Saturday, 25 October 2014 10:38

ተክሌ ዘዋሸራ እንዲያ አልዘረፉም

Written by  ኦርዮን ወ/ዳዊት
Rate this item
(3 votes)

ሕፅንም ጭን እንጂ ባዶ ቦታ አይደለም!
ባለፈው ሳምንት በወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ጥበብ አምድ ላይ “ምድጃ ዳር ፥ ለገላ ነው ለትዝታ?” በሚል ርዕስ አብደላ ዕዝራ በተባሉ ጸሐፊ የቀረበውን ጽሑፍ በጥንቃቄ አንብቤያለሁ፡፡ በጥንቃቄ ስል የአብደላን ጽሑፎች በፍቅር ስለማነብባቸው “ዛሬስ ምን አዲስ ነገር ይዞልን መጣ ይሆን?” ከሚል ጉጉት የመነጨ ነው፡፡
አብደላ የጽሑፉ መስፈንጠሪያ ያደረገው በኤፍሬም ሥዩም “ተዋነይ ብሎይ የግዕዝ ቅኔያት ፍልስፍና” መጽሐፍ ውስጥ ያለውንና 65ኛውን ጉባኤ ቃና ነው፡፡ ጉባኤ ቃናው የሊቁ ተክሌ ዘዋሸራ መሆኑን በትውፊትም በመጻሕፍትም የተገኙ መረጃዎች ያረጋግጣሉ፡፡ ለጽሑፌ መነሻ የሆነኝ ግን የጉባኤ ቃናው የባለቤትነት ጥያቄ አይደለም፤ ይልቁንም አብደላ ለጉባኤ ቃናው የሰጠው ፍካሬያዊ ትርጉም ነው የጽሑፌ ዋና ዓላማ፡፡
ሊቁ ተክሌ ይህንን ጉባኤ ቃና የዘረፉት የድንግል ማርያም መታሰቢያ ዕለት ነው፤ ድንግል ማርያም ጌታን (ኢየሱስ ክርስቶስን) ስትወልድ ገና 15 ዓመት እንኳ በወጉ ያልሞላት ልጅ ነበረች፡፡ ይህን ሲያደንቅ ነው ሊቁ ተክሌ፡-
“ድንግል ወለት ትመስለነ ዕቤርተ፤
አኮኑ ትውዕል እንዘ ተሐቅፍ እሳተ”
የሚል ቅኔ የዘረፉት፡፡ ትርጉሙ “ማርያም ድንግል ገና ህፃን ሳለች እመበለት ትመስላለች፡፡ ምክንያቱም እሳት ታቅፋ ትውላለችና!” ማለት ነው፡፡ ይህ ሰሙ ነው፤ ወርቁ ግን ድንግል ማርያም ሰማይና ምድር መሸከም ያልቻሉትን የእግዚአብሔርን ልጅ ወልድን፤ አባ ሕርያቆስ የተባለው ሊቀ ጳጳስ “አብ እሳት ነው፣ ወልድ እሳት ነው፤ መንፈስ ቅዱስም እሳት ነው” ብሎ ባህርየ መለኮቱን ግርማ ርዕየቱን ያደነቀውን እሳት ለመታቀፍ የበቃችበትን ተአምራዊ ኃይል ለማድነቅ ነው እንጂ አብደላ እንደተገነዘበው በምንም መንገድ ከፍትወት ጋር የተያያዘ ምስጢር የለውም፡፡
አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም ላይ ይህንኑ ጉዳይ በአንክሮ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፤ “… ኦ ድንግል ሶበኀደረ ውስተ ከርስኪ እሳተ መለኮት፤ ገጹ እሳት፣ ልብሱ እሳት፣ ክዳኑ እሳት እፎኒ ኢያው ዐየኪ?” ነጠላ ትርጉሙ “ድንግል ሆይ! ፊቱ እሳት፣ ልብሱ እሳት፣ መሸፈኛው እሳት የሆነ የመለኮት እሳት በማህጸንሽ ባደረ ጊዜ እንዴት አላቃጠለሽም?!” ማለት ነው፡፡
