Saturday, 13 December 2014 11:10

የመንፈሱ ጉብኝት ምናባዊ ጉዞ (ፋንታሲ)

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(0 votes)

            የአውቶብሱ አፍንጫ በተለምዶ አጠራር ደሴ መንገድን ይዞ ይምዘገዘጋል። በውስጡ ካቀፋቸው መንገደኞች በተጓዳኝ ከተሳፋሪው አይን የተሰወረ የሙት መንፈስ አብሮ እየተጓዘ ነው። በመንፈስ አይን አማላይ በሆነች ሴት አጠገብ ያንዣብባል። መንፈስ ለውብ ገላ ቦታ የለውም። ስጋ እና መንፈስ ለየቅል ናቸው። መንፈስ ስጋ ገፎ የጣለ እርቃን ነፍስ ነው። ለእርቃን ገላ ሳይሆን ለእርቃን ነፍስ ነው ቀልቡ የሚከጅለው፡፡ እርቃኗን ወደታየችው ሴት አጠገብ በሚገኘው አየር ላይ ማህለቁን ጣለ። ሴትየዋ በድሪዋ ተከናንባ ትተክዛለች። ከአጠገቧ የተቀመጠው ኮበሌ ከጨበጠው ጫት እንድትቀም እጁን ዘረጋላት። መቃም እንደማትፈልግ ጭንቅላቷን ግራ ቀኝ በማማታት ገለጸችለት። መንፈሱ ባለ ድሪዋ ውቧ ሴት ጭንቅ ጥበብ የምትልበትን ሀሳብ ለመሰለል ወደ ውስጧ ዘልቆ ገባ፡፡
“ቀምበጥ ነኝ፤ መልአከ ሞት የሚሰነዳዳብኝ ቀምበጥ፤ ኧረዲያ…..የትኛው ባለጠግነት ሊቀር ነው..ይልቅ የፈሪ ዱላውን ሳያሳርፍብኝ ማልጄ ልጀግንበት……….ይህ ሰባራ አውቶብስ እየተንቀጠቀጠ አልፈጥን አለኝ እንጂ………እኔማ.. ከወሰንኩ ሰንብቻለሁ።” እልህ እየተናነቃት ከንፈሯን እየደጋገመች ትነክሳለች፡፡
መንፈሱ የባለድሪዋን ሙግት  ማድመጡን ገታ አደረገና ወደ ራሱ ተመለሰ። ስጋ ለብሶ በምድር ለመጨረሻ ጊዜ የቆየበት 1966 ዓ.ም ታወሰው። በ“ሶሻሊዝም” ፍልስፍና ልቡ የጠፋበት ፣አለም ሁሉ በእጁ መዳፍ የተቀመጠች ያህል የተሰማው ጊዜ፤ የቁም-ሞትን ቀድሞ የምር-ሞትን የሞተበተ የአፍላ ዘመን፤ ፍልስፍናው ከሁለመናው ዘልቆ ገብቶ ብስባሽ ስጋውን ለአላማው ለመሰዋት ሲንደረደር ሲንቀዠቀዥ የነበረበት ቀውጢ ሰዓት፤ የልቡን መሻት አይታ ደረቱን ለመንደል ስትምዘገዝ የነበረች የጥይት ቀለሀ መልሳ መላልሳ በምናቡ መጣችበት። የባለድሪዋ የምር-ሞትን አጥብቆ መሻት ከእርሱ ገጠመኝ ጋር መንታ መሆኑ ደንቆታል።
