Saturday, 14 February 2015 14:56

በሥነ ምግባር ያልተመራ ቢዝነስ መጨረሻው ውድቀት ነው

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(2 votes)

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ም/ቤት ለአገሪቷና ለቢዝነስ ሰዎች ከፍተኛ ጥቅም እንደሚሰጥ የታመነበትን “የኢትዮጵያ ቢዝነስ ተቋማት ሞዴል የሥነ ምግባር መመሪያ” ለመጀመሪያ ጊዜ አዘጋጅቶ አስመረቀ፡፡
ባለፈው ሳምንት በሒልተን ሆቴል በፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ የተመረቀው የሥነ ምግባር መመሪያ፣ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋ በንግድና አገልግሎት፣ እንዲሁም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተዘጋጀ ሲሆን የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት እንደየሥራቸው ባህርይ በመተርጐም ሥራ ላይ የሚያውሉት እንደሆነ ታውቋል፡፡
አንድ የንግድ ድርጅት ከሠራተኞቹ፣ ከደንበኞቹ፣ ከባለአክሲዮኖቹ፣ በሥራው አጋጣሚ ከሚገናኛቸው ተቋማት፣ ከመንግሥትና ከሌሎች ባለድርሻ አባላት ጋር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ሊኖረው የሚገባው ግንኙነት ሕጋዊ መሠረት ያለውና በሥነ ምግባር መርህ የተደገፈ ሊሆን እንደሚገባ የጠቀሱት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ፤ ማንኛውም የንግድ እንቅስቃሴ በዚህ መልክ ታስቦበትና ታቅዶበት ካልተሠራ በስተቀር ለተወሰነ ጊዜ አትራፊ መስሎ ቢታይም መጨረሻው ግን ውድቀት ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም ብለዋል፡፡
የኢኮኖሚው አንቀሳቃሽ ሞተር፤ የግሉ ኢኮኖሚ ዘርፍ በአግባቡ እንዲሠራና ውጤታማ እንዲሆን መንግሥት የሚሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ዶ/ር ሙላቱ፣ የንግዱ ዘርፍ አባላትም በግልፅነት፣ ተጠያቂነትና ተአማኒነት እንዲሁም በማኅበራዊ ኃላፊነት ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ፅኑ ፍላጐት እንዳለው ገልፀዋል፡፡
ማንኛውም ሙያ የራሱ ሥነ ምግባር አለው፡፡ በተለይም የቢዝነስ ዘርፍ በርካታ ፍላጐቶችና ስሜቶች የሚንፀባረቁበት በመሆኑ የቢዝነስ ሥነ ምግባር ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ይመለከታል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ የሥነ ምግባር መመሪያው መዘጋጀቱ በራሱ አንድ ትልቅ ሥራ ሆኖ በመመሪያው ውስጥ የተጠቀሱ ቁምነገሮችን እያንዳንዱ የንግድ ተቋም ተቀብሎ በተግባር ቢተረጉማቸው ሀገራዊ ፋይዳቸው እጅግ ትልቅ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከዓለም አቀፍ ገበያ ጋር ትስስር እየፈጠረ ስለሆነ በንግዱ ማኅበረሰብ የሚተገበር የቢዝነስ ሥነ ምግባር ማዘጋጀት እንዳስፈለገ የጠቀሱት የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ም/ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን አፈወርቅ፤ የሥነ ምግባር መመሪያው በራሱ የሚተማመን ማኅበረሰብ እንዲፈጠር ከማስቻሉም በላይ ሙስናን እንዲፀየፍና እንዲዋጋው ስለሚያግዘው በሥነ ምግባር የታነፀ የንግድ አሠራር እንዲፈጠር ጉልበት ይሆነዋል ብለዋል፡፡
