Monday, 29 December 2014 07:31

የዘጠኙ ፓርቲዎች ትብብር ሁለተኛ ዙር የተግባር እንቅስቃሴውን ይፋ አደረገ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

ትብብሩ ለሁለት ወሩ እንቅስቃሴ የ1.2 ሚ. ብር በጀት አፅድቋል
-    የሰማያዊ ፓርቲ የክልል አመራሮች የአመራር ክህሎት ስልጠና እየወሰዱ ነው
  የዘጠኙ ፓርቲዎች ትብብር የ“ነፃነት ለፍትሃዊ ምርጫ” ሁለተኛ ዙር የተግባር እንቅስቃሴ ፕሮግራሙን በትላንትናው እለት ይፋ ያደረገ ሲሆን ለሁለት ወር እንቅስቃሴው ማስፈፀሚያ የ1.2 ሚሊዮን ብር በጀት አፅድቋል፡፡ በሌላ በኩል የሰማያዊ ፓርቲ የክልል አመራሮች ካለፈው እሁድ ጀምሮ ጠቅላላ የአመራር ክህሎት ሥልጠና በፓርቲው ጽ/ቤት እየወሰዱ እንደሆነ ታውቋል፡፡
የትብብሩ አስተባባሪ ኮሚቴ ትናንትና በሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት ሁለተኛ ዙር ፕሮግራሙን ይፋ ባደረገበት ወቅት፤ በመጀመሪያው ዙር እንቅስቃሴ ከጎኑ በመቆም አላማውን ለደገፉ በአገር ቤትና በውጭ ለሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ምስጋናውን ያቀረበ ሲሆን “ትግሉን ለማደናቀፍና ትግላችንን ለመግታት ለሰላማዊ ዜጋ ቀርቶ ለጠላት የማይገባ ኢ-ህገ-መንግስታዊ ተግባር ለፈፀማችሁ የመንግስት አካላት ወደ ህሊናችሁ እንድትመለሱ ጥሪ እናቀርባለን” ብሏል፡፡
የትብብሩ አስተባባሪ ኮሚቴ በእለቱ በሰጠው መግለጫ፤ በቀጣዩ ሁለት ወራት አዲስ አበባን ጨምሮ በ15 ተመረጡ ከተሞች ላይ የተለያዩ የአዳራሽና የአደባባይ ህዝባዊ ውይይቶች፣ ሰላማዊ ሰልፎችን እንደሚያደርግም አስታውቋል፡፡ የእንቅስቃሴዎቹ አላማ ቀጣዩን ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ተዓዕማኒና አሳታፊ እንዲሆን መንግስት የጠየቅናቸውን ጥያቄዎች ትኩረት ሰጥቶ እንዲመልስ የሚያሳስብ ነው ያሉት አስተባባሪ ኮሚቴዎቹ፤ በተለይም የካቲት 15 በተመሳሳይ ሰዓት በ15ቱም ከተሞች ሰላማዊ ሰልፎች እንደሚደረጉ ጠቁመዋል፡፡
በመጀመሪያው ዙር እንቅስቃሴ የልማት ስራ በሚከናወንባቸው ቦታዎች ሰልፍ እየወጡ መንግስትን ይፈታተናሉ በሚል ከመንግስት ወቀሳ ቀርቦባችኋል በሚል ከጋዜጠኞች ለተነሳው ጥያቄ፤ “መንግስት ትግላችንን ለማወክና የህዝብ ድምፅ ለማፈን በርካታ እንቶ ፈንቶ ምክንያቶችን ሲደረድር ቆይቷል” ያሉት የትብብሩ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል፤ “ቀደም ሲል ቤልኤር ሜዳ  እና አበበ ቢቂላ ስታዲየም ህዝባዊ ውይይት ለማድረግ ጠይቀን ተከልክለናል፤  በኋላ እኛ ግን ተከለከልን ብለን ትግላችንን አናቆምም፤ አናፈገፍግምም” ሲሉ በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁከት