Saturday, 20 December 2014 12:57

“እናትክን በሉልኝ!”

Written by  ኦርዮን ወ/ዳዊት
Rate this item
(1 Vote)

የገሞራው መልእክት፤)
“ለፈፀመው ደባ፣ ለሰራውም ግፉ፣
እናትክን በሉልኝ በዚያ የምታልፉ”

    ገሞራው /ኃይሉ ገብረ ዮሐንስ/ ኪነትንና የኪነጥበብ ቤተሰቦችን በሚያሳዝን ሁኔታ በሞት የተለየ ብርቅ ባለቅኔ ነበር፡፡ በህይወት በቆየባቸው ዘመናት ሁሉ ብዙ ነገር ታዝቦ፣ የታዘበውንም በብዕሩ ሰቅስቆ የማድማት ልዩ ተሰጥኦ የነበረው ገጣሚ ነው፡፡ ገሞራው የተፈጥሮንም ሆነ ሰው ሰራሽ ህግጋትን አጥብቆ ይሞግት፣ ልዩ ሃብቱ በሆነው የግጥም ኃይሉ ይፋለም የነበረ ጽኑዕ ደራሲ ነው፡
“በረከተ መርገም” በሚለው ግጥሙ ዝናን ብቻ ሳይሆን ፍዳን የተቀበለው ገሞራው፣ የሚታወቀው እጅግ ረጃጅም በሆኑ ግጥሞቹ ነው፡፡ ከዚህ ሌላ ገሞራውን ልዩ የሚያደርጉት መለያዎችም ነበሩት፤ አገሩን ከነፍሱ በላይ ይወድ ነበር፡፡ መንግሥታት ሁሉ አይጥሙትም፡፡ ለገሞራው መንግሥት ማለት በህዝብ ላይ የወደቀ አላል ማለት ነው፡፡ ገሞራው የዓለም ድሆች ሁሉ ጠበቃ ነበር፤ ለድሆች የማይበጁ ከሆነ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፤ ህግና ዳኝነት፣ ጥበብና ጠቢባን ገደል ቢገቡ፤ ጅሃነም ቢወርዱ፣ ወደ አዘቅት ቢወረወሩ ጉዳዩ አልነበረም፡፡
በገሞራው እምነት ጥበቡ ሁሉ፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤቶች በመላ ለድሃ ጥቅም መዋል አለባቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ ወንዞች፣ አየሩ፣ ባህሩ፣ ሜዳውና ሸንተረሩ ሁሉ ለድሃ ጥቅም ሊውሉ ይገባል፡፡ አለዚያ የእርግማን በረዶውን ያዘንብባቸዋል፡፡ “እናትክን በሉልኝ!” በሚል ርዕስ 132 ገፅ የፈጀ ግጥሙን የጻፈውም ዓባይን ለመውቀስ ነው፡፡
ግን ዓባይን የወለደችው የዓባይ እናት ማን ናት? እናት ከሌለውስ እንዴት “እናትክን በሉልኝ!” ተብሎ ይሰደባል? ለነገሩ እናቱ እንጂ እሱንማ ምን ብሎ ይሰድበዋል? ገሞራው የስድብ ሱስ የለበትም፤ ግን ሁሉም ነገር ለድሃ ጥቅም ካልሰጠ የእርግማን ናዳውን ያወርድበታል፡፡
“ይንፏፏል ይሉኛል፣ ማንሔ ያንፏፏው፤
ውሃ ጠምቶት ሲረግፍ ወገኔ ያ ሁል ሰው፤
ሀገሩን ቆራርጦ ለባዕድ የሚወርደው፣
ያ ዐባይ የሚሉት የወንዝ ምናምንቴው!