አውቶብሱ እንደ እባብ እየተሳበ፣ ከደሴ መግቢያ አፋፍ ላይ ደርሷል። ሹፌሩ ያጎረሰው ካሴት እየተነፋነፈ የሚያወጣው ድምጽ ባለ ድሪዋንም መንፈሱንም ከገቡበት የሀሳብ ሰምጥ ውስጥ ጎትቶ አወጣቸው። አቀንቃኙ የደሴን ስም አንስቶ አይጠግብም፡፡ በዘፈኑ ውስጥ ያሉት ስንኞች በሙሉ በደሴ ተጀምረው በደሴ ነው የሚያልቁት፡-
ገራዶ ፈቀቅ በል ደሴን ልይበት
ፍቅር እና ሸማ ሲያልቅ አያምርበት፣
አይቻለሁ በአይኔ መች ቀረሁ በዝና
ከሀገርም ደሴ አለ ከወንዝም ቦርከና፣
ደሴ ግራር እንጂ አያበቅልም ጥድ
ፍቅር ለመጨረስ ያልታደልኩትን፣
ዜማው መንፈሱን በጊዜ ታንኳ አሳፍሮ በምድር ቆይታው ከአርባ ዓመት በፊት የታደመባትን ከተማ ዳግም እንዲጎበኛት በግብዣ አግደረደረው። አካል አልባ ሰውነቱን ከወዲህ ወዲያ አንከላወሰና እንደ ንፋስ ሽው ብሎ ከሹፌሩ ፊት ለፊት ከተደነቀረው መስታወት ላይ ተለጥፎ ከተማዋን ማማተር ጀመረ። በትልቅ ጎድጓዳ ሳህን ውስጥ በፍቅር የተቃቀፉ አረጋውያን ቤቶችን ለአይን የምትመግብ ርህሩህ ባልቴት ከተማ ሆነችበት፤ ከላይዋ ላይ የተከናነበችውን አዳፋ ኩታ  በተቀነቀኑላት ውዳሴዎቿ ጀቡና ሽር ብትን የምትል፣ ጎብኚውን የምታጥበረብር ባልቴት ሴት መስላ ታየችው፡፡
በአእምሮ አልባው ጭንቅላት አሰበላት፣ አወጣ አወረደ፤ በአንጀት አልባው ሆድ እቃው ሊያዝንላት ቢፈልግም አልቻለም።
ውቧ ሴት ሻንጣዋን ለመሸከፍ ስትንደረደር ተመስጦው ደፈረሰ። አውቶብሱ ወደ መነኻሪያ በሚወስደው ልብ አውልቅ መንገድ ላይ ከግራ ወደ ቀኝ ዥዋዠዌ እየተጫወተ፣ ከቅጥር ግቢ ውስጥ ሰተት በሎ ገባ። አዳር በደሴ፡፡
ልጅ እግሩ ሹፌር ማልዶ ለጉዞ ለመንቀሳቀስ የአውቶብሱን ጡሩንባ ከልክ በላይ እያስቧረቀው ነው። ተሳፋሪዎቹ በጉዞ ድካም የተጫጫናቸውን የማለዳ እንቅልፍ ለማባረር ደጋግመው እያፋሸኩ፣ ከአውቶብሱ ውስጥ አንድ በአንድ ተሞጀሩ። መንፈሱ የባለድሪዋን አካባቢ ጎብኘት አደረገ። የጎደለ ሰው የለም። ውቧ ሴት-የምር ሞት ናፋቂዋን ገርመም አደረጋትና፤
«እንዲህ በቀላሉ ፍንችር ማለት ይቻላል ብለሽ ነው። እኛም ስንት ዝተን ነበር መሰለሽ» አለ በመንፈስ ቋንቋ፡፡
ሌላ ባለተራን ለመሰለል ዙሪያ ገባውን ማማተር ፈልጓል፤ ከመስኮት አጠገብ የተቀመጠች ባልቴት ባለተራ እንደሆነች ገባው፤ ፈጥኖ ቀረባትና በላይዋ ላይ እያንዣበበ የውስጧን ትርምስ ለማድመጥ ሁለመናውን ተከለ፡፡
በአፏ የወጠረችው የጫት ተርዚና እንደ ቀፈት ተወጥሯል፤ ለራሷ ስለ ራሷ መላልሳ በውስጧ ታነበንባለች፤
