Saturday, 25 October 2014 10:28

የህፃናት ጥግ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ሞቶ ገዳይ
እግሬን ዛሬ ወስዶ - እጄን እያስቀረ
እያማ ሊበላኝ - ማሰቡ ካልቀረ
የግፍ ጥርሱ ገጦ----
በኔ ጣር አጊጦ-----
ይኖራል እንዳይል የአዳኜ ሹል ስልጣን
አፈንድቼ እምጥል - ስለምሆን ቁንጣን
ቀስ በቀስ ስሞት እንዳይበዛ ነውሬ…፣
            ባንዴ እሚሰለቅጥ - እዘዝልኝ አውሬ፡፡
     ድኖ መግደል!
አምና የዛሬ አመት  - እሁድ አጠባብ ላይ
ሳይፈልጠው ሳይቆርጠው - ታዝዞበት ከላይ
በእለተ ፋሲካ - በሚዳንበት ቀን
ልጅ ሞቶብን ድንገት . . . ከአፈር ጋር አስታርቀን
ቀብረነው ስንመጣ . . . ቢሆነን ሰቀቀን
ይህን ብላቴና . . . ገና እሱ ተፈርቶ
እንዴት ይወስደዋል - ያለ ቀኑ ጠርቶ
አየ የሱ ነገር - አይገርመው እይጨንቀው
የእናትና ልጅን ነገር እያወቀው
ከቀንም ቀን መርጦ ያውም በፋሲካ
ይኸ የማርያም ልጅ . . .
እንዲያው ባል አያውቅም - ስራ አይፈታም ለካ
እያልን እያማን ሳል . . .  ፈጣሪን በትዝብት
መፅናናት ልንፈጥር ለሟቹ እናት አባት
ድንገት የልጁ አባት - ስሜቱ ገንፍሎ
በሚያባባ ዜማ - ጉሮሮውን ስሎ
ፈጣሪን ወቀሰው - አማው እንዲህ ብሎ
“እንደዚህ ያለ ፍርድ - የተገመደለ
በትንሳኤው ምድር - ስንት ቀን እያለ
ኧረ የጉድ አገር - እግዜር ተሳስቶ
ልጄን ገደለብኝ - የራሱን ተነስቶ”፡፡
(ለእየየ)

ስርዝ ድልዝ
ደም የሚፈሰው ልብ በሹል ጦር ተወግቶ
ከጎን ፅጌሬዳ . . .
እምቡጡ ፈንድቶ በቀይ እስክሪቢቶ …
ከሳለችበት ሉክ ከጥቅሱ ቀጥሎ
የላከችልኝን የፍቅር ደብዳቤ …
ሊያነብ እጄ ሲገልጥ እጥፋቱን ነጥሎ
ቁልጭ ካለው ፅሁፍ ከተደረደረው
ልቤ የጓጓለት ሊያነበው ያማረው
መቼ ዝርዝሩን ሆነ የፍቅሯን ሀተታ
ድልዙን ቃል እንጂ . . .
ያስቀረችብኝን ሰርዛ አመንትታ፡፡

(በቅርቡ ለንባብ ከሚበቃው “ቁመታም ጾም” የተሰኘው የአያሌው እውነቴ የግጥም መድብል)

Read 1238 times