Saturday, 17 January 2015 10:55

እውን ኢትዮጵያ “ልዩና ድንቅ አገር” ናት?

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(18 votes)

የያኔውን የስልጣኔ ባህል የምናፈቅር፣ የያኔዎቹን የስልጣኔ ጀግኖች የምናከብር ከሆነ፣ ያወረሱንን ነገር የሙጢኝ ይዘን መቀመጥ ሳይሆን፣ በአርአያነታቸው ተነቃቅተን፣ የእውቀትና የፈጠራ ባህላቸውን በመከተል ገና ድሮ ድሮ፣ ከሸክላ ቴክኖሎጂ በተጨማሪ የብረትና የፕላስቲክ ቴክኖሎጂ መፈልሰፍ፣ ከጠላና ጠጅ አልፈን የወይን ጠጅና የቢራ ፋብሪካ መፍጠር በቻልን ነበር። ግን አላደረግነውም። የያኔው የስልጣኔ ባህል ተዘንግቶና ጠፍቶ፣ የስልጣኔ ቅርስና ቅሪት ብቻ ነው የተረፈን - እንስራና እንስሪት። ይሄ፣ ያፈጠጠ ያገጠጠ የውድቀትና የኋላቀርነት አርማ ነው።
አሳዛኙ ነገር፤ ይህንን አርማ በማውለብለብ ከውድቀት የምንድን ይመስላቸዋል። የውድቀታችንን ምንነትና ሰበቦችን አልተገነዘብነውም ያልኩት በዚህ ምክንያት ነው።

  • በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የተመዘገቡ የስልጣኔ ቅኝቶች ከ15 እንደማይበልጡ ብዙ የታሪክ ምሁራን ይገልፃሉ። 7ቱ ጠፍተዋል። ከቀሪዎቹ መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ስልጣኔ ነው፤ በዚህም ኢትዮጵያ ከአለም ልዩ ናት ይላሉ - ሳሙኤል ሃቲንግተን።
  • ነገር ግን፣ አገራችን ግን፤ “ልዩና ድንቅ” የሆነችበትን ምክንያት ብዙዎቻችን በቅጡ አናውቀውም። “ልዩና ድንቅ” የሆነችው፣ በጠላ እና በድፎ ዳቦ እየመሰለን፣ ቢራን እና ኬክን እንደ “ባህል ወረራ” ከቆጠርናቸው፤ የአገሪቱ የጥንት ስልጣኔና ታሪክ ባእድ ሆኖብናል ማለት ይቻላል።  

በጣይቱ ሆቴል ቃጠሎ ሰበብ የተፈጠረውን ንትርክ ስመለከት፣ ለገና በዓል በተዘጋጀው የቴሌቪዥን ፕሮግራም የአቶ ውብሸት ወርቃለማሁና የአቶ ዳንኤል ክብረት ንግግሮችን ስሰማ፣ “አቤት የዚህች አገር ሸክም መብዛቱ!” አሰኘኝ። ሁለቱ ታዋቂ ሰዎች፣ በ“ምዕራባዊያን ባህል” እንደተወረርንና የኢትዮጵያ ባሕል እንደተሸረሸረ በቁጭት እየተንገበገቡ ሲያማርሩ፣ ብዙ ታዳሚዎች በድጋፍ አጨብጭበዋል። በእርግጥ፣ ቁጭቱና ምሬቱ፣ “የገና ዛፍ” ላይ ያነጣጠረ መሆኑ አስገራሚ ነው።
ማለቴ... እጅጉን የሚያስቆጩ ስንትና ስንት ትልልቅ ጉዳዮች በተትረፈረፉባት አገር፣ በ“ገና ዛፍ” መንጨርጨርን ምን አመጣው? በሰው ልጅ ታሪክ ላይ በጣት ከሚቆጠሩ የስልጣኔ ማዕከላት መካከል አንዷ እንዳልነበረች፣ ባለፉት ሺ አመታት አንዳች ተጨማሪ እውቀትን፣ ሙያዊ ጥበብን፣ ብልፅግናንና የስኬት ሰብእናን መፍጠር ተስኗት፤ የጭፍን እምነት፣ የኋላቀር ልማድ፣ የድህነትና የሚስኪንነት መናሃሪያ ለመሆን የተዳረገች አገር ውስጥ ነው የምንኖረው። ከምር በዚህ እንቆጫለን? አይመስለኝም። እንዴት መሰላችሁ?
