Saturday, 29 November 2014 11:53

“ነገም ሌላ ቀን ነው”ን የትና እንዴት ተረጐምኩት

Written by  ነቢይ መኰንን
Rate this item
(1 Vote)

ከ“ያልታተመው መግቢያ” ግለ - ታሪክ መጽሐፌ የተወሰደ)

ማርጋሬት ሚሼል መጽሐፏን ጽፋ ለመጨረስ አሥር ዓመት ፈጅቶባታል - ከ1926 -1936 ዓ.ም!! ይኼውም ታማ የአልጋ ቁራኛ ሆና በነበረበት ጊዜ ነው፡፡
እኔም የማርጋሬት ሚሼልን Gone With The Wind “ነገም ሌላ ቀን ነው” ብዬ ለመተርጐምና ለማሳተም አሥር ዓመት ፈጅቶብኛል - ከ1980-1990፡፡ የማርጋሬት ህመምና የኔ ህመም ባይመሳሰልም ሁለታችንም ህመምተኞች መሆናችን ያቀራርበናል፡፡ እሷ ቁርጭምጭሚቷን ታማ የአልጋ ቁራኛ፡፡ እኔ ደሞ የሀገር ህመም ታምሜ የእሥር ቁራኛ!
መጽሐፉን እተረጐምኩበት ቦታ ለመድረስ ብዙ ተጉዣለሁ፡፡ ብዙ ደክሜያለሁ፡፡ እንዴት? ለምን? የት? መቼ? ከማጋር? እነሆኝ:-
ጐን ዊዝ ዘ ዊንድ (ነገም ሌላ ቀን ነው) የተተረጐመበት ቦታ ከላይ ጣራ ቢኖረው ኖሮ ዋሻ ይመስላል፡፡ ብዙ የሚውጥ፣ ጥቂት የሚተፋ የድንጋይ ዋሻ፡፡ ግርግዳው ግንብ፣ ጣራው ግንበ፣ ወለሉ ሲሚንቶ፡፡ የዋሻው ኮሪዶር የታደለ ሲሚንቶ ነው፡፡ በየቀኑ በኦሞ ይፈተጋል፡፡ ነፃ ጉልበት ይፈስስበታል፡፡ ቁጥሩ የማይታወቅ ውሃ በባሊ ይቸለስበታል፡፡ ስለዚህ ማንም የዚያ ዋሻ አባል ያልሆነ የውጪ ዓለም ሰው ከሚገምተው በላይ ንፁህ ነው፡፡ ነዋሪው ህዝብ ሲተባበርና ሲረዳዳ ለጉድ ነው፡፡ ፕሮግራም አውጥቶ ተራ ገብቶ ግቢዬ የሚለውን የዋሻውን ኮሪዶር ከሚገባው በላይ ያፀዳዋል፡፡ ምናልባትም የውጪውን ዓለም ቤቱን ከሚያፀዳበት ሺ ጊዜ በበለጠ፡፡ ለራሱ ጤንነት ሲል ነዋ!
