራቅ ነው እንጂ እውቅና መስጠትና ማባባስ ነው ወይ የጥበብ ድርሻዋ? እዚህ ላይ የመስፍን በቀለን “ደመላሽ” ማንሳትና ማመስገን ይገባል፡፡ ልማድ ወጥሮት ደም መቃባትን እንደ አንድ የኑሮ አካል የያዘን ማህበረሠብ፣ የፍቅርን ጉልበትና ኃያልነት ልማዱን ገድሎ ያሳየን ሙዚቃ ነው፡፡ እንዲህ ነው ጥበብ ማህበረሠብን አንድ እርምጃ ስትቀድም፣ ጥበብ በቂም ሀረግ የተተበተበውን የደም ጥም በፍቅር ስላቷ ስትበጥስ፡፡ የአንድ ሰው ግላዊ የስነልቦና እሳቤ በመኖሩ ላይ ከመንፀባረቅ አልፎ ወደ ቤተሠብ፣ ጎረቤት እያለ ወይ ማህበራዊ እሳቤ ያድጋል፤ ይህ ከሌሎች ጋር ሲጠራቀም ደግሞ ያንዱን ማህበረሠብ የኑሮ ዘይቤ ይሠራል፡፡ ይህ ማለት ያንድ ሠው ቀናም ሆነ እኩይ አስተሳሰብ ለማህበረሠቡ ግብአት ነው ማለት ነው፡፡ እኛ በራሳችን እንደግለሠብ እንኳን ቀናና አስተማሪ ስራ ሰራን ማለት ቢያንስ አንድ ጉድፍ እንዳጠራን ይቆጠራል፡፡ ይህ በብዙዎች ዘንድ እያደገ ሲመጣ ደግሞ ለውጥ ይሆናል፡፡ ይህን ማድረግ ባንችል እንኳን ዝምታን መርጠን መቀመጥና ለጎጂው ማህበራዊ እሳቤ አንድ ድጋፍ መቀነስ አለብን፡፡ ስለዚህ እባካችሁ እናንት ትምክህተኛ የባህል ዘፋኞቻችንና ገጣሚዎቻቸው፤ ጥበባችሁ ፈቅዶ ባታስተምሩን እንኳን እሳት አትለኩሱብን፡፡ ዝም በሉን፡፡

Read 2834 times