ከድህነትና ከረሃብ በመውጣት ኑሮን ማሻሻልና መበልፀግ ባለመቻላችን ሳይሆን፤ ረሃብተኛና ተመፅዋች መባላችን ሲቆረቁረን አስቡት። በየዓመቱ በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ወጣቶች ተስፋ ቆርጠው እንዲሰደዱ የሚገፋፋ ከባድን ድህነትና ችግር ውስጥ መሆናችን ሳያሳስበን፤ ሳዑዲና ኩዌት ሄደው በግርድና መስራታቸው “የአገርን ገፅታ ያበላሻል” እያልን እንንጨረጨራለን። አይገርምም? የድሮውን የሚያሻሽል ነገር መስራትና መፍጠር አለመቻላችን ሳያስቆጨን፣ ሌሎች ሰዎች የፈጠሩትን ተውሰን በመጠቀማችን እርር ትክን እንላለን። በሌላ አነጋገር፣ ቅደመ አያቶች የፈጠሩትን አኗኗር ይዘን፣ ያንኑ እየደጋገምን፣ እዚያው በነበሩት ቦታ ቆመን መቅረት ነው የምንፈልገው። እና ይህንን ደግሞ፣ “ባህልን ማወቅ” “ባህልን ማክበር” ወይም “ባህልን መጠበቅ” ብለን እንጠራዋለን። በተቃራኒው፣ “ባህልን አለማወቅ”፣ “ባህልን ማርከስ” እና “ባህልን ማጥፋት” ብንለው ይሻላል።
እንደ ጥንቶቹ የስልጣኔ አያቶች፣ በእውቀት የመራቀቅ፣ በሙያዊ ጥበብ አዳዲስ የተሻለ ነገር የመፈልሰፍና የመስራት ባህል ቢኖረን ኖሮ፣ ወይም ደግሞ ቢያንስ ቢያንስ እንዲያ አይነት ባህል እንዲኖረን የምንፈልግ፣ የምንሞክርና የምንጥር ቢሆን ኖሮ... ያኔ “ባህልን ማወቅ፣ ማክበርና መጠበቅ” ስንል ትክክለኛ ትርጉም ይኖረው ነበር። ግን፣ ከመነሻው የባህልን ምንነት ስላላወቅነው፤ ሸማ፣ የሳር ጎጆ፣ የበሬ እርሻ፣ እንስራ የመሳሰሉ... ከሺ ዘመናት በፊት በታላቅ የፈጠራ ባህል አማካኝነት የተፈለሰፉና ከትውልድ ትውልድ በልማድ የወረስናቸውን ነገሮች እንደታቀፍን ቆመን ስንቀርና ደንዝዘን ስንቀመጥ፣ የባህል ባለቤት የሆንን ይመስለናል። እነዚያ የፈጠራ ሰዎች፣ እንዲህ ሆነን ቢያዩን በጣም ነበር የሚያዝኑብን። ለምን በሉ።     
ከሺ ዓመታት በፊት የነበሩ የቀድሞ አያቶችኮ፣ ከትውልድ የወረሱትን ቅርስ ታቅፈው እዚያው እየረገጡ መቀመጥን የሚፀየፉ ስለነበሩ፣ የስልጣኔ ባህልን የሚያሰፍን የፈጠራና የስኬት ሰብዕናን የገነቡ አዋቂዎች፣ ጥበበኞችና ጀግኖች ስለነበሩ ነው፣ ድፎ ዳቦንና እንጀራን፣ ጠላንና ጠጅን፣ ማረሻንና ገንቦን፣ ሸማንና ስልቻን፣ ጎተራንና ጎጆን፣ ቤተመንግስትን እና የቀን መቁጠሪያን፣ ቋንቋንና ሰዋስውን፣ ፊደልንና ፅሁፍን፣ የአድናቆት ሃውልትንና ግጥምን፣ የሙዚቃ መሳሪያንና ዘፈንን... በአጠቃላይ የእውቀት አድማስን ለማስፋት፣ ኑሮን ለማበልፀግና የሕይወትን ጣፋጭነት ለማጣጣም የሚጠቅም ነገር ሲፈጥሩና ሲያሻሽሉ የኖሩት።
እኛ ግን፣ ከአላዋቂነታችን የተነሳ፣ የቅድመ አያቶች የፈጠራ ውጤቶችን ስናይ፣ ለምሳሌ የፊደልና የፅሁፍ ስልጣኔ ቀላል ሊመስለን ይችላል። የንግግር ድምፆችን የሚወክሉ ምልክቶችን መፍጠር በጣም ከፍተኛ እውቀትንና ጥረትን ስለሚጠይቅ፣ ብዙ ቋንቋዎች ፅሁፍ የላቸውም። እንደ እብራይስጥ በመሰሉ ፅሁፍ ያላቸው ቋንቋዎች እንኳ፣ “አናባቢዎችን” የሚወክል ምልክት መፍጠር አቀበት እንደሆነባቸው ምዕተ ዓመታት ተቆጥረዋል። ይሄ የመጨረሻው ቃል ያለ “አናባቢ” ሲፃፍ “ተቀጠረወለ” የሚል ይሆናል። “ቁጠር” እና “ቆጠሩ” የሚሉ ቃላት ያለ አናባቢ ብንፅፋቸው “ቀጠረ” በሚል በግርድፍ ስለሚቀሩ አንዱን ከሌላው መለየት አንችልም። የተሟላ የፊደልና የፅሁፍ ስርዓት መፍጠርን ትተን፣ የቁምነገሩን ክብደት የምትጠቁም ቀለል ያለች አንዲት ነጠላ ምሳሌ ልጥቀስላችሁ። ዛሬ በዘመናችን በርካታ የዚሁ ቋንቋ ምሁራን፣ “ቷ” የሚለው ፊደል፣ “ትዋ” ወይንም “ቱዋ” ከሚሉ ድምፆች የትኛውን እንደሚወክል ሲምታታባቸው ይታያል። ትክክለኛው “ትዋ” ነው።
ምን ለማለት ፈልጌ ነው? ከማረሻና ከድፎ ዳቦ እስከ ፅሁፍና የመንግስት ስርዓት ድረስ፣ አንዳችም እንደ ዝናብ ከሰማይ የወረደ እውቀትና ጥበብ የለም። የስልጣኔ ባህልን የገነቡ አዋቂ የፈጠራ ሰዎች በየዘመናቸው በፈርቀዳጅነት ስለፈጠሩትና ስላሻሻሉት ነው እውን ሆኖ የምናየው። በአጭሩ፣ ፈር ቀዳጅ የፈጠራ ሰዎች ነበሩ። ምኒልክም በአቅማቸው፣ የመጀመሪያውን ዘመናዊ የሳይንስ ትምህርት ቤት፣ ጣይቱ የመጀመሪያውን ሆቴል የከፈቱትም በፈር ቀዳጅነት ነው። እኛ ግን፣ እንደነሱ አይነት የፈጠራና የስኬት ሰብዕና የተበራከተበት የስልጣኔ ባህል አልገነባንም፤ የግንባታ ጅምርም ሆነ ውጥን የለንም። ጨርሶ በሃሳባችን ውስጥ አይገባም። የቱን ያህል ብርቅና ድንቅ የስልጣኔ ባህል እንደቀረብን በቅጡ ባለመገንዘባችን አልያም የመገንዘብ ፍላጎት ስለሌለን፤ “ትልቅ ነገር አጣን” ብለን አንቆጭም። እናም፣ የቅድመ አያቶች የፈጠራ ውጤቶችን ወይም የስልጣኔ ቅርሶችን ታቅፈን፣ የፈጠራ ባህላቸውንና የስልጣኔ ሰብዕናቸውን በትንሹ ለማወቅ፣ ለማክበርና ለማሳደግ አንዳች ጥረትና ሙከራ ልናደርግ ይቅርና ቅንጣት ፍላጎት ወይም ምኞት እንኳ አይታይብንም። ይባስ ብለን፣ ከስልጣኔ ባህል የተገኙ ቅርሶችን፣ ወደፊት የስልጣኔ ባህል እንዳይፈጠር ለማጨናገፍና ብቅ ካለም በእንጭጩ ለመቅጨት እንጠቀምባቸዋለን። የስልጣኔን ራዕይ ለማውለብለብ፣ የፈጠራ ባህልን ለማነቃቃት፣ የስኬት ፋናን ለመለኮስ አለኝታ ሊሆኑን የሚችሉ የስልጣኔ ዘመን ማስታወሻ ቅርሶችን፣ በተቃራኒው የስልጣኔ ተስፋን ለማጨለም፣ የፈጠራ ጭላንጭልን ለማዳፈንና የስኬት ሰብዕናን ለማኮላሸት የሚያገለግሉ የጥፋት አርማና መሳሪያ እንዲሆኑ አድርገናቸዋል። የስልጣኔ ባህል ምንነትን አለማወቅ፣ ማርከስና ማጥፋት ማለት ይሄ ነው - ከዚህ የባሰ ክፉ ኋላቀርነት ምናለ? የሳር ጎጆ፣ የውሃ እንስራ ወይም ሌላ ቅርስ እንደ “ባህል” ማሳያ ተደርጎ ሲቀርብ፤ ምን አይነት ሃሳቦች እንደሚሰነዘሩ መታዘብ ትችላላችሁ። ከሺ አመታት በፊት እነዚህን ነገሮች የፈለሰፉ ሰዎች ታላቅ የፈጠራ ባህል እንደነበራቸው በማስታወስና በአርአያነታቸው በመነቃቃት፣ እኛም እንደነሱ ከድንዛዜ የሚያላቅቅ የፈጠራ ባህል በመገንባት ሕይወትን ይበልጥ የሚያሻሽሉ ነገሮችን እንፍጠር የሚል መልእክት ያዘለ አስተያየት ሰምታችሁ ታውቃላችሁ? በተቃራኒው አዲስ የተሻለ ነገር ሳንፈጥር፣ ከሳር ጎጆ እና ከውሃ እንስራ ጋር ተጣብቀን የመቀጠል ቅዱስነት ዘወትር ይሰበካል። በጣይቱ ሆቴል ቃጠሎ ሰበብ ከተለኮሰው