Saturday, 10 January 2015 10:05

10ሺ ሜትር ሩጫ እየጠፋ ነው

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

•    በየዓመቱ በመላው ዓለም የሚካሄዱት ውድድሮች 5 አይሆኑም
•    ዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ውድድሩን  ከ2016 ኦሎምፒክ በኋላ ሊሰርዘው ይችላል
•    የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች ፍፁም የበላይነት  ምክንያት ተደርጓል
•    ከፍተኛ ውጤት የነበራቸው ኢትዮጵያውያውንም ከውድድሩ ርቀዋል
በዓለም አትሌቲክስ   የረጅም ጊዜ ታሪክ ያለው 10ሺ ሜትር  እየጠፋ ነው፡፡ ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ውድድሩን የብራዚሏ ከተማ ሪዮ ዲጄኔሮ በ2016 እኤአ ከምታስተናግደው  31ኛው ኦሎምፒያድ በኋላ ከኦሎምፒክ መድረክ ለመሰረዝ ማቀዱ ከወር በፊት ተሰምቷል፡፡ ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር አይኤኤኤፍም በ10ሺ ሜትር በመላው ዓለም ይካሄዱ የነበሩ ውድድሮች መመናመናቸው አሳስቦት ውድድሩን በዓለም ሻምፒዮና ለማካሄድ የሚያስፈልገው ሚኒማን በ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ለመወሰን እያጤነው መሆኑም ተነግሯል፡፡ ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ከትራክ የአትሌቲክስ ውድድሮች መካከል 10ሺ ሜትርን ለመሰረዝ ያለውን እቅድ በማጋለጥ ደግሞ የመጀመርያውን ዘገባ የሰራው የአውስትራሊያው ሚዲያ ዘ ኤጅ ነበር፡፡ ከዚያ ዘገባ በኋላ በጉዳዩ ዙርያ የተለያዩ ሃተታዎች እና አስተያየቶች ከመላው ዓለም ሲወጡ የሰነበቱ ሲሆን በየአቅጣጫው የሚነሱ ሃሳቦች የውድድሩን እጣፋንታ ለመወሰን አዳግተዋል፡፡ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ በ2022 እኤአ የጃፓኗ ከተማ ቶኪዮ ከምታስተናግደው 32ኛው ኦሎምፒያድ ላይ ወይንም ከዚያ በኋላ 5 የውድድር መደቦችን ከኦሎምፒክ መድረክ ለመቀነስ ማቀዱ በይፋ የተሰማው ከወር በፊት ነበር፡፡ ከኦሎምፒክ መድረክ ሊሰረዙ ይችላሉ የተባሉት ውድድሮች 10ሺ ሜትር በሁለቱም ፆታዎች፣ የወንዶች 200 ሜትር፣የወንዶች ርምጃ ውድድር፤ የአሎሎ ውርወራና ሱሉስ ዙላይ በሁለቱም ፆታዎች ናቸው፡፡ ዓለም አቀፉን የአትሌቲክስ ማህበረሰብ ያስደነገጠው ይህ እቅድ በተለይ በ10ሺ ሜትር ውድድር እጣ ፋንታ ላይ በመነጋገር ላይ ነው፡፡
