Saturday, 17 January 2015 11:23

ሰባራ መስታወት

Written by  ሴና ታደሰ
Rate this item
(1 Vote)

ወግ
“ከነታሪኩ ጋር ወደ ብረት ድልድዩ ሄድን” አለ በኩራት፡፡ የሁሉም ታላቅ ነው፡፡ ራሱን ጀብደኛ አድርጎ ይቆጥራል፡፡ ቢያምኑትም ባያምኑትም ከእርሱ በላይ ያሉት ሲያደርጉት ያየውንና ሊያደርጉት ያቀዱትን ሰምቶ እንደራሱ ተግባር በቃላት አሳምሮ የመጠረቅ ተሰጥዖ አለው፡፡ ታናናሾቹ በእድሜ ከሚልቋቸው ታላላቆቻቸው ጋር ስለሚውል ይፈሩታል፡፡ አፍ አውጥተው አይናገሩ እንጂ ሁሉም ህፃናት እንደሱ ከትልልቆቹ ጋር መዋል አጥብቀው ይሻሉ፡፡ ይብዛም ይነስም የገነነ ምኞታቸውን በቅጥፈት ታሪክ እየለወሱ፣ ከእነርሱ ለሚያንሱት የመተረክ ጥልቅ ምኞት አላቸው፡፡
 ልጅነታቸው የበላይ ለመሆን ከመመኘት አላገዳቸውም፡፡ የሁሉም ታናሽ ትንሹ ልጅ ብቻ ታሪኩን እያዳመጠ በራሱ ሚጢጢ ዓለም ውስጥ ይላወሳል፡፡ አባቱ ሁሌም “ራስህን ሁን” ይለዋል ትንሹን፡፡
አባቱ ራሱ ባለፈ ህይወቱ ራሱን መሆን ያልቻለባቸው የክፉ ቀናት እጣ ላይ ወድቆ ያውቃል፡፡ ራስን ስለመሆን ማሰብ የጀመረው ተስፋውን ጥሎባቸው የተመሳሰላቸው ሰዎች ከውስጡ እንደ አየር በነው ከጠፉ በኋላ ነበር፡፡ ተስፋ ነፍስ የሚያኝክ ጥርስ ያለው ክፉ አውሬ ነው፡፡ ራሱን መምሰል መሆን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ሲያምን ልጁን፤
“ራስህን ብቻ ምሰል” ይለዋል እቅፉ ውስጥ ከቶ ፀጉሩን እያሻሸለት፡፡
“ራስህን ብቻ…”
ጠጠር ያሉ ቃላትን በመለማመድ ላይ ያሉት ትንንሽ ጆሮዎቹ ተቀስረው አባቱ የሚለውን ትንሹ ያዳምጣል፡፡ ራስ መሆንና ራስ መምሰል የሚሉ እንግዳ ቃላት ሲደጋገሙበት ትርጉሙን ሊያስስ በልጅ ደመነፍሱ ማሰብ ጀመረ፡፡ ምሉዕ ትንተና ባያገኝለትም “ራስህን ሁን” መባሉ ራሱን አለመሆኑን ነገረው፡፡ ራሱን መሆን እንዲረዳው ስለ ራሱ በቅጡ ማወቅ እንዳለበት አመነ፡፡ ራሱን ለማወቅ ደግሞ ሌሎችን መምሰል አማራጭ መስሎ ታየው፡፡ ውስጡ ይህን ነግሮታል፡፡ ራሱን የሚያይበት የመልክ መስታወቶቹ እኩዮቹ እንደሆኑ ስለገባው፣ በጥንቃቄ ራሱን እነርሱ ውስጥ መፈለግ ጀመረ፡፡ በወጉ ያልበሰለው አንጎሉ፣ ራሱን ያልተቋጨ ጅምር ሃሳብ እንደሆነ አስረዳው፡፡ ሙሉ እንዳልሆነ ሲገባው  ደመነፍሱ በድንጋጤ ተሸማቀቀ፡፡ ጎዶሎ ሆኖ መገኘት ተፈጥሮ ስፍራ የሰጠችን ነፍስ የሚያንዘፈዝፍ ቀዝቃዛ ፍርሃት ነው፡፡ እንጭጭ ፍርሃቱም ወደ ጠጣር ባይተዋርነት አደገ፡፡ የእድሜ አቻዎቹ መካከል ሆኖ ነፃነት የለውም፡፡ እንደነርሱ አይስቅም አይጫወትም፡፡