ይህ ማለት ታዲያ የመለኮትን ኃይል፣ ሙሴና ኤልያስ እንኳ ደፍረው ከፊቴ ለመቆም ያልቻሉትን እንዴት አንቺ በማህጸንሽ ለዘጠኝ ወራት ተሸከምሽው? እንዴትስ እሳቱን ታቅፈሽ እንደ ህፃን አጫወትሽው?” እያለ ረቂቁን ባህርየ መለኮት አጠየቀ እንጂ አብደላ እንዳሰበው ከርካሹ ዓለማዊ ፍትወት ጋር የሚያቆራኘው አንድም ምክንያት የለም፡፡
“ከጳጳሱ ቄሱ” እንዲሉ ካልሆነ በቀር መቸም አብደላ የአለቃ ተክሌን ቅኔ ከተክሌ በላይ ሊገነዘበው አይችልም፤  ያ ባይሆን ኖሮ “ከትዳር ቀለበት ሾልከው፣ ሌላውንም በወሲብ መቅመስ ሳይደፍሩ የቀሩት፤ በስተርጅና ለመቆጨትም በትዝታም ለመፍለቅለቅ እንደ ስንቅ ነው፤ ዕድሜ መች መክሰም ብቻ ሆነ? ዘዋሸራ ተክሌ ከነገረ መለኮት ሱባኤ ስሜታቸውን ጎትተው ግራ ቀኝ ገላምጠው ድንግል ልጃገረድ ያቀፈችው እሳት እንዴት አባበላቸው? እንዴት ለመቀኘት እርሾ ሆናቸው? ቢያሰኝም በሄዋን ውበትና እጣፈንታ መመሰጥ ለባለ ቅኔ አንድ የህይወት ሰበዝ ነው፡፡ … ዘዋሸራ የተቀኘላት ልጃገረድ የታቀፈችውን እሳት ከሰብለወንጌል ጀምሮ በአያሌ ልብወለድ ተቀርፃለች” ሊል አይደፍርም ነበር፡፡
አዎ ድፍረት ነው፤ ቅድስት ማርያም በድንግልና ፀንሳ በድንግልና አምላክን መውለዷን መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ቅዱስ ቁርዓን ያረጋግጣሉ፡፡ ባለቅኔውም እንደ ጸሐፊው እምነት ፍትወት አቃጥሏቸው፣ የልጃገረድ ፍቅር አማልሏቸው የዘረፉት ሳይሆን ባህርየ መለኮትን በድንግልና እናትነትን ገለጹበት እንጂ ስለተባለው ነገር በቅኔው ውስጥ የሰናፍጭ ቅንጣት ያህል ሰበብ እንኳ የለም፡፡
እናም ቅኔን ሲፈቱ ታሪኩን ማወቅ በእጅጉ ጠቃሚ ከመሆኑም በላይ፤ የቅኔው ባህርይ ወይም ዓይነት ሰምናወርቅ፣ ወይም ውስጠዘ፣ ወይም ህብር፣ ሰረዝ፣ ወፍ እግር፣ ዝምዝምወርቅ፣ ወዘተ መሆኑን መለየት ትክከለኛ ትርጉሙን ለመስጠት ይረዳናል፡፡ ክርክር የገጠምንበት የአለቃ ተክሌ ጉባኤ ቃና ግን “ሰምና ወርቅ” በሚባለው መንገድ የተዘረፈ በመሆኑ አስተያየት ስንሰጥም የሰምናወርቅ ቅኔ ህግጋት የሚጠይቁትን መስፈርት ግምት ውስጥ በማስገባት ቢሆን የግድ ነው፡፡
ሌላውና አብደላ በተደጋጋሚ ጊዜ ተገቢ ባልሆነ መንገድ የተጠቀመበት የቅኔው ባለቤት ስም ነው፡፡ የቅኔው ዘራፊ “አለቃ ተክሌ ዘዋሸራ” ይባላሉ፤ “አለቃ” የማዕረግ ስማቸው ሲሆን ትክክለኛ ስማቸው “ተክሌ” ይባላል፡፡ “ዘዋሸራ” ማለት ግን “የዋሸራው” ማለት ነው፡፡ በአንድነት “ተክሌ ዘዋሸራ” ሲባል ግን “የዋሸራው ተክሌ” ተብሎ ይነበባል፤ ወይም ይታወቃል “አብደላ ዕዝራ ከሰነአ እንደማለት፡፡
