Saturday, 29 November 2014 10:50

የውጭ አገር ሥራ ስምሪት ረቂቅ አዋጅ እያወዛገበ ነው

Written by 
Rate this item
(35 votes)

ፈቃድ ለማግኘት ከ1ሚ. ብር በላይ ካፒታልና 2 ሚ. ብር ዝግ ሂሳብ ያስፈልጋል
ኤጀንሲዎች ከተጓዥ ክፍያ ሊጠይቁ አይችሉም፡፡ 8ኛ ክፍል ያላጠናቀቀና የሙያ ማረጋገጫ የሌለው መሄድ አይችልም፡፡
ባለፉት 7 ወራት 50ሺ ኢትዮጵያውያን በህገ ወጥ ጉዞ የመን ገብተዋል፡፡

ወደ አረብ አገራት የሚሄዱ ሰራተኞች ላይ የሚደርሰውን ችግርና እንግልት ለማስቀረት በሚል ከአንድ ዓመት በላይ ተቋርጦ የቆየውን አሰራር ለማስጀመርና ለመቆጣጠር የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ውዝግብ አስነሳ፡፡
በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ወደ ውጭ አገር ሰራተኞችን የሚልኩ ኤጀንሲዎች፣ የግለሰብ ድርጅት ከሆነ አንድ ሚሊዮን ብር የሽርክና ማህበር ከሆነ ደግሞ አምስት ሚሊዮን ብር ካፒታል ሊኖረው ይገባል ይላል፡፡ ኤጀንሲው ለሰራተኛው መብትና ደህንነት ዋስትና ማስከበሪያ የሚውል 100 ሺህ ዶላር (ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ) በዝግ ሂሳብ የማስቀመጥ ግዴታ አለበት፡፡
 ኤጀንሲዎች ለስራ ወደ ውጭ አገር የላኳቸውን ሰራተኞች ለኢትዮጵያ ኤምባሲ በ15 ቀን ውስጥ ማስመዝገብና የስራ ፈቃድ ማግኘታቸውን የሚያረጋግጥ መረጃ ለሚኒስቴሩ ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ኤጀንሲዎች ለሚሰጡት አገልግሎት ምንም ዓይነት ክፍያን መጠየቅ አይችሉም፡፡ ረቂቅ አዋጁ በውጭ አገር ስራ ለመሰማራት የሚፈልጉ ዜጎችን ዕድል የሚያጠብና ህገ ወጥነትን የሚያባብስ ነው ሉ በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩ ሰዎች ተናግረዋል፡፡ ኤጀንሲዎች በስራው ለመሰማራት የሚያስችሏቸውን መስፈርቶች በሙሉ አሟልተው ለመቅረብ በእጅጉ እንደሚቸገሩና ረቂቅ አዋጁ መሻሻልና መታረም እንደሚገባውም ተናግረዋል፡፡ የአረብ አገራት ጉዞ በመንግስት ከታገደ ወዲህ ባሉት ሰባት ወራት 50 ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን የመን መግባታቸውንና ባለፈው ጥቅምት ወር ብቻ በህገወጥ መንገድ የመን የገቡ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ስምንት ሺህ መድረሱን የተባበሩት መንግስታት ሪፖርት አመልክቷል፡፡


Read 11041 times