የዋሻው ሆድ - ዕቃ በርካታ ሰዎችን በውስጣቸው ያጐሩ ዘጠኝ ክፍሎችን ይዟል፡፡ በተዛነፉ አራተ ባንድ ፎት አምስት በአንድ ፊት፡፡ ክፍሎቹ የብረት መዝጊያ አላቸው፡፡ የብረቶቹ መዝጊያዎች እክፍሉ ውስጥ ያሉትን ሰዎች በደምብ ይጠብቃሉ፡፡ ብረት ናቸዋ መዝጊያዎቹን ደግሞ የሚጠብቁ በጣሪያ የለሹ የዋሻ ኮሪደር አናት ላይ ካናት ጥግ እና ጥግ ሆነው ቁልቁል ያፈጠጡ የብረት አፈሙዞች አሉ፡፡ የብረቶቹ አፈ - ሙዞች የብረቶቹን መዝጊያዎች ማንም እንዳይነካቸው ይጠብቁዋቸዋል፡፡ አፈ - ሙዞቹ ጠንካሮች በመሆናቸው አስተማማኝ ናቸው፡፡ ግን እነሱም ቢሆኑ ጠባቂ አላቸው፡፡ የያዙዋቸው እጆች በደምብ ይጠብቋቸዋል!! የእጆቹ ባለቤቶች ኮስተር ኮስተር ያሉ ጭካኔን የተካኑ፤ በየጊዜው የሚለዋወጡ የቀንና የሌሊት ተረኛ ሰዎች ናቸው፡፡ ለጠባቂው ሁሉ ጠባቂ አለው - አለቃ፡፡ እንግዲህ የብረቶቹ አለቃ ሰው፣ የሰው አለቃ ደግሞ ሌላ ሰው ነው፡፡ ከዚያም በላይ፣ ከዚያም በላይ በላይ የሆነ የበላይ ሰው አለ፡፡ ለጠባቂው ሁሉ ጠባቂ አለው!! እንዲህ እንዲህ እያለ ፍጥረቱ ሁሉ ሲጠባበቅ ይኖራል!
ከእነዚያ እዋሻው ክፍሎች ውስጥ ከታጐሩት ሰዎች፣ እሥረኞች፣ ማህል እንደብረቱ መዝጊያ ብረት ልብ ያላቸው አሉ፡፡ ከጥጥ የተሠራ ይመስል የሚሳሳ፣ የሚባዘት፣ የሚዳወር የሚበጫጨቅ፣ ልብ ያላቸውም አሉ፡፡ ከጥጡ እስከ ብረቱ ልብ ያላቸውን ሰዎች ሁሉ ያ የብረት መዝጊያ በዓይነ ቁራኛ ይጠብቃቸዋል፡፡ ለአንዳቸውም አልራራ ባይ ነው፡፡ አልፎ አልፎ መርጦ ከሚያስወጣቸው በቀር፡፡ አንዳንዴ ገርበብ ብሎ ይከፈትና ትንሽ አየር ይመፀውታቸዋል፡፡ (የእስረኞች የስር ስነ- ስርዓት ኃላፊ የሚባል አለ፡፡ አየር ያከራያል ለ5 ደቂቃ 5 ብር ያስከፍላል፡፡ ፍቃድ የሌለው የአየር ነጋዴ ወን! ወደፊት እናየዋለን የክፍሉ በር) ሲያሰኘው በደምብ ብርግድ ብሎ ይከፈትና በሙሉ ሣምባቸው አየር እንዲተነፍሱ ይፈቅድላቸዋል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ጠባቂው ከከፋው፣ ወይም የጠባቂው ጠባቂ ከከፋው ወይም ሌላኛው ጠባቂ የሚኖርበት ሠፈር ሰላም ካልሆነ፣ ያ የብረት መዝጊያ ጥርቅም ብሎ ይዘጋና አትተንፍሱ! አትናፈሱ! አትጠጉኝ! ዋ ዛሬ ሁልሺም ቀንሽ ደርሷል! ይላል፡፡ ለምሳሌ ከከርቸሌ እስረኛ ካመለጠ በቃ አለቀልን ብረት መዝጊያው አንድ ሁለት ቀን ተከረቸመ ማለት ነው፡፡ ብረት መዝጊያው አንዳንዴ ተዓምር ይሠራል፡፡ ጠባቂዎቹን በጥበብ ከጣራው ያወርዳቸውና እክፍሉ ውስጥ አስገብቶ ያስቀምጣቸዋል፡፡ እነሱም ይታሰራሉ፡፡ ከእሥረኛ ይቀላቅላቸዋል፡፡ ጠባቂውን ተጠባቂ ያደርገዋል! እሥረኛ ዜጋ!