 የፍንደቃቸው ምስጢር ከሙሉነታቸው እንደመጣ ስለሚቆጥር፣ በሚሰበሰቡበት ስፍራ ሁሉ ደፍሮ መቀላቀል ይሳነዋል፡፡ ወኔውን አሰባስቦ ቢቀላቀላቸው እንኳን አያስታውሱትም፡፡ የሚከለልበትን ትከሻ ፈልጐ ከኋላቸው ሄዶ ይቀመጣል፡፡ ጀብደኛው የጀመረውን የጀብድ ታሪክ እየወሸከተ ያወራል፡፡
“እኔ…” አለ “…እጆቼን ዘርግቼ በድልድዩ ብረት ላይ ቀጥ ብዬ ቆሜ ተራመድኩ፡፡…” የተከፈተ አፋቸውን ከዝንብ እየተከላከሉ ያዳምጣሉ፡፡ ቃላቱ ጆሯቸውን አልፎ ልባቸው ጋ ሲደርስ ነጥሮ ይመለሳል፡፡ ትንሹ ግን በተከፈተ ጆሮው የሚሰማውን ወደ ውስጡ እያፈሰሰ ሌላ ግብዓት እያደረገው ነው፡፡ በፍርሃት ምክንያት የጎደለው እርሱነቱ እንዲሞላለት የሚሰማውን የድፍረት ታሪክ ወደ ማቆሪያው በፀጥታ ይቀዳል፡፡
“ቴዲ ሞክሮ አቃተው፡፡ በሆዱ እየተሳበ ሊሄድ ሲል ወድቆ ነበር፡፡ አሞራ ትመስላለህ ብሎኛል” አለ ፊቱ ላይ መንታ ገፅ እየታየ፡፡ እርካታና ውሸቱ እንዳይታወቅ የመስጋት መልክ በአንድ ላይ እንደ ቀለም ተደባልቆ ፈሷል፡፡ አድማጮቹ ግን ውሸቱን እንደሆነ ቢያውቁም ደፍረው አይናገሩትም፡፡ ለውሸት ጀብዱው የውሸት ፈገግታና አድናቆት እየለገሱት ይስቃሉ፡፡ እርሱ ታላቃቸው ነውና፡፡ እነርሱም እንደዚያ የማድረግ ገሃድ ያልወጣ ድብቅ ምኞትም ስላላቸው፡፡ ትንሹ ብቻ በባለታሪኩ ዓይን ውስጥ ያየውን እርሱነቱን በነፍሱ ጥርሶች እያኘከ ያደቃል፡፡ ከእነርሱ ጋር ሆኖም በጭምት ነፍሱ እንደተገለለ ነው፡፡ ፀሐይ እያሽቆለቆለች ወደ ሰንኮፏ ልትከተት ትንደረደራለች፡፡ ደመነፍሳቸው እየመሸ መሆኑን ሲነግራቸው እንኳን ማድመጥ አልፈለጉም፡፡ የቤተሰቦቻቸው ጥሪ ከተቀመጡበት እስኪቀሰቅሳቸው ይጠብቃሉ፡፡ “ትልቁ የዝግባ ዛፍ ላይ ወጥተን ደግሞ ከታሪኩ ጋር የጋጋኖ እንቁላል ይዘን ወረድን” አለ ጀብደኛው ልጅ፡፡ ትንንሾቹ ከራቀው ሰማይ ላይ የድፍረት እንቁላል ለማርባት እንደ ዝግባው የገዘፈ ምኞታቸውን በመሰላል ሲወጡ አፋቸው ለሃጭ ያረባል፡፡ ባለ ጀብድ ታሪኩ በዚህ እርካታ ይሰማዋል፡፡
ለዓይን ያዝ ማድረግ ሲጀምር ከየአቅጣጫው የወላጆች ጥሪ ተሰማ፡፡ በልምድ የአንዱ ወላጅ ጥሪ ለሁሉም እንደሆነ ቢያውቁም የራሳቸው ወላጆች እስኪጠሯቸው ይጠብቃሉ፡፡ ተፈላጊ ልጅ ብቻ ተነስቶ ይሄዳል፡፡ ያልተጠሩት ጊዜ ቸርችረው የቀራቸውን እንጥፍጣፊ የምሽት ጨዋታ ለመጫወት ጆሯቸውን አንቅተው መቆየት አለባቸው፡፡ ወላጆችም ከጐረቤቶቻቸው ጋር በጥሪው ይግባባሉ፡፡ አንደኛው ወላጅ ሲጣራ ሌሎቹ የእነርሱም ልጆች እስኪመጡ ጊዜ ይሰጧቸዋል፡፡ ሁሉም ሲበተኑ ያወሩትና የሰሙትን፤ የተወሰደባቸውንና የነጠቁትን ከጨለማው ጋር የነበሩበት ትተው ወደ ቤታቸው ይገባሉ፡፡ ቤት ውስጥ ደግሞ የሚጠብቃቸው ሌላ የልጅነት ህይወት ቅብብሎሽ አለ፡፡
