Saturday, 29 November 2014 11:40

የአፍሪካ ዋንጫ ከ30ኛው በኋላ ወደ ምዕራብ አጋድሏል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(4 votes)
  • ናይጄርያ ፤ ግብፅና ምስራቅ አፍሪካም የሉበትም
  • የዋልያዎቹ የውድቀት ሰበብ፤ ባሬቶ ወይስ ፌደሬሽኑ?

      30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ከ62 ቀናት በኋላ በኢኳቶርያል ጊኒ አዘጋጅነት ይጀመራል፡፡ ምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር በአራት ዓመት ውስጥ ሁለት አፍሪካ ዋንጫዎች ለማዘጋጀት በቅታለች፡፡ የመጀመርያው በ2012 እኤአ ከጋቦን ጋር በጣምራ ያዘጋጀችው 28ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ነው፡፡ በኢቦላ ወረርሽኝ በመታመስ ሊስተጓጎል የነበረውን 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ  ውድድሩ 5 ወር ሲቀረው መስተንግዶዋን በውዝግብ እና ቅጣቶች በተወችው ሞሮኮ  ምትክ ኢኳቶርያል ጊኒ አዘጋጅ ሆናለች፡፡ የአገሪቱ በበጀት አቅም፤ በአዳዲስ ስታድዬሞች እና በአስፈላጊ መሰረተ ልማቶቿ መሟላት የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽንን ታድጓል፡፡ በኒሳን ኩባንያ ስፖንሰር ለተደረገው 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ  አዲስ ኳስ ‹‹መርሃባ›› በሚል ስያሜ በአዲዳስ እንደቀረበች ታውቋል፡፡
በ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ ለሆኑት 16 ብሄራዊ ቡድኖች  የምድብ ድልድል በሚቀጥለው ሳምንት ይወጣል፡፡ በእጣ አወጣጡ ስነስርዓት አገራቱ በአራት ማሰሮዎች  ለእጣ ይቀመጣሉ፡፡ በማሰሮ 1 ኢኳቶርያል ጊኒ፣ ጋና፣ ዛምቢያና ቡርኪናፋሶ፤ በማሰሮ 2 አይቬሪኮስት፣ ማሊ፣ ቱኒዚያ እና አልጄርያ፤ በማሰሮ 3 ኬፕቬርዴ፣ ጋቦን፣ ዲ ሪፖብሊክ ኮንጎ እና ደቡብ አፍሪካ እንዲሁም በማሰሮ 4 ካሜሮን፣ ሴኔጋል፣ ጊኒና ኮንጎ ይገኛሉ፡፡ በ16ቱ ብሄራዊ ቡድኖች የሚገኙት 399 ተጨዋቾች በዝውውር ገበያው አጠቃላይ የዋጋ ግምታቸው 713.10 ሚሊዮን ዩሮ ይገመታል፡፡
የአፍሪካ ዋንጫው ወደ ምዕራብ  ማጋደል
ከ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ  አንስቶየአህጉራዊው ውድድር የሃይል ሚዛን ወደ ምዕራባዊው ዞን ማጋደሉ በግልፅ ይስተዋላል፡፡ ከምዕራባዊው የአፍሪካ ዋንጫ ዞን የተወከሉ ቡድኖች በምድብ ማጣርያ በስታትስቲክስ የነበራቸው ብልጫ የመጀመርያው ማስረጃ ነው፡፡  28 ብሄራዊ ቡድኖች በ7 ምድብ ተከፍለው ያከናወኑት የምድብ ማጣርያ ሶስት ወራትን የፈጀ ነበር፡፡ 84 ጨዋታዎች 193 ጎሎች ከመረብ ሲዋሃዱ የምዕራብአፍሪካ ብሄራዊ ቡድኖች ዋና ተዋናዮች ነበሩ፡፡ የቡርኪናፋሶው ጆናታን ፕሪቶፕያ በ6 ጎሎች ከፍተኛው ግብ አግቢ ሆኗል፡፡ በምድብ ማጣርያው ብዙ በማግባት 13 ጎሎች ያስመዘገበው ደግሞ የኮትዲቯር ቡድን  ነው፡፡ እያንዳንዳቸው አንድ ጎል ብቻ ተቆጥሮባቸው ከፍተኛ የመከላከል ብቃት ያሳዩት ደግሞ ካሜሮን እና ሴኔጋል ናቸው፡፡ በምድብ ማጣርያው ደቡብ አፍሪካ፤ ካሜሮን፤ ጋቦንና ቱኒዚያ ያለሽንፈት ማለፋቸውን ማረጋገጣቸው ብቻ የምእራቡን ብልጫ ያጠበበ ነው፡፡  በምድብ ማጣርያው የሰሜን አፍሪካ ቡድኖች አልሆናቸውም፡፡ ሁለት አገራት ሊቢያ እና ሞሮኮ አንዱ ባለመረጋጋት ሌላው በኢቦላ ስጋት የአፍሪካ ዋንጫንበአዘጋጅነት የመሳተፍ እድል ማጣታቸው የመጀመርያው ክስረት ነው፡፡  7 ጊዜ የአፍሪካ ሻምፒዮን በመሆን በከፍተኛ ውጤት ክብረወሰን የያዘችው ግብፅ ሶስተኛ ተከታታይ የአፍሪካ ዋንጫ ሳታልፍ መቅረቷ ደግሞ ሁኔታውን አባብሶታል፡፡  ከምእራብ አፍሪካ ያልተሳካለት ያለፈው አፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮን የሆነው የናይጄርያ ቡድን ነው፡፡ ለውድቀቱ ደግሞ በእግር ኳስ ፌደሬሽን አካባቢ የተፈጠረው ፖለቲካዊ ትርምስ እና ዋና አሰልጣኙ ስቴፈን ኬሺ ተጠያቂ ተደርገዋል፡፡ በ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከሚሳተፉ አገራት  የአንበሳውን ድርሻ የያዘው በ9 አገራት የተወከለው ምዕራብ አፍሪካ ነው፡፡ ሴኔጋል ፤ ኬፕቬርዴ ፤ማሊ ፤አይቬሪኮስት ፤ጋና ፤ጋቦን ፤ቡርኪናፋሶ፤ ጊኒና አዘጋጇ ኢኳቶርያል ጊኒ ናቸው፡፡ በካሜሮን፤ ኮንጎ እና ዲሪ ኮንጎ የሚወከለው ማዕከላዊው አፍሪካ ይሆናል፡፡  ሰሜን አፍሪካ በቱኒዚያና  አልጄርያ  ሲወሰን ደቡባዊው አፍሪካ በመወከል  ደግሞ በደቡብ አፍሪካ እና በዛምቢያ ይገኛሉ፡፡ ምስራቃዊው የአፍሪካ ክፍል ግን  ከ2 ተከታታይ የአፍሪካ ዋንጫዎች በኋላ ተወካይ አይኖረውም፡፡ የደቡብ እና የምስራቅ አፍሪካ አገራት በአፍሪካ ዋንጫ ለመግባት በማጣርያውእና ከዚያም በዋናው ውድድር ውጤታማ ለመሆን ቸግሯቸዋል፡፡ በደቡባዊው የአፍሪካ ዋንጫ ክፍል የሚወዳደሩ አገራት ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ መክበድ አልነበረበትም፡፡ ደቡብአፍሪካ በዓለም ዋንጫ እና በአፍሪካዋንጫ አዘጋጅነት፤ በሊግ ውድድድሯ ጥንካሬ እና የክለቦቿ አህጉራዊ ውጤታማነት እንደምንም ለውድድሩ መብቃቷ አልቀረም፡፡ በአስተማማኝ ሁኔታ ያለፈችው የኛው የአፍሪካዋንጫ ዛምቢያ ናት፡፡ እነ አንጎላ፤ ማላዊ እና ዚምባቡዌ እና በተሳትፏቸውም ስኬት ለማግኘት ተቸግረዋል፡፡ በዋናነት ስፖርቱ በመሰረታዊ ደረጃ ስላልተሰራበት እንደሆነ የሚገልፀው የሱፕርስፖርት ትንታኔ ነው፡፡ አንዳንዶቹ አገራት በበቂ በጀት አለመስራታቸው ደካማ አድርጓቸዋል፡፡ ፌደሬሽኖች የጉዞ ወጭን ለመሸፈን ተቸግረዋል፡፡ የውስጥ የሊግ ውድድሮች አለመጠናከርም ከምእራብ አፍሪካው እግር ኳስ እጅግ ወደኋላ እያስቀራቸው ነው፡፡  ምስራቃዊው የአፍሪካ ክፍል በውድድሩ ክብደት መፎካከር ያቃተው ከደቡቡ በባሰ ነው፡፡ ባለፉት ሶስት አፍሪካ ዋንጫዎች ሱዳንና ኢትዮጵያ ዞኑን በመወከል እግር ኳሱን ሊያነቃቁ ሞክረዋል፡፡ አስተማማኝ ቡድን ያለው አገር ግን የለም በሚል የሚተነትነው የሱፕር ስፖርት ሀተታ ነው፤ የዞኑ እግር ኳስ በአፍሪካ ደረጃ ደካማ የሆነባቸው ምክንያቶች ብዙ ናቸው፡፡የፌደሬሽኖች ድክመት፤ የአሰልጣኞች የስራ ውጣውረድ፤ የበጀት አቅም መዳከም እና በአህጉራዊ ውድድሮች የክለቦችየፉክክር ደረጃ ማነሱን ዘርዝሯል፡፡ ለነገሩ የምስራቅ አፍሪካ አገራት እንኳንስ በአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ ይቅርና የዞኑን ዋና ውድድር ሴካፋሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ የሚያዘጋጅ ጠፍቶ በአሳሳቢ ውድቀት ውስጥ ይገኛል፡፡ በተያያዘ  የሚነሳው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ዞናዊ እና አህጉራዊ ውድድሮችን የማስተናገድ ምኞቱ በአቅም ማነስ እና በእቅድ ባለመስራት እንደተበላሸበት ነው፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ የዛሬ ሳምንት ማዘጋጀት የነበረበትን የ2014 ሴካፋ ሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ በበጀት እጥረት ላለማስተናገድ የወሰነው ከወር በፊት እንደሆነ አይዘነጋም፡፡ ውሳኔው የዞኑን የእግር ኳስ ምክር ቤት አስቀይሟል፡፡ የሴካፋ ዋና ውድድር የሆነውን ሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ የሚያዘጋጅ አገር በ11ኛው ሰዓት ሲታቀብ የመጀመርያው አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ውድድሩን ከማስተናገድ የተቆጠበችው ከስፖንሰርሺፕ እና ከብሄራዊ ቡድን አጠቃላይ ዝግጅት በተያያዘ ውስብስብ ሁኔታዎች ስለተፈጠሩ እና የኤቦላ ወረረሽኝ ስጋት ሰበቦቿ እንደሆኑ ተዘግቧል፡፡ ኢትዮጵያን በመተካት የሴካፋው ፕሬዝዳንት መቀመጫ የሆነችው ታንዛኒያ እንድታዘጋጅ የዞኑ እግር ኳስ ምክር ቤት ደጅ እየጠና ነው፡፡ ሱዳንም ምላሽ ከመስጠት መቆጠቧ አዘጋጅ መገኘቱን አጠራጣሪ አድርጎታል፡፡ ምናልባት የምስራቅ አፍሪካ  ብሄራዊ ቡድኖች በአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ እድል የሚኖራቸው ውድድሩን በማዘጋጀት ብቻ ይመስላል፡፡ አፍሪካ ዋንጫን የማዘጋጀት እድል ግን አሁንም በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ምርጫ ወደ ምእራብ አተኩሮ ለሚቀጥሉት አራት የአፍሪካ ዋንጫዎች መቀጠሉ የእግር ኳስደረጃቸውን በይበልጥ እንዳያዳክመው ያሰጋል፡፡
የሰሜን አፍሪካ  ክፍል ሁለት አፍሪካ ዋንጫዎችን ባለማስተናገዱ የአፍሪካ እግር ኳስ ፌደሬሽን ለአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት ወደ ምእራቡ ክፍል አድልቷል፡፡  በምዕራብ አፍሪካ እግር ኳስ ባለው እድገት፤ ለስፖንሰሮች በሚገኝ ትኩረት እና ጥቅም በመሳብ  ካፍ የአፍሪካ ዋንጫውን ወደዚያው ዞን እንዲቀጥል ወስኗል፡፡ ከ30ኛው ጀምሮ ቀጣዮችን የአፍሪካ ዋንጫዎች 3 የምእራብ አፍሪካ አገራት እንዲያስተናግዱ መስጠቱ ማረጋገጫ ነው፡፡  በ2019 እኤአ ካሜሮን 32ኛውን፤ በ2021 እኤአ ኮትዲቯር 33ኛውን እንዲሁም በ2023 እኤአ   ጊኒ  34ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ እንዲያዘጋጁ መመረጣቸው ይታወቃል፡፡ አዘጋጁ ያልታወቀው በማሃል የሚገኘው የ2017 እኤአ 31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ነው፡፡ ለማዘጋጀት የሚፎካከሩት የምእራብ እና የሰሜን አፍሪካ አገራት አልጄርያ፤ ግብፅ፤ ጋቦንና እና ጋና ናቸው፡፡  በአፍሪካ ዋንጫ የ29 ዓመታት ታሪክ ታሪክ 10 ዋንጫዎችን በመውሰድ የሚመራው ሰሜናዊው ዞን ነው፡፡ ግብፅ ለሰባት ጊዜያት እንዲሁም አልጄርያ፤ ሞሮኮ፤ ቱኒዚያ እኩል አንድ ግዜ ሻምፒዮን ሆነዋል፡፡ ምእራባዊው ዞን በስምንት ዋንጫዎች ይከተላል፡፡ ጋና አራት፤ ናይጄርያ 3 እንዲሁም ኮትዲቯር አንድ ዋንጫ አላቸው፡፡፤ ማዕከላዊ ዞን በሰባት ዋንጫዎች ሲመዘገብ፤ ካሜሮን አራት፤ ዲሪ ኮንጎ 2 እንዲሁም ኮንጎ ኪንሻሳ 1 ዋንጫ በማሸነፋቸው ነው፡፡ ምስራቃዊ ዞን በኢትዮጵያ እና በሱዳን እንዲሁም ደቡባዊው ዞን በደቡብ አፍሪካ እና ዛምቢያ እኩል ሁለት የአፍሪካ ዋንጫ ድሎች አግኝተዋል፡፡
ሰበበኞቹ  የማርያኖ ውጣ ውረዶች
በ2013 እኤአ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከ31 ዓመታት መራቅ በኋላ በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በታሪኩ ለ10ኛ ጊዜ ለመሳተፍ መብቃቱ ትልቅ መነቃቃትን የፈጠረ ነበር፡፡ ከዓመት በኋላ ግን ይህን ስኬት መድገም አልቻለም፡፡ ቡድኑ ወደ 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በቀጥታ ምድብ ማጣርያ ውስጥ ከገቡ 24 ቡድኖች አንዱ ነበር፡፡ ቅድመ ማጣርያ ሳያደርግ ለምድብ ማርያ የተደለደለው በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በመሳተፉ  ነበር፡፡ በምድብ ማጣርያው  ካደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎቹ አንዱን አሸንፎ፣ በአራቱ ተሸንፎ እና በአንዱ አቻ ተለያይቶ፣ ሊያገኛቸው ከሚችላቸው 18 ነጥቦች አራቱን ብቻ አግኝቶ ከምድቡ የመጨረሻውን ደረጃ ይዞ አጠናቅቋል፡፡ በተለያዩ ሰበበኛ ውጣውረዶች እና በእግር ኳስ ደረጃው መዳከም ለ11ኛ ጊዜ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ማልፍ ሳይችል ቀርቷል፡፡የተሸነፈባቸው ጨዋታዎች ከሜዳው ውጭ በማላዊ 3ለ2 እንዲሁም በአልጄርያ 2ለ0፤ እንዲሁም በሜዳው በአልጄርያ እና በማሊ በተመሳሳይ 2ለ0 ውጤት በመረታቱ ነበር፡፡ በምድብ 2 የአራተኛ ዙር ጨዋታ ከሜዳ ውጭ ማሊን 3ለ2 ሲያሸንፍ፤ ብቸኛውን የአቻ ውጤት ደግሞ ከማሊ ጋር 0ለ0 በመለያየት ሜዳው ላይ አስመዝግቧል፡፡ በዚህ መሰረት ዋልያዎቹ በምድብ 2  በ4 ነጥብ እና በ5 የግብ እዳ ጨርሰዋል፡፡ ዋና አሰልጣኙ ማርያኖ ባሬቶ በብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝነት ስምንት ወር ሊሆናቸው ነው፡፡ ባደረጓቸው የነጥብ ስድስት ጨዋታዎች  25 በመቶ ድል፤ 30.4 በመቶ አቻ እንዲሁም 44.6 በመቶ ሽንፈት ያስመዘገቡ ሲሆን በአንድ ጨዋታ መገኘት ከሚገባው ነጥብ 0.67 በማግኘት ብቃታቸው በትራንስፈርማርኬት ድረገፅ ተለክቶታል፡፡ እና ለብሄራዊ ቡድኑ የአፍሪካ ማነው ሊጠየቅ የሚችለው ዋና አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ ወይንስ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ
በእርግጥ ዋልያዎቹ ለ30ኛው አፍሪካዋንጫ ለማለፍ በምድብ ማጣሪያ የነበራቸው ጉዞ በብዙ የአቅም ችግሮች ፤ በአወዛጋቢ አጀንዳዎች፤ በአንጋፋ ተጨዋቾች ስንብት፤ ጉዳት እና የትውልድ ሽግግር በውጣውረድ የተሞላ ነበር፡፡ ዋናው ተጠቂ ደግሞ ብሄራዊ ቡድኑን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲያደርጉ ከስምንት ወራት በፊት የተቀጠሩት ዋና አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ ናቸው፡፡ የምድብ ማጣርያው እንደተጠናቀቀ ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ በኮንትራታቸው ዙሪያ እና በፈቃዳቸው ከስልጣናቸው ይለቁ እንደሆነ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡
በ2015 ለሚደረገው 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ቡድኑን ማሳለፍ በኮንትራታቸው ላይ እንዳልሰፈረ እና እሳቸውም በፈቃዳቸው እንደማይለቁ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በአገልግሎት ዘመናቸው እንደ ግብ ያስቀመጧቸውዋና  ነገሮች ለአፍሪካዋንጫ ማለፍአይደለም በሚል ተሟግተዋል፡፡
በሃላፊነቱ በቆዩባቸው 8 ወራት ለወጣቶች እድል መስጠት እና የተጨዋቾችን ብቃት ማሳደግን ማሳካት እንደቻሉ በልበሙሉነት ተናግረዋል፡፡ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ውጤታማነት  ጊዜያዊ መፍትሄ ማሰብ አያወጣም ያሉት አሰልጣኙ፤ የረዥም ጊዜውን በማሰብ መስራት እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡ ስለ መጫወቻ ሜዳዎች እጥረት እና ስለ መንገድ ላይ እግር ኳስ አለመኖር እንዲሁም በወጣቶች እድገት እና በክለቦች ተጨዋች አያያዝ እና በተመሳሳይ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ዋና አሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ ስራቸውን ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ በወዳጅነት ጨዋታዎች አለመኖር፤ በተጨዋቾች ምርጫ ሰፊ አማራጭ በማጣት እንዲሁም በልምምድ ሁኔታዎች አለመመቸት ቅሬታቸውን ሲገልፁ ነበር፡፡ በምድብ ማጣርያው የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች ለብሄራዊ ቡድኑ የልምምድ መስሪያ ትጥቆችና ሌሎች ቁሶች አቅርቦቶች ባለሟሟላቱ ደስተኛ አልነበሩም፡፡ ሊሟሉ የሚገባቸው ነገሮች በፌደሬሽኑ በኩል ባለመፈፀማቸው ፤  ወደ ሜዳ ከወጡ በኋላ ልምምዱን ሳያሰሩ ተጨዋቾቻቸውን ሰብስበው ወደ ሆቴል ተመልሰዋል፡፡
አሰልጣኙ ለነባሮቹም ሆነ አዲስ ለሚመረጡት ተጨዋቾች ፌዴሬሽኑ በግዜው የመጫወቻም ሆነ የመለማመጃ ትጥቆችን በስርዓቱ እንዲያቀርብ ጠይቀው ነበር፡፡ በተጨማሪ 30 የመለማመጃ ኳሶች እና ተንቀሳቃሽ ጎሎችም እንዲዘጋጁላቸውም አመልከተው ነበር፡፡
 እነዚህ አስፈላጊ አቅርቦቶች ስላልተሟሉላቸው ዝግጅታቸው ተስተጓጉሏል፡፡  
በትጥቅ ጉዳይ ግን ፌዴሬሽኑ   ከስፖርት ኮሚሽን ወይም ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እና ሌሎች ድጋፎች ባሻገር ከስፖንሰርሺፕ ውሎች ማግኘት አለመቻሉ ችግሩን እንደፈጠረ መገንዘብ አያዳግትም፡፡፡ በዋልያዎቹ ዋና አሰልጣኝነት ላለፉት ስምንት ወራት የሰሩት የ57 ዓመቱ ማርያኖ ባሬቶ አምስት ቋንቋዎች እንደሚናገሩ ይገለፃል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመስራት በቂ በእንግሊዘኛ የመግባባት ሁኔታዎች ባለመኖራቸው ራዕያቸውን በአስተማማኝ መሰረት ለመገንባት መቸገራቸው አልቀረም፡፡ በጋና፤ በሩስያ፤ በሳይፕረስ እና በሳውዲ አረቢያ የእግር ኳስ ባህሎች በቂ የስልጠና ልምዳቸውን በአጭር ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ በመተግበር ስኬታማ ለመሆን ቢያንስ እስከ 4 ዓመታት ጊዜ ያስፈልጋቸዋል፡፡
