Saturday, 11 October 2014 15:50

የመፅሐፍት አየር ትንበያ

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(4 votes)

          ትላንት ወደ ፒያሳ አካባቢ ብቅ ብዬ ነበር፡፡ ወደ ፒያሳ ብቅ ስል ዘወትር የመፅሐፍት ሜትሮሎጂን በራሴ አቅም ለመተንበይ እሞክራለሁ፡፡ የመፅሐፍት ሜትሮሎጂ እንደ አየር ፀባይ ትንበያ ይመስልና በአንዳንድ ድርሰቶች ላይ ግን አሳሳች ሊሆን ይችላል፡፡
ትላንት የተመለከትኩት ትንበያ ምንም ስህተት የለውም፡፡ የመፅሐፍት አዟሪዎቹ ደረታቸውን አስደግፈው ከሚከምሩት መፅሐፍ አገጫቸው ስር ያለችዋ… የቀኑን የመፅሐፍት አዋዋል የምትተነብይ ናት፡፡ አንዳንድ መፅሐፍት ከአንድ ቀን በላይ በክምሩ አናት ወይንም በአዟሪው አገጭ ስር አይውሉም፡፡ ሌሎቹ ደግ አመቱን ሙሉ የአዟሪ እና የአንባቢ ደረትን ተደግፈው ይዘልቃሉ፡፡
ትላንት በተመለከትኩት ትንበያ፣ አንድ መፅሐፍ ሁሉም ክምር ላይ የበላይ ሆኖ ውሏል፡፡ መፅሐፉ በአዟሪ አገጭ ስር ብቻ ሳይሆን በሰውም እጅ ገብቷል፡፡ ወቅታዊ መፅሔት ይመስል ሁሉም በእጁ ይዞታል፡፡ ያልያዘው ደግሞ ለመያዝ የተቻለውን ያደርጋል፡፡ ከአዟሪው ላይ ወይንም በመሬት (አስጥተው ከሚሸጡት) መፅሐፉን ጠይቆ ይቀበልና …ፊት እና ጀርባውን አገላብጦ በአይኑ ይስመዋል፡፡ ይቀጥልና እጁ ላይ ይመዝነዋል፡፡ በአንድ እጁ የመፅሐፉን ክብደት፣ በሌላ እጁ የራሱን አእምሮ ክብደት… በልቡ ደግሞ የኪሱን ክብደት እያነፃፀረ መሆኑ ያስታውቅበታል፡፡
ከፒያሳ ወረድ ብዬ እስከ ፖስታ ቤት… ከፖስታ ቤት ብሔራዊ ትያትር አካባቢ አየሩን ለካሁት፡፡ አየሩ አንድ አይነት ነው፡፡ በአንድ ቀንም ሆነ በአንድ ወር ውስጥ የሚለወጥ አይመስልም፡፡ የአየሩ አርዕስት አንድ ነው “መረቅ…” …መላውን ከተማ እየዞርኩ ናሙና ብወስድ እንኳን የተለያየ ውጤት አላገኝም፡፡
ትንበያዬን በድፍረት ለራሴ አወጅኩ፡- “ለስድስት ወር አየሩ ሞቃታማ ነው የሚሆነው… የሙቀቱ መጠን በዲግሪ ሴንቲግሬድ “አዳም ረታ” ይሆናል፡፡ የሙቀቱ መንስኤ በስድስት መቶ ገፆች ታትሞ የተለቀቀ ነው፡፡ ሙቀቱን መቋቋም የሚችሉት መፅሐፉን ማንበብ የቻሉት ብቻ ናቸው፡፡ ለማንበብ ትጋት ያስፈልጋል፡፡ የመፅሐፉን ውራጅ ለማግኘት የሚጠብቁ እንዳሉ ሁሉ፣ በወቅቱ ገንዘባቸውን አውጥተው የሚገዙት ግን አይለዋል፡፡ ለማንበብ የሚጐብዙ ለመግዛት አቅማቸው ሲሰንፍ አይቼ አዝናለሁ፡፡
***
የአየር ጠባዩ ድንገት ሊለወጥ አይችልም፡፡ ምክንያቱም የመፅሐፍ አየር ጠባይ የዛሬውን እውነት ብቻ ይዞ የሚፈስ አይደለም፡፡ የትላንትም አየር ጠባይ ዛሬ እንደገና ያገረሻል፡፡ “የመረቅ” ሙቀት እና The Adam Reta effect ለቀጣዩ ስድስት ወራት ተቆጣጥሮ ስለመቆየቱ በእርግጠኝነት የምናገረው ከቀድሞዎቹ መፅሐፍቶቹ ተነስቼ ነው፡፡ አዲስ መፅሐፍ ከፃፈ ሰው ይልቅ በተከታታይ መፅሐፍቶቹን ሲያቀርብ የቆየ ሰው በአንድ አይነት ሙቀት በአንድ ጊዜ ከተማዋን ይነግስባታል፡፡ አዲስ አበባንም በመረቁ ያጥለቀልቃታል፡፡ቀድሞም የነበረ ሙቀት በቀደሙት መፅሐፍቶቹ ምክኒያት ፍም ሆኖ ከስር ይጠብቅ ነበር፡፡ ፍሙ እየተራገበ ነው የቆየው፡፡ ድሮውኑ እሳት ነበር… አዲስ ነዳጅ ሲጨመር አዲስ አበባ በአንደ ሙቀት ትጥለቀለቃች፡፡ ሙቀቱ መፅሐፉን ገዝተው ላነበቡት ብቻ የሚሰማ አይደለም፡፡
