Saturday, 13 December 2014 10:56

የ“አደፍርስ” ዳግም መታተም

Written by  ታደሰ አ.
Rate this item
(0 votes)

   የ“አደፍርስ”ን ዳግም መታተም በሰማሁ ጊዜ ልቤን ደስ አለው፡፡ ደራሲው ዳኛቸው ወርቁ በቀደመ ህትመቱ ስሜቱ ተጎድቶ ከገበያ ላይ የሰበሰበው “አደፍርስ” ድጋሚ መታተሙን አውቆ ቢያርፍ እንዴት ሸጋ ነበር፡፡ ደራሲው በህይወት በነበረበት ዘመን ድርሰቱን ፈልገው ለሚሄዱ ሰዎች ወይም ተማሪዎች ይሸጥ ነበር አሉ፡፡ ዝም ብሎ ግን አይሸጥም፤ ስለ መጽሃፉ ጥያቄዎችን ጠይቆ፣ የገዥውን የአእምሮ አቅም ለክቶ ነው፡፡ ምን ያድርግ በዚያ ጊዜ የነበሩ ሃያሲያን ወይም አንባቢያን መጽሃፉን አብጠልጥለውት ነበርና ነው፡፡ በርግጥ “አደፍርስ” ለየዋህ አንባቢ አይደለም ለተባ አንባቢም ፈተና ነው፡፡ እያንዳንዱ ቃል፣ ሀረግ፣ አረፍተ ነገር፣ ሥርዓተ ነጥብ… ሁሉ በምክንያት የገባ ነው፡፡ የደራሲውን ስራዎች ፈልጌ ለማንበብ ሞክሬያለሁ፤ ራሱ “የጽሑፍ ጥበብ መመሪያ” የሚለው ማጣቀሻ የጽሁፍ ማስተማሪያው መምሪያ ሳይሆን መመራመሪያ ነው፡፡ “እንቧ በሉ ሰዎች” (ዩኒቨርስቲ እያለ የጻፈው ግጥም) በአብዛኛው የተቃውሞ ይዘት ያላቸው ግጥሞቹ፣ “The Thirteenth Months Sun” (1973 G.C) የሚለው እንግሊዝኛ ልቦለዱ እንደ “አደፍርስ” ሁሉ ጠንካራ ናቸው፡፡ ተውኔቶችም፣ አጫጭር ልቦለዶችም አሉት፡፡ ሰውየው ከጻፈ ለሰስ ማድረግ አያውቅም!!
“አደፍርስ” በትውፊታዊ አቀራረብ የዳበረ፣ ረቂቅ ሀሳብን በሚወክሉ ገጸ ባህሪያትና የታሪክ ደጀኖች የበለጸገ ሲሆን በታሪኩ ውስጥ የቀረቡት የእንግዳ አቀባበል፣ የሰላምታና ጭውውት፣ የቤተሰብ ወግና ስርዓት፣ እሰጥ አገባ፣ ባዕድ አምልኮውና ክርስትናው፣ ስንብቱና ውይይቱ ስራውን ፍጹም ኢትዮጵያዊ ባህርይ ያጎናጽፉታል፡፡
እስኪ አንዲት ነጠላ ሀሳብ እንምዘዝና እመልከት፡-
“… ሙቶች ሙታናቸውን ይቅበሩ፡- ጌታ ያለው የፈቀደው ሲፈጸም እኮ ነው፡፡ ለራሱ ያለውን ማን ይወስድበታል?”
ከላይ የቀረበው ደራሲ ዳኛቸው ወርቁ በ1962 ዓ.ም “አደፍርስ” በሚል ርዕስ ካሳተመው ልቦለድ ታሪክ ውስጥ የተቀነጨበ ነው፡፡ ይህ የመጨረሻው ምዕራፍ ከላይ በተጠቀሰው አባ ዮሐንስ ንግግር ከመጠናቀቁ በፊት ጺወኔ ለአለም ያላት አመለካከት ግራ መጋባት ይታይበታል፡፡
በዙሪያዋ ያሉት ሁሉ “ለእሷ ብለው” የተለያየ ምክር ለግሰዋታል፡፡
ምናልባት የግራ መጋባቷ መንስኤም ይህ ሊሆን ይችላል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ከነዚህ ሰዎች መካከል አንዱ ደግሞ አባ ዮሐንስ ናቸው፡፡
አለምን ተያት፣ አለሙ በጌጥ ቢጥበረበር፣ አለሙ አለምን ሁሉ ሊያተርፍ ቢሻ አንች አትመልከችው፤ መንኝ እያሉ የአለምን ከንቱነት ይሰብኩላታል፡፡
እዚህ ላይ መረዳት ያለብን በልቦለዱ ውስጥ የቀረቡት ታሪኮችና ድርጊያዎች የቀረቡበትን ውክልና ነው፡፡ “ትእምርት” (symbol) በአደፍርስ ውስጥ ዋና የታሪክ ማስኬጃም፣ ማምለጫም፣ የታሪኩ ማጉያና የስራው ውበታዊ ፋይዳ ሆኖ ይታያል፡፡ ዋርካው ከነቅርንጫፉ፣ የዋርካው ስር ለምለም ሳር፣ ታይታ የምትጠፋው ምንጭ፣ አደፍርስ ወደ ውሃው የወረወራት ጠጠርና የጺወኔ በወታደሩ መጠለፍ … ሁሉ ትዕምርታዊ ዳራቸው ታሪኩን ለመረዳት የሚረዱ ናቸው፡፡
ለምሳሌ በልቦለዱ ውስጥ አንድ ዋርካ ቅርንጫፉ ሰፍቶ የተንዘራፈጠ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ታቹ ለምለም ሳር ነው፤ ከዋርካው ስር አንዳንዴ የምትፈልቅ ምንጭም አለች፡፡ ዋርካው ንጉሱ፣ ቅርንጫፎቹ ከእርሳቸው በታች ያሉት ባለሟሎች፣ ለምለሙ ሳር ለዘመናት የማይቆረቁረው፣ የማይጎረብጠው፣ የመጣው ሁሉ የሚቀመጥበት የኢትዮጵያ ህዝብ፣ አልፎ አልፎ የሚመነጨው ምንጭ ደግሞ በየጊዜው የተነሱት አመጾች ናቸው፡፡ ይህ ከሆነ በኋላ “አደፍርስ” የተባለው ባለ ታሪክ ማህበረሰቡን ሳይሆንና ሳያክል እንዲሁም ውስጣቸው ሳይገባ ልለውጣችሁ አላቸው፡፡ ሳይለውጣቸው ቀረ! ይህ በጠጠር የተመለከተው ትዕምርት (ምሳሌ) እንዲህ ነው፡፡ አደፍርስ ከአንዲት ኩሬ ዳር ሆኖ ወደ ኩሬው ጠጠር ወረወረ፡፡ መጀመሪያ ክብ ከዚያ ትልቅ ክብ፣ ከዚያ ትልልቅ፣ ትልልልቅ… ክብ እየሆነ ሄደ፡፡ እንደ ሃሳቡ ማህበረሰቡን መጀመሪያ ትንሽ መለወጥ፣ ከዚያ ከፍ ከፍ… በማድረግ መለወጥ ነበረ፡፡ ግና ምን ያደርጋል ዳር ሆኖ ጠጠሩን ወረወረና (ወደ ህዝቡ ሳይገባ) የጠበቀው ለውጥ ሳይመጣ ቀረ፡፡ መጨረሻም ያንን የረጋ ውሃ (ውሃው ህዝቡ ነው) ሳይቸግረው በጥብጦ ኢትዮጵያን አሳልፎ ሰጣት፡፡ ጺወኔ (ጥንታዊት ኢትዮጵያ) በወታደሩ መጠለፏን ልብ ይሏል፡፡ ለዚህ ነው ደራሲ ዛሬን ሳይሆን ነገን፣ ከነገ ወዲያን የሚመለከትበት መነጽር አለው የሚያስብለው፡፡ ደራሲ ትንቢተኛ ነው ብንልም ያስኬዳል፡፡ ዳኛቸው ከተነበየው አንድም እንኳ ያልሆነ የለም፡፡
