Saturday, 14 February 2015 14:47

በፊደላችን ጉዳይ የመቋጫ ሃሳብ

Written by  ግፍታሔ ገኃተ
Rate this item
(3 votes)

   ባለፈው ሳምንት ባቀረብኩት ጽሑፍ፤ የፊደላችን እያንዳንዱ ሆህያት በጽንፈ - ዓለም ውስጥ ያላቸውን ሠፊ ውክልናና በተሰጧቸው የቁጥር ኮድ አማካኝነት በዚሁ ጽንፈ - ዓለም የተከናወኑ፣ እየተከናወኑ ያሉትንና ወደፊትም የሚከናወኑትን ኩነቶች የማወቂያ ስልቶች እንደሆኑ በዋናነት ለማመላከት ሞክሬአለሁ፡፡
ከዚህ አንፃር የግዕዝ ፊደላት ከማንነት ቅርስነታቸው ባሻገር የምስጢር ባሕር በመሆናቸው በወጉ ሳንመረምርና ሳናውቅ ፊደላቱ ይቀነሱ፣ ይሻሻሉ ወይም ይለወጡ ማለት ሀገርን፣ ትውልድና ታሪክን ሊጠቅም እንደማይችል ማሰብ ተገቢ እንደሆነ በድጋሚ ለመግለፅ እወዳለሁ፡፡ የፊደላችንን ጥንታዊነትና እንዲያውም ለሌሎች ቋንቋዎች ፊደላት መነሻ እንደሆነ ለማመን የሚያስችሉ የምርምር አቅጣጫዎችን መከተል እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ የግዕዝ ፊደል ተጠቃሚ ሆነን አማርኛ ቋንቋ ለመምረጥ የቻልንባቸውንም ምስጢራት አበክሮ ለማወቅ መጣጣር የጥንታዊ ማንነታችንን ለማረጋገጥ ጠቃሚ ነው፡፡
በአሁኑ ጊዜ በአፍሪካ የራሷን ፊደል ተጠቃሚ አገር ኢትዮጵያ ብቻ እንደሆነች ተደጋግሞ የሚነሳ ሌላው ነጥብ ነው፡፡ በእርግጥ በፊደልና ቋንቋ ማለትም በሰው ዘር ሥነ - ልሳን አጀማመር አኳያ ታሪኩ በማያዳላ ሁኔታ ከተጠናና ወደ ነባር ቦታው ከተመለሰ አፍሪካን  የሚቀድም እንደሌለ ሊሠመርበት የሚገባ እውነት ነው፡፡ በዚህም ሐቅ መሠረት ቢያንስ በሰሜን አፍሪካ የዛሬውን ግብፅ፣ ኑቢያ፣ ሞሪታኒያና የመሳሰሉት አካባቢ በተሠማሩትና ለረጅም ዘመናት በቆዩት የካም ዘሮች የተፈጠረው ዐረብኛ ፊደል አፍሪካዊነት ብዙም የሚያከራክር አይመስለኝም፡፡ በዚህ እሳቤ ከሄድን የግዕዝን ፊደል በአፍሪካ “ብቸኛ” ለማለት የሚሻክር ይመስለኛል፡፡ ከዚያም በላይ በሀገራችን ሰሜኑ ክፍል ጥንታዊ የነበረው “የሳባውያኑ ፊደል” ከምን ተነስቶ የት በመድረስ እንደተተካ ወይም እንደጠፋ ባለመታወቁ እንጂ አፍሪካ የሌላም ፊደል ባለቤት እንደሆነች መናገር የሚከብድ አልነበረም።
ስለሆነም የግዕዝ ፊደልን በአፍሪካ ብቸኛ እንደሆነ ለማረጋገጥ ተጨማሪ ጥናት እንደሚያስፈልግ ይሰማኛል፡፡ በዚህ ረገድ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፤ የአፍሪካን በተለይም የካም - ኩሽ ሥነ - ልሳናትን በሠፊው ማጥናቱ የሚታወቅ ሲሆን በርካታ የጥናት ጥራዞቹ ወዴት እንዳሉ አፈላልጐ ለህትመት እንዲበቁ ወይም ለሌሎች ምርምር አመቺ በሆነ መንገድ እንዲገኙ የጉዳዩ ባለድርሻዎች በፍጥነት ሊተጉ ይገባል፡፡