ለማስነሳት ለሚጥሩ ፓርቲዎች ቀይና ቢጫ ካርድ ይሰጣቸዋል ማለታቸውን በተመለከተ አስተያየታቸውን ተጠይቀው ሲመልሱ፤ “ረጅም ታሪክና ባህል ላለው ህዝብ የሚመጥን አባባል አይደለም” በማለት የጠቅላይ ሚኒስትሩን አባባል ያጣጣሉት ኢንጅነሩ፤ “እንደ አገርና እንደ ህዝብ የሚናገሩት ካለ እንጂ በአሁኑ ሰዓት ከእሳቸው ምክርም ትምህርትም የምንፈልግ አይደለንም፤ ቢጫና ቀይ ካርድ የሚለውም አነጋገር ለመረዳት ያስቸግረናል” ብለዋል፡፡
በቀጣዩ ምርጫ ትብብሩ ይሳተፍ እንደሆነ የተጠየቁት ኢ/ር ይልቃል፤ “በምርጫ ውስጥ ከሌለን እንዴት ምርጫው ፍትሃዊና ግልፅ ይሁን ብለን እንጨሃለን” ሲሉ በጥያቄ መልሰዋል፡፡ “የሰላማዊ የስልጣን ሽግግር መሳሪያ ነው ብለን ስለምናምን በአግባቡ፣ ግልፅና ተአማኒነት በተሞላው መንገድ መከናወን አለበት፤ ያለበለዚያ ግን በምርጫው መሳተፍ ለህገ-ወጥነትና ለአገር ሀብት ብክነት መተባበር ነው” ሲሉም አክለዋል፡፡ ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “ተቃዋሚ ፓርቲዎች መንግስትን መገዳደር አይችሉም” በሚል የሰነዘሩት ማስፈራሪያ አከል ንግግር ህዝብን ለማዳናገር የተፈጠረ ነው ያሉት አስተባባሪ ኮሚቴዎቹ፤ ከትግላቸው የሚያግዳቸው አንዳችም ነገር እንደሌለ ገልፀዋል፡፡ ይህን ተከትሎ ባወጡት ባለ አራት ነጥብ መግለጫም የጉዳዩ ባለቤት ኢትዮጵያዊያን በሰላማዊ መንገድ ተፅአኖ በማሳረፍ መንግሥት ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ ራሱን እንዲያዘጋጅ፣ የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አመራሮች የተጣለባቸውን አገራዊና ህዝባዊ ግዴታ ያለ አድልዎ በመወጣት ከታሪክ ተወቃሽነት እንዲድኑ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለይም የመግባቢያ ሰነዱ የጥናት ሪፖርት ላይ እስከመጨረሻው የነበሩ ከፓርቲ መሪዎች የግል ፍላጐትና ከፓርቲ ጥቅም የሚልቀውን የህዝብ ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት መጪው ምርጫ ፍትሃዊ ይሆን ዘንድ ከትብብሩ ጐን እንዲቆሙ ጠይቀዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከ50 በላይ የሚሆኑ የሰማያዊ ፓርቲ የአመራር አካላት ከባፈው እሁድ ጀምሮ በጠቅላላ የአመራር ክህሎት ዙሪያ ዘርፈ ብዙ ስልጠናዎች እየወሰዱ ሲሆን ስልጠናው እስከመጪው እሁድ እንደሚቀጥል የፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ የፓርቲው አመራሮቻች በክህሎት የዳበሩ፣ በእውቀት የበለፀጉና በቀጣዩ ሰላማዊ ትግል ህዝብን በማደራጀት፣ በማስተባበርና በማሳተፍ በኩል ጉልህ ሚና እንዲኖራቸው ታስቦ ስልጠናው መዘጋጀቱንም ጨምረው ገልፀዋል፡፡
 

Read 1253 times