ሰሞነኛ ንትርክ የምታገኙት መልእክትም ተመሳሳይ ነው። የጣይቱ ሆቴል ላይ የደረሰው ቃጠሎ እንዲያ አነጋጋሪ የሆነው ለምን እንደሆነ ራሳችሁን ጠይቁ። የህንፃው የሆቴል አገልግሎት ልዩና ድንቅ ስለሆነ አይደለም። ቅርስ ስለሆነ ነው። ነገር ግን በቅርስነት ዋጋ የሚኖረው፣ በፈርቀዳጅነት የተሰራ በመሆኑ፤ የፈርቀዳጅነት ባህልን የምናከብር ከሆነ ብቻ ነው። እንግዲህ ፍረዱ። በቃጠሎው ዙሪያ ሲጧጧፍ በሰነበተው ንትርክ፤ የፈርቀዳጅነት ሰብእናንና ባህልን ስለማክበር ሲነሳ ሰምታችኋል? ዛሬ በዘመናችንም በሆቴል አገልግሎትም ሆነ በሌላ መስክ እጅግ የተሻሉ አዳዲስ ሆቴሎች ወይም ሕንፃዎች ወይም ሌሎች ስራዎች እንዲገነቡ የሚያነሳሳ ቅርስ ነው ሲባል አጋጥሟችኋል? አይመስለኝም።    
እንግዲህ የየአገራችንና የዘመናችን ነገር እንዲህ ነው። እዚህ አገር፣ ጥንታዊ የስልጣኔ ታሪክ ተፈጥሮ እንደነበር እናውቃለን - ትክክለኛ ምንነቱንና ዋነኛ መንስኤዎቹን ግን በደንብ አናውቃቸውም። የስልጣኔው ታሪክ ተዳክሞና ተሸርሽሮ፣ በቦታው ውድቀትና ኋላቀርነት እንደተተካ በተወሰነ ደረጃ ይገባናል - የውደቀቱን ሰበቦችንና የኋላቀርነቱን ምንነት በውል አልተገነዘብናቸውም። አቶ ውብሸትን እና አቶ ዳንኤልን በምስክርነት ላቅርብላችሁ፡፡
የአመት በዓል ዝግጅቱን ስፖንሰር ያደረገው የጊዮርጊስ ቢራ ድርጅትን በማመስገን የጀመሩት አቶ ውብሸት፣ የድርጅቱ ትብብር በርካታ አስርት አመታትን ያስቆጠረ ነው በማለት አድናቆታቸውን ገልፀዋል። የፌሽታ ስሜታቸው የተቀየረው፣ ስለ ኢትዮጵያ ባህል ሲናገሩ ነው። አገሪቱ በኢኮኖሚ እያደገች ቢሆንም በባሕል ግን እየከሰረችና ወደ ታች እየወረደች መሆኗን አቶ ውብሸት ገልፀው፣ የገና በዓል አከባበርን በምሳሌነት ጠቅሰዋል። የአገራችን ባህል፣ በገና ጨዋታና በጭፈራ፣ ጠላና ድፎ ዳቦ አዘጋጅቶ አብሮ በመብላትና በመጠጣት በዓሉን ማክበር ነው ያሉት አቶ ውብሸት፣ የገና ዛፍ ባዕድ ነው፤ የውጭ ባህል ወረራ ነው በማለት በቁጭት ካወገዙ በኋላ፣ ፈረንጆች በሚያዘወትሩት ትልቅ ሆቴል ካልሆነ በቀር የገና ዛፍ አያስፈልግም ብለዋል። በአገራችን ባህል፣ ለገና በዓል አቅም ያለው ጋን ሙሉ ጠላ ይጠምቃል፤ ሌላው እንደ አቅሙ በእንስራ ይጠምቃል፤ አቅም ያነሰው ደግሞ እንስሪት በምትባል ይጠምቃል በማለትም አብራርተዋል - አቶ ውብሸት። ግን፣ ቢራ ማምረትንና ቢራ መጠጣትን እንደ ባህል ወረራ በስም ጠቅሰው አላወገዙም።
በአቶ ውብሸት አስተሳሰብ ከሄድን፣ ጠላ፣ ድፎ ዳቦ፣ ጋን፣ እንስራና እንስሪት የመሳሰሉ ናቸው የአገራችን ትልልቅ ነገሮች። እነዚህ ከጥንት የወረስናቸውን እቃዎችና ልምዶች ይዘን መቀጠል ነው ትልቁ ቁም ነገር። ምንኛ ተሳስተዋል! የአገራችንን ጥንታዊ ስልጣኔና ባህል ፈፅሞ አናውቀውም ማለት ነው። የያኔዎቹ የስልጣኔ ሰዎች፣ ከአያት ከቅድመ አያት የወረሱትን ነገር ብቻ ይዘው የሚቀጥሉ ሰዎች አልነበሩም። የፈጠራ ሰዎች ነበር።
