Saturday, 17 January 2015 10:41

የነፃ ገበያ ውድድር ትሩፋት - በቢራ ምርት

Written by 
Rate this item
(5 votes)

በሲሚንቶ ገበያ የታየው ለውጥ በቢራ እየተደገመ ነው

   ከነባር የሲማንቶ አምራቾች ላይ ግዙፉ የደርባ ሚድሮክ ፋብሪካ ከዚያም የድሬዳዋው ናሽናል ሲሚንቶ ሲታከልበት እንደታየው በቢራ አምራቾች የተጧጧፈ ውድድርም በአጭር ጊዜ አስደናቂ የዋጋና የአቅርቦት ልዩነት እየታየ ነው፡፡ የዋጋ ንረት በተለመደበት አገር ደንበኞችን የመማረክ ብርቱ ፉክክርና ከፍተኛ የዋጋ ቅናሽ ከመታየቱም በተጨማሪ፤ ዘንድሮ ውድድሩን የሚያጠናክሩ አዳዲስ ግዙፍ ፋብሪካዎች ስራ የሚጀምሩበት ዓመት ሆኗል፡፡
ሰሞኑን ሄኒከን ካስመረቀው ፋብሪካ ብዙም ሳይቆይ፣ በጥቂት ሳምንታትና ወራት ሃበሻ ቢራና  ሌላ ግዙፍ የዳሽን ቢራ ፋብሪካ ገበያውን ይቀላቀላሉ፡፡
በቢዝነስ ውስጥ የመንግስት ድርሻና ጣልቃ ገብነት በቀነሰ ቁጥር፣ የምርቶች ዋጋና የአገልግሎት ጥራት እንደሚሻሻል እንደ ዶ/ር እሌኒ ገብረመድህን የመሳሰሉ ምሁራን በበርካታ አመታት ጥናትና ምርምር ያረጋገጡ ቢሆንም የነፃ ገበያ ውድድር ትሩፋት ያለጥናትና ምርምር በገሃድ ከታየባቸው መስኮች አንዱ የሲሚንቶ ገበያ ነው፡፡ አነስተኛ የግንባታ ስራ የጀመሩ ዜጐች በሲሚንቶ የዋጋ ውድነት፣ ትልልቅ ፕሮጀክት የጀመሩ ኢንቨስተሮች ደግሞ ለባለ አስር ፎቅ ህንፃ የሚበቃ ሲሚንቶ ሲጠይቁ የአንድ ፎቅ ብቻ እየተፈቀላቸው፣ ለዚያውም ተራ እስኪደርሳቸው ግማሽ አመት እየዘገየ፣ የዋጋው ውድነት ታክሎበት ለዓመታት ከፍተኛ እንቅፋት ሆኖ እንደቆየ ይታወቃል፡፡ አንዳንድ አነስተኛ የሲሚንቶ ፋብሪካ ኢንቨስትመንቶችና የነባሮቹ የማስፋፊያ ውጥኖች ላይ ግዙፉ የደርባ ሚድሮክ ሲሚንቶ ማምረት ሲጀምር ግን የቀድሞው የምርት እጥረትና የዋጋ ንረት ተረት ሆነ፡፡ የሲሚንቶ ዋጋ በግማሽ ቀነሰ፡፡ የድሬዳዋው ናሽናል ሲሚንቶ መጠናቀቁና ወደፊትም የናይጄሪያው ናሽናል ሲሚንቶ መጠናቀቁና ወደፊትም የናይጄሪያው ባለሃብት ፕሮጀክት እየተስፋፋ መሆኑ ደግሞ፤ የሲሚንቶ ችግር በነፃ የገበያ ውድድር ለዘለቄታው እንደሚቀየር ይጠቁማል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ መንግስት ከቢራ ቢዝነስ እየወጣ በመጣ ቁጥር፣ የምርትና የአገልግሎት ማሻሻያዎች  እየታዩ መምጣታቸው የሚታወቅ ሲሆን የነፃ ገበያ ፉክክሩና ትሩፋቶቹ ጐልተው የታዩት ከአዲስ አመት መግቢያ ጀምሮ ነው፡፡ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሄኒከን፤ ዋልያ ቢራ ምርቱን በ10 ብር ሲያቀርብ ነው፤ አይቀሬው የነፃ ገበያ ትሩፋት በራሱ ጊዜ መዛመት የቀጠለው፡፡ ሌሎቹም ግንባታው እያጠናቀቁ ነው - ለዚያውም በየፊናቸው ሪኮርድ የሚሰብሩ ግዙፍ ፋብሪካዎችን፡፡ እዚህም ጋ ኒያላ፣ ዘመን የመሳሰሉ ምርቶችን ከማስተዋወቅ ጋር፣ ደንበኞችን ለመማረክ የዋጋ፣ የአገልግሎት ፉክክር አጧጥፈዋል፡፡ ቢጂአይ  በ11 ብር የሚሸጠውን አንድ ጃንቦ ብርጭቆ ድራፍት “ሃፒ ሃወር” በማለት ማክሰኞ፣ ሐሙስና ቅዳሜ በ8 ብር መሸጥ ጀመረ፡፡ ዲያጆ በፊናው፤ በዘጠኝ ብር ይሸጥ የነበረውን አንድ ጃንቦ ሜታ ድራፍት በ8 ብር እንደሚሸጥ ካስታወቀ በኋላ፤ በቅርቡ “ዘመን” በማለት የሰየመውን የቢራ ምርት በ10 ብር መሸጥ ጀምሯል፡፡ ቢጂአይ በበኩሉ፤ ከሰሞኑ  ሁለት ጠርሙስ ጊዮርጊስ ቢራ ለሚጠጣ ደንበኛ አንድ ጠርሙስ መመረቅ ጀምሯል፡ ደንበኞችን ለመማረክ የሚደረገው የዋና የአገልግሎት ፉክክር በዚህ አይቆምም፡፡ በቅርቡ ወደ ገበያ ለመግባት የተቃረቡ አዳዲስ ቢራ ፋብሪካዎች ከደጃችን እየደረሱ ነው፡፡ ሃበሻ ቢራ በቅርብ ሳምንታት ወደ ገበያ እንደሚገባ የገለፀ ሲሆን፣ ዳሽን ቢራ በደብረ ብርሃን የማስፋፊያ ግንባታውን አጠናቆ በመጋቢት ወር በቀን 3 ሚሊዮን ጠርሙስ ቢራ የሚያመርት ግዙፍ ፋብሪካ ያስመርቃል፡፡ ራያ ቢራም ግንባታውን ጨርሶ ወደ ገበያ ለመግባት እየተንደረደረ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ አዳዲስ ቢራ ፋብሪካዎች ምርቶቻቸውን ወደ ገበያ ሲያስገቡ ፉክክሩ ይበልጥ እንደሚጦፍ መገመት ይቻላል፡፡ የሄኒከን እና የዳሽን ቢራን ዘገባ በገጽ 11 መልከቱ፡፡

Read 3004 times