ይንሿሿል ይሉኛል አማቱን ያንሻሻው፤
ውሃ ውሃ እያለ ወገኔን እያየው፣
ባጠገቡ ገፍቶ ያ ዐባይ ሲሸሸው፣
ያ ዐባይ የሚሉት ወንዛችን ከሃዲው!” በማለት የስድብ ዶፉን ያዘንብበታል፡፡
መጽሐፉ የታተመው እ.ኤ.አ በ1981 ስዊድን ውስጥ ነው፤ ገሞራው ዐባይን እንደ ሰው በአካል ቢያገኘው ጥቂት ርህራሄ የሚያደርግለት አይመስልም፡፡ “ወገኔ በውሃ ጥም ሲያልቅ አንተ ለባዕዳን ለመድረስ ነፍስህ እስኪጠፋ ትጣደፋለህ” ነው የግጥሙ ዋና የትዝብት ጭብጥ፡፡
“ደርቡሽን ሲያጣላ የኖረ ከሐበሽ፣
አይደለም ወይ ዐባይ የነበር ሲረብሽ!!
አይደለም ወይ ዐባይ ሠራዊት ያስፈጀ?
ከሺ ዘመን በላይ ሲያታግል ያስረጀ፡፡
አይደለም ወይ አባይ ራስ ያስቆረጠ፣
ንጉሠ ኢትዮጵያን ጐራዴ ያስዋጠ፡፡
አይደለም ወይ ዐባይ በጦር ሲያከሳክስ፣
ቱርኮችን ከደርቡሽ የኖረ ሲያጣቅስ፡፡
በኢርቱዕ መንገድ የወገን ደም ሲያፈስ፣
ዘለዓለም የኖረ እስከ ዛሬ ድረስ፡፡
ስንቱ ነፍጠኛ ነው ኢትዮጵያዊ ሞረሽ፣
ለሀገሩ ብሎ ያለቀው በደርቡሽ?
ኢርቱዕ መነሻ እየሆነ ዐባይ፣
በሃይማኖት ሲያፋጅ የኖረ አይደለም ወይ?
*    *    *
ለማጋደል ተግባር ከሆነ ያንተ መኖር፣
ለምንድን ነው ከቶ የህላዌህ ምሥጢር፣
ክችች፣ ክርር አርጐህ ደርቀኸው የማትቀር?”
ሲል ዐባይን ከአፉ ሳይሆን ከንፁህ ልቡ ያወግዘዋል፣ ይረግመዋል፡፡ እንደ ገሞራው እምነት፤ ዐባይ ለአገራችን ህዝብ የፈየደው ቁምነገር ቢኖር ከተራው ዜጋ እስከ ንጉሠነገሥቱ እንደ ጭዳ በግ ለዕርድ ከማብቃት የዘለለ ዕርባና የለውም፡፡ ዐባይ በሃይማኖት ሰበብ ብዙ ምስኪን ነፍሳት የተቀጠፉበት፣ ዕልፍ ጀግኖች አንገታቸውን ለጐራዴ፣ ደረታቸውን ለጥይት የገበሩበት ትልቅ ጣኦት ነው፡፡
“ኧረ ሰዎች በሉ፣ ድረስ ነፊ ወንፊት፣
ሀገሩ ተዝቆ ተንዶ ሳይሸፍት፣
ዶማና አካፋ ያ አባይ ሆኖበት፣
እንደቡልዶዘርም ነድሎ ገፎ ወስዶት፣
ራቁቱን ሳይቀር፣ አባይ ተወን በሉት፤
ሀገር ባዶ ሳይሆን አፈር አልባ ግተት፣
አፈሩን ማጋዙን ቢተወው ምናልባት”
ከዚህ በላይ ያሉት ስንኞች “መገደብ ባይቻል እንኳ አፈሩን በወንፊት እየነፉ የሚያስቀሩ ብልሆች ያስፈልጉናል፤ አለዚያ አፈሩ እንደሰው ሸፍቶ በረሃ ይገባና መመለሳቸው ያስቸግራል” የሚል የማስጠንቀቂያ ደወሎች ናቸው፡፡
“በቆላው ሀገር ውስጥ ለሚቧርቅ ፈረስ፣
በታችኛው ምድር ለሚፈነጭ ፈረስ፤
እጓዳ ዠማ ውሃ በመስክ ለሚደንስ፣