ለዳር ቋሚ ተመልካችም ይተርፈዋል፡፡ ሙቀት የመፍጠር ደረጃ ላይ ያልደረሰ ደራሲ ገጥሟችሁ እንደሚያውቅ እርግጠኛ ነኝ፡፡ እኔ ገጥሞኛል፣ ምክንያቱም እኔም ቀዝቃዛው እርከን ላይ ያለሁ ደራሲ ነኝ፡፡ ሙቀት መፍጠር ደረጃ ያልደረሰ ደራሲ መፅሐፍ አውጥቶ… ካወጣበት ሰፈር ወደ ሌላ ሲሄድ መፅሐፍ ማውጣቱን ማንም የሚያውቅ የለም፡፡ መፅሐፉ ከሰፈር ሰፈር… መንገዱን… በሰው እጅ ላይ በወረቀት ገፆች ዘርግቶ እየተገላበጠ እና እየተነበበ አይዘልቅም፡፡
የሙቀት መጠኑ ከRoom temperature የማያልፍም መፅሐፍ አለ፡፡ አንድ ክፍል ውስጥ ብቻ ያሉ ሰዎች ተቀባብለው የሚያነቡት፡፡ መፅሐፉ በአንድ ክፍል ወይ መስሪያ ቤት ካሉ ዝምድናዎች ውጭ ሙቀት ስለሌለው እዚያው ተቀብሮ ይቀራል፡፡የአዳምን መፅሐፍ የሙቀት መጠን ለመለካት እየጣርኩ ነው፡፡ እኔ በተወሰኑ የአዲስ አበባ ማእከሎች ተዘዋውሬ እሳቱ ከእጅ ወደ እጅ ሲቀጣጠል ማየት ብችልም… ከአዲስ አበባ ውጭም ሙቀቱ መሻገሩ አያጠራጥረኝም፡፡
አገር አቀፍ የሜትሮሎጂ ትንበያ መሆኑ አይቀርም የእኔ ግምት፡፡ በአዳም ረታ የተለኮሰው መፅሐፍ፤ አለም አቀፍ መሆን አለመቻሉ ያሳዝነኛል፡፡ መፅሐፉ እና ሙቀቱ የሚሰራው በአንድ ቋንቋ ነው፡፡ ቋንቋው አማርኛ ነው፡፡ አማርኛ በሌለባቸው ሀገሮች ሙቀቱ አይሰራም፡፡ ሙቀቱ አማርኛ በሚነገርበት የአየር ንብረት ብቻ የሚገንን ነው፡፡ነገር ግን አበሻ አማርኛውን ይዞ ያልተሰደደበት የምድር ክፍል የለም፡፡ እንጀራ በሁሉም የአለም ክፍል ገብቷል፡፡ እንጀራ በገባበት ሁሉ አዳም ረታ መኖሩ አያጠራጥርም፡፡ እንጀራ በገባበት ሁሉ አበሻ አለ፡፡ “መረቁ” ባለበት ይፈስበታል፡፡የሙቀት መጠኑ በሀገር ውስጥ እየበረደ ሲመጣ፣ ከሀገር ውጭ ያሉት ተቀብለው ያርገበግቡታል፡፡ እነሱ እያርገበገቡት መሆኑን ሀገር ውስጥ ወረቱ የበረደለት አንባቢ ሲሰማ በድጋሚ ሙቀቱ ማገርሸቱ አይቀርም፡፡
ሀገር አቀፍ ዘፋኝ እንዳሉን እናውቃለን…. ጠፍቶብን የቆየው ሀገር አቀፍ ደራሲ ነበር… የሜትሮሎጂ ትንበያውን ስመለከተው፣ ሀገር አቀፍ ደራሲ መፈጠሩን እርግጠኛ መሆን ችያለሁ፡፡ “የአዳም” መፅሐፍት አንባቢዎች የተነጠሉ ወይንም የተለየ ፍላጐት ያላቸው ስለመሆናቸው ከዚህ ቀደም ይታማ ነበር… ዛሬ ግን የአዳም መንገድ እና የሀገሬው መንገድ አንድ መሆን ችለዋል፡፡ ስለዚህ … የአየር ጠባይ በአዲስ አበባ፣ በደሴ፣ በደብረማርቆስ፣ በሐረር፣ በድሬዳዋ ተብሎ የተለያየ የሙቀት እና ቅዝቃዜ መጠን መተንበይ አያስፈልገውም፡፡ መፅሐ
ፍትን በተመለከተ…. ተመሳሳይ የአየር ጠባይ ለስድስት ወር በሀገሩ ላይ በአጠቃላይ ይሰፍናል፡፡ የአየሩ ጠባይ ደግሞ ሞቃት ነው የሚሆነው…. የሙቀቱ መንስኤ አዳም ረታ ነው፡፡ የሙቀቱ ልክ “መረቅ” ይሰኛል፡፡

Read 2459 times