Saturday, 17 January 2015 11:19

በ4ኛው የሰላም ፌስቲቫል ዛሬና ነገ የሙዚቃ ድግስ ይካሄዳል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

ሰሞኑን በኢትዮጵያ የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣንና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባህል ማዕከል በተለያዩ የኪነ-ጥበብ ዝግጅቶች የተጀመረው 4ኛው ሰላም ፌስቲቫል፤ ዛሬና ነገ በትሮፒካል ጋርደን በሙዚቃ ድግሶች ደምቆ ይቀጥላል፡፡ ለአንድ ሳምንት የዘለቀው ፌስቲቫሉ፤ ጥናታዊ ፊልሞች፣ ዎርክሾፖችና ሴሚናሮችን ጨምሮ የዲጄ ፓርቲ፣ የሰርከስ ትርኢትና ባህላዊ ውዝዋዜዎችም የሚያካትት ሲሆን እስከ 10ሺ ተመልካቾች እንደሚታደሙት ይጠበቃል፡፡
 ባለፈው ረቡዕ “አፍሪፒዲያ” የተሰኘ የአፍሪካን መልካም ገፅታዎች የሚያሳይ ጥናታዊ ፊልም የቀረበ ሲሆን የኢትዮጵያን ባህላዊ ውዝዋዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ባነገሰው አርቲስት መላኩ በላይ ላይ የህይወት ታሪክ የሚያጠነጥን ጥናታዊ ፊልምም ለተመልካች ቀርቧል፡፡ ከትናንት በስቲያ “ጃሚንግ አዲስ” የተሰኘ ጥናታዊ ፊልም ለዕይታ ቀረበ ይህ ጥናታዊ ውስጥ ፒያኒስት ሳሙኤል ይርጋ፣ የአዲስ አኩስቲክስ የሙዚቃ ቡድን አባላት ግሩም መዝሙርና ሌሎች ሙዚቀኞች እንዲሁም የበገናው ንጉስ ዓለሙ አጋ እና የድራመር ተጫዋቹ ፕሮፌሰር አብይ ፎርድ ላይ ያተኮረ እንደሆነ ታውቋል፡፡
ሰላም ፌስቲቫል ከሙዚቃ ድግሶች ጎን ለጎን የተለያዩ ጥበብ ላይ ያተኮሩ ፕሮጀክቶችን የሚያከናውን ሲሆን ከእነዚም መካከል አይነስውራን በሙዚቃ ትምህርት እንዲጎለብቱ የሚያበረታታው ‹‹ኢነር ቪዥን›› የተሰኘ ፕሮጀክት ተጠቃሽ ነው፡፡ ‹‹ኢነር ቪዥን›› የዘንድሮው የሰላም ፌስቲቫል አበይት ትኩረት መሆኑን የተናገረው የሰላም ፌስቲቫል መስራችና ዳይሬክተር ተሾመ ወንድሙ፤ በኢትዮጵያ የሚገኙ መስማት የተሳናቸው ወጣቶች ድጋፍ እየተደረገላቸውና ትምህርት እየተሰጣቸው በሙዚቃ ሙያ የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ የሚሰራ ፕሮጀክት ነው ብሏል፡፡ በፕሮጀክቱ በኩል በተደረገ እንቅስቃሴም ለብዙ ዓመት ተዘግቶ የቆየውን ማየት የተሳናቸው የሙዚቃ ትምህርት ቤት ተከፍቶ በአዲስ መልክ ማስቀጠል መቻሉን የገለፀው ዳይሬክተሩ፤ በአሁኑ ሰዓት 14 ማየት የተሳናቸው ወጣቶች በሙዚቃ የዲፕሎማ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙ ተናግሯል፡፡ በ“ኢነር ቪዥን” ፕሮጀክት የተገኘው ሌላ ትልቅ ውጤት ማየት የተሳናቸው በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ተቀባይነት አግኝተው እንዲማሩ ከስምምነት ላይ መደረሱ ነው ብሏል፤ ተሾመ፡፡ሰላም ፌስቲቫል በተለያዩ ኪነጥበባዊ ሴሚናሮች፣ ዎርክሾፖችና ጥናታዊ ፊልሞች ላይ አተኩሮ እየሰራ መሆኑን ሲያስረዳም፤ በተለይ የኢትዮጵያ ባህል በዘመናዊ መልኩ እንዲደራጅ፤ በማይናጋ መሰረት ላይ ቆሞ እድገት እንዲያሳይ እንዲሁም በተማረ የሰው ሃይል እንዲገነባ በትጋት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ተናግሯል፡፡