ልጓሙ ደጋ ነው ከያዙት የማይፈስ” ሲልም ዐባይን መያዝ፣ መቆጣጠር የሚቻለው ከላይ ከደጋው፣ ከምንጩ አካባቢ እንጂ ጉልበቱን እያፈረጠመ ወደ ቆላው ወይም ወደ ጥልቅ ሸለቆ ከደረሰ በኋላ ለመያዝም ሆነ ለመግታት እንደማይቻል አስገንዝቦናል፡፡
ገሞራው ለረጃጅም ግጥሞቹ አዝማች ያበጅላቸዋል፤ ልክ ብዙ ሠራዊት ያለው ኃይል አዝማች እንደሚያስፈልገው መሆኑ ነው፡፡ የ “እናትክን በሉልኝ”  አዝማችም እንዲህ የሚል ነው፡-
“ይፈስሳል ይሉኛል አባይ ዐይኑ ይፍሰስ፤
ያን ስንቱን ወገኔን የውሃ እጦት ሲያምስ፣
የድርቀት ጋንጩራ ሲበላ ስንቱን ነፍስ፤
ውሃ ውሃ እያለ ለጋው ሲቀነጠስ፣
ናይል አባያችን አለ፤ ነበር ሲፈስስ፡፡
ለፈጸመው ደባ፣ ለሰራውም ግፉ፣
እናትክን በሉልኝ በዚያ የምታልፉ”
ገሞራው ለአገሩ ባዳ ሆኖ በስደት ከሚኖርበት ሀገረ ስዊድን የወገኑን በረሃብ መማቀቅ፣ በጠኔ መውደቅ በመገናኛ ብዙኃን ሲሰማ ልቡ ክፉኛ ደማ፡፡ የሚያደርገው ቢያጣ ለምስኪን ወገኖቹ ዳቦ መስጠት ባይችል፤ ተፈጥሮን በተለይ ዐባይን መስደብ የቁጭቱ መወጫ አድርጎ ወሰደው፡፡
“... እናትክን በሉኝ!” ሲልም በመልእክት ዘለፈው፡፡
“ዓይኑ ይፍሰስና እዩት አባይ ሲፈስ፣
እንደ ቀትር እባብ ሲነጉድ፣ ሲርመሰመስ፣
ላልተወለደበት ችሮታ ሊለግስ፣
ያ ስንቱ ወገኑ በጥማት ሲታመስ፤
ድረስና አርጥበኝ እያለው ስለነፍስ፣
እንዲያ ሲለምነው፣ እሪ ሲል ቢመለስ”
ገሞራው በዐባይ ላይ ያለው ጥላቻ ማብቂያ ያለው አይመስልም፡፡ ዐባይ ብቻ ሳይሆን ሐይቆችና ሌሎች በዓለም ያሉ ወንዞች ሁሉ ለድሃ ካልጠቀሙ፣ ድርቅን መከላከል ካላስቻሉ ከንቱ ፍጥረታት መሆናቸውንም በምሬት ይገልፃል፡፡
ለምሳሰሌ ከተሰጣጠቀ መሬት ፎቶግራፍ ሥር እንዲህ በሚል ግጥሙ የልቡን ተንፍሷል፡-
“ምድሪቱን ተመልከት፣ አፏን ከፍታ ስትጮህ፣
ዋይ ዋይ ድረስልኝ እያለች ተማጥናህ፣
እያለች ወዳንተ ኧረ የውሃ ያለህ፣
በደረቅ ጉሮሮ፣ እሪ ስትል ምድርህ፣
ምን ይሆን ያ ጆሮህ መስማት የተሳነህ?”
* * *
… ወገን ሲያልቅ በድርቀት ውሃዋን ካልሰጠች፣
ምድረ ሐይቅ በመላ ለምን ተፈጠረች?
ለምንስ ዓላማ እንዲያ ትኖራለች?”
ገሞራው ዐባይን ብቻ አይደለም “እናትክን በሉልኝ!” የሚል፤ ሃይቆችን ሁሉ ያወግዛል፡፡ “ምድረ ሐይቅ በመላ ለምን ተፈጠረች?” ሲል የወንዞችን፣ የሃይቆችንና ኩሬዎችን ጥንተ ተፈጥሮ ጭምር ያለመታከት ይጠይቃል፡፡ ብሎት ብሎት አቅም ሲያጣ ወደ ተለመደው እርግማኑ ይገባል፤ እንዲህ እያለ፡-
“ቀድተህ አፍስልኝ በፅዋ፣ በገንቦ.