የመመርመር፣ የመማር፣ የማወቅ ፍላጎት የነበራቸው የአገራችን የስልጣኔ ሰዎች፣ የፈጠራ፣ የሥራና የመሻሻል (የመበልፀግ) ፍቅራቸውም የዚያኑ ያህል ተአምረኛ ነበር። ከዛፍ እየሸመጠጡ የመብላትና ዋሻ ውስጥ የማደር ልምድን ከአባቶቻቸው ስለወረሱ ያንኑን የሙጢኝ ብለው ሕይወታቸውን ከመግፋት ይልቅ፤ አእምሯቸውን ተጠቅመው እውቀትንና ሙያን አዳብረው፣ በበሬ የማረስ ዘዴንና የጎጆ ቤት አሰራርን ፈጥረዋል። ጋንና እንስራን የማበጀት፣ ጠላና ዳቦ የማዘጋጀት ጥበብን ፈልስፈዋል።
የያኔውን የስልጣኔ ባህል የምናፈቅር፣ የያኔዎቹን የስልጣኔ ጀግኖች የምናከብር ከሆነ፣ ያወረሱንን ነገር የሙጢኝ ይዘን መቀመጥ ሳይሆን፣ በአርአያነታቸው ተነቃቅተን፣ የእውቀትና የፈጠራ ባህላቸውን በመከተል ገና ድሮ ድሮ፣ ከሸክላ ቴክኖሎጂ በተጨማሪ የብረትና የፕላስቲክ ቴክኖሎጂ መፈልሰፍ፣ ከጠላና ጠጅ አልፈን የወይን ጠጅና የቢራ ፋብሪካ መፍጠር በቻልን ነበር። ግን አላደረግነውም። የያኔው የስልጣኔ ባህል ተዘንግቶና ጠፍቶ፣ የስልጣኔ ቅርስና ቅሪት ብቻ ነው የተረፈን - እንስራና እንስሪት። ይሄ፣ ያፈጠጠ ያገጠጠ የውድቀትና የኋላቀርነት አርማ ነው። አሳዛኙ ነገር፤ ይህንን አርማ በማውለብለብ ከውድቀት የምንድን ይመስላቸዋል። የውድቀታችንን ምንነትና ሰበቦችን አልተገነዘብነውም ያልኩት በዚህ ምክንያት ነው። በእርግጥ ይሄ ጉድለትና ስህተት፣ የአቶ ውብሸት ብቻ አይደለም። የብዙዎቻችን ነው። በዚያ ላይ የፍልስፍና ወይም የታሪክ ምሁር ባለመሆናቸው፤ ነገሩን ቢስቱት ብዙም አይገርምም።         
የአቶ ዳንኤል ስህተትም ተመሳሳይ ነው። የገና ዛፍና ከረሜላ የመሳሰሉ ነገሮች ባዕድ መሆናቸውን በመጥቀስ፣ ከበዓሉ በፊት ለአንድ ወር ያህል የሚዘልቅ የገና ጨዋታ ውድድር እንዲዘጋጅ ሃሳብ ያቀረቡት አቶ ዳንኤል፤ የበዓሉ እለት የፍፃሜ (የሻምፒዮና) ውድድር የሚካሄድበት ቀን መሆን እንደሚገባው ተናግረዋል። እስቲ አስቡት የገና ጨዋታ ለወር ያህል ሲካሄድ! ማለቴ፣ የጨዋታ ውድድር በተፈጥሮው አዝናኝ መሆን የለበትም እንዴ? ለጨዋታ ያህል፤ ከእንጨት የተሰራችውን ትንሽ ኳስ፣ ከቆልማማ እንጨት በተሰራ ከዘራ የመሰለ እንጨት እየለጉ መሯሯጥ፣ በአመት አንዴ ምንም አይደለም። ከጨዋታ አልፎ የጨዋታ ውድድር ለመሆን ግን፣ ጨዋታው ከ“መሯሯጥ” ያለፈ አዝናኝ ባህርያት ሊኖሩት ይገባል። ከነዚህ ባህርያት መካከል አንዱ፣ የተጫዋችን ብቃት በቀጥታ ለማየትና ለማድነቅ ያስችላል ወይ የሚል ጥያቄ ያመጣል። የገና ጨዋታ ከመለጋትና ከመሯሯጥ ያለፈ ብቃት ለማየት አያመችም። ሁለተኛው የማራኪ ውድድር ባህርይ፣ ለተመልካች ያለው አመቺነት ነው። የገና ጨዋታ ለተመልካች አያመችም - ተጫዋቾችን እየተከተለና እየሮጠ መመልከት አለበት ካልተባለ በቀር። ሦስተኛ የማራኪ ውድድር ባህርይ፣ የሚያረካ ግብ ወይም ልብ የሚሰቅል የግብ ሙከራ ነው። የገና ጨዋታ ግን፣ እየለጉ ከመንጎድ ውጭ በውል የሚታወቅ ሌላ ግብ የለውም። በአጠቃላይ፣ በተለምዶ የሚታወቀው የገና ጨዋታ፣ (በአንዳች የፈጠራ ሃሳብ ካልተሻሻለ በቀር... ማለትም በስልጡን የፈጠራ ባህል አንዳች ለውጥ ካልተደረገበት በቀር) የመዝናኛ ውድድሮችን መመዘኛ አያሟላም። ተወዳጅነትንና ተዘውታሪነትን ያላተረፈው ለምን ሆነና?