በፊደላችን ጉዳይ አስተያየት ያቀረቡ ብዙ ጸሐፍት፤ በተለይ በአሁኑ ጊዜ እጅግ ያሳሰባቸው የፊደላቱ በተናጠልም፣ የሆህያቱ የአጻጻፍ ስህተቶች ያለቅጥ እየተበራከቱ የመምጣታቸው  ሁኔታ ነው፡፡ ይህን ጉዳይ አቅልሎ የማየቱ አካሄድ በበኩሌ እጅግ አሳዛኝና ይቅርታ የሌለው ጥፋት መሆኑን በአንክሮ ማስረገጥ እፈልጋለሁ፡፡ ጉዳዩ “ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ፣ ባለዕዳ አይቀበለውም” እንዲሉ፣ በፊደላቱ ሳይሆን በራስ ማንነት ላይ በደል መፈፀም ማለት ነው፡፡ “በኪነጽሕፈት ጊዜ የፊደላት አቀማመጥ ወይም ኪነጥበብ ሥነ ጥበብ ዘጠነኛ” በሚል መጽሐፍ (ገጽ መ) “…በከተማው ስዘዋወር በዋና ዋና መንገዶችና ሱቆች የተዘረጉ ጋዜጣ፣ መጽሔትና መጽሐፍ በያሉበት የሀገራዊ ፊደል የአጻጻፍ ስልታቸውን ስመለከት ፊደላቱ ድምጻቸው በማይገለጽበት ያለ ቦታቸው እየተደነቀሩ፣ በደማቅ ቀለማትና ፎቶግራፍ ብቻ ደምቀው የሚንፀባረቁ ናቸው፡፡ ማንም ላያውቅልኝ እንደዚህ በመሳሰሉ ሁሉ ስከፋና ሳዝን ውዬ እመለሳለሁ፡፡” ሲሉ ይትባረክ ገሠሠ  ምሬታቸውን በጽኑ ይገልጻሉ፡፡ እኚህ ተቆርቋሪ በአዲስ አበባ ከተማ ሲዘዋወሩ ያዩአቸውን ተነባቢ ጽሑፎች እያመላከቱን ነው፡፡ በፖስተር፣ በድርጅትና የንግድ ስሞች፣ በባነርና በየአደባባዮቹ ታላላቅ መልዕክት እንዲያስተላልፉ የተተከሉና የቆሙ የማስታወቂያ ሰሌዳዎች ሁሉ የሚጽፏቸው ቃላት ፊደሎቻቸው መልዕክቱን በትክክል የማያስተላልፉ እየሆኑና አንዳንዶቹም አሰዳቢዎች መሆናቸው በርክቷል፡፡
ዛሬ በምንቸገረኝነት ወይም የማይረባ ከንቱ አስተሳሰብ ለማራመድ ተብሎ በቸልታ የሚሠራና የሚተላለፍ ጉዳይ ውሎ አድሮ ወይም በረጅም ዘመን ሂደት ዋጋ ያስከፍላል፡፡ መጪው ትውልድ የሥራችንን ብላሽነት በተረዳበት ቅጽበትም ታሪካችንን ይፍቀዋል፡፡ በመሆኑም ፊደሎቹ በትክክል ስለመጻፋቸው ማረጋገጥ የሁሉም ዜጎች ኃላፊነት ነው፡፡
የፊደል ሐብት ከታደሉ ጥቂት ሀገራት ውስጥ ለዚህ ታላቅ ቅርስ ሐውልት ወይም መታሰቢያ ያላቆመች ኢትዮጵያ ብቻ ነች፡፡ ይህም ቢሆን ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ በየአቅጣጫው የሚነሱና ታሪክና ትውልድ ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ ጉድለቶች በሚመለከታቸው አካላት የማይታረሙ ከሆነና የጠቋሚዎቹ ፋይዳ “እንደ ቁራ ጩኸት” እየታየ ከታለፈ፣ ጤነኛ የዕድገት ሂደት ለመከተል እንደማይመች ከወዲሁ መገንዘብ ብልህነት ነው፡፡ የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፤ የአገራችንን የቋንቋ ፖሊሲ ይፋ ለማድረግ እንደተዘጋጀ ተሰምቷል፡፡ የፊደሉ ቅርስነትና ሀብትነት ከህገመንግስታዊ ክብርና ጥበቃው ጋር በፖሊሲው ውስጥ እንደሚካተት ተስፋ አለኝ፡፡ የኪነ ጥበብ ዘርፉ በተለይም በድርሰት ዙሪያ የተደራጁ ማህበራት በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አማካኝነት በሚሰጡት ሀሳብ መሰረት ፊደላችን ቋሚ መታሰቢያ ሊቆምለት እንደሚገባ በአጽንኦት መግለጽ ይገባኛል፡፡ ጉዳዩን ሰፋ አድርገን ካየን በአሁኑ ጊዜ ፊደላችንም ሆነ የግዕዝ ቋንቋ የህዝብ ባለቤትነት ደረጃ አግኝተው የመጠናት፣ የማደግና የመስፋፋት ዕድላቸው በከፍተኛ ደረጃ ሊታሰብበት የሚገባ አቢይ ተግባር ነው፡፡ ምክንያቱም የዕውቀትና የጥበብ፣ የታሪክና የማንነት አውድን በመከተል፣ በራሳችንም ኮርተን የቻልነውን ሁሉ ብናደርግ ፍሬውን ሳይዘገይ ልናይና በሥራችንም ታላቅነት ልንኮራ እንችላለን፡፡