ወደ ተነሳንበት እንመለስና፣ የጺወኔ ውክልና በዘመኑ ለነበረው ስርዓት ነው፡፡ ይህች ደግሞ የፊውዳል ስርአት እየገነነባት የመጣችው ጥንታዊት ኢትዮጵያ ናት፡፡ በንጽህናዋ፣ በአለችበት አቅም፣ ዕውቀት፣ ባህልና ወግ አደፍርስ አጥብቆ የሚወዳት እና የሚፈልጋት፡፡ በሌላ መንገድ የአደፍርስን ልብ የምትከፍልበት ሮማን ናት፡፡ እሷ ደግሞ ለውጥ ለመቀበል ያቆበቆበችው፣ ህዳሴ ያማራት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ምሳሌ ናት፡፡ አደፍርስም የዚህ ዘመን አካል በመሆኑ (በትምህርትም ስለገፋ) ወደ ሮማን (ዘመናዊነት) ማጋደሉ እውነት ነው፡፡ በመጨረሻው ምዕራፍ የአደፍርስ የመጨረሻ ዕጣ በሞት መሆኑ በሁለቱ ኢትዮጵያዎች መካከል (በሮማንና በጺወኔ የተወከሉት) ያለውን ድልድይ መዘርጋት ሳይችል፣ ሀሳቡ ሳይቋጭ መቅረቱን የሚያሳይ ነው፡፡
እንግዲህ አንኳር የሆነ ሀገራዊ ጉዳይን አንስቶ ዳር ሳያደርስ በሞተው አደፍርስ ቀብር ላይ ነው ጺወኔ ከነበረው ማህበረሰብ ራሷን አሸንፋ የራሷ ሰው ሆና ተነጥላ የምትጓዘው፡፡
 መድረሻዋ በርግጥ አይታወቅም - ዘመኑን ልብ ካልን የኢትዮጵያም መድረሻ አይታወቅም ነበር፡፡ አካሄዷ ግን የመወሰን ነው፡፡ “ኢትዮጵያ ለለውጥ እርምጃ መጀመሯን ማመልከቱ ይሆን” ያሰኛል፡፡ በዚህ ጊዜ ነው አባ ዮሐንስ ከመፅሐፍ ቅዱስ የሉቃስ ወንጌል ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚናገረውን ጠቅሰው የሚከተሏት፡፡
“ሌላውንም ተከተለኝ አለው፡፡ እርሱ ግን አለ፡፡ አቤቱ እዘዘኝ እሄድ ዘንድ አስቀድሜ አባቴን ለመቅበር፡፡ ኢየሱስም አለው፡፡ ሙታንን ተው ሙታናቸውን ይቅበሩ፡፡ አንተስ ሂድ የእግዚአብሄርንም መንግስት አስተምር፡፡” (ሉቃስ 9፤ 59-60)
ይህ ሰው ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲከተለው ሲጠይቀው አባቴን ልቅበር በማለቱ ነው ይህ ቃል የመጣው፡፡ በርግጥ አባቱ ሞቷልን? አልሞተም፡፡ በዚያ ዘመን በነበረው ልማድና አነጋገር (አሁንም በአንዳንድ የሀገራችን ክፍሎች ይባላል) አባቴ እድሜው ደርሶ እስከሚሞት ጦሬው፣ ሲሞትም በወጉ ቀብሬው ልምጣ (ጧሪ ቀባሪ እንዲሉ) እንደ ማለት ነው፡፡ ክርስቶስ ግን የነበረውን ማህበረሰብ የእምነት ጉድለት በዚህም የቁምና የመንፈስ ሞታቸውን በማመስጠር፣ የቁም ሙቶች የሞቱትን ይቅበሩ፤ አንተስ ለመንፈሳዊ ዘለአለማዊነት ተመርጠሃልና እግዚአብሄርን ተከተል፤ ስለ እሱም አስተምር ሲለው እንመለከታለን፡፡
