Saturday, 31 January 2015 12:54

በተጨዋቾች የዝውውር ገበያ የአውሮፓ አትራፊነት፤ የኢትዮጵያ ኋላቀርነትና የአፍሪካ ባርነት]

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

     ፊፋ የዓለም  እግር ኳስ የተጫዋቾች ዝውውር ሪፖርትን ሰሞኑን ይፋ አድርጓል፡፡ ሪፖርቱ እንዳመለከተው በ2014 እኤአ  በዓለም እግር ኳስ 13090 ፕሮፌሽናል ተጨዋቾችን ያሳተፉ  ግብይቶች ነበሩ፡፡  ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጭ እንደሆነም ታውቋል፡፡  የተጨዋቾች ብዛትና ዋጋ እድገት ማሳየቱን የገለፀው ሪፖርት፤ የዓለም ዋንጫ ስለተካሄደበት ፤ የብሮድካስት ገቢ በመጨመሩና  ስፖርቱ ለተጨማሪ የገበያ እድሎች ስለተመቸ ነው ብሏል፡፡  
ሪፖርቱን በፊፋ ሚሰራው ትራንስፈር ማቺንግ ሲስተም የተባለው ዲፓርትመንት  ነው፡፡በዓለም አቀፍ ደረጃ የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጨዋቾችን ዝውውር በመከታተል በፊፋ በኩል ሪፖርት ሲያቀርብ አራተኛ ዓመቱ ነው፡፡ መረጃዎቹ ቢያንስ ለሰባት ዓመታት ሲሰባሰቡ ቆይተዋል፡፡ የሚዘጋጅበት ዋና ምክንያት በዓለም የእግር ኳስ ስፖርት ያሉ ባለድርሻ አካላት የስፖርቱን የገበያ ሁኔታ በመረጃ በተደገፈ እውቀት ለመከታተል እንዲያስችል ነው፡፡ አይቲኤምኤስ የተባለው የፊፋ አካል የሆነ ተቋም በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር አባል በሆኑ ሁለት መቶ አገራት ውስጥ ከሚገኙ ስድስት ሺ ክለቦች ጋር በመስራት ድጋፍ ያደርጋል፡፡
በዝውውር ገበያው ብራዚላውያን ተጨዋቾች ከፍተኛውን ብዛት ያስመዘገቡ ሲሆን 646 እዚያው በአገራቸው  689 ደግሞ በመላው ዓለም በመሰራጨት በገበያው ከፍተኛ ተፈላጊ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡ ብራዚላውያኑ ተጨዋቾች 567 ሚሊዮን ዶላር ወጭ ሆኖባቸዋል፡፡ 801 አርጀንቲናውያን፤ 596 እንግሊዛውያን እንዲሁም 507 ፈረንሳውያን ተጨዋቾች የገበያው አካል ሆነው ተከታታይ ደረጃ ወስደዋል፡፡ በሪፖርቱ እንደተዳሰሰው  የእግር ኳስ ትልቁ ገበያ በሚካሄድባቸው የአውሮፓ አምስት ታላላቅ ሊጎች ላይ 1.35 ቢሊዮን ዶላር ወጭ ተደርጓል፡፡
የአንድ ተጨዋች አማካይ የዝውውር ሂሳብም ሚሊዮን ዶላር 10.1 ሚሊዮን ተተምኗል፡፡ በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግና በስፔን ላሊጋ የዝውውር ገበያው ተሳትፎ ሲጨምር፤ በጀርመን ቦንደስ ሊጋ በፊት ያልነበረው ግብይት በከፍተኛ ደረጃ  አድጓል፡፡ በፈረንሳይ ሊግ እና በጣሊያን ሴሪኤ የወጭው መጠን በየዓመቱ ከግማሽ በላይ መቀነሱን ቀጥሏል፡፡
ገበያው በከፍተኛ ሁኔታ የደራባቸው ሁለት አገራት እንግሊዝ እና ስፔን ቢሆኑም እግር ኳስ አትራፊ  በሆነበት አውሮፓ  በገበያው ወጭ 87 በመቶ ድርሻ ነበረው፡፡ በእንግሊዝ ያሉ ክለቦች ከወጪው 67 በመቶ ድርሻ በመውሰድ እስከ 770 ሚሊዮን ዶላር ሲያፈስሱ የስፔን ክለቦች ወጭ ደግሞ እስከ 308 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ዝውውሮችን ያቀላጠፉ ፊፋ የሚያውቃቸው ህጋዊ ኤጀንቶች እና ወኪሎች እስከ 236 ሚሊዮን ዶላር የኮሚሽን ክፍያ አግኝተዋል፡፡
