Saturday, 29 November 2014 10:37

ፈተና ሲርቅ ይቀላል?

Written by  ነ.መ
Rate this item
(0 votes)


በዚች ጠባብ ዓለም
መቼም አያጋጥም የለም
    ያንድ ጓደኛዬን ወንድም፣ ለፈተና ላዘጋጀው
    እስቲ ማትሪክ ይቅናው ብዬ፣ ትምህርቱን በወግ ላስጠናው
    ለፍቼ  አንድ ዓመት ሙሉ፣ በል ይቅናህ? ብዬ ሸኝቼው
    ሞራል ባርኬ ሰጥቼው
    ያለኝን ዕውቀት ለግሼው፡፡
    አመስግኖኝ ሄደ ፈጥኖ፣ የጭንቁን ቀን ሊጋተረው!
    መቼም የየኑሮው ፍልሚያ፣ ግቡ ፈተናን ማለፍ ነው!
ዛሬ ጊዜው የእርም ቀን ነው
“ይቅናህ!” እንጂ ሰው ቃል የለው
ያውም ደጉ ቢገኝ እንጂ፣ ልቡ እንደኪሱ ባዶ ነው!
ፈተና መፈተን በቀር
ማለፍ ጠቦ እንደገነት በር
ስንቱ ደጁ ሲንፈራፈር
ይታያል በየክፍሉ ፈር፡፡
*      *     *
የማትሪክ ፈተና አለቀ … ያስጠናሁት ልጅ አልመጣም
አንድ ወር ሁለት ወር አለፈ …. አጅሬ ግን ዝር አላለም!
“የዛሬ ልጅ!” አልኩ አዝኜ … ቅስሜን ቢቀጨኝ ድርጊቱ፡፡
“አይ ወጣቱ!”
ከበደኝ ቀለለኝ ሳይል … ምስጋና እንኳ መሰሰቱ!
*      *     *
አንድ ሶስት ወር አለፈና
ስጓዝ ባንድ አውራ ጎዳና
ያን ያስጠናሁትን ወጣት
ፊት ለፊት ባገኘው ድንገት
ቀልቡ ከላዩ ረግፎ፣ ዐይኑ ሲፈጥጥ አየሁት
“ኧረ አይዞህ” “አይዞህ አይዞህ”፣ አልኩት በቅን ለማፅናናት
“ያለፈው አልፏል እንግዲህ፣ እንዳይለምድህ ለወደፊት
እንደው የሆነስ ሆነና፣ ፈተናውስ እንዴት ነበር?”
ብዬ አርግቤ ብጠይቀው፣
ተንፍሶ ቁና ቁና
ጥቂት አየር ወሰደና
“አሁን ቀለል እያለኝ መጥቷል!” ብሎ መለሰ ወጣቱ
ይሄ ነው ጊዜው ክፋቱ!
ፈተናውን ሸሸው እንጂ፣ አይቀርለትም ውጤቱ!
ለካስ እየራቁት ሲኬድ፣ ፈተና ይቀላልሳ  
ሲጨብጡት ሲቀርቡት ነው፣ ህይወት ጭንቁ መቶ - ታምሣ
ቸል ብለው ሲቀመጡ፣ እየረሳሱት ሲሄዱ
እጅግ ከባዱም ፈተና፣ ይደበዝዛል ጣር ጉዱ!
ክፉ - ጉድ ሲርቅ ይረግባል
እያደር ቀን ሲገፋ ግን፣ የጠፋ መስሎ ያጠፋል!
*      *     *
እንደዚህ ነው ፈተናችን፣
የዛሬው ቀሳፊ ዘመን!
የሰከነ ልብ ላለው፣ የሰከነ ኑሮ ላሻ
ለየቀኑ ክቡር ህይወት፣ ንፁህ ተስፋን መጠንሰሻ
ለሰው ቅን ማሰብ ነው ደጉ፣ አገር በውል መፈወሻ!
የየፈተናችን ሀቁ
መስራትና ወገን ማዳን፣ እውነት መናገር ነው ጭንቁ፤
ቀርቦ ማየት ነው ራቡ፣ ሰውን ማስታመም ነው ሰቁ!!
የወገናችን ጭንቅ ቀን፣ ምጡ ምንም ቢጎነጎን
አጥንተን ማለፍ ነው እንጂ፣ ፈተናን መሸሽ አይጠቅመን!
ዛሬ የሚቀስፈን ህመም፣ ያገር ህመም ሰቆቃችን
በተስፋ አቅም ይሸነፋል፣ በልባም ልጅ ብርሃን ቀን
ፈተናውን መጋተር ነው፣ ማጥቃትና መከላከል
ያኔ ነው የህመማችን፣ ፈተናው ቀለለ እሚባል!!
ባይቀናን ብንወድቅም እንኳ ዳግም መፈተን አለብን
ማጥናትና መጥናት እንጂ፣ የትም አንደርስም ተሰደን፡፡
(ከችግር ለማምለጥ ችግር ውስጥ ለሚገቡ ወገኖቼ)
ታህሣሥ 28 1995 ዓ.ም

Read 1964 times