 በአሰልጣኝነት ዘመናቸው እነ ሊውስ ፊጎ፤ ሪካርዶ ካልቫሆ፤ ማይክል ኤስዬንና እና ሌሎችን ያፈሩ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል፡፡
 በኢትዮጵያ ታዳጊዎችን አውጥተው ለዚህ ደረጃ ለማብቃት የሚያቀርቧቸውን ስትራቴጂዎች በአግባቡ እየተረጎመ የሚሰራ ፌደሬሽን መኖሩ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ ውጤታማ ብሄራዊ ቡድን ለመገንባት የሀ12 እና ሀ14 ታዳጊ ቡድኖች ውድድር መጀመር ወሳኝ እንደሚሆን በተደጋጋሚ መክረዋል፡፡  በሀ20 ይሰራ ብለው ሃሳብ አቅርበዋል፡፡ እግር ኳስ ፌደሬሽኑ በእነዚህ ደረጃዎች በስፋት የሚሰራበትን አቅጣጫ ሙሉ በሙሉ እየሰራ ግን አይደለም
በፌደሬሽኑ ካዝና መራቆት ውድቀቱ መባባሱ
 አሁን በስልጣን ላይ የሚገኘው የእግር ኳስፌደሬሽን ስራውን ከጀመረ 1 አመት ሊሆነው ነው፡፡ ከሳምንት በኋላ ጠቅላላ ጉባኤውን ያካሂዳል፡፡ ፌደሬሽኑ የውስጥ ውድድሮችን በተሳካ መንገድ እያከናወነ ቢቆይም በአስተዳደራዊ ድክመቶችና በበጀት እጥረት  ውጤታማ ተግባራትን ለማከናወን አልቻለም፡፡ እግር ኳሱን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የማድረግ እቅድም አጀማመሩ እያማረአይደለም፡፡ ይህ ደግሞ የብሄራዊ ቡድኑን የአፍሪካ ዋንጫ ውድቀት አባብሶታል፡፡ ለዋልያዎቹ ሁለት ቀሪ የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣርያ ጨዋታዎች በቂ በጀት የለኝም በሚል እግር ኳስ ፌደሬሽኑ ከወር በፊት ያዘጋጀው ገቢ ማሰባሰቢያ ሁሉንም ችግር በገሃድ አሳይቷል፡፡ ትልልቆቹ የአፍሪካ ብሄራዊ ቡድኖች ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ እስከ 70 ሚሊዮን ብር በጀት ያወጣሉ፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራት ቢያንስ ግማሹን ያህል በጀት አቅርበው መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በበቂ በጀት ካልተሰራ ለአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ እድል የተመናመነ እንደሚሆን ገምቶ መስራቱ የፌዴሬሽኑ ኃላፊነት ነበር፡፡
አሁን በስልጣን ላይ የሚገኘው ፌደሬሽን ብሄራዊ ቡድኑን ዓለም አቀፍ ተፎካካሪ ለማድረግ ተነስቻለሁ ብሎ ስልጣኑን ቢረከብም በተግባር ስራውን አለመከወኑ ይስተዋላል፡፡ ከብሄራዊ ቡድኑ  አጠቃላይ የውድድር ሂደት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የፉክክር አቅም የሚያስገኙ የስፖንሰርሺፕ ድጋፎች አለመጠናከራቸውም ሌላው አሳሳቢና መሰረታዊው ችግር ነው፡፡
  ከ2 ሳምንት በፊት በሸራተን አዲስ በተደረገው የፌደሬሽኑ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ለ1100 ጥሪ ተደርጎ የተገኙት ግማሽ ያህሉ ነበሩ፡።
በገቢ ማሰባሰቢያው  20 ሚሊየን ብር  ለማግኘት ቢታቀድም በእለቱ  በቃል እና በተግባር የተገኘው ድጋፍ ከ4 ሚሊዮን ብር ያነሰ ነበር፡፡ ይህም ገቢ ማሰባሰቢያው የተሳካ እንዳልነበር ያረጋግጣል፡፡

Read 3614 times