በዓለም እግር ኳስ የዝውውር ገበያ ተፈላጊ የሚሆኑ ተጨዋቾች አማካይ እድሜ 25 ዓመት ከ6 ወር መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት በዓለም እግር ኳስ ገበያ 160 አገራትን በማሳተፍ ከ35ሺ በላይ የተጨዋቾች የዝውውር ተፈፅመዋል፡፡ የአውሮፓና ደቡብ አሜሪካ ተጨዋቾች በከፍተኛ ዋጋቸው  እስከ 20ኛ ያለውን  ደረጃ የተቆጣጠሩ ሲሆን  ከ50 እስከ 119 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ በአንፃሩ የአፍሪካዊ ተጨዋች ከፍተኛው ዋጋ ተመን ከ4.5 እስከ 31.8 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ የዓለም እግር ኳስ የዝውውር ገበያ የኢትዮጵያዊ ፕሮፌሽናል ተጨዋች ከፍተኛው  ዋጋ በስዊድኑ ክለብ ቢኬ ሃከን የሚጫወተው የመሃል ተከላካዩ ዋልድ አታ የተተመነበት 601 ሺ ዶላር  ነው፡፡
በፊፋ የተሰራጨው የዓለም እግር ኳስ የፕሮፌሽናል ተጨዋቾች የዝውውር ገበያ ሪፖርት መነሻ ያደረገው የስፖርት አድማስ ዘገባ ሰሞኑን አነጋጋሪ በሆነውና በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የቀረበውን ረቂቅ ህገ ደንብ በጨረፍታ ይዳስሳል፡፡
ዛሬ ወደ ሩብ ፍፃሜ ከሚሸጋገረው 30ኛው አፍሪካ ዋንጫ በተያያዘ ደግሞ አፍሪካውያን ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች በዓለም እግር ኳስ እየተበደሉ መሆናቸውን ይመለከታል፡፡ አፍሪካውያን በዓለም እግር ኳስ ገበያ የተሰጥኦዋቸውንና የጉልበታቸውን ያህል ተጠቃሚ አለመሆናቸውን ያሳያል፡፡  በፍልሰት፤ በህገወጥ ዝውውርና ዘመናዊ ባርነት ስለመጎዳታቸው  በተለያዩ ጊዜያት የተሰሩ ትንታኔዎች፤ ጥናታዊ ሪፖርቶች እና ዘገባዎችን በመንተራስ  ቀርቧል፡፡
ኢትዮጵያ ገና በተጨዋቾች ደረጃና የዝውውር ረቂቅ ሕገ ደንብ ላይ
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በክለቦች ላይ የሚታየውን የተጨዋቾች የዝውውር ስርዓት ወደ ዘመናዊ አሰራር የሚቀይር ያለውን የተጨዋቾች ደረጃና የዝውውር ረቂቅ ሕገ ደንብ ከሳምንት በፊት ይፋ አድርጓል፡፡  ፌደሬሽኑ ረቂቅ ህገ ደንቡን አለም የሚከተለውን አሰራር ለመተግበር አዘጋጅቸዋለሁ በማለት ከጥር 25 ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሚያደርገው አስታውቋል፡፡ ይሁንና በተለያዩ ሁኔታዎች ረቂቅ ህገ ደንቡ ባለድርሻ አካላትን እያወዛገበ ነው፡፡  በተጨዋቾች ዝውውር ኪራይ ሰብሳቢዎች፣ ያልታወቁ ደላሎችና አጭበርባሪዎችን ለመከላከል እንደሚያግዝ፤ የክለቦች እና የመንግስትን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ የተባለው ደንቡ በዘጠኝ ክፍልና በ28 አንቀጽ ተከፋፍሎ ቀርቧል፡፡ እስከ  10 በሚደርሱ አንቀፆች የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በውዝግብ እና በጭቅጭቅ ላይ ናቸው፡፡ የተጨዋቾች ደረጃና የዝውውር ረቂቅ ሕገ ደንቡ በዋናነት ብዙ ቅሬታዎችን የፈጠረው የተጨዋቾች ፤ የክለብ ባለቤቶችና አስተዳዳሪዎች ሐሳባቸውን እንዲገልፁበት በቂ እድል አልሰጠም በሚል ነው፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ግን ረቂቅ ህገ ደንቡን ያዘጋጀው ከኢትዮጵያ ቡና፣ ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ከዳሸን ቢራ፣ ከአርባ ምንጭ ከነማ፣ ከሊግ ኮሚቴ፣ ከይግባኝ ሰሚ ኮሚቴና ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት የተውጣጡ ባለሙያዎች ባካተተ የጥናት ቡድንን እንደሆነ አስታውቋል፡፡  በደቡብ አፍሪካ እግር ኳስ የሚተገበረውን ህገ ደንብ ተንተርሶ እንደተዘጋጀ፤  የዓለም አቀፉን እግር ኳስ ማኅበርን ሕግጋት መሠረት እንዳደረገና የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ)፣የተጨዋቾች የዝውውር መርሕን እንደሚከተልም ገልጿል፡፡  ፌደሬሽኑ  በአገሪቱ የሚፈፀመው የእግር ኳስ ተጨዋቾች ደረጃና ዝውውር በሕግና በሥርዓት እንዲመራ   ህገ ደንቡ ወሳኝ እንደሆነ ሲያስገነዝብም ፤በፊፋ ዝቅተኛውን የተጨዋቾች ደረጃና ዝውውር መስፈርት ያሟላ እንዲሆን፣ በተጨማሪም አሠራሩ በሕጋዊ ወኪል እንዲመራና ሒደቱም ተጨዋቾችን፣ ክለቦችንና መንግሥትን ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደሆነም አመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ የዝውውር ገበያ ካለፈው 4 ዓመት ወዲህ በ50ሺ ብር የፊርማ ክፍያ ተጀምሮ፤ ወደ 100ሺ ብር ከዚያም ወደ 200ሺ ብር፤ 300ሺብር ዋጋዎቹ እያደጉ መጥተው ዘንድሮ ለአንድ ተጨዋች የሚከፈለው የፊርማ ገንዘብ ወይም የዝውውር ሂሳብ በአማካይ እስከ 500ሺ ብር ደርሶ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ዳዊት እስጢፋኖስን ለ2 ዓመት ኮንትራቱን እንዲያራዝም የከፈለው 1.2 ሚሊዮን ብር ደግሞ  ሪኮርድ የፊርማ ሂሳብ ነበር፡፡  
የፕሪሚዬር ሊግ ተጨዋቾች ወርሃዊ ደሞዝ በአማካይ 3ሺ ብር  እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡  ዘንድሮ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ከመጀመሩ በፊት በተካሄደው የዝውውር ገበያ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ መውጣቱ  ተዘግቦ ነበር፡፡ በወቅቱ አዲስ ተጨዋች  በማስፈረም እና ውሎችን በማደስ 8 ክለቦች ንቁ ተሳትፎ የነበራቸው ሲሆን ግብይቱ በ73 ተጨዋቾች ላይ የተንቀሳቀሰ ነበር።  መከላከያ እስከ 91 ሚሊዮን ብር፤ ንግድ ባንክ እስከ 62 ሚሊዮን ብር እንዲሁም ሙገር  እስከ 47 ሚሊዮን ብር ፈሰስ ማድረጋቸው የገበያውን መሟሟቅ የሚያመለክት ነበር፡፡