10ሺ ሜትር በዓለም የአትሌቲክስ ስፖርት ታሪክ አበይት ሆኖ የሚጠቀስ ትልቅ ውድድር ነበር፡፡ የውድድር አይነቱ የአትሌቲክስ ብቃት መገለጫ፤ የአትሌቶች ፍጥነት እና ፅናትን መለኪያ እና በአስደናቂ ፉክክር ተወዳጅነት ያተረፈ ነበር፡፡ ስፖርት አድማስ በዓለም አትሌቲክስ እየጠፋ ስለመጣው የ10ሺ ሜትር ውድድር የሚከተለውን ሙያዊ ትንተና አጠናቅሯል፡፡
የ10ሺ ውድድሮችን እያጠፉ ያሉ ምክንያቶች
ባለፉት አምስት ዓመታት በዓለም አትሌቲክስ የ10ሺ ሜትር ውድድር የሚካሄድባቸው ከተሞች እየተመናመኑ ናቸው፡፡ በርቀቱ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸውን አትሌቶች በመጋበዝ በብቸኝነት የሚያወዳደሩት በአሜሪካ እና በጃፓን ያሉ ከተሞች ሆነዋል፡፡ ከ10 ዓመታት በፊት ይህ ሁኔታ አልነበረም፡፡ 10ሺ ሜትር በአይኤኤኤፍ ስር በሚካሄደው የጎልደን ሊግ፤ በዓመታዊ የዙር ውድድሮችና በተለያዩ የዓለም ከተሞች ብዛት ይካሄድ የነበረና በሚያስተናግዳቸው የምርጥ አትሌቶች ትንቅንቅ አበይት ትኩረት የሚያገኝ ነበር፡፡ በ2012 እኤአ ከተካሄደው የለንደን ኦሎምፒክ በኋላ ግን  ሁኔታዎች ተቀይረዋል፡፡ በ10ሺ መወዳደርያነት ይታወቁ የነበሩ ከተሞች ውድድሩን ከማካሄድ መቆጠብ ጀምረዋል፡፡ በተለይ በአውሮፓ የሚገኙ የ10ሺ መወዳደርያ ከተሞች በሌላ የውድድር አይነት እየተኩት ናቸው፡፡ በ10ሺ ሜትር የዓለም ሪከርድ በተደጋጋሚ የተመዘገበባት እና በቅርብ ዓመታት ለኢትዮጵያ አትሌቶች የዓለም ሻምፒዮና እና የኦሎምፒክ ተሳትፎ ሚኒማ ማስመዝገቢያ መወዳደርያ የነበረችው የሆላንዷ ሄንግሎ ከተማ ውድድሩን እንዳማተዘጋጅ ያስታወቀችው በ2014 የውድድር ዘመን ነበር፡፡ የቤልጅዬሟ ከተማ ብራሰልስም የ10ሺ ሜትር ውድድርን በሌላ የመቀየር እርምጃን ባለፈው የውድድር ዘመን ተግባራዊ አድርጋለች፡፡ በብራሰልስ የሚገኘውና የቫንዳም መታሰቢያ የሆነው ስታድየም ከአምስት አመታት በፊት የ10ሺ ሜትር ዋና የውድድር መድረክ ነበረ፡፡ ካለፈው ዓመት ጀምሮ  ግን የ1500 ሜትር ውድድር የሚያስተናግድ ሆኗል፡፡ ከሄንግሎ እና ከብራሰልስ ከተሞች ባሻገር ሌሎች የ10ሺ ሜትር ውድድር ይካሄድባቸው የነበሩ የአውሮፓ አገራት ከተሞችም ውድድሩን ከማስተናገድ የተቆጠቡ ሲሆን  የስዊድኗ ስቶክሆልምና የቼኳ ኦስትራቫ ከተሞች ተጠቃሾች ናቸው፡፡
ውድድሩን የሚያዘጋጁ ከተሞች ከመመናመናቸው ባሻገር 10ሺ ሜትር ውድድር ከውድድር መድረክ እየጠፋ የሚገኘው  በተለያዩ ምክንያቶች ነው፡፡ ውድድሩ በመላው ዓለም የሚካሄድባቸው ቦታዎች መመናመናቸው ውድድሩን ለመሰረዝ ከተጠቀሱ መንስኤዎች የመጀመርያው ነው፡፡ በሌላ በኩል በስታድዬም የ400 ሜትር የትራክ መም ለ25 ዙሮች የሩጫው ውድድር ሲካሄድ በስታድዬም እና በቲቪ የሚከታተል ተመልካችን ማሰልቸቱ ሌላው ምክንያት ሆኖም ይጠቀሳል፡፡  በተለይ ደግሞ ባለፉት 20 ዓመታት የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች በውድድሩ ያስመዘገቡት የውጤት የበላይነት  የሌሎች አገራትን የተፎካካሪነት እድል ማጥበቡ ለግዙፍ ስፖንሰር አድራጊ ኩባንያዎች አለመመቸቱ መንስኤ እንደሆነ ይገልፃል፡፡