አገር አቀፍ የገና ሻምፒዮንሺፕ ያስፈልጋል የሚሉት አቶ ዳንኤል ግን፣ ከዚህም በተጨማሪ፣ በየቤታችን በገና ዛፍ ፋንታ ከዘራ የመሰለችውን እንጨት ተክተን በመብራቶች እናስውባት ብለዋል። ከዘራ የመሰለችውን እንጨት እንዴት እንደምናቆማት እንጃ። የገና ዛፍ፣ ቢያንስ ቢያንስ የልምላሜ ምኞትንና ተስፋን ያመላክታል። በቀለማት ሲደምቅና በመብራቶች ሲንቆጠቆጥ ደግሞ፣ የብሩህነትን መንፈስ ይፈጥራል። ከዘራ የመሰለ እንጨት ግን... ደግሞምኮ፣ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ መብራቶች “የኢትዮጵያ ባህል” አይደሉም። ምን ለማለት ፈልጌ ነው፤ በነበርንበት ቦታ ላይ እየረገጥን ወይም ባለንበት ቦታ ላይ እንደተቀመጥን እንኑር የሚል ሃሳብ፣ የስልጣኔና የፈጠራ ባህልን ሳይሆን የውድቀትና የድንዛዜ ባህልን የሚያበረታታ ሃሳብ ነው። መፍጠርና መሰልጠን ያልቻለ ደግሞ፤ ያው ከኩረጃ ውጭ አማራጭ የለውም። በሌላ አነጋገር፣ የውድቀት መንስኤና ሰበብ የሆኑ ነገሮች ናቸው እንደ መፍትሄና ፈውስ እየተቆጠሩ ያሉት።
እንግዲህ፣ የአገራችን ነገር እንዲህ ከሆነ፣ “ልዩና ድንቅ አገር” የሚያስብላት ነገር ምንድነው? አገሪቱ የድንዛዜ ወይም ቆሞ የመቅረት አስተሳሰቦች እንደነገሱባት የሚመለከት ሰው፣ “ልዩና ድንቅ አገር” መሆኗን ቢጠራጠር አይገርምም። ምናልባት፣ በየአለም ዙሪያ በየአገሩ የሚኖሩ ሰዎች፣ በየፊናቸው የየራሳቸው አገር ብርቅና ድንቅ ሆኖ ስለሚታያቸው ይሆን፣ ኢትዮጵያ ልዩና ድንቅ ናት የምንለው? “ሁሉም የየራሱን ሲያደንቅ እሰማለሁ” ተብሎ እንደተዘፈነው ማለቴ ነው። ግን አይደለም። ለምሳሌ የአውሮፓን የስልጣኔ ባህል የማይወዱ፣ የሚያንቋሽሹና ለማፈራረስ ሌት ተቀን የሚምሱ የአውሮፓና የአሜሪካ ምሁራን ቁጥራቸው ቀላል አይደለም።
እንዲያውም በ20ኛውና በ21ኛው ክፍለ ዘመን የምዕራባዊያንን ስልጣኔ ማንቋሽሽ የአብዛኛው ምሁርና የብዙ አለማቀፍ የሚዲያ ተቋማት ዋና ምልክት እስከ መሆን ደርሷል ማለት ይቻላል። ከእንግሊዝ ዘ ጋርዲያን ጋዜጣና ቢቢሲን፣ ከአሜሪካ ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ፣ ሃፊንግተን ፖስት ድረገፅ፣ እና ሲኤንኤን ቴሌቪዥን... በየአጋጣሚው የአፍሪካን ባህልና አኗኗርን ሲያሞካሹ ተመልከቱ - የአውሮፓንና የአሜሪካን እያጣጣሉ። በቃ፤ እንደ ወግ ይዘውታል። የምሁርነት፣ የፍትሃዊነትና የቅድስና ምልክት ይመስላቸዋል።
አይግረማችሁ። በአዲስ አበባ የሚኖር ደራሲ፣ ዘፋኝ፣ ሙዚቀኛ፣ ወይም ጋዜጠኛ፣ ወደ ቆላማ አካባቢ የሃመር ተወላጆች  ወደሚኖሩበት አካባቢ ሄዶ፣ አኗኗራቸውን ሲያደንቅና ከተሜነትን ሲያንቋሽሽ እንደምንሰማው ማለት ነው። የወገኛ ነገር! እዚያ እጅጉን በአድናቆት ያሞገሰው አካባቢ ውስጥ መኖር አይፈልግም፤ ወደሚያንቋሽሸው የከተማ ኑሮ ለመመለስ ይሮጣል። ለሰው ልጅ ትልቅ አክብሮትና ፍቅር ያለው ሰው፤ የቆላማው አካባቢ የድህነት ኑሮና ኋላቀር አኗኗር እንዲሻሻል ይመኛል እንጂ፤ የተመቻቸውና የደላቸው ይመስል አኗኗራቸውን እያደነቀ፣ “ሳይበረዝና ሳይከለስ” እንዲቀጥል ይፈልጋል? ማለቴ፣ ልብስ አለመልበስ እንዴት እንደ ስልጣኔና እንደ ባህል ይቆጠራል? ባህል ማለትኮ በሰፊው ስር ለመስደድ የበቃ የፈጠራ ውጤትና ስኬት ማለት ነው - ለምሳሌ ልብስ መስራትና መልበስ።
