Saturday, 08 November 2014 10:56

ከኮንዶሚኒየም ተመዝጋቢዎች ከ4 ቢ. ብር በላይ ተሰብስቧል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(13 votes)

ከ140ሺ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ አልተጠናቀቀም

በአዲስ አበባ መሚገነቡ የ20/80፣ 10/90 እና 40/60 እንዲሁም ከመኖሪያ ቤት ህብረት ሥራ ማህበራት ተመዝጋቢዎች በቁጠባ መልክ የተሰበሰበው ገንዘብ 4.1 ቢሊዮን ብር መድረሱ ተገለፀ፡፡
በሥራ ተቋራጮችና በአማካሪ ኩባንያዎች ብቃት ማነስ ሳቢያ ከ140ሺ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ አልተጠናቀቀም ተብሏል፡፡
የከተማ ልማት ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መኩሪያ ኃይሌ ሰሞኑን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ዕቅድና የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ እንደገለፁት፤ ለኮንዶሚኒየም ቤቶች ከተመዘገቡና ከመኖሪያ ቤት ህብረት ሥራ ማህበራት ምዝገባ 4.1 ቢሊዮን ብር ተሰብስቧል፡፡ “ይህም የቤት ልማቱን ዘላቂነት ያረጋገጠ ሆኗል” ብለዋል- ሚኒስትሩ፡፡ በከተማው በ2003 እና በ2004 ዓ.ም በ20/80 ፕሮግራም የተጀመሩ 71ሺ 127 ቤቶች ግንባታቸው ሙሉ በሙሉ እንዲጠናቀቅ የታቀደ ቢሆንም በዕቅዱ መሠረት ግንባታው አለመጠናቀቁን አቶ መኩሪያ ተናግረዋል፡፡ በ2006 ግንባታቸው እንዲጀመር ከታቀዱት 50ሺ ቤቶች ግንባታቸው የተጀመረው 13ሺ014 ብቻ እንደሆኑ ጠቁመው በ10/90 ቤቶች ልማት ፕሮግራም በመገንባት ላይ የሚገኙት ቤቶች 24ሺ 288 ሲሆኑ የእነዚህም የግንባታ አፈፃፀም 62.17 በመቶ ብቻ መሆኑን ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡
 ለግንባታዎቹ መዘግየት ከጠቀሷቸው ምክንያቶች መካከል የሥራ ተቋራጮችና የአማካሪ ኩባንያዎች ብቃት ማነስ፣ የባለሙያዎች እጥረት፣ የመሠረተ ልማት አቅርቦት ችግር፣ የመሬት አቅርቦት እጥረትና የክትትልና ድጋፍ ውስንነት ዋንኞቹ እንደሆኑ አብራርተዋል፡፡ ዘንድሮ በ10/90 ቤቶች ፕሮግራም 10ሺ340 ቤቶች፣ በ20/80 ቁጠባ ቤቶች ፕሮግራም 60ሺ740 ቤቶች፣ በ40/60 ቤቶች ፕሮግራም ደግሞ 17ሺ870 ቤቶችና በማህበራት 4870 መኖሪያ ቤቶች ለመገንባት ዕቅድ መያዙንም አቶ መኩሪያ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ ገልፀዋል፡፡

Read 4578 times