የእሥር ቤት ማህበራዊ ኑሮ
በየክፍሉ የሚኖሩት ዜጐች የራሳቸው የአኗኗር ዘዴ አላቸው፡፡ ማኅበራዊ ኑሮ ይባላል፡፡ የዛው ዋሻ መከራና ረሀብ የፈጠሩት ኑሮ ነው፡፡ በየትኛው ዘመን እንደተመሠረተ ባይታወቅም የመጀመሪያዎቹ ከቤቱ ከዋሻው ጋር የተሠሩት እሥረኞች የፈጠሩት ሳይሆን አይቀርም የሚል ጠንካራ ግምት አለ፡፡ አብሮ ይበላል፡፡ አብሮ ይጠጣል፡፡ አብሮ ይተኛል፡፡ አብሮ ይወጋል፡፡ አብሮ ይነጋል፡፡ አብሮ ይገፋል፡፡ በለስ ካልቀናም አብሮ ይሞታል፡፡ ማኅበራዊ ህይወትና ማኅበራዊ ሞት የዚያ ዋሻ ዜጐች ተገደው የፈቀዱት ደምብ ነው፡፡ ከአብሮ መኖሩ ጋር ሀሳብን ለመክፈል ሲባል መጨዋወትና መዝናናት አይቀርም፡፡ የስቃዩ ዋሻ ከአብራኩ ፌሽታን የሚወልድበት ጊዜ አለ፡፡ ከምጥ በኋላ እልል ማለትን ሰው ያውቅበት የለ? ታዲያ ሲዝናኑ የውጪውን ዓለምም ይረሱታል፡፡ ህልማቸውም ቅዠታቸውም ከዋሻ ህይወታቸው ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ ህልምም ይታሠራል! ያሰኛል! ለካ እዋሻው ሆድቃ ሲገቡ ብዙ ነገር ይረሳል፡፡ ቤት ንብረት ይረሳል፡፡ ሠርግና ቀብር ይረሳል፡፡ የቅርብ የሥጋ ዘመድም ቢሆን፤ በየቀኑ ስንቅ ባያመጣ ኖሮ መረሳት አይቀርለትም ነበር! ከሁሉ ነገር ይልቅ፣ ከሰውም ይልቅ ዜጐቹ ሁሉ የማይረሱት የታሠሩበትን ጉዳይ ነው፡፡ እራስ አይረሳማ! ከራስ በላይ ንፋስ ወይም ከራስ በላይ ጠባቂ ነው እንግዲህ በዜጐቹ አኗኗር ውስጥ ካሉት ህግጋት ውስጥ የኢኮኖሚ ህግጋት፣ የአመጋገብ ህግጋት፣ የጤና አጠባበቅ ህግጋትና የመዝናናት ህግጋት አሉ፡፡ ሁሉም ህግጋት ደህና ፀሐፊ ቢያገኙ ወደል ወደል መጽሐፍ ይወጣቸዋል፡፡ እኔ ለመግቢያ ያህል የመዝናናቱን ነገር ባጭሩ አነሳዋለሁ፡፡
በየክፍሉ የሚኖሩት ዜጐች የመዝናኛ ተጠሪ የሚባል አንድ አንድ ሰው ይመርጣሉ፡፡ በዛ ዘመን እንደዛሬው የግቢ መዝናኛ ኮሚቴ አልነበረም፡፡ የግቢ መዝናኛ ኮሚቴ አሁን በቅርቡ የተፈጠረ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ የምናወራው የአንዱን ክፍል ተጠሪ ጉዳይ ብቻ ይሆናል፡፡ የመዝናኛ ተጠሪው ዋንኛ ኃላፊነቱ አዲስ ሰው ሲመጣ በዘልማድ በየፖሊስ ጣቢያው እሥር ቤት “የሻማ” እየተባለ የሚጠራውን ከውጪው አለም (ከሞላ ጐደል ከተመቸ ኑሮ የመጣ ነው ተብሎ የሚታመነውን አዲስ ገቢ (ያው ለወጉ) “እንኳን ደህና መጣህ!” ለማለት የቤቱን ሰው ይሰበስብና ሁለት ዓይነት ጥያቄዎችን ይጠይቀዋል፡፡ አንዱ የኢኮኖሚ፡፡ አንደኛው የመዝናኛ፡፡ የኢኮኖሚ የሚባለው እነዚያ ከአንድ ወር እስከ አራት አምስት ዓመት ዋሻው ውስጥ የቆዩ ዜጐች ይበሉት ምግብ፣ ይለብሱት ልብስ፣ ይጠጡት ሻይ የሌላቸው በመሆናቸው ካዲሱ ዜጋ ጥቂት የኢኮኖሚ ምፅዋት ብናገኝ ብለው እጅህ ከምን? የሚሉበት ዘመናዊ ልመና ግን ከህልውና ሊነጠል የማይችል ጉዳይ ነው፡፡ አዲሱ ሰው የዜግነት መታወቂያውን ለማግኘት ለነባሮቹ ዜጐች አቅሙ የፈቀደውን ለመርዳት ቃል ይገባል፡፡ የደነገጠ ዘመድ ወዳጅ ገንዘብ ሲልክለት የቃሉን ይፈጽማል፡፡ ሌላኛው ጉዳይ መዝናኛ የሚባለው ሲሆን አዲሱ ዜጋ ከኢኮኖሚው ጥያቄ ባላነሰ ሁኔታ ማሟላት ያለበት ግዴታ ነው፡፡ ወይ መዝፈን ወይ መቀለድ አሊያም ሰውን ጥቂት ያጫውታል፣ ያዝናናል የሚለውን ነገር መናገር ነው፡፡ የራሱንም አስገራሚ የህይወት አጋጣሚ ቢሆን፡፡ ይህን ሲፈጽም ሙሉ ዜጋ ይሆናል፡፡ የውጪውን ዓለም ዜግነቱን ሽሮ የዋሻውን ዓለም ዜግነት ያገኛል፡፡ ማለት ነው የመኖሪያ ፍቃዱን ይወስዳል፡፡ የመታሠር መብቱን ያስከብራል፡፡ የመታሠር ሊቼንሳውን ይረከባል፡፡
ከዚያ ወዲያ ነፃነት የሚባል፣ አገር፣ እንደልብ መሆን፣ የሚባል ነገር የት አግኝቶት፡፡ ዓለምን በሰላም ጭብጥ ኩርምት ብሎ ይገፋል፡፡ ያ ምልዕተ - እሥረኛ ገበያ ቀዝቅዞ ወደዋሻው የሚገባ ሰው ሲጠፋ አዲስ ወሬ የሚያመጣለት፣ አዲስ ፊት የሚያሳየው፣ አዲስ እርጥባን የሚለግስለት ትኩስ ዜጋ ያጣ ጊዜ፤ አቤት ያለ ዐይን ማፍጠጥ! አቤት ያለ ድብርት! አቤት የሰው ረሀብ! አቤት መሰላቸት! ደግነቱ ዜጋ ሆዬ ከረጅም ጊዜ ልምዱ በመነሳት እርስ በርስ ተፋጠን ከምንሰለቻች ጨዋታ እንፍጠር! ከምንደበር መላ መትተን ጊዜ እንግፋ ይላል! ለዚህ እንግዲህ ቴያትር ያዘጋጃል (ባይፈቀድም ውስጥ ውስጡን ተስማምቶ ድምፁን አጥፍቶ ይሠራዋል) ግሩም ቴያትር ያውም ድምጽ አጥፍቶ ተሠርቶ!