ለማንኛውም፣ ከኛው ወገኞች ባልተናነሰ መልክ፣ የአፍሪካን ወይም የኢትዮጵያን ባህልና ታሪክ እየቆጠሩ ድንቅ ሃተታ የሚያቀርቡ ወገኛ የውጭ ምሁራን ጥቂት አይደሉም። ነገር ግን፣ ከወገኞቹ ተርታ የማይመደቡ ምሁራን መኖራቸውም አይካድም። ታዋቂው የታሪክና የፖለቲካ ምሁር፣ ሳሙኤል ሃቲንግተን የኢትዮጵያ ስልጣኔ ከዓለም ሁሉ የተለየ እንደሆነ የሚናገሩ ቢሆኑም፣ ከወገኞቹ ተርታ አይደሉም። ለማስመሰልና ለወጉ ያህል፣ ወይም ዘረኛ ላለመባል በማሰብ የአፍሪካ ባህልን ለማድነቅ አይሯሯጡም። እንዲያውም፣ “አፍሪካዊ” ሊባል የሚችል ስልጣኔ ወይም የባህል ቅኝት የለም ይላሉ - ሃቲንግተን። እና ለምን ይሆን፣ ኢትዮጵያ ከሌሎቹ ሁሉ ትለያለች በማለት የፃፉት?
Clashes of Civilizations በተሰኘው መፅሃፋቸው ሰፊ የታሪክና የፖለቲካ ትንታኔ ያቀረቡት ሃቲንግተን፣ በአጠቃላይ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ፣ ከጥንት እስከ ዛሬ በታሪክ ተመዝግበዋል ተብለው ብዙ የታሪክ ምሁራን የሚስማሙባቸው የስልጣኔ ቅኝቶች ከ15 እንደማይበልጡ ይገልፃሉ። ከእነዚህ ውስጥ፣ ጥንታዊውን የግብፅ ስልጣኔ ጨምሮ፣ 7ቱ ስልጣኔዎች ዛሬ የሉም። ጠፍተዋል፣ እንደ ግብፅ ፒራሚዶች ቅርስ ብቻ ነው የቀራቸው። እንዴት መሰላችሁ? ዛሬ የአብዛኞቹ ግብፃዊያን አስተሳሰብና እምነት፣ አኗኗርና ቋንቋ ከጥንታዊው የግብፅ ስልጣኔ ጋር ብዙም ግንኙነት የለውም። የጥንታዊ ግብፅ ቋንቋ፣ ከዛሬዎቹ ግብፃዊያን ቋንቋ ይልቅ ለኢትዮጵያዊያን ቋንቋ የቀረበ ነው በሚል አነስተኛ መዝገበ ቃላት የታተመውም በዚሁ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም። እንደ ተረት የሚቆጠረው የሜሶፖታሚያ - የባቢሎን ስልጣኔም እንዲሁ፣ ከዛሬዎቹ የኢራቅ ነዋሪዎች ጋር ይህ ነው የሚባል ግንኙነት የለውም፤ የያኔው ስልጣኔ ሞቷል። የሞተው ሞቶ፣ ዛሬ ያሉት መሰረታዊ የባህል ቅኝቶች 7 ወይም 8 እንደሆኑ የሚናገሩት ሃቲንግተን፤ በስም ይዘረዝሯቸዋል - የቻይና ዙሪያ የባህል ቅኝት (እነ ኮሪያንና ቬትናምን ያካተተ)፣ የጃፓን የባህል ቅኝት፣ የራሺያ ዙሪያ የባህል ቅኝት፣ የአውሮፓና የአሜሪካ የባህል ቅኝት፣ የመካከለኛው ምስራቅና የመሰሎቹ የባህል ቅኝት፣ የህንድ ዙሪያ የባህል ቅኝት፣ እንዲሁም የላቲን አሜሪካ የባህል ቅኝት።
እነዚህ ሰባት መሰረታዊ የባህል ቅኝቶችን የዘረዘሩት ሃቲንግተን፣ አብዛኞቹ ምሁራን “አፍሪካዊ” ሊባል የሚችል የባህል ቅኝት እንደሌለ ይስማማሉ በማለት ያክላሉ። ሰሜን አፍሪካ፣ በመካከለኛው ምስራቅ ቅኝት የሚካተት ነው። ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገራት፣ እርስ በርስ የሚያስተሳስር የባህል ቅኝት የላቸውም - የጎሳ ስሜት የተንሰራፋባቸው ናቸውና። ምናልባት ወደፊት፣ በደቡብ አፍሪካ አስኳልነት፣ “የአፍሪካ” ሊባል የሚችል የባህል ቅኝት ሊፈጠር እንደሚችል ሃቲንግተን ይገልፃሉ - Throughout Africa tribal identities are pervasive and intense, but ... conceivably sub-Saharan Africa could cohere into a distinct civilization, with South Africa possibly being its core state (ገፅ 47)።