በሌላ በኩል  ከአምስት እና ስድስት ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ተጨዋቾች ከአገር ውጭ የመጫወት እድል ያላቸው በየመን ሊግ ብቻ ነበር። ባለፉት ሁለት ዓመታት ግን በግብፅ እና በምስራቅ አውሮፓ እንዲሁም አፍሪካ ውስጥ በሱዳን ፤ በሊቢያና በደቡብ አፍሪካ ሊጎች በጣት የሚቆጠሩ ተጨዋቾች ዝውውር መፈፀማቸው ይጠቀሳል፡፡ በተያያዘ ዘንድሮ በኢትዮጵያ ለመጫወት ከአፍሪካ 6 አገራት የተውጣጡ ከ26 በላይ ተጨዋቾች በ7 ክለቦች በመቀጠር ለቀጣይ የውድድር ዘመን ህጋዊ እውቅና አግኝተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ  ለመጫወት እውቅና ያገኙት ከሌላ አገር የመጡት ተጨዋቾች ብዛታቸው 26  ይሆናል። 8 ከካሜሮን፤ 7 ከናይጄርያ፤ 6 ከጋና፤ 3 ከኡጋንዳ እንዲሁም ከኬንያ እና ከደቡብ አፍሪካ የመጡ ናቸው፡፡ ከ26ቱ የሌላ አገር ተጨዋቾች ጊዮርጊስ 7፤ ኤልፓ እና ሀረር ቢራ እያንዳንዳቸው 5፤ ደደቢት 4፤ ኢትዮጵያ ቡና እና ድሬዳዋ ከነማ እያንዳንዳቸው 2 እንዲሁም ኒያላ ለ1 ተጨዋች ቅጥር ማረጋገጫ ተሰጥቷቸው ነበር፡፡  በፊፋ ህጋዊ እውቅና ተሰጥቷቸው በተጨዋች ወኪልነት የሚሰሩ ባለሙያዎች በጣት የሚቆጠሩ መሆናቸውን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በነበረው አሰራር እንደተጨዋች ወኪል ሆነው  ዝውውርን የሚደልሉት የቀድሞ ተጨዋቾች እና አሰልጣኞች፤ የየክለቡ አሰልጣኞች እና ተፅእኖ አድራጊ ተጨዋቾች፤ የሚዲያ ባለሙያዎች እና የደጋፊዎች ማህበራት ነበሩ፡፡
በኢትዮጵያ  የነበረው አሠራር  ለክለቦች፣ ተጨዋቾችና መንግሥት ምንም ዓይነት ጥቅም አላስገኘም የሚለው የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ፤ ይልቁንም የክለቦችን የፋይናንስ አቅም ያዳከመ መሆኑንም ይገልፃል፡፡ ተጨዋቾችም በፊርማ ክፍያ እንደወሰዱ ተደርጎ የሚነገረው ገንዘብ ሙሉ በሙሉ የእነሱ እንዳልሆነ፣ በመሐል ለሕገወጥ ደላሎች እንደሚውል፣ በሕገወጥ አሠራር በፕሮፌሽናል ስም ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ተጨዋቾች መኖራቸው አንዳንዶቹ የፊርማ ገንዘብ ወስደው እንደጠፉ፣ በፕሮፌሽናል ስም ከሌላ አገር የሚመጡት ብዙዎቹ ተጨዋቾች ችሎታቸው እንደሚያጠያይቅ፣ ተጨዋቾች ከደመወዝ ይልቅ ለፊርማ  ክፍያ እንደሚደራደሩና ተቀብለው ተገቢውን አገልግሎት እንደማይሰጡ፣  ክለቦች  አሳድገው ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም በማሳጣቱ ለታዳጊና ለወጣት ተጨዋቾች  ትኩረት እንዳይሰጡ ማድረጉንም እንደማስረጃዎቹ በዝርዝር አቅርቧል፡፡ በአንድ የውድድር ዓመት ለተጨዋቾች ዝውውር በፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ብቻ 140 ሚሊዮን ብር ሲንቀሳቀስ መንግሥት ከገቢ ግብር ሊያገኝ የሚገባውን እስከ 42 ሚሊዮን ብር ማሳጣቱም ተጠቅሷል፡፡
