Saturday, 29 November 2014 12:01

ፀጋዬንና ግጥሞቹን እኔ እንዳየኋቸው

Written by  ነ.መ
Rate this item
(5 votes)
  • ለዛሬ የፀጋዬን ግጥሞች አንድ ሰባት ሰበዝ መዝዤ ልያቸው፡፡
  • ፀጋዬ በቦታዎች ላይ - ምነው አምቦ፣ አድዋ፣ ማይጨው፣ ሐረር፣ ወዘተ
  • ፀጋዬ በጀግንነትና በብሔራዊ ስሜት ላይ - የመቅደላ ስንብት፣ ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት፣ አበበ እንጂ ሞተ አትበሉ
  • ፀጋዬ በፍቅር ላይ - መሸ ደሞ አምባ ልውጣ፣ ትዝታ፣ ጌራ፣ ተወኝ፣
  • ፀጋዬ በፍልስፍና ውስጥ - ክልስ አባ ልበ - እግረኛ፣ መተማን በህልም፣
  • ፀጋዬ ማህበራዊ ጉዳይ ላይ - ማነው ምንትስ
  • ፀጋዬ - አገሬውን፣ ገጠሩን፣ ብሔረሰቡን የሚያይበት ዐይን - የምታውቀኝ የማላቅህ፣ አቴቴ ዱብራ ኦሮሞ
  • ፀጋዬ የማሕበረሰብን ዝቅጠት ለመከላከል ሲፅፍ - አባቴስ ወንድ ወለድኩ ይበል፣ እንዳይነግርህ አንዳች ዕውነት
  • ፀጋዬ በማናየው አቅጣጫ ላይ፣ ህግን መጣስ ይችላል - እንቅልፍ ነው እሚያስወስድህ፣ መትፋት የስነውራል
  • የፀጋዬ አፃፃፍ ከጠቅላላ ወደ ዝርዝር የመግባት ባህሪ አለው፡፡ በቦታ ላይ በሰፊው ጽፏል፡፡ ከላይ የጠቀስኳቸውን ላቆያቸውና ከመጨረሻው ልጀምር፡፡