የዳማ፣ የቼዝ፣ የዶሚኖ ውድድር ማዘጋጀትም ተለምዷል! ቢንጐ ያጫውታል በየክበቡ አዲሳባ እንደሚታየው  የተሟላ አይደለም፡፡ ኑሮ ካሉት ፍሪጅም ይሞቃል፡፡ እዚህም በሲጋራ ካርቶን ሠንጠረዡን ሠርቶ የብርቱካን ልጣጩን ቆራርጦ የሠንጠረዡን ቁጥሮች በልጣጭ እየደፈነ ቢንጐውን ይከሰሳል! ኧረ ብዙ ጨዋታ ይፈጥራል! ሞገደኛ እሥረኛ! እጅ እግሩን በካቴና በፌሮና በእግረሙቅ ቢጠፍሩት፣ “አንጐሌን አላሳስር!” ብሎ በር ተዘግቶበት፣ በስንት ጠባቂ አፈሙዝ ተደግኖበት እንኳ የውጪውን ዓለም ጨዋታ እንደልቡ ይጫወታል፡፡ ነገር የገባው እስረኛ እንዲህ ነው!
ተው ሲሉት በጄ አይል - በምናቡ እሩቅ አገር ይሄዳል!
ሌላው መዝናኛ መጽሐፍ ነው፡፡ በዛ ቢባል በዚያ ዋሻ ውስጥ በእኔ ጊዜ ሁለት ወይ ሶስት መጽሐፍ አለ፡፡ ለዛ ሁሉ ዜጋ መቼም ገጽ እየተበጨቀ ካልተሰጠ በቀር ለንባብ ማዳረስ አይቻልም፡፡ ስንት የተጠማ ዐይን፤ ስንት የተጠማ አዕምሮ እዚያ ታጅሎ ሁለት መፅሐፍ እንዴት ትብቃው? ያም ሆኖ ሰው መች ዘዴ ያጣል ወንድሜ! በስክ ያነበዋል፡፡
ስክ የዋሻው ውስጥ መዝገበ - ቃላት ያፈራው ቃል ነው፡፡ ያው የመከራ ምጥ የወለደው መግባቢያ! ልክ እንደተናጋሪዎቹ!  አመጣጡ እንደሚከተለው ነው፡- ያ እስር ቤት ክፍሉ ጠባብ ነው፡፡ ዜጋው ብዙ ነው፡፡ የቆዳ ስፋትና የህዝብ ብዛት አልተመጣጠኑም፡፡ ያለ ፕላን እያሠሩ ምርቱ በዝቶ መጋዘኑ ተጣቧል፡፡ ብቻ ምን ያረጋል፤ ሰውም ሠራ የሚባለውን ወንጀል በፕላን አይሠራ! እንዳመቸው ይሯሯጣል፤ ሳይዘጋጅ ይታሠራል፡፡ መች ተማረ! (ማንስ ከማን መች ልማር ይላል፡፡ ዝም ብሎ በየተራ ይታሠራል፤ ይቀፈደዳል) ታዲያ ያ የተትረፈረፈ ዜጋ ማታ ልተኛ ሲል ስንቱ ሊተኛ?! ቦታ የለም፡፡ እንግዲያው መላ ምቱ ተባለ፡፡ መላ ተመታ፡፡ ዘዴ ተገኘ፡፡ በፈረቃ መተኛት፡፡ ተፈራርቆስ መች ሆነ፡፡ ያለ ፕላን የሚታሠረው ታሣሪ ዜጋ በላይ በላዩ ሲመጣ በፕላን የሚተኛውን ፕላነ - ቢስ ያደርገዋል፡፡ በዚህ ምክንያት በተቻለ ተጣቦ የመተኛት የመጨረሻው የቦታ ቁጠባ ፕላን ተነደፈ፡፡ ጐጆ እሚባል የቦታ ሽንሸና ተመሠረተ፡፡ አንዱ ክፍል አራት ጐጆ ይኖረዋል፡፡ አራቱ ጐጆዎች የክፍሉን ዜጋ ሁሉ በእኩል ተካፍለው ያስተናግዳሉ፡፡ የሚበላው ምግብ የጎጆው ነው፡፡ የሚነጠፈው አንሶላ የጐጆው ነው፡፡ የሚለበሰው ብርድልብስ የጐጆው ነው፡፡ እያንዳንዱ ዜጋም የጐጆው ነው፡፡ ጐጆው የክፍሉን አንድ አራተኛ ክልሉን ጠብቆ ለመተዳደር እጅግ ተጠጋግቶ መተኛት ነበረበት፡፡ ተኛ፡፡