“ሂድ.. እንግዲህ፤ አዚምን.. ሸረኛን… ሟርተኛን… ከጎጃችን… ከቀዬአችን.. አብርልን፤ ጣረሞትን…. መላአከ ሞትን.. በሩቁ…. ያዝልን፤ ማጀታችንን በተድላና ፍስሃ…… ሙላልን፤ ለንሰሃ.... ሳንበቃ…. ፈጥነህ… አትከውነን፤ አብሽር አቦ …» ምርቃቱን አሳረገች፡፡
በውስጧ ያጫጫሰችው ሃድራ ሲቆምና የሚቦርቅ ጨቅላ ወደ እርሷ ሲገሰግስ አንድ ሆነ። ከእናቱ እቅፍ እያፈተለክ የሚሯሯጠው ኩታራ፤ ሴትየዋ ያለችበትን አካባቢ ጸጥታ እያደፈረሰ አስቸገረ። ከትከት ብሎ ይስቃል። ይፈነድቃል። በተብታባ አንደበቱ ያገኘውን ያወጋል።
መንፈሱ ጨቅላውን ከላይ እስከ ታች ለመዳሰስ ወሰነ። ደባበሰው። ውስጡን በረበረው። ጓዳ ጓድጓዳውን አገላብጦ ሰለለው፡፡ በጨቅላው ውስጥ ምንም ነገር ሊቃርም አልቻለም። ውስጡ እንደ አንደበቱ አይደለም። ሆድ እና ጀርባ። ጸጥ ረጭ። የተወረረ ከተማ ይመስላል።
 በየተራ ሲያደምጥ በነበረው የውስጥ ሙግት የተነሳ ከደሴ በኋላ ያሉትን ጥቃቅን ከተሞች ሳያያቸው እንደ ዋዛ አመለጡት። የተቀረቱን ለማየት ራዳሩን በውጪው ላይ ተከለ። አንድ ሁለት እያለ ከተሞችን ይቆጥር ያዘ። ደንቆታል። ከተሞቹን አውቶብሱ ሲያልፋቸው አንድ ይሆናሉ። ሁሉም በትእዛዝ በአውቶብሱ ሽንጥ ልክ የተሰሩ ይመስላሉ። በጣም ሚጢጢዬ ከተሞች። አውቶብሱም ሽው። ከተሞቹም ሽው። በከተሞቹ ላይ እየተሳለቀ ብዙም ፈቀቅ ሳይል ድንገት አውቶብሱ እንደ መንገጫገጭ ብሎ ቆመ። የአውቶብሱ ጉዞን ለማስተጓጎል ሆን ብሎ ያቀደ የሚመስል የግመል ሰራዊት በአስፓልቱ ሆድ ላይ ተነጠፈ። የሰራዊቱ ቁጥር በስሌት አይገፋም። ስፍር ቁጥር ከሌለው የግመል ሰራዊት መካከል አንድ ባለ ሪዛም-ግመል በኩራት ይጀነናል። መንፈሱ በግመል ቋንቋ ይህንን ባለ ሪዛም ግመል ሊያናዝዘው በመስኮት ሽው ብሎ ወጣ።
“ጥያቄያችሁ ምንድን ነው?“ አለ መንፈሱ፤ ወደ ሪዛሙ ግመል ጠጋ ብሎ
“የአመጻው ፍሬ ነገር ወዲህ ነው፤ ይህንን ሁሉ የግመል መንጋ ያገተውን ጌታችንን ወግድ ለማለት የቆረጥንበት ቀን ዛሬ ነው። እንደ እድል ሆኖ እናንተን አገኘን”
“የእናንተ አመጽ ከመንገደኛው ጋር ምን ያይዘዋል?”
”በደንብ ይገናኛል እንጂ። ብቻችንን ጌታችን ላይ ለማመጽ የግመል ተፈጥሯችን አይፈቅድልንም”
“በዚህ ጎዶሎ አሳዳሪያችሁ ላይ ፊታችሁን ማጥቆር ነው የተሳናችሁ?”
“ያልተነካ ግልግል ያውቃል። ነጻነት ያለ ዋጋ አይገኝም። አሳዳሪያችንን ወግድ ብንል ለከርሳችን  አቤት ማን ይልልናል? እህል ውሃ ፍለጋ  ላይ ታች ልንዳክር? ይህ ከሚሆን ጠግቦ ባሪያ መሆን ይመረጣል”
”ምን የሚሉት ማምታት ነው። ጨለማና ብርሃን አንድነት የላቸውም። ይልቅ አሳዳሪያችሁን በሻኛችሁ……… ” መንፈሱ ንግግሩን ሳይጨርስ የደነበረ በሬ የግመሎቹን አሳዳሪ መቀመጫ ሰቅስቆ ወደ ላይ ሲያጎነውና የተነጠፈው የግመል መንጋ ወደ የአቅጣጨው ሲበተን አንድ ሆነ፡፡
አውቶብሱ ተንቀሳቀሰ። ተሳፋሪው በሁኔታው ግር ተሰኝቷል፡፡ “አይ የ8ኛው ሺ ግመል ……” የሚል ደምጽ ከመንፈሱ ጆሮ ድንገት ጥልቅ አለ። ቃሉን ያወጡት ሹፌሩ አካባቢ ያሉ አዳፋ ቀሚስ የለበሱ አዛውንት ናቸው። ለጉስቁልና እጅ ሰጥተዋል። ትንሽ እልፍ ብሎ ከፊታቸው ወዝ የሚቀዳ፣ ድሎት ዘልቆ የገባቸው፣ ጥቁር ካባ የተከናነቡ፣ ጺማቸውን ያጎፈሩ ጎልማሳ ሰው አሉ። እጃቸው ላይ በጣም ዘመናዊ ስልክ ይታያል። የስልካቸውን ስክሪን እየነካኩ ጌም ይጫወታሉ። በጌሙ በጣም ተመስጠዋል። መሀል መሀል ላይ ለሚደወልላቸው ጥሪ በስጨት እያሉ መልስ ይሰጡና መልስው ወደ ጌሙ ይተከላሉ፡፡ መንፈሱ ወደ ጎስቋላው አዛውንት ተሳበና የውስጣቸውን ትርምስ ማድመጥያዘ፤
«እንዲህም ተኩኖ የእግዚሀርን መንግስት መውረስ፤ ግድየለም  ይህ በጨዋታ፣ በአልባሌ የመንፈዝ ልምድህ ይጠቅምሀል፤ በገሀነብ ለዳቢሎስ በእሳት ላይ የመሄድ ትርእይት  ታሳያዋለህ፤» በውሳጣቸው እያጉተመተሙ ከፉኛ ተብሰለሰሉ፤ የአዛውንቱን ብሽቀት በሰማበት ቅጽበት መንፈሱ  መንፈሳዊ ፈገግታውን በአየሩ ላይ ለቀቀው  ።
ተረኛውን ለማሰስ ተነሳሳ። በመስኮት አሻግሮ ወደ ወጪ ይመለከታል። አውቶብሱ አላማጣ ጋ ሲደርስ ወደ መሖኒ የሚያስገነጥለውን መንገድ ይዞ ተፈተለከ።
 በመንገዱ ጠርዝ ባሻገር ባለው አውላላ ሜዳ ላይ የአቧራ ማእበል እየደጋገመ ይነሳል። የአቧራው ሱናሜ በአካባቢው ላይ ነግሷል። አቧራውን ለብሰው የሚሯሯጡ ጨቅላዎች፤ ተራራን ራስጌ ያደረጉ ትልልቅ ቋጥኞች፤ የደረሱ የበለስ ተክሎች፡፡ ሁሉንም በወፍ በረር ከግራ ከቀኝ ሽው ሽው እያለ በመስኮቱ አሻግሮ ጎበኛቸው፡፡ ስራ የፈቱ፤ ያለ ጭንቅ የተዘረጉ ብዙ አውላላ ሜዳዎችን እየቆጠረ ነው የመጣው፡፡ የሰው ብዛት ከእርሱ ዘመን በንጽጽር እጅጉንም እንዳልተጋነነ እርግጠኛ ሆኗል፡፡ ብዛቱ ቢያይልማ ጠጠር መጣያ አይገኝም ነበር።