ረቂቅ ህገ ደንቡ በተለያዩ አገሮች የተጨዋቾች ደረጃና የዝውውር ሥርዓትን በአስረጂነት እንደተዘጋጀ ቢገለፅም፤ በክለቦችእና በተጨዋቾች በስፋት ትችት እየቀረበበት ነው። የክለቦችና የተጨዋቾች መብቶችን የሚጋፉ አንቀፆች መካተታቸውን በመግለፅ የቀረቡት ቅሬታዎች ይበዛሉ፡፡ እንደነዚህ ዓይነቶቹን ደንብና መመሪያዎች በሚወጡበት ወቅት ጉዳዩን ከሕግና መሰል ጉዳዮች ጋር አጣጥመው ማስኬድ የሚችሉ የሕግ ባለሙያዎችን ማካተት ይገባ እንደነበር የተቹም ይገኙበታል፡፡ የኢትዮጵያ ተጨዋቾችን በመወከልም ሃሳብን ለመግለፅ በሚል ለፌደሬሽኑና ለሚዲያ አካላት በተሰራጨው ግልፅ ደብዳቤ ቢያንስ 5 አንቀፆች ላይ የቀረቡ ቅሬታዎች ቀርበዋል፡፡ ዝርዝሩን ሳምንት በስፋት የምንመለስበት ይሆናል፡፡
አፍሪካውያን  በፍልሰት ፤ በዘመናዊ ባርነትና በጉልበት ብዝበዛ ላይ
አፍሪካውያን ፕሮፌሽናል በአውሮፓ ሊጎች 15 በመቶ ውክልና አላቸው፡፡ በ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ከተሳተፉት  368 ተጨዋቾች 248 ያህሉ በ32 የአውሮፓ አገራት  የሚጫወቱ ናቸው፡፡ 75 ከፈረንሳይ፣ 27 ከስፔን፣ 23 ከእንግሊዝ፣ 21 ከቤልጅዬም ሊግ ተገኙ ናቸው፡፡ አፍሪካ ዋንጫው  በ4 አህጉራት፣ በ57 አገራት የሚገኙና 243 ክለቦችን የወከሉ ተጨዋቾች ይሳተፉበታል፡፡   በየአገራቸው የሚጫወቱ  107 ሲሆኑ በ17 አገራት ያሉ 58 ክለቦችን የወከሉ ናቸው፡፡ አፍሪካውያን በመላው ዓለምም ተሰራጭተዋል፡፡ ከአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች አገራት ባሻገር በምስራቅ አውሮፓ፤ በመካከለኛው ምስራቅ እና በሩቅ ምስራቅ ኤስያም አርሜንያ፤አንዶራ፤ጂብራላተር እና ኢስቶንያ፤  ሆንግ ኮንግ፤ በቻይና፤ ህንድ፤ ባንግላዴሽ እና በኢራን፤ በሰሜን አሜሪካ ሜክሲኮ ውስጥ በሚገኙ የሊግ ውድድሮች አፍሪካዊ ፕሮፌሽናል ተጨዋች አይታጣም፡፡
አፍሪካውያን አህጉራቸውን በመልቀቅ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተሰራጩበት ምክንያት በስፖርቱ በተሻለ ኢኮኖሚ ተጠቃሚ ከመሆን አንፃር ነው። የሚገባቸውን ያህል ባያገኙበትም በተፈጥሯዊ ብቃታቸውና ተሰጥኦቸው አፍሪካውያን ተፈላጊ ናቸው። አፍሪካ ውስጥ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾችን በደህና ደሞዝ በመቅጠር የሚያጫወቱ አገራት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው።   በግብፅ፤ በደቡብ አፍሪካ፤ በአንጎላ፤ በዲሪ ኮንጎ ያሉ ክለቦች ብቻ በዝቅተኛ ደረጃ የፕሮፌሽናል ተጨዋቾችን ፍልሰት የመገደብ አቅም ያዳበሩ ናቸው። ይሁንና በእነዚህ አገራት ያሉ ክለቦች ወርሃዊ ደሞዝ ቢከፍሉ ዝቅተኛው 150 ከፍተኛው 600 ዶላር ነው፡፡ በአውሮፓ ሳይሆን ለምሳሌ ያህል በባንግላዲሽ ለአንድ አፍሪካዊ ተጨዋች እስከ 2000 ዶላር ወርሃዊ ደሞዝ ይታሰባል፡፡ ስለሆነም የአህጉሪቱ ክለቦች የፋይናንስ አቅም ተወዳዳሪ አለመሆንና  በፕሮፌሽናል ደረጃ ያን ያህል አለማደጋቸውም ተፅእኖ ፈጥሮ ፍለሰቱን እንዳባባሰውም ይገለፃል፡፡
ከወር በፊት በታዋቂው የእንግሊዝ ታብሎይድ ዴይሊሜል በተሰራጨው ዘገባ በመላው ዓለም በ34 አገራት ያሉ ሊጎች የደሞዝ ሁኔታ ተዳስሶ ነበር፡፡ የአንድ ፕሮፌሽናል ተጨዋችን አማካይ ደሞዝ በማስላት ደረጃ ለማውጣት ነበር፡፡ በከፍተኛ ደሞዝ ከፋይነት የመጀመርያውን ደረጃ የወሰደው ለአንድ ፕሮፌሽናል ተጨዋች 66.4ሺ ዶላር በሳምንት የሚከፍለው የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ሲሆን፤ የጀርመን ቦንደስ ሊጋ 42.2 ሺ፤ የጣሊያን ሴሪኤ 38 ሺ፤ የስፔን ላሊጋ 35.3 ሺ እንዲሁም የፈረንሳይ ሊግ 1 28.5 ሺ ዶላር ሳምንታዊ ደሞዝ በመክፈል እስከ አምስት ያለውን ደረጃ አከታትለው ወስደዋል፡፡