ምንም እንኳ ከአብደላ ሥራ ጋር ባይገናኝም በዚሁ ጋዜጣ ጥበብ አምድ ላይ “ዮሐንስ ገለታ” የተባሉ ጸሀፊ “የአዳም ረታ ሕጽናዊነት ምንድን ነው?” ሲሉ በተጠቀሙበት ቃልም ትንሽ ማብራሪያ መስጠት አስፈላጊ መስሎ ታይቶኛል፡፡
ጸሐፊው ህፅናዊነትን ሲተረጉሙት “የቃሉ አፈጣጠር/ አመጣጥ ሕጽናዊነትና ዘይቤ ምን አገናኘው ብሎ የሚጠይቅ ይኖር ይሆናል፡፡     ሕጽን የግዕዝ ቃል ሲሆን ትርጉሙም በሁለት ፊደሎች መሃል ያለው ክፍተት ማለት ነው፤ ጽሑፍ ሊነበብ የሚችለው ይሄ ባዶ ቦታ በየፊደላቱ መካከል በመኖሩ ምክንያት ነው፡፡ በፊደል ገበታ ውስጥ ያሉት ክፍት ቦታዎች ደግሞ ማህጸን ይሰኛሉ” ብለዋል፡፡ ከየትኛው የግዕዝ መፍትሔ ቃላት ላይ እንዳገኙት ባላውቅም እንዲህ የሚል የግዕዝ መጽሐፍ ወይም መፍትሄ ቃላት አላየሁም፡፡
በግዕዝ መፍትሔ ቃላት ዝግጅት እስካሁን ተጠቃሽ የሆኑት ሊቁ አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ “መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ፣ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ” በተባለው ታላቅ መጽሐፋቸው ለሕፅን የሰጡት ትርጉም እንዲህ የሚል ነው፡፡
“ሕፅን በቁሙ፣ ማቀፊያ፣ ጭን፣ ደረት፣ ደረትና የእጅ መካከል ብብት፣ ጎን፣ ግብጣ፣ እንቢርቢጣ፣ የቀሚስ ሰላጤ፣ በሰላጤው ላይ የሚሰፋ ኪስ፣ ጀብ፣ ጥግ፣ ቅርብ፣ አጠገብ፣ የቦታ” የሚል ትርጉም ሰጥተዋል፡፡
ለማስረጃነትም “ውስተ ሕፅነ እሞሙ፤ አንበሮሙ ውስተ ሕፅኑ፡፡ ደይ እዴከ ውስተ ሕፅንከ (… በእናታቸው ጭን ውስጥ፤ በጭኑ ላይ አስቀመጣቸው፤ እጅህን በብብትህ ውስጥ አኑር…)” የሚሉ ጥቅሶችን ከማርቆስ ወንጌል 10፥16፣ ኦሪት ዘፀዓት 4፡6 እና 7 እንዲሁም ኩፋሌ ስምንትን በማስረጃነት በማስደገፍ አሳይተዋል፡፡
የቅኔና የትርጓሜ መጻሕፍት ሊቁ መምህር አፈወርቅ ተክሌ በ2005 ዓ.ም ባሳተሙትና “መጽሐፈ ታሪክ ወግስ” የሚል ርዕስ በሰጡት የመፍትሔ ቃላት መጽሐፋቸው ለ “ሕፅን ሕፀን፣ ታናሽ ልጅ፣ ብብትና ክንድ አጠገብ፣ እንግዴ ልጅ” የሚል ትርጉም ሰጥተዋል፡፡
ለዚህም ነው የአቶ ዮሐንስ ገለታ ጽሑፍ ዋና ፍሬ ሃሳብ የሆነው ሕንጽ የትመጣው አይታወቅም የምለው፡፡ ከሁለቱም ሊቃውንት መጻሕፍት ውጭ ያሉ ተመሳሳይ መፍትሔ ቃላትንም ለማየት ሞክሬያለሁ፤ ግን አንድም ከአቶ ዮሐንስ ትርጉም ጋር የሚቀራረብ ቃል እንኳ ማግኘት አልቻልሁም፡፡ እናም እባክዎ አቶ ዮሐንስ የተጠቀሙበትን ምንጭ ይንገሩን?

Read 3927 times