የቢዝነስ ተቋማት ሞዴል የሥነ ምግባር መመሪያው ሁለት ዓላማ ይዞ ነው የተዘጋጀው፡፡ የአገራችን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ከዓለም ኢኮኖሚ ጋር እየተወዳጀና እየተቆራኘ ስለሆነ ሰፊ ጥያቄና ከፍተኛ ዕድልም ይዞ እየመጣ ነው ያሉት የንግድ ም/ቤቱ ም/ዋና ጸሐፊ አቶ እንዳልካቸው ስሜ፣ የዓለም ኢኮኖሚ በከፍተኛ ጥንቃቄና ሥነ ምግባር የሚንቀሳቀስ ስለሆነ ጥያቄውን በትክክል መመለስ ከቻልን ተጠቃሚ እንሆናለን ብዋል፡፡
“ንግድና ኢንቨስትመንት ለማኅበረሰቡና ለአካባቢው ተጠያቂነት ከሌለው ዘላቂነት የለውም፡፡ ማኅበረሰቡ ገበያው ሲሆን አካባቢው ደግሞ የምርቱ ግብአት መገኛ የተፈጥሮ ስጦታ ነው፡፡ ለቢዝነስ ቀጣይነት፣ ከእነዚህ ክፍሎች ጋር ኃላፊነት የተሞላበት ግንኙነት ከሌለ ለወደፊት ችግር ይፈጥራል” ብለዋል፡፡ ዓለምአቀፍ ቢዝነስ በዚህ መንገድ የተቆራኘ ነው፡፡ በአገራችን የግሉ ዘርፍ ከዕድሜው ለጋነትና ከኢኮኖሚው ኋላቀርነት የተነሳ ብዙ የሥነ ምግባር ግድፈቶች እየታዩ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ቀለል ባሉ ነገሮች ላይ የሚታዩት የዋጋ መናር፣ የጥናት ጉድለት፣… በኢኮኖሚው ውስጥ ከፍተኛ ችግር መኖሩን ያሳያል፡፡ ኢኮኖሚው ማደግ ካለበት፣ ለማኅበረሰቡና ለአካባቢ ያለንን ኃላፊነት ከወዲሁ እየገነባን መሄድ አለብን ብለዋል፡፡ የሥነ ምግባር መመሪያውን ማዘጋጀት ያስፈለገበት ሌላው ምክንያት ለደንበኞቻችንና ለአካባቢያችን ተጠያቂ የምንሆንበት መንገድ መገንባት ስላለብን ነው፡፡ ምክንያቱም ደንበኞቻችንና አካባቢያችን፣ ለቀጣይ ቢዝነሳችን መሠረቶች ስለሆኑና ንግድ ም/ቤቱ በእነዚህ ነጥቦች ላይ በሚገባ መሠራት እንዳለበት ስላመነ የተለያዩ አገራት ልምድና ተመክሮ ተመርምሮ፣ ሦስትና አራት ጊዜ በተደረጉ ወርክሾፖች ግብአት ዳብሮ፣ ሌሎች የቢዝነስ ተቋማት ከዚህ ውስጥ እየተወሰዱ ለየተቋማቸው የሚመጥን የሥነ ምግባር መመሪያ እንዲያወጡ የተዘጋጀ ሞዴል መመሪያ ነው በማለት አብራርተዋል፡፡
እያንዳንዱ ድርጅት፣ ፋብሪካም ሆነ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ከዚህ ከዋናው ሞዴል ጋር በማጣጣም የራሱን እንቅስቃሴ በሚመጥን መልኩ ተግባራዊ የሚያደርግበት ቀጣይ ሥራ ይኖራል፡፡ ይህን መመሪያ ተግባራዊ ያደረጉ ተቋማት በአገር አቀፍ ደረጃ እውቅና እንዲያገኙ በቀጣይነት እየተሰራ ነው ያሉት አቶ እንዳልካቸው፤ ይህን የሥነ ምግባር መመሪያ ተግባራዊ ያለማድረግ የሚያስከትለውን አደጋም ሲገልፁ፣ በውጭ አገራት ባደገ ኢኮኖሚ ውስጥ ተሰማርተው የሚሰሩ የውጭ ኢንቨስተሮችና ነጋዴዎች ቢዝነስ በሚሰሩባቸው አገራት የለመዱት አሰራር አለ፡፡ በእነዚያ አገሮች ህግና ስርዓት ያለው ሞራላዊ እንቅስቃሴ የተለመደ ነው፡፡ እዚህ መጥተው ለመስራት ያንን የለመዱትን የስነ ምግባር መመሪያ ይጠይቃሉ፡፡ የውጭ ኢንቨስተሮች ጥሬ ዕቃ ሲገዙ፣ ምርት ