Monday, 05 January 2015 07:43

የ“ኢትዮ ታለንት ሾው” አሸናፊ ሊፋን አውቶሞቢል ይሸለማል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(6 votes)

“የኢትዮ ታለንት ሾው” ሃሳብ ከሌሎቹ የተለየ በመሆኑ ልንሸልም ወደናል  (ሊፋን ሞተርስ)

            ለሁለት ዓመት ከስድስት ወር በስምንት ዘርፎች በኢቴቪ 3 ሲካሄድ የቆየው የ“ኢትዮ ታለንት ሾው” ምርጥ 10 የተሰጥኦ ተወዳዳሪዎች የጥምቀት እለት ከብሄራዊ ቴአትር አዳራሽ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢብኮ) በሚተላለፍ ቀጥተኛ ስርጭት እንደሚሸለሙ የታወቀ ሲሆን አንደኛ በመውጣት ያሸነፈ 275ሺ ብር ዋጋ ያላት “ሊፋን 320” ሞዴል አውቶሞቢል ይሸለማል ተብሏል፡፡
የአምባሰል ሙዚቃ ቤት ባለቤትና የ“ኢትዮ ታለንት ሾው” መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ፍቃዱ ዋሪ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ በዳኞችና በኤስ ኤም ኤስ መልዕክት በህዝብ የተመረጡ 10 ተወዳዳሪዎች በግልና በቡድን ተለይተዋል፡፡
የሊፋን ሞተርስ የግብይትና ሽያጭ ክፍል ሃላፊ አቶ ዳንኤል ታምራት በበኩላቸው፤ ኩባንያቸው “ኢትዮ ታለንት ሾው” ባለተሰጥኦዎችን ለማበረታታት የተለያዩ ዘርፎችን በማካተት የሚሰራውን ስራ  በመደገፍ ሽልማቱን ለመስጠት መወሰኑን ተናግረዋል፡፡
“እስከ ዛሬ የምናያቸው አይዶል ሾዎች፣ ዘፈንና ጭፈራ ብቻ የያዙ ናቸው” ያሉት አቶ ዳንኤል፤ ኢትዮ ታለንት ሾው ግን በበርካታ ዘርፍ ችሎታ ያላቸውን ባለተሰጥኦዎች ለማፍራት የጀመረውን ሃሳብ እንደወደዱት ጠቁመው፤ አቶ ፍቃዱ እየሰሩ ባለው ስራ ድርጅታቸው መደሰቱን ተናግረዋል፡፡ አስሩ ምርጦች የተለዩት ከ18 ዓመት በላይ እድሜ ያላቸው ተወዳዳሪዎች በድምፅ፣ በውዝዋዜ፣ በግጥም፣ በድራማ፣ በኮሜዲ፣ በስዕል፣ በስፖርትና “ልዩ ችሎታ” በሚል ዘርፍ ለ120 ሳምንታት በተካሄደ ውድድር ሲሆን አንደኛ የሚወጣው መኪና የቀሩት ደግሞ የአይነትና የገንዘብ ሽልማት እንደሚሸለሙ አቶ ፈቃዱ አብራርተዋል፡፡
“ላለፉት 37 ዓመታት ሙዚቃና ፊልሞችን አሳትመን በማከፋፈል ለኢትዮጵያ የኪነ-ጥበብ ኢንዱስትሪ ጉልህ ሚና ተጫውተናል” ያሉት አቶ ፈቃዱ ዋሪ፤ በእነዚህ ጊዜያት እንደነ ጥላሁን ገሰሰ፣ ብዙነሽ በቀለ፣ ማህሙድ አህመድ፣ ይርጋ ዱባለና ሌሎች አንጋፋና አይረሴ ድምፃዊያንን ከህዝብ ሲያገናኙ እንደቆዩ አብራርተው፣ በአሁኑ ወቅት ሙዚቃ አሳትሞ የማከፋፈሉ ስራ አስተማማኝ ባለመሆኑ በ“ኢትዮ ታለንት ሾው” ባለሙያዎችን በማፍራት ዘርፉን ለመደገፍ አስበው ወደ ስራው መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡
የጥምቀት በዓል እለት በአንጋፋው ብሄራዊ ቴአትር ባለተሰጥኦዎችን ስሸልም ትልቅ ደስታ ይሰማኛል ያሉት ስራ አስኪጁ፤ “ከዓመታት በፊት በዚሁ በብሄራዊ ቴአትር አዳራሽ የዓለም የአዕምሮ ንብረት ድርጅት (World Intellectual Property Organization (WIPO) ሙዚቃን በቪዲዮ፣ በኦዲዮና በመሰል ዘዴ አቀናብሮና አሳትሞ በማቅረብ የ“ልዩ ተሰጥኦ” ተሸላሚ ያደረጋቸው መሆኑን አስታውሰው፤ ያን እለት የተሰማቸውን ደስታ በሌሎች ላይ ለማየት በመቃረባቸው በስት መጥለቅለቃቸውን ገልፀዋል፡፡
 አቶ ፍቃዱ አክለውም፤ የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ በዕለቱ በኢብኮ ከምሽቱ 2 ሰዓት ጀምሮ ለሚተላለፍ የመዝናኛ ፕሮግራም ቀረፃ ማካሄዳቸውን ገልፀው ፕሮግራሙ በኢትዮ ታለንት ሾው ውድድር እስከ ምርጥ 25 ድረስ በኮሜዲ፣ በድምፅና በድራማ የተካተቱ ተወዳዳሪዎች ስራዎቻቸውን የሚያቀርቡበት ይሆናል ብለዋል፡፡

Read 3109 times