ወደፊት ሊፈጠር ይችላል የተባለለት የአፍሪካ ቅኝትን ጨምሮ፣ በጥቅሉ የዛሬዋን አለማችን በ8 የባህል ቅኝቶች ይከፋፍሏታል - ሃቲንግተን። ኢትዮጵያ ግን ወደፊት በሚፈጠረው የአፍሪካ አገራት ቅኝት የምትመደብ አይደለችም። ከሌሎቹ የባህል ቅኝቶችም ውስጥም እንደማትካተት የሚናገሩት ሃቲንግተን፣ “ከታሪክ አንፃር፣ ኢትዮጵያ ራሷን ችላ የምትጠቀስ የባህል ቅኝት ናት” ብለዋል (Historically, Ethiopia constituted a civilization of its own)።  
ከሞላ ጎደል፣ ሁሉም አገራት በእነዚህ 8 የባህል ቅኝቶች ውስጥ የሚካተቱ ናቸው - ከሁለት አገራት በስተቀር። ብቸኛ አገራት “Lone Countries” ተብለው በሃቲንግተን ከተፈረጁ አገራት መካከል አንዷ፣ ሃይቲ ናት - ከየትኛውም ቅኝት ያልሆነችና የራሷ ቅጥ የያዘ የባህል ቅኝት የሌላት አገር። ሃቲንግተን በመፅሃፋቸው ገፅ 136 ላይ እንደገለፁት፣ ሁለተኛዋ ብቸኛ አገር፣ ኢትዮጵያ ናት - ራሷን ችላ እንደ ልዩ የባህል ቅኝት የምትቆጠር። ጃፓን እንደ ሦስተኛዋ ብቸኛ አገር እንደምትመደብ በመጥቀስም፣ ራሷን የቻለች የአለማችን አንድ የባህል ቅኝት አድርገዋታል።
ሃቲንግተን ኢትዮጵያ ልዩ አገር መሆኗን የጠቀሱት፣ በባህል ቅኝት አመዳደብ ብቻ አይደለም። በባህል ቅኝቶች መካከል በሚኖር ግንኙነትም፣ ኢትዮጵያ በጣት ከሚቆጠሩ ልዩ አገራት መካከል አንዷ ናት። የዛሬዎቹ የባህል ቅኝቶችም ሆኑ በሰው ልጅ ረዥም የበርካታ ሺሕ ዓመታት ታሪክ ውስጥ የተመዘገቡ 15 ያህል የባህል ቅኝቶች፣ በብዙ መልኩ የሚለያዩ ቢሆኑም ሙሉ ለሙሉ የተነጣጠሉ ናቸው ማለት አይደለም።
የባህል ቅኝቶች፣ በየዘመናቸው እርስበርስ አዎንታዊና አሉታዊ ግንኙነቶችን እንደሚያካሂዱ ሃቲንግተን ገልፀው፤ የንግድ ግንኙነትንና  የድንበር ወረራን በምሳሌነት ጠቅሰዋል። የግሪኩ እስክንድር፣ እስከ ህንድና ግብፅ፣ እስከ አፍጋኒስታንና ራሺያ ድንበር ድረስ ወረራ የማካሄዱን ያህል፣ የሞንጎል ንጉስም በአለም ታሪክ ወደር የሌለው ሰፊ ወረራ በማካሄድ ሰፊ ግዛት ተቆጣጥሯል። የቱርክ፣ የግብፅ እና የአረብ ገዢዎችም በየአቅጣጫው ዘምተው ገዝተዋል። የመጨረሻው የግዛት ወረራ የተካሄደው በአውሮፓ ገዢዎች እንደሆነ ይታወቃል - አፍሪካ በቅኝ ግዛት ስር የወደቀችበት ወረራ። በአጠቃላይ ሲታይ፣ ሃቲንግተን እንደሚሉት፣ በአንድ ወይም በሌላ ወቅት፣ በወረራ ወይም በሌላ ምክንያት፣ ቅኝ ያልተገዛ አገር ወይም ያልተንበረከከ የባህል ቅኝት የለም ማለት ይቻላል - ከሶስት አገራት ወይም ከሶስት የባህል ቅኝቶች በስተቀር። ጃፓን፣ ራሺያ እና ኢትዮጵያ ናቸው ሶስቱ አገራትና ሶስቱ የባህል ቅኝቶች። Only Russian, Japanese, and Ethiopian civilizations, all three governed by highly centralized imperial authorities, were able to resist... and maintain meaningful independent existence - ገፅ 51።
እሺ፣ ኢትዮጵያ ብርቅና ድንቅ አገር ናት። ግን፣ ብርቅና ድንቅ አገር ናት የምትሰኝበትን ባህሪዋንና ምንነቷን ከነመንስኤው ማወቅ ያስፈልጋል።      

Read 4515 times