አውቶብሱ መንገዱን እየገመሰ ከሆነ አቀበት አካባቢ ደረሰ። አቀበቱ ምጥ ሆኖበታል። የጣር ድምጽ እያሰማ ቀስ ብሎ ይጎተታል። አቀበቱን ጨርሶ ለጥ ባለው መንገድ ላይ ሲንደረደር መንፈሱን አንድ ክስተት ቀልቡን ያዘው።
ከሲታ በሬዎችን የጠመደ ኪሲታ ገበሬ አለታማውን መሬት ለማረስ ይታገላል። ከኋላው ዘር በእርቦ የያዘች ጎስቋላ ሴት ትከተለዋለች። የለበሰችው ቀሚስ በላይዋ ላይ አልቋል። መንፈሱ እንደ መረበሽም እንደ መደንገጥም አደረገው። ግና መንፈስ ነውና በቅጡ መረበሽም መደንገጥም አልቻለም።
መሬት ለአራሹ በብርቱ ሲያዜመው የነበረው መፈክር ነበር። የኑሮውም የሞቱም መንስኤ ከገበሬ ጋር የተቆራኘ ነው። ከገበሬ ተወልዶ ለገበሬ ሞተ። ጠብ ያለ ነገር ግን የለም። ከርሞ ጥጃ። ከጥጃ ፈቀቅ ያለ ትእይንት እስካሁን አላስተዋለም። አሮጌውን ማንነት እንዳስቀመጠው ነው። የዱሮው በሬ ቀለሙ እንኳን አልወየበም። ከዛሬ አርባ አመት በፊት በአደራ መልክ ያኖረው ድንቁርና ከእነ ፍጥርጥሩ  እንዳገኘው ሲሰማው፣ በሞት አለም ውስጥ እያለ ያመለጠው ነገር እንደሌለ እርግጠኛ ሆነ። ድንገት እንደ እርጎ ዝንብ በህያዋን አለም ውስጥ ጥልቅ ብሎ  የተመለከታቸውየተቃርኖ ትእይንቶች ሰላሙን ተፈታትነውታል። ለሞት የምትጣደፈው ውቧ ሴት፤በምርቃት የማትጠረቃዋ ባለተርዚናዋ ሴት፤ጥድፊያ አልባ አለም ውስጥ የሰጠመው ህጻን፤ለስጋ ፊት የማይሰጡት ጎስቋላ አዛውንት፤ስጋን በብርቱ የጠገቡት ባለ ካባው ጎልማሳ። ሁሉም በተቃርኖው አለም ፈተና ውስጥ ወድቀዋል።
መንፈሱ ወደ ራሱ አለም ለመመለስ ተሰናዳ። ከህያዋን አለም ያገኘው ደስታ የለም፤ትካዜ ብቻ፤የሚተክዙ ከተሞች፤ የተከዙ ሜዳዎች ፤የተከዙ መንገደኞች። ሌላ ምንም የለም። የመንፈስ አለሙ ክፉኛ ናፈቀው። ሽው ሽው አለና በረዳቱ መስኮት በኩል ተፈተለከ። አውቶብሱም የሚተክዙ መንገደኞቹን እንዳቀፈ፣ የተራቆቱ ሜዳዎችን ከኋላው እየተወ መሄዱን ቀጠለ። የጉዞ መዳረሻውን እርሱም በከርሱ ውስጥ እንዳጨቃቸው ተሳፋሪዎቹ በእጅጉ ይናፍቃል።



Read 1712 times