በዴይሊ ሜል ጥናታዊ ዘገባ መሰረት አፍሪካ ውስጥ የሚካሄዱ የሊግ ውድድሮች ለተጨዋቾች በሚከፍሉት ደሞዝ በደቡብና ሰሜን አሜሪካ አህጉራት፤ ከኤስያ፤ ከመካከለኛው ምስራቅ እና ከምስራቅ አውሮፓ አገራት የሊግ ውድድሮች እጅግ ዝቅ ያሉ ናቸው፡፡ በደረጃ ውስጥ ለመግባት የቻሉትም በሁለት የአፍሪካ አገራት የሚካሄዱ ሊጎች ናቸው፡፡ በአልጄርያ የሚካሄደው የሊግ ውድድር ለአንድ ፕሮፌሽናል ተጨዋች በሳምንት 2005 ሺ ዶላር አማካይ ሳምንታዊ ደሞዝ በመክፈል 28ኛ ደረጃ ሲያገኝ ለናይጄርያ ሊግ ደግሞ 196 ዶላር አማካይ ሳምንታዊ ደሞዝ እየተከፈለ 31ኛ ደረጃ ተሰጥቷል፡፡
አፍሪካውያን በእግር ኳስ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ወደተለያዩ የዓለም ክፍሎች መፍለሳቸው የአህጉሪቱን እግር ኳስ ከማዳከሙም በላይ አስከፊ እየሆነ የመጣው ይህ የፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ህልማቸው ለዘመናዊ  ባርነት አጋልጧቸው መጎሳቆላቸው ነው፡፡ አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በ20ሺዎች የሚገመቱ አፍሪካውያን በፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጨዋችነት ህልም ተታትለው ወደ አውሮፓ በመሰደድ የጎዳና ተዳዳሪዎች ሆነዋል፡፡ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር እና በየአህጉሩ ያሉት የእግር ኳስ ተቋማት እድሚያቸው ከአስራ ስምንት ዓመት በታች የሆኑትን በእግር ኳስ ምክንያት ማዘዋወር የሚከለክል ህግ ቢኖራቸውም ተግባራዊነቱ ደካማ መሆኑ በእግር ኳስ ዘመናዊ ባርነት መኖሩን አጋልጦታል፡፡ አፍሪካውያን ታዳጊዎች  በየአገሮቻቸው ባሉ አካዳሚዎች በ12 እና 13 ዓመት እድሜያቸው በቂ ስልጠና እና ትምህርት ሳያገኙ በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ህልም ወደ አውሮፓ እየተላኩ ናቸው፡፡ ይህ ሁኔታም በተለይ በምእራብ አፍሪካ የሚገኙ አካዳሚዎች በአሳሳቢ ሁኔታ ተስፋፍቶ ይስተዋላል፡፡ አካዳሚዎቹ ታዳጊዎችን 70 በመቶ በማሰልጠን ለፕሮፌሽናል ደረጃ አብቅተው በማሰልጠን 30 በመቶውን በአውሮፓ እግር ኳስ እንዲያሳድጉ ማድረግ ነበረባቸው፡፡
በተገላቢጦሽ የሚከተሉት አሰራር ግን የበርካታ አፍሪካውያን ወጣቶች ህልምን በአጭሩ እያስቀረ ይገኛል፡፡ ብዙዎቹ አፍሪካውያን እግር ኳስ ተጨዋቾች በየአገራቸው ካሉ አካዳሚዎች በወጣትነታቸው ወደ አውሮፓ እና የተለያዩ ዓለም ክፍሎች በመሰደድ ላይ ናቸው፡፡ በተለያዩ ህገወጥ የዝውውር ደላሎች ተታልለው መፍለሳቸው የሚመኙትን የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተመክሮ እንዳያሳኩ ሆነዋል፡፡
በማይረባ ክፍያ እና ጥቅም ጉልበታቸው እየተበዘበዘም ነው፡፡ በእድሜያቸው ገና የሆኑ አፍሪካውያን ታዳጊዎችም በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ህልም ለጉልበት ብዝበዛ፤ ለከፋ ድህነት እና ጉስቁልና እየተዳረጉ ናቸው። እድሜያቸው ከ13 በታች የሚሆናቸውን አፍሪካውያን በህገወጥ ፍልሰት የሚያሰቃዩ ሃሰተኛ የተጨዋቾች የዝውውር ደላሎች በዝተዋል፡፡ የፈጠሩት ስግብግብ የንግድ መረብን ለመቆጣጠር የሚያዳግትበት ደረጃም ተደርሷል፡፡ በምእራብ አፍሪካ ውስጥ ህገወጥ እና ሀሰተኛ የእግር ኳስ ዝውውር ደላሎች ብቻ ሳይሆኑ ፍቃድ የሌላቸው አካዳሚዎች በሺዎች ሆነው መንቀሳቀሳቸው ችግሮቹን አባብሷቸዋል፡፡
ለታዳጊ ተጨዋች ቤተሰቦች የአውሮፓ እግር ኳስን የፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ህልም ቃል በመግባት እና እስከ 10ሺ ፓውንድ በማስከፈል ህገወጥ ዝውውር የሚያደርጉ ህገወጥደላሎች መኖራቸውም ይጠቀሳል። በተለያዩ ጊዜያት ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ አስተዳደር ተቋማት፤ የስፖርት ባለሙያዎች እና ምሁራን እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፤ በአፍሪካውያን የእግር ኳስ ባርነት በተለይ በምእራብ አፍሪካ አካዳሚዎች የተበላሸ አሰራር እና ህገወጥ የተጨዋቾች ዝውውር አጀንዳዎች ዙርያ የተቃውሞ ድምፃቸውን አሰምተዋል፡፡ የፊፋው ፕሬዝዳንት ሴፕ ብላተር እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶችን በዓለም የእግር ኳስ ገበያ ላይ ማሳተፍን የ21ኛው ክፍለ ዘመን ዘመናዊ የባርያ ንግድ ብለው በተደጋጋሚ ያወገዙት ሲሆን፤ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ፕሬዝዳንት ሚሸል ፕላቲኒ በበኩሉ የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ የከፋ ደረጃ በሚል ተቃውሞውን ገልጿል፡፡ በዓለም እግር ኳስ የአፍሪካዊ ተጨዋች ዋጋም ከሚኖረው አስተዋፅኦ ጋር ከሌላው ዓለም በንፅፅር ሲታይ ዝቅተኛ ነው፡፡ በአፍሪካዊ ተጨዋች አዲስ የዝውውር ሂሳብ ሪከርድ በዓለም እግር ኳስ የተመዘገበው ባለፈው ሰሞን ነው፡፡ የ26 ዓመቱ ኮትዲቯራዊ ዊልፍሬድ ቦኔ ከእንግሊዙ ክለብ ስዋንሲ ሲቲ  ወደ ማንችስተር ሲቲ የተዛወረበት 422 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ዊልፍሬድ ቦኔ ባለፉት አምስት ዓመታት የአውሮፓን እግር ኳስ ትኩረት ስቦ የቆየ ተጨዋች ነበር፡፡ በአፍሪካ ኮከብ ተጨዋችነት ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ በካፍ ለመሸለም የበቃው ያያ ቱሬ እና ኤጀንቱ ዲምትሪ ሲሊክ የአፍሪካውያን ችሎታ እና አስተዋፅኦ በአውሮፓ እግር ኳስ ያን ያህል የሚገባውን ዋጋ እያገኘ እንዳልሆነ እና ክብር እንደማይሰጣቸው በተደጋጋሚ ሲያማርሩ ተሰምተዋል፡፡