ዋጋውን ስጥልኝ በሚካኤል፣ ባቦ፡፡
የሚቻልም ቢሆን እርጭና ያን ቤንዚን.
በእሳት አቃጥልልኝ ተኮማትራ እስክትበን፤
ድብን፣ ጭርር ብላ ትቅመሰው ድርቀትን፡፡
አደራ አቃጥልልኝ፣ እንደደላት አትቅር፤
ወገኔ እንዲያ አልቆ እሷ ተዝናንታ አትኑር፡፡
           *  *  *
እስከዚያው ድረስ ግን ስድቤን አድርስልኝ፣.
ለሰራችው ወንጀል ዋጋዋን ስጥልኝ፤
ከተኛሽበት ላይ ያድርቅሽ በልልኝ”
ገሞራው የወገኑ በድርቅ መሰቃየት እንጀቱን ዘልቆ አንገብግቦታል፡፡ ረሃቡ ይሞረሙረዋል፤ ጥሙ ያቃጥለዋል፡፡ በአውሮፓ የሚኖር ቢሆንም የሀገሩን ዜጎች ስቃይ ይሰቃያል፤ ያስብ ያስብና አማራጭ ሲያጣ ውሃውን መራገም ይጀምራል “ያቃጥልህ፣ ያኮማትርህ ወዘተ” እያለ የስድብ ናዳውን ያዥጎደጉዳል፤ ርግማን የወገንን ጠኔ ያስታግስ፣ የችግር ድውያንን ይፈውስ ይመስል፡፡
ገሞራው ለወራጅ ውሃ ሁሉ ወህኒ ቤቱ መስኖ ነው ብሎ ያምናል፤
“ወንጀለኛ ውሃን ሥርዓት ካላሰረው፣
ብዙ የሚያጠፋ ባለጌ ዋልጌ ነው፤
በጣም አደገኛ አድርቆ ገዳይ ሰው!!
ማረሚያው እስር ቤት ለመረን ልቅ ውሃ፣
አንድ‘ኮ መስኖ ነው አርጣቢ በረሐ፡፡
ታዲያ‘ኮ ለምን ነው ዐባይ ያልታገረ፣
በመስኖው እስር ቤት ሳይገባ የቀረ፣
በዋልጌነት ግብሩ ሲቃበጥ የኖረ?”
ገሞራው ይጠይቃል፤ ግን መልስ አያገኝም፡፡ ለጠየቀው ጥያቄ መልስ ሲያጣም እርግማኑን ይቀጥላል፡፡
“ይፈስሳል ይሉኛል  ያ ዐባይ ትልቁ፣
ዓይን ካለው ይፍሰስ፤ ይውጣ ውልቅልቁ፤
ወገኖች ካልረዳ በውሃ ጥም ሲያልቁ!
እመትርህ ነበረ ቁርጥርጥ አድርጌ፣
በመስኖ ጎራዴ ከራስጌ ከግርጌ፤
ከውሃህ መንፈግህ ነህና ባለጌ”
ከእርግማኑ በኋላ የቦታም የአቅምም ርቀት እንዳለ ሲገነዘብ ገሞራው የሚከተለውን ብሏል፡-
“ግና ምን ያደርጋል፤ አንተ ወዲያ ማዶ
እኔ ደግሞ ወዲህ እቅድ ተወላግዶ፣
ለጊዜው ድነሃል አወይ እኔ ነዶ!”
ገሞራው ይህን ቁጭትና ርግማን የተሞላበት ግጥም ያሳተመው በ1981 ነው፤ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ የዐባይ ግድብ መጀመሩን ሲሰማ ምን ብሎ ይሆን? ምን አይነት ስሜትስ አድሮበት ይሆን? ስሜቱን በወጉ ሳንረዳለት ድንገት አለፈ፡፡



Read 3511 times