በሌላ በኩል በአሁኑ ጊዜ አትሌቶች ከ10ሺ ሜትር የትራክ ውድድር ይልቅ የ10 ኪሜ የጐዳና ላይ ሩጫ ተሳትፎ መምረጣቸውም ጠንካራ ተወዳዳሪዎችን እያጠፋ ስለመጣ በውድደሩ ሊኖር የሚችል ፍላጎት እያሳጣ መጥቷል፡፡ በ10ሺ ሜትር የተመዘገቡ የዓለም ሪከርዶች ለረጅም ዓመታት ሳይሰበሩ መቆየታቸውም ከዚህ ሁኔታ ጋር ተያይዞ የሚነሳ ይሆናል፡፡  አትሌቶች ከትራክ ውድድሮች ይልቅ በጐዳና ላይ ሩጫዎች ፤ በግማሽ ማራቶንና በማራቶን ውድድሮች መሳተፍን መምረጣቸውና በዳይመንድ ሊግ እና ሌሎች ዓለምአቀፍ ውድድሮች ከረጅም ርቀት ይልቅ የመካከለኛ ርቀት ውድድሮች ተመራጭ መሆናቸው 10ሺ ሜትርን ከዓለም አትሌቲክስ እያጠፉ ያሉ ሌሎቹ ምክንያቶች ናቸው፡፡
የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች የበላይነትና የተቀረው ዓለም
ከ15 ዓመታት በፊት በተለያዩ የአትሌቲክስ ውድድር መድረኮች በተለይ በ10ሺ ሜትር የማሸነፍ እድሉ ለምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች ብቻ አልነበረም፡፡ የአሜሪካ፤ አውሮፓ እና ኤስያ አትሌቶችም ለውድድሩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ይሳተፉ እና ውጤታማ ይሆኑም ነበር፡፡ ባለፉት 10 ዓመታት ግን በረጅም ርቀት በተለይ በ10ሺ ሜትር ውድድሮች ከምስራቅ አፍሪካ ወዲያ የሌሎች አህጉራት ተሳትፎ ተዳክሟል፡፡ በረጅም ርቀት ከተመዘገቡ 100 ፈጣን ሰዓቶች ከ75 በመቶ በላይ  በምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች የተገኘ ነው፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ እና የኬንያ አትሌቶች በ10ሺ ሜትር ከተመዘገቡ 340 ፈጣን ሰዓቶች 37 በማስመዝገብ የሚስተካከላቸው አገር አልተገኘም፡፡ በ10ሺ ሜትር የምንግዜም 25 ፈጣን ሰዓቶች ደረጃ ላይ የመጀመርያዎቹን ሁለቱን ፈጣን ሰዓቶች በወንዶች ያስመዘገቡትን ኃይሌንና ቀነኒሳን ጨምሮ 6 አትሌቶች ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ  14 ኬንያውያንም በዝርዝሩ ተወክለዋል፡፡  በሴቶች ደግሞ በ10ሺ ሜትር የምንግዜም 25 ፈጣን ሰዓቶች 9 ኢትዮጵያያን ሲገኙ የኬንያ ውክልና በ3 ተወስኗል፡፡