የራስን ጉዳይ በማጉላት፣ የጎደለውንም በምርምር በማሟላት በትጋት መሥራት ያለበት በሁሉም የባህልና የታሪክ ዘርፎች ሲሆን በተለይም የትምህርት ጎራው ይህንኑ አቢይ ጉዳይ ያማከለ ቢሆን ሁኔታዎች የሚስተካከሉበት ሂደት የሚፋጠን ይመስለኛል፡፡ ክቡር ዶ/ር ሐዲስ ዓለማየሁ /ደራሲ/ በዚህ ረገድ እጅግ ታግለው እንደነበር ይታወቃል፡፡ በተለይ የትምህርቱን ዘርፍ ከታችኛው እርከን እስከ ከፍተኛው ድረስ ሀገራዊ በሆነው ማህበራዊና ባህላዊ መደላደል ላይ መመስረት እንዳለበት በጽሑፍም ሆነ በቃላቸው ሲታገሉ እንዳለፉ ብዙዎች ይመሰክሩላቸዋል፡፡ በቋንቋ በኩልም የሚሰጠው ትምህርት፣ የግዕዝ ስነ ጽሑፍን ጭምር እንዲያካትት ሐዲስ አለማየሁና ሌሎችም ሳይታክቱ አሳስበዋል፡፡ አሁንም ተስፋ የሚጣለው በተለይ በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ እየተደረገ ባለው የኃላፊነት እንቅስቃሴ ነው፡፡ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲም የግዕዝ ቋንቋና ሥነ--ጽሑፍ ጉዳይ እየታሰበበት እንደሆነ ፍንጮች ታይተዋል፡፡ በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የክቡር ዶ/ር ሐዲስ አለማየሁን የባህል ማዕከልን በመመስረት በየዓመቱ በፊደልና በቋንቋዎቻችን ዙሪያ ግዕዝንም ጭምር በርካታ የምርምር ወረቀቶች (ጥናቶች) እየቀረቡ ይገኛሉ፡፡ ይህ ጥረትና ትጋት እየተጠናከረ ከሄደ ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በሂደት የጥንታዊ ቋንቋዎቻችን ጥናት ማዕከል ወይም አካዳሚ ለመመሥረት እንደሚችል ብሩህ ተስፋ ይታያል፡፡ ይህ ደግሞ ከቆረሰው አጉርሶ፣ ከለበሰው አልብሶና የአብነት ት/ቤቶችን፣ ገዳማትና አድባራትን በመንከባከብ፣ የግዕዝ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ ከነሙሉ ክብሩ እስከዛሬ እንዲዘልቅ ጥረቱን ሲያስተባብር ለቆየው ለጎጃም ህዝብ ትልቅ እውቅናና ልግስና ነው፡፡ ይገባዋልም፡፡ በዚያን ጊዜ የግዕዝ ሁለንተናዊ ታሪክና ሀብትነት በሚገባ ታውቆ በማያወላውል ሁኔታ ህዝብ የባለቤትነቱን ኃላፊነት ይረከባል፡፡ መንግስትም የበኩሉን ድርሻ ይወጣል የሚል እምነት ማሳደር ይቻላል፡፡
እዚህ ላይ አስረስ የኔሰውን ጠቅሼ ጽሑፌን ላብቃ፡፡ “የካም መታሰቢያ” የተሰኘውን የምርምር መጽሐፋቸውን ያቀረቡበትን ምክንያት ሲገልፁ፤ “… በእውነተኛ መንገድ እርግጠኛውን ታሪክ ለሚፈልጉ ነው እንጂ እንዲሁ እንደ ገደል ማሚቶ የሰማውን ሁሉ እየተቀበለ አብሮ ለሚጮኸው ማለቴ አይደለም፡፡ ለግብዞች አልጻፍኩም፡፡ እኔ ልጽፍ ያሰብኩና የተነሳሁ በእርግጥ ስለ ቅዱሳት መጻሕፍት ምስጢርና ዘመን ምርመራ ለሚደክሙ ሰዎች መሆኑን አስቀድሜ ላንባቢዎች አመለክታለሁ፡፡”  የዘመኑ አንባቢዎችም በዚሁ አኳያ ልብ እንዲሉ አሳስባለሁ፡፡ መልካም ጊዜ!!


Read 1479 times