የሳውንድ ኢንጂነሪንግ የእውቀት ሽግግር ለማድረግ የተካሄደውን ዎርክሾፕ በምሳሌነት የጠቀሰው ተሾመ፤ በዘንድሮው ፌስቲቫል የሳውንድ ኢንጅነሪንግ ስራውን የሚያከናውኑት ከኬንያ የመጡ ባለሙያዎች እንደሆኑ ገልጿል፡፡ “ኢትዮጵያውያኑ ከኬንያውያን ባለሙያዎች ጋር ረዳት ሆነው እንዲሰሩ በማድረግ ልምድ እየቀሰሙ ነው፤ ወደፊት ይህን ሃላፊነት ተረክበው ራሳቸውን ችለው ይሰራሉ፡፡” ብሏል ዳይሬክተሩ፡፡ የ4ኛው ሰላም ፌስቲቫል ዋና ዝግጅቶች ዛሬና ነገ በትሮፒካል መናፈሻ የሚቀርቡት የሙዚቃ ድግሶች ሲሆኑ ተመሳሳይ የሙዚቃ ድግሶች በዓለም አቀፍ መድረኮችም እንደሚቀርቡ ታውቋል፡፡ ዛሬና ነገ በትሮፒካል መናፈሻ በሚቀርቡት የሙዚቃ ዝጅቶች ላይ ወጣቱ ፒያኒስት ሳሙኤል ይርጋ፣ ድምፃዊ ሚካኤል በላይነህ፣ አቤል ሙሉጌታ፣ ሄለን በርሄ፣ ፀጋዬ እሸቱ፣ ታደለ ገመቹና ኤደን ገብረስላሴ ይሳተፋሉ ተብሏክ፡፡
በዓለም አቀፍ መድረክ በሚቀርበው የሙዚቃ  ድግስ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ሙዚቀኞች በተጨማሪ ፈርቀዳጅ በሆነ ስራቸው የኢትዮጵያን ሙዚቃ ለዓለም ያስተዋወቁት ኢትዮጵያውያን የኤሌክትሮኒክ ሙዚቀኞች ሚካኤል ሰይፉና እንደገና ሙሉ እንደሚሳተፉ ታውቋል፡፡ ሁለቱ ወጣት ሙዚቀኞች ‹‹ ኢትዮጵያዊ ኤሌክትሮኒክ›› የሙዚቃ ስልትን በፈር ቀዳጅነት በመጀመር ይታወቃሉ፡፡ ዲጄ ጄዚ ዴቭ (ዳዊት አስራት አለማየሁ) የዲጄ ፓርቲ ያቀርባል ተብሏል፡፡
ከአፍሪካና ከአውሮፓ ስምንት ሙዚቀኞች በሚሳተፉበት ዓለም አቀፍ የሙዚቃ ድግሱ፤  ከባንዱ ጋር በመላው ዓለም ከ600 በላይ የሙዚቃ ኮንሰርቶችን ያቀረበው ጊታር ተጫዋቹ ሃቢብ ኮቴ ከማሊ፣ ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው ደቡብ አፍሪካዊው ዲጄና ራፐር ስፓይክ ማታምቦ፣ በአውሮፓ ሙዚቃ የተካነችውና በራፐርነት የታወቀችው አና ራብ (ጋኑቺ) ከስዊድን፣ በታዋቂው የአሜሪካ የቲቪ ሾው “ዴቭድ ሌተርማን” ላይ በእንግድነት የቀረበችው ራፐር ማፔዬ ከስዊድን፤ ታዋቂዋ ድምፃዊ ጄሚ ያው ሳናህ ከኡጋንዳ፣ ሰባት አባላት ያሉት “ሳራቢ” የሙዚቃ ቡድን ከኬንያ እንዲሁም የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሂፕሆፕ አርቲስት ሌክሰስ ሌጋል ስራቸውን እንደሚያቀርቡ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ከዚህ ቀደም በፌስቱቫሉ ላይ የተሳተፉ የኢትዮጵያ አርቲስቶች አንጋፋነታቸውን መሰረት በማድረግ መመረጣቸውን ያስታወሰው የሰላም መስራችና ዳይሬክተሩ፤ ዘንድሮ ደግሞ ለወጣት አርቲስቶች ልዩ ትኩረት ሰጥተናል ብለዋል፡፡
መቀመጫውን በስዊዲን ያደረገው ሰላም ፌስቲቫል የተጠነሰሰው ከአስር ዓመት በፊት ሲሆን  መስራቹና ዳይሬክተሩ ተሾመ ወንድሙ፤ የቀድሞ የኢትዮጵያ ባህር ኃይል የሙዚቃ  ቡድን የክላርኔትና  ሳክስፎን ተጫዋች ነበር፡፡
የሙዚቃ ባለሙያው ተሾመ ሞስኮ በሚገኝ የሙዚቃ አካዳሚ የኮንዳክተርነት ትምህርት የተከታተለ ሲሆን በእሱ መስራችነትና አመራር የተቋቋመው ሰላም ፌስቲቫል በወርልድ ሙዚቃ አዋርድ “ቤስት ፕሮሞተር” ተብሎ በ2010 ተሸልሟል፡፡ ሙዚቃን እንደ መገናኛ መድረክ የሚጠቀመው ሰላም ፌስቲቫል፤ በስውዲንና በምስራቅ አፍሪካ አገራት መካከል የሙዚቃ ትስስር በመፍጠር ባህልና ሙዚቃን ለማዳበር እንዲሁም ለማስተዋወቅ አልሞ የሚንቀሳቀስ ድርጅት መሆኑን መስራቹ ተሾመ ወንድሙ ይናገራል፡፡

Read 1646 times