 ባለፉት 10 ዓመታት በ10ሺ ሜትር ያለው የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች የበላይነት ከ2 ዓመታት በፊት ያልተጠበቀ አቅጣጫ ውስጥ መግባቱ የፈጠረው ተስፋ ነበር፡፡ በመላው ዓለም ውድድሮች በተመናመኑበት ጊዜ  ባለፉት ሁለት የዓለም ሻምፒዮና እና ኦሎምፒክ በእንግሊዛዊው አትሌት ሞፋራህ እና በአሜሪካዊው ጋለን ሩፕ የተመዘገቡ ድሎች ለየት ያሉ ሁኔታዎች ታይተው ነበር፡፡ ሁለቱ የአሜሪካ እና የእንግሊዝ አትሌቶች ላሳዩት ውጤት ደግሞ አልበርቶ ሳልዛር የተባለው አሰልጣኝ በምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች ዙርያ ያደረገው ምርምር እና ጥናት በመንተራስ የተደረገ የስልጠና እና የልምምድ ስትራቴጂ አስተዋፅኦ ነበረው፡፡
በእርግጥ በ10ሺ ሜትር የውድድር ታሪክ ከምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች ባሻገር በትልቅ ውጤታቸው ከሚጠቀሱ አትሌቶች መካከል በወንዶች ኤሚል ዛቶፔክ ከቼኮስሎቫኪያና ፓቮ ኑርሚ ከፊንላንድ ዋናዎቹ ናቸው፡፡ በሴቶች ደግሞ የ10ሺ ሜትር ሪከርዷ ላለፉት 15 አመታት ያልተደፈረባት ቻይናዊቷ ዋንግ ዠንሲያ፤ ኖርዌዬጂያኗ ኢንግሪድ ክርስትያንሰንና እንግሊዛዊቷ ፓውላ ራድክሊፍ ይጠቀሳሉ፡፡ ከለንደን ኦሎምፒክ በኋላ አትሌቲክስ ዊክሊ የተባለ የአትሌቲክስ ስፖርት ዓለም አቀፍ ድረገፅ በረጅም ርቀት በተለይ በ10ሺ ሜትር እና በ5ሺ ሜትር ውድድሮች የምንግዜም ምርጥ አትሌቶችን ለሁለቱም ፆታዎች ከ1 እስከ 10 ደረጃ በማውጣት ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ አንደኛ ደረጃን የወሰደው በረጅም ርቀት በኦሎምፒክ 3 የወርቅ እንዲሁም አንድ የብር፤ በዓለም ሻምፒዮና 5 የወርቅ እና 1 የብር እንዲሁም በዓለም አገር አቋራጭ 11 የወርቅ እና 1 የብር ሜዳልያዎችን የሰበሰበው፤ እንዲሁም በ10ሺ ሜትር እና በ5ሺ ሜትር የዓለም ሪከርድን ለ10 የውድድር ዘመናት ይዞ የቆየው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በ285 ነጥብ ነው፡፡ ፊንላንዳዊው ፓቮ ኑርሚ በኦሎምፒክ 4 የወርቅ እንዲሁም 3 የብር ሜዳልያዎችን በመሰብሰብ እና የ10ሺ ሜትር የዓለም ሪከርድን ለ14 የውድድር ዘመናት እንዲሁም የ5ሺ ሜትር ሪከርድን ለ9 የውድድር ዘመናት ይዞ በመቆየት 258 ነጥብ አስመዝግቦ  ሁለተኛ ደረጃ ወስዷል፡፡ በኦሎምፒክ ሁለት የወርቅ፤ በዓለም ሻምፐዮና 4 የወርቅ፤ 2 የብርና 1 የነሐስ ሜዳልያዎችን ያስመዘገበው ኃይሌ ገብረስላሴ በ222 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን አግኝቷል፡፡ በሴቶች ደግሞ የምግዜም ባለከፍተኛ ውጤት አትሌት ተብላ አንደኛ ደረጃን ያገኘችው በረጅም ርቀት በኦሎምፒክ 3 የወርቅ እና ሁለት የነሐስ፤ በዓለም ሻምፒዮና 5 የወርቅና 1 የነሐስ እንዲሁም በዓለም አገር አቋራጭ 4 የወርቅ እና 2 የብር ሜዳልያዎችን የተቀዳጀችው ጥሩነሽ ዲባባ በ178 ነጥብ ነው፡፡ እሷን ተከትለው ደረጃ የተሰጣቸው ከስዊድን፤ ከእንግሊዝ፤ ከአሜሪካ፤ እና ከራሽያ የተውጣጡ አትሌቶች ናቸው፡፡