በአደፍርስ ውስጥ አባ ዮሐንስ ይህን የታላቁን መፅሐፍ ቃል ለመናገር መምረጣቸው የጺወኔን መንፈሳዊ ህያውነት ለማሳየት ይመስላል፡፡
 የዘመኑ ማህበረሰብ የአመለካከትና ልማድ ሙትነት በመፅሐፉ ውስጥ ተሰናስሎ ቀርቧል፡፡
 ይህ ጥቅስ የዳኛቸውን የትረካ ስልት ያዳበረና ያበለፀገ፣ በውስጡም ብዙ ብልሃቶችን ያካተተ እንዲሆን አድርጐታል፡፡ የታሪኩ ፍሰት ቀልብን ይዞ ከግዙፉ ታሪክ ባሻገር በቅኔያዊ (ትዕምርታዊ ፍካሬው) በልፅጐ መነሻውን ከመጨረሻ ውጤቱ ጋር ያዋደደ ነው፡፡በምዕራፍ 23 ገፅ 140 ላይ ጴጥሮስ፤ ሮማን የተሸከመችውን ውሃ የያዘ እንስራ ይሰብርባታል፡፡ ምክንያት - አደፍርስ ምንጩ ዳር ሲነካካት እንደነበር ስለሰማ በቅናት ተነሳስቶ፡፡
 በዚህ ጊዜ በውሃ እንደበሰበሰች ወደ ምንጩ ስትመለስ አደፍርስ ደነገጠ፤ ሊያቅፋትም እጆቹን ይዘረጋል፡፡ እጁ ሳይደርስ ግን የእነወርዶፋ ዱላ ይወርድበታል፡፡
ከላይ እንዳመለከትኩት ሮማን ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ ትዕምርት ናት፡፡ አደፍርስ ሊያቅፋት ሊደርስባት የሚፈልጋት ኢትዮጵያም እሷ ናት! እስኪ ኢትዮጵያ ከፊውዳሉ ስርዓት በኋላ የተጓዘችበትን መንገድ አስተውሉ፡፡ እስኪ በዘመኑ የነበሩትን የተማሪዎች እንቅስቃሴ ዘወር ብላችሁ ተመልከቱ፡፡ አደፍርስ እኮ ወኪል እንጂ ግዘፍ ነስቶ የምናገኘው አካላዊ ሰው አይደለም፡፡ በእሱ መነፅር ግን ያች ሊያቅፏት፣ ሊደግፏት፣ ሊያዘምኗት የነበረች ኢትዮጵያ (በሮማን ተወክላ) በድንገት ደራሽ ሀይል ለልጆቿ እልቂት፣ ለእሷም ቆሞ መቅረት ምክንያት መሆኗን እናያለን፡፡ እዚህ የንቃት ደረጃ ላይ ያልደረሰው ማህበረሰብ የከፈለው ደግሞ - ዱላ፡፡
ይህ የሃሳብ ልዩነቱም ይመስለኛል የመጨረሻውን የሞት ፅዋ ያስጐነጨው፡፡
ታሪኩ በዚህ መልክ ሲፈስ ከቆየ በኋላ አንድ ግብ ላይ ይደርሳል፡፡ የራሷን ንፅህና ለአደፍርስ ደህንነት ስትል የከፈለችው ጺወኔ፤ የሀሳብ መቃተት የሚያበቃውም በውሳኔዋ የሚፀናውም ይሄኔ ነው፡፡ የጺወኔ ጉዞ የተሻለ አለም ለማግኘት የሚደረግን የሃሳብ ጥረት ያመላክታል፡፡
ባለፉት ምዕራፎች በአንድ ጐን የምድራዊውን ዓለም ከንቱነት፣ በሌላ በኩል የሰማያዊውን ዓለም የፅድቅና የቅድስና ኑሮ፣ ለዚህም የሚደረግ ትጋትን ሲሰብኳት የነበሩት አባ ዮሐንስም በመጀመሪያ አካባቢ የተፃፈውን መፅሀፍ ቅዱሳዊ ቃል እየተናገሩ ይከተሏታል፡፡ በዘመኑስ የኢትዮጵያን መጻኢ እድል መተንበይ የቻለ ነበርን? ልክ እንደ ጺወኔ ተጓዘች እንጂ መድረሻዋን እሷም እኛም አናውቅም ነበር፡፡

Read 1725 times