ትንሹ ጆሮው የሰበሰበውን በሙሉ የዋህ ልቡ ላይ ቋጥሮ ይመለሳል፡፡ ሁሉም ጥለው የሄዱትን የሚያነሳው እርሱ ብቻ ነው፡፡ ሚጢጢ ልቡ አሻክራ የቀየጠችው እውቀት በድንገት ብልጭ አለለት፡፡ ራስን ሆኖ የመገኘት ብልሃት የተከሰተለት መሰለው፡፡ ራሱን ጀብደኛ ሆኖ አገኘ፡፡ የፍርሃት እውቀታችን ከሽፋኑ ሲገለጥ የሚወስደን ዓይናችን ወደሚያስተውለው ተጨባጭ ያልሆነ የምኞት ጥግ ነው፡፡ ራስን የመሆን የሙሉነት ፈተናውን ጀብደኞችን መስሎ እንደማያልፈው ተሰምቶታል፡፡ መልሱን ያገኘ በመሰለው ቁጥር ጥያቄውን ረሳ፡፡ የተጣመመው መልስ ቀጥ ያለውን የውስጥ ጥያቄውን አጣሞበት ከራሱ ጋር ተላለፈ፡፡ እነርሱን ሲመስል ራሱን መሆን አቆመ፡፡ ራስን አለመሆን ምንም ያለመሆን ብኩን የተፈጥሮ ምላሽ ይመስላል፡፡ እነርሱን መምሰል ራሱን ካለመሆን የጨለማ እስር ነፃ ያወጣዋል፡፡ ሆኖ ያለመገኘት ገመዱን እነርሱን በመምሰል ድርጊት ያለውል ቋጠረው፡፡ ዱባ መሆንን በመምሰል፣ ቅል አጠላልፎ እየገመደ፡፡ ነገ ለእኩዮቹ ተራኪ የሚሆነው እርሱ መሆን እንዳለበት እያሰበ፣ ከመንደራቸው ጀርባ ወዳለችው አነስተኛ ኩሬ አመራ፡፡ ሀሳቡ ደሙን አሙቆት እንፋሎቱ ገንፍሎ ወጣ፡፡ ልብሶቹን አወላልቆ ወደ ኩሬው ዘለለ፡፡ ዋኝቶ ባያውቅም ዛሬ እንደሚችል ምስጢረኛው ደመነፍሱ አረጋግጦለታል፡፡ አየሩ ላይ ሲንሳፈፍ፣ ነገ በድልድዩ ብረት ላይ እጆቹን እንደ አሞራ ክንፍ ዘርግቶ በድፍረት ስለመሄድ እያሰበ ነበር፡፡
 እንደአሁኑ በጨለማ ሳይሆን በደማቅ ብርሃን የሚንቁት እኩዮቹ በዓይናቸው እያዩት፡፡ በንቀት የተነፋ ልባቸው፣ ሲቀኑ በሚቀላ ዓይናቸው ውስጥ ሲፈነዳ የሚያገኘውን እርካታ እየተጠባበቀ፡፡
ኩሬዋ ለአዋቂ ጉልበት ታስባ ስያሜ ቢወጣላትም በህፃን ቁመት ባህር ሆና ስያሜዋንና ትንሹን ከጨለማው ጋር ተስማምታ ለመዋጥ ትችላለች፡፡ አባቱ “ራስህን ሁን” ሊለው መፅሐፍ የሚያነብበትን መነፅር ዝቅ አድርጎ ወደ ውጭ እየቃኘ፣ ልጁን በመጠበቅ ላይ ይሆናል፡፡ ያለፈ ዘመኑ ሌሎችን የመምሰል ባተሌነት በልጁ እንዲደገም ባለመሻት፣ የተጋረደ ማንነቱን ፍለጋ በሰባራ ዓይናቸው ውስጥ ስብርባሪ ገፁን በትዝታ እየለቀመ ይሆናል፡፡ ካለፈ ህይወቱና ከመፃሕፍት ባገኘው ድምር እውቀት መለኪያ ግን ልጁ ራሱን መምሰል አለበት፡፡ የአባትየው ትግል የልጁ መልክ ከሌሎች ፊት ጋር እንዳይመሳሰልበት ነው፡፡ ልጁ ሰዎች ራሳቸውን አዘቅዝቀው የሚመለከቱበት የተሰበረ መስታወት መሆኑ እስኪገባው ድረስ፡፡
(መሆሰል - መሆንና መምሰል ለማለት)   

Read 2033 times