በሌላ በኩል በ10ሺ ሜትር የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች የሰዓት ሪከርድ ከተቀረው ዓለም ጋር ያለውን ልዩነት ያመለክታል፡፡ የመጀመርያው የዓለም ሬከርድ በወንዶች ምድብ በአይኤኤኤፍ እውቅና አግኝቶ የተመዘገበው በ1912 እኤአ ሲሆን ጂን ባውኒን በተባለ አትሌት 30 ደቂቃ ከ58.8 ሰከንዶች በሆነ ጊዜ ነበር፡፡ ከዚህ ክብረወሰን በኋላ አሁን በቀነኒሳ ለ10 ዓመታት ተይዞ እስከቆየው ክብረወሰን 37 ጊዜያት ሪከርዱ ተሻሽሏል፡፡ በ2005 እኤአ ላይ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ያስመዘገበው የ10ሺ ሜትር የዓለም ሪከርድ 26 ደቂቃዎች ከ17.53 ሰከንዶች ሲሆን ይህ ክብረወሰን ምንግዜም ላይሰበሩ ይችላሉ ከተባሉት የአትሌቲክስ ሪከርዶች አንዱ ነው፡፡ በሴቶችም ያው ነው፡፡ በቻይናዊ አትሌት ቤጂንግ ላይ 29 ደቂቃዎች ከ31.58 ሰከንዶች1 በሆነ ጊዜ ሪከርድ ከተመዘገበ  ከ22 ዓመታት በላይ ሆኖታል፡፡  በሴቶች ምድብ ደግሞ በአይኤኤኤፍ እውቅና አግኝቶ የተመዘገበው በ1981 እኤአ ላይ ሲሆን በ1993 እኤአ ላይ በቻይናዋ አትሌት ተመዝግቦ እስካሁን ያልተሰበረው ጊዜ 29 ደቂቃ ከ31.78 ሰከንዶች ነው፡፡
የኢትዮጵያ ተሳትፎ መዳከሙ
በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እና በኦሎምፒክ የኢትዮጵያ አትሌቶች የበላይነት ካልተነቀነቀባቸው የውድድር ርቀቶች ዋንኛው 10ሺ ሜትር ነበር፡፡ በ10ሺ ሜትር ኢትዮጵያ ከ1983 እኤአ ጀምሮ በተካሄዱ 14 የዓለም ሻምፒዮናዎች ኢትዮጵያ  በሁለቱም ፆታዎች በድምሩ 15 የወርቅ ሜዳልያዎች በማግኘት ተሳክቶላታል፡፡ በአጠቃላይ በዓለም ሻምፒዮና የኢትዮጵያ ተሳትፎ ታሪክ በ10 ሺ ሜትር ወንዶች 9 የወርቅ፣ 4 የብርና 4 የነሐስ እንዲሁም በሴቶች 6 የወርቅ፣ 5 የብርና 3 የነሐስ ሜዳልያዎችን ሰብስባለች፡፡ በኦሎምፒክ መድረክም በ10ሺ ሜትር ኢትዮጵያ ያገኘችው ስኬት ከኬንያ በስተቀር እምብዛም የሚቀናቀነው አልተገኘም፡፡  በ10ሺ የኦሎምፒክ ሪኮርዶች በሁለቱም የተያዙት በኢትዮጵያውያን ነው፡፡ በወንዶች ቀነኒሳ በቀለ ያስመዘገበው ደግሞ 27 ደቂቃ ከ01.17 ሰኮንዶች እንዲሁም  በሴቶች ጥሩነሽ ዲባባ የያዘችው 29 ደቂቃ ከ54.66 ሰኮንዶች ናቸው፡፡ በተለይ በ10ሺ ሜትር የዓለም ሪከርድ በወንዶች ምድብ የኢትዮጵያ አትሌቶች አስተዋፅኦ የላቀ ነበር፡፡ የርቀተን ሪከርድ ላለፉት 10 ዓመታት ተቆጣጥሮ የቆየው ቀነኒሳ ነው፡፡ በ10ሺ ሜትር የሪከርድ ታሪክ ኢትዮጵያውያኑ ኃይሌ እና ቀነኒሳ 5 አዳዲስ ክብረወሰኖችን አስመዝግበዋል፡፡ በ2005 እኤአ ላይ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ያስመዘገበው የ10ሺ ሜትር የዓለም ሪከርድ 26 ደቂቃዎች ከ17.53 ሰከንዶች ሲሆን ይህ ክብረወሰን ምንግዜም ላይሰበሩ ይችላሉ ከተባሉት የአትሌቲክስ ሪከርዶች አንዱ ነው፡፡ በሴቶችም ያው ነው፡፡ በቻይናዊ አትሌት ቤጂንግ ላይ 29 ደቂቃዎች ከ31.58 ሰከንዶች1 በሆነ ጊዜ ሪከርድ ከተመዘገበ  ከ22 ዓመታት በላይ ሆኖታል፡፡  
ከላይ በቀረቡት የ10ሺ ሜትር የውድድር ታሪኮች የጎላ ሚና እና ውጤት የነበራቸው የኢትዮጵያ እትሌቶች ከውድድሩ እየራቁ መምጣታቸውን የሚያመለክት ዘገባን ከሁለት ሳምንት በፊት ያስነበበው የአይኤኤኤፍ ድረገፅ ነበር፡፡ ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር  በ2014 የውድድር ዘመን በተካሄዱ የረጅም ርቀት ውድድሮች ላይ ባቀረበው የክለሳ ዘገባ  ሽፋን ያገኙት ሁለት እና ሶስት የአስር ሺ ሜትር ውድድሮች ናቸው፡፡ በ2014 በወንዶች ምድብ በ10ሺ ሜትር የተካሄደው አንድ ዋና ውድድር ብቻ ነው፡፡ በአሜሪካዋ ከተማ ዩጂን የተካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድር ነበር፡፡ በዚሁ ውድድር ላይ ከ27 ደቂቃ በታች የገቡ አራት አትሌቶች መገኘታቸውን የሚያመለክተው የአይኤኤኤፍ ዘገባ፤ አሜሪካዊው ጋለን ሩፕ ውድድሩን ሲያሸንፍ ያስመዘገበው 26 ደቂቃ ከ44.36 ሰኮንዶች የዓመቱ ፈጣን ሰዓት እንደሆነ ይገልፃል፡፡ በ2014 እ.ኤ.አ የ10ሺ ሜትር ምርጥ ፈጣን ሰዓት ደረጃ ከአሜሪካዊው ጋለን ሩፕ በኋላ እስከ 10 ባለው ደረጃ ያሉት ኬንያውያን ናቸው፡፡ በዚሁ የደረጃ ዝርዝር አንድም ኢትዮጵያዊ አልተካተተም፡፡ በሌላ በኩል በሴቶች ምድብም የ10ሺ ሜትር ውድድር እምብዛም የለም፡፡ የሴቶች 10ሺ ሜትር ውድድርን በማዘጋጀት ዋናዋ አገር ጃፓን እንደሆነች የሚጠቀሰው የአይኤኤኤፍ ዘገባ፣ በተጨማሪ በአሜሪካ ስታንፎርድ የሚዘጋጅ ሌላ ውድድር መኖሩን አውስቷል፡፡ እንደውም ይህ የአሜሪካ ውድድር የዓመቱ ፈጣን ሰዓት እንደተመዘገበበት ገልጿል፡፡ በሴቶች በ10ሺሜትር ምርጥ ብቃት ካሳዩ የዓለም አትሌቶች በተለይ በኤሽያ የአትሌቲክስ ሻምፒዮና የዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ እና የቻይና አትሌቶች ዋናዎቹ ናቸው፡፡ በውድድር ዘመኑ 18 አትሌቶቹ ከ32 ደቂቃ በታች መግባታቸውም ሲገለፅም በዝርዝሩ የኬንያ፣ የጃፓን፣ የመካከለኛው ምስራቅ አትሌቶች በብዛት ሲጠቀሱ ኢትዮጵያውያን ተሳትፏቸው የደከመ እንደነበር ተመልክቷል፡፡

Read 3310 times