ሴኔጋላዊው ዴምባ ባ በአፍሪካውያን ተጨዋቾች ላይ በዓለም እግር ኳስ ገበያ ላይ ያለውን ዝቅተኛ ዋጋ አሰጣጣጥ ለማሳየት ሂሳብ ምሳሌ ማድረግ ይቻላል፡፡ ባ በሶስቱ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ክለቦች ዌስትሃም፤ ኒውካስትል እና ቼልሲ ስኬታማ የውድድርዘመናትን በማሳለፍ ካገኘው ከፍተኛ ልምድ በኋላ አምና ወደ ቱርኩ ክለብ ቤሲክታስ የተዛወረው አስቀድሞ ከነበረው የዋጋ ግምት 100 ፐርሰንት ርካሽ ሂሳብ ቀርቦለት በ7.1 ሚሊዮን ፓውንድ ብቻ ነበር፡፡ ለአፍሪካውያን ተጨዋቾች በዝውውር የሚወጣው ሂሳብ ከላቲን እና ከአውሮፓ ተጨዋች አላግባብ ያነሰ እንደሆነም ተንታኞች ይገልፃሉ። አፍሪካውያን ተጨዋቾች ወደ አውሮፓ ክለቦች ሲዘዋወሩ የሚገባቸውን ክፍያ ከማግኘት ይልቅ በወረደ ሂሳብ እንዲፈርሙ ይገደዳሉ፡፡ አላግባብ ጉልበታቸው ይበዘበዛል፡፡ በየክለቦቹ ጉልበት እና ሃይል ሰጪ ሆነው ብቻ ይታያሉ፡፡ ከእነ ሳሙኤል ኤቶ፤ ከዲድዬር ድሮግባ እና ከእነኤስዬን በኋላ በመላው አውሮፓ በሚገኙ ትልልቅ ክለቦች በመዘዋወር በከፍተኛ የዝውውር ሂሳብ እና ደሞዝ የሚቆጠር አፍሪካዊ ተጨዋች ከያያ ቱሬ በኋላ እንደማይኖር ይገለፃል፡፡
በስዊዘርላንድ ተቀማጭ የሆነው ሴንተር ፎር ስፖርት ስቲዲስ በ2014 እኤአ የዓለማችን 120 ውድ ተካፋይ ተጨዋቾች ዝርዝር ሠርቶ ነበር ፡፡ ዓለም አቀፉ ተቋም ዝርዝሩን ለማጠናቀር ከ2009 ጀምሮ እስከ 2014 የተፈፀሙ ከ1500 በላይ ዝውውሮችን ዳስሷል። በዚሁ ዝርዝር 4 አፍሪካውያን ብቻ መካተታቸው ተስተውሏል፡፡ በዓለም እግር ኳስ ምን ያህል እየተጎዱ እንደሆነና በዝውውር ገበያው በርካሽ እየተነገደባቸው መሆኑን ያመለክታል፡፡ የአራቱ አፍሪካውያን አጠቃላይ የዝውውር ሂሳብ ከ136 ሚሊዮን ዶላር በታች ነው፡፡ 45ኛ ላይ የሚገኘው ለማንችስተር ሲቲ የሚጫወተው ኮትዲቯሯዊው ያያ ቱሬ ለዝውውር በወጣበት 37.7 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ሌሎቹ ሁለት ኮትዲቯራዊያን ተጨዋቾች በጣልያኑ ኤስ ሮማ የሚገኘው ጀርቪንሆ እና በስዋንሴ ሲጫወት በ27.1 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ የነበረው ዊልፍሬድ ቦኒ ናቸው፡፡ አራተኛው ተጨዋች በጀርመኑ ባየር ሙኒክ የሚገኘው አልጄርያዊው መሃዲ ቤናት ለዝውውር በተከፈለበት 22.6 ሚሊዮን ዶላር በ87ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
አፍሪካውያን ተጨዋቾች በዓለም የእግር ኳስ በባርነት ከመጎሳቆላቸው፤ አነስተኛ ደሞዝ ተከፋይ ከመሆናቸው ባሻገር ከሜዳ ውጭ በሚያገኙት የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችም የተበደሉ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ያህል ኮትዲቯራዊውን ያያ ቱሬ  በሱ ደረጃ ካሉ ትልልቅ ፕሮፌሽናሎች በማስታወቂያ እና በስፖንሰርሺፕ ውሎች ዓመታዊ ገቢው ብናነፃፅር ገቢው በአምስት እጥፍ እንደሚበልጥ እንረዳለን፡፡ እነ ቱሬ በማስታወቂያ እና በስፖንሰርሺፕ ውሎች በዓመት በአማካይ እስከ 4.5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ሲኖራቸው ብዙዎቹ የአውሮፓ ተጨዋቾች ግን በአማካይ ከ15.1 ሚሊዮን ዶላር በላይ  የሚያገኙ ናቸው፡፡

Read 3477 times