Saturday, 11 October 2014 15:43

ህፃናት ለአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች የፃፏቸው ደብዳቤዎች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ውድ ፕሬዚዳንት ኬኔዲ፡-
የእኔ ፍላጎት ኤፍቢአይ መሆን ነው፡፡ አንድ ቀን የፕሬዚዳንቱ ጠባቂ ሆኜ እመረጥ ይሆናል፡፡ ገና ልጅ ስለሆንኩ ግን ትንሽ ይቆያል፡፡
አርተር - የ11 ዓመት ህፃን
ውድ ፕሬዚዳንት ኬኔዲ፡-
የመጨረሻ ደብዳቤዬ ደርሶህ እንደሆነ አላውቅም፡፡ በዚያ ደብዳቤ ላይ ከ12 ዓመት በኋላ ወደ ጨረቃ የምጓዝ የመጀመሪያው ሰው መሆን እንደምፈልግ ፅፌልሃለሁ፡፡ ያን ጊዜ አንተ ፕሬዚዳንት ላትሆን ትችላለህ፤ ነገር ግን ወንድምህ ቦብ ኬኔዲ የሚሆን ከሆነ፣ ይሄን ደብዳቤ ለሱ ስጥልኝ፡፡ አመሰግናለሁ፡፡
ስንታሊ - የ11 ዓመት ህፃን
ውድ ፕሬዚዳንት ኬኔዲ፡-
ባለቤትህ በጣም ቆንጆና በጣም ጥሩ ሴት ትመስለኛለች፡፡ በጣም ቀልደኛም ሳትሆን አትቀርም፡፡ ሁለታችሁንም እወዳችኋለሁ፡፡
ናንሲ - የ8 ዓመት ህፃን
ውድ ፕሬዚዳንት ቡሽ፡-
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የመከላከያ ሚኒስትርና የገንዘብ ሚኒስትር እያሉህ፣ የህፃናት ሚኒስትር የሌለህ ለምንድነው? ህፃናትም እኮ ድምፅ መስጠት ይችላሉ፡፡ እነሱም መብት አላቸው፡፡
ቼሲ - የ8 ዓመት ህፃን
ውድ ፕሬዚዳንት ቡሽ፡-
የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዚዳንት ለመሆን እፈልጋለሁ፡፡ በጣም ጎበዝ ነኝ፡፡ በትምህርቴም ጥሩ ውጤት ነው የማመጣው፡፡ እናቴ በጣም ንፁህና ጠንቃቃ እንደሆንኩ ትነግረኛለች፡፡ ስለዚህ ዋይት ሃውስን አላዝረከርክም፡፡
አቢጌል - የ9 ዓመት ህፃን
ውድ ፕሬዚዳንት ቡሽ፡-
አጎቴ ማርዮ ፀጉር አስተካካይ ነው፡፡ ዋይት ሃውስ መጥቶ ያንተን ፀጉር ማስተካከል ይፈልጋል፡፡ 50 ሳንቲም ብቻ ነው የሚያስከፍልህ፡፡ ምክንያቱም ፕሬዚዳንት ስለሆንክ አንተን ማስተካከል ብዙ ደንበኞች እንደሚያመጣለት ነግሮኛል፡፡
አልበርት - የ8 ዓመት ህፃን
ውድ ፕሬዚዳንት ቡሽ፡-
እኔ ገና መፃፍ ስለማችል ይሄን ደብዳቤ የፃፈችልኝ እናቴ ናት፡፡ አንድ ቀን ግን መፃፍ እችላለሁ፡፡ ያኔ ድምፅ መስጠት ስለምችል ድምፄን የምሰጠው ለአንተ ነው፡፡ ለደብዳቤዬ መልስ እንድትፅፍልኝ… እሺ፡፡ መፃፍ ባልችልም ማንበብ እችላለሁ፡፡
ሲድኒ - የ5 ዓመት ህፃን
ውድ ፕሬዚዳንት ቡሽ፡-
ዋይት ሃውስ ውስጥ ሃላፊው ማነው? አንተ ነህ ወይስ ቀዳማዊት እመቤት? የእኛ ቤት ሃላፊ እናቴ ናት፡፡
ካርል - የ9 ዓመት ህፃን
ውድ ፕሬዚዳንት ቡሽ፡-
አባቴ ግብር ሲከፍል ነው እንጂ ሌላ ጊዜ በጣም ነው የሚወድህ፡፡
ብሩክ - የ9 ዓመት ህፃን
ውድ ፕሬዚዳንት ቡሽ፡-
የሴት ጓደኛዬ አሊሳ ሪፐብሊካን ስትሆን እኔ ዲሞክራት ነኝ፡፡ አንድ ቀን መጋባታችን አይቀርም፡፡ ዲሞክራት ሪፐብሊካንን ማግባትና ደስተኛ መሆን ይችላል? እኔ 12 ዓመቴ ሲሆን ጓደኛዬ 11 ዓመቷ ነው፡፡ 18 ዓመት ሳይሞላን በፊት መልስህን እንፈልጋለን፡፡ አመሰግናለሁ፡፡
ሪያን - የ12 ዓመት ህፃን
ውድ ፕሬዚዳንት ቡሽ፡-
የአብርሃም ሊንከንን ንግግሮች ማንበብ ያለብህ ይመስለኛል፡፡ ያን ጊዜ ሰዎች ያንተን ንግግር እየሰሙ ማንቀላፋት ይተዋሉ፡፡
ጂሚ - የ10 ዓመት ህጻን
ውድ ፕሬዚዳንት ቡሽ፡-
ከሚስትህ ጋር ከተጋባህ ምን ያህል ጊዜ ሆነህ? አንተና ቀዳማዊት እመቤት ተጣልታችሁ ታውቃላችሁ? እናትና አባቴ ከተጋቡ 20 ዓመት ሲሆናቸው ሲተኙ ካልሆነ በቀር ሁልጊዜ እንደተጣሉ ነው፡፡
ካያ - የ13 ዓመት ህፃን

Read 1647 times