ለምሣሌ ድሬዳዋን በጅምላ ጆግራፊዋን፣ የያዘችውን ህዝብ፣ መልክና ውበቷን ያሳየናል
…ዲሬ - ዳዋ - ድሬ ዳዎ
የምሥራቅ አድባር ጥላዋ
ላገር ጎሣ ድምር - ጽዋ
ኅብረ - ጠባይ ማጥለያዋ
ድሬ - ዳዋ ውስጠ - ደማቅ
ሽፍንፍን እንደአባድር - ጨርቅ፣ ብልጭልጭ እንደሩቅ ምሥራቅ
ከዚያ በዝርዝር ድሬዳዋ ጉያ ውስጥ ይገባል
…በየጉድባሽ ጫት ሲሰጣ
ጣይ ያደከመው ወፈፌሽ፣ አራራ ጥሎት ሲንጣጣ
ብሌኑ እንደጐሽ - ግት ፈጦ
ጉድ ከየአንደበቱ ፈልቆ….
“ብሌኑ እንደ ጎሽ - ግት ፈጦ” የሚለውን ምስለታ ተመልከቱ፡፡ በእግሩ መካከል ነጩ ብቻ የፈጠጠ ያጋተ ጡትና ዐይኑ የፈጠጠ ባለሐራራ ነው የሚያመሳስልልን፡፡
አሥመራ
አዘቦን ዳግም አየሁዋት
ሌሎቹ በቦታ ላይ የተቀኘባቸው ሥራዎች ናቸው፡፡
ጋሽ ፀጋዬ አህጉራዊም አለም አቀፋዊም ብዕር አለው
ጋሽ ፀጋዬ በእንግሊዝኛም ይገጥማል፡፡ በዚያም የአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ብዕሩን አሳይቷል፡፡ እንደ ኤዞፕ፣ ዘ ኤይዝ ሐርሞኒና የአፍሪካ ህብረት መዝሙር፣ እንዲሁም ፕሮሎግ ቱ አፍሪካን ኮንሳይንስ የሚሉትን ግጥሞች ለአብነት ብጠቅስ ይበቃል፡፡
“This is the land of the 8th harmony
In the rainbow: Black
It is the dark side of the moon
Brought to light.”
በቁሙ ብተረጉመው እንዲህ የሚል ይሆናል:-
ጥቁር
የስምንተኛው ብርሃን ህብር
ይህ የቀስተ - ደመና ምድር
የጨረቃ ጭልም ወገን፣ ወደ ብርሃን ሲከተር
እንጂ ሌላም አደል ጥቁር!
ጥቁር
“አባይ” በሚለው ግጥሙ ውስጥም ይህንኑ ባህሪ እናያለን፡፡
…አባይ የጥቁር ዘር ብሥራት
የኢትዮጵያ ደም የኩሽ እናት
የዓለም ሥልጣኔ ምስማክ
ከጣና በር እስከ ካርናክ
…አባይ የአቴስ የጡቶች ግት
ለዓለም የሥልጣኔ እምብርት” ይለዋል
ስለፍቅርም ይቀኝ ነበር ጋሽ ፀጋዬ - በእንግሊዝኛ፡፡ በ1950ዎቹ መጨረሻ ከፃፋቸው ውስጥ Gladiator’s Love
Gladiator’s Love
Though the stars no more glitter
And the cloud does no more rain
Though the moon shall not be borne
Yet your love is not in vain
Though I bid fare-well to life
Where you too are included,
Breaking the law of nature
Your loving has intruded.
ቀለል ለማድረግ ብዬ በወል ተርጉሜዋለሁ፡-
    ከዋክብት አይበሩም
ዳመናው አይዘንብም
ጨረቃ በቅቷታል ዳግሚያ አትወለድም
ያንቺ ፍቅር ብቻ አለው አንድ አብነት
ፍጥረት ሲለዋወጥ ፀንቶ የመቆየት፡፡
አንቺንም ጨምሬ ሁሉን ለመለየት
ኑሮዬን ደህና ሁን ብዬ ስሰናበት
ፍቅርሽ ግላዲያተር ማን ያዘኛል ያለ
አንቺንም ሸኝቼ፣
የዓለም ህግ ጥሶ፣ ይሄው አብሮኝ አለ!!
Prologue to African conscience ሌላው የእንግሊዝኛ ግጥሙ ነው፡፡ ቀንጭቤ ላቅርብላችሁ ከነትርጉሙ
…It looks right
It looks left
It forgets to look into its own self:
The broken yoke threatens to return
Only, this time
In the luring shape
Of luxury and golden chains
That frees the body
And enslaves the mind.
    የአፍሪካ ህሊና
ወደቀኝም ያያል
ወደ ግራም ያያል
ግና ራሱን ውስጡን ማየቱን ዘንግቷል
የሰበርነው አስኳል መልሶ ሊመጣ
አሁን በሌላ መልክ ታይቷል ሲቀናጣ
ግና የአሁነኛው
ለቅንጦት ለአዱኛ፣ ለወርቅ ሰንሰለት፣ እንድናደገድግ
ነው አንዳች ወህኒ ውስጥ የሚያስረን ከራር ድግ፤
ገላን ነፃ አውጥቶ፣ አንጐል ባሪያ እሚያረግ
ለጋሽ ፀጋዬ “እንደ” የሚለው የተማስሎ ቃል - ትልቁ ብቃቱና ኃይሉ ነው እላለሁ፡፡ ልዩ ምስል ይቀር
ፅበታል፡፡ “እንደ” ብሎ በተማስሎ መጠቀም ይችልበታል፡፡
ለአብነት ጥቂት ላሳያችሁ:-
ከአይ መርካቶ
    የከበረ እንደመረዋ፣ ረብጣ አፍኖት ሲያስገመግም
    የከሰረ እንደፈላስፋ፣ በቁም ቅዠት ሲያልጐመጉም
    ከቃል ቃተተ
    ቃላችንን ካስጐሰበትን፣ እንደሥራ-ቤት ልፈፋ
እንደቀፈፋ አቆማዳ፣ ምሥጢር ካፎቱ ከሰፋ
እንደባለጌ መቀነት፣ ውሉ በልፊያ እየገፋ
እንደአቃቢት ግብር ውሃ፣ ገበና የትም ሲደፋ፣…
ጋሽ ፀጋዬ ባለሁለት ወይም ሦስት ፊደል ቃል መጠቀሙ ሌላው ልዩ ችሎታው ነው ቁጥብ ያደርገዋል፡፡
ከርዕሶች እንጀምር
ክልስ አባ ልበ እግረኛ
በቃኝ
ቦረን
አዋሽ
ምንም አልል
ምንም አልል
ልሳኔን ሲያስነሳ ሲያስጥል
ቃላቴን ሲቃኝ ሲያጋግል
ክል ሲል ትር ድም፤ ሲል

ማዳመጥ
ማስታመም እንጂ፣ ሌላ ምንም ምንም አልል
እነዚህን ባለሁለትና ሦስት ፊደል ቃላት ልብ ይሏል፡፡
ከአዋሽ
    …መጫ ቋጥሮ ሸዋ ፀንሶ፣ ሰባት ቤት     ጉራጌ አርግዞ
    ከዳዳ ምንጭ አሩሲ እምብርት፣ ከነ     ቅሪቱ  ተጉዞ
    ከአላባ ጣፋ ሼህ ሁሴን፣ አዳል ሞቲ     ሽሉን ይዞ
    ከከረዩ ማታ ሐራ፣ ከኢቱ እስከ አፋር አምጦ…
(ይቀጥላል)

Read 3914 times