 ታዲያ እራስ ለራስ ተገናኝቶ ሲተኙ ብዙ ቦታ መያዝ መጣ፡፡ ለዚህ ሌላ መፍትሔ ተገኘ፡፡ እራስጌና ግርጌ እየሆኑ መተኛት፡፡ አንደኛው ያንደኛውን እግር አቅፎ መተኛት፡፡ ስሙንም “ስክ” አሉት፡፡ ሰው እንደጨፈቃ ተጨፍቆ፣ እንደ አሹቅ ሾቆ፣ ሰው በሰው ማህል ተሰክቶ የሚያድርበት ዓለም “ስክ” ተባለ፡፡ ሆኖም ሙሉ ለሙሉ ጥበቱ አልተገወደም፡፡ እንደገና ሰብስቦ መላ ተመታ፡፡ በጀርባ ወይም በደረት መተኛት ዋና የቦታ ጠር ነው ተባለ፡፡ በተግባር ታየ፡፡ ዕውነት ሆነ፡፡
 ሁልህም በጐን በጐንህ ተኛ - ይዞታህ በጐንህ ስፋት ልክ ነው የሚል ህግ ወጣ፡፡ ይኸውም ከሰውነት ሁሉ ጠባቡ ስፋት ያለው በጐን በኩል ነውና በሰያፍ የሚተኛበት ዘዴ ሆኖ ፀደቀ፡፡ ስሙንም “ጩቤ ስክ” አሉት፡፡ የሰው ስለቱ ተገኘና “ጩቤ” የሚል ስም ወጣለት ማለት ነው፡፡ ይሄ ስክ የሚል ቃል አገልግሎቱ እንደ እሥር ዘመኑ ስፋትና እንደመጪው ዜጋ ብዛት ተስፋፋና መጽሐፍ ለማንበብም ዋና ዘዴ ሆኖ ተገኘ፡፡ የቀኑ ሃያ አራት ሰዓቶች በየአንድ አንድ ሰዓት ሃያ አራት ቦታ ይሸነሸኑና ሃያ አራት ሰው ይመደብባቸዋል፡፡
እያንዳንዱ ሰው አንድ ሰዓት ይደርሰዋል፡፡ በዚሁ ጊዜ ሰዓቷን ሳያባክን ያነብባታል፡፡ እንግዲህ በቀኑና በማታው ጊዜ ውስጥ ሃያ አራት የመጽሐፍ ስክ አለ ማለት ነው፡፡
በዚህ ዓይነት የንባብ ስክ ሥርዓት ከፍተኛ የመነበብ ዕድል በማግኘት፣ ብትንትኑ እስኪወጣ ድረስ ህልውናው እፈተና ላይ የወደቀ ታላቅ መጽሐፍ፤ የማርጋሬት ሚሼል ጐን ዊዝ ዘ ዊንድ ነበር፡፡
ዘመነኛ ጓደኞቹ የሆኑት መጻሕፍት በሁለት በሦስት ዓመት ጡረታ ሲወጡ፤ እሱ በታተመ በሰላሳ ስድስት ዓመቱ፣ የወላጅ እናቱን የማርጋሬትን ዕድሜ ተሸክሞ፣ ጥቁር ከነጭ ፀጉር ካበቀለ በኋላ እንኳ፤ ጭራሽ ጉርምስና ተሰምቶት የቀኑ አልበቃው ብሎ ሌሊቱን ሙሉ ከእጅ ወደእጅ ሲዞር፤ ሲነበብ ያድራል፡፡ ሰዓት እላፊ - አያቅ፣ ዘመን - እላፊ አያቅ፣ ድንበር - እላፊ አያቅ እንዲሁ የጊዜና የቦታ ኬላ እንዳጣሰ ኖሮ፤ ይኸው ይባስ ብሎ እሥር ቤት ድረስ ገብቶ የዜጐቹን እንቅልፍ ይነሳል! በዚህ ሁኔታ እንቅልፍ ካጡት ዜጐች ማህል እኔ አንዱ ነኝ፡፡ ማንበብ ከጀመርኩበት እስከጨረስኩበት ሰዓት ድረስ አገሬን አገሬን እንደሸተተኝ ቆየ፡፡ ደግሜ ስክ ገባሁ፡፡ አነበብኩት፡፡ ከዜጐች ጋር ተወያየሁበት፡፡ በጣም ወደድነው፡፡ በደምብ ካነበብኩት፣ ከወደድኩት፣ የሥነጽሑፍ ችሎታው ካለኝና ከሁሉም በላይ ደግሞ ባገሬ የእስር ዋሻ ውስጥ እያለሁ አገሬን አገሬን ከሸተተኝ፤ የማልተረጉመው ሞቼ ነው ቆሜ? ደሞስ ከመቶ ሃያ ዓመታት በፊት ሌላ አገር ውስጥ የታየ ጦርነትና አስከፊ ውጤቱ፤ ዛሬ እኔ አገር ላይ ሲዘንብ እያየሁ፤ ይህን መጽሐፍ አንብቤ፣ ተርጉሜ ላላየ ወገኔ ዐይንና አዕምሮ ብሆነው፤ ብሞትስ ብቆምስ ግዴታዬም፣ አላማዬም አይደል እንዴ!!
መተርጐም አለብኝ ብዬ፣ ግጥምና ቴያትር ከመፃፍ አልፌ ወደ ትርጉም ተሸጋገርኩ!
ትርጉም ስራውን ለመጀመር ያነሳኋቸው አምስት ጥያቄዎች በጣም ጠጣር ነበሩ፡፡
እዋሻው ውስጥ ነኛ! የራስ ነፃነት ሳይኖር ለሌላው ነፃነትን ለማሳየት ሲፍጨረጨሩ አቤት ያለው ሳንካ! አቤት ያለው እንቅፋት! አቤት ያለው በወንጀል ላይ ወንጀል የማከል ስጋት!  የመጀመሪያው ጥያቄ በምን ሰበብ ልፃፍ? መፃፍ አይፈቀድማ! 2ኛው ጥያቄ በምን ላይ ልፃፍ? ወረቀት አይገባማ! ሦስተኛው ጥያቄ በምን ልፃፍ? እስክሪብቶ ከቤት ተጠሪ እጅ አይወጣማ - የተሾመልን ቤት- ተጠሮ ደሞ ፔናውን ለራሱና ለኢኮኖሚ ተጠሪው በቀር እንዳያውል ቃል የገባ ቤት - ተጠሪ! ደግሞም የመንግስት አደራ የማይበላና አፍቅሮተ - መንግስት እልቡ ውስጥ እንደጧፍ የሚነድ ጓድ ነው - ያውም” “ግለሰብ ነው እንጂ አብዮት አላሰረኝም” የሚል! አራተኛው ጥያቄ የት ልፃፍ? ቦታ የለማ! አምስተኛው ጥያቄ - ፅፌስ? ማውጫ የለማ! ፍቺም ሆነ ግመሽ ፍፊ (ከርቸሌ)፣ ቢገኝ ሲወጡ ከጥፍር እስከ ጠጉር ተፈትሾ ነው፡፡
አንድ ሺህ ሃያ አራት ገጽ ያለው መጽሐፍ፤ ተደክሞ ተተርጉሞ (ከኦርጅናሌው መብለጡ አይቀርምና) ምን ሊኮን ነው? የገረመኝ ነገር ከጥያቄዎቹ ሁሉ ከባዱንና የመጨረሻውን መጀመሪያ ለመመለስ መቻሌ! ጽፌስ? ብዬ ጠይቄ ጥቂት ካሰብኩ በኋላ መልሴን ሰጠሁ - ባወጣ ያውጣው! ነገም ሌላ ቀን ነው አልኳ! እንደ እስካርሌት!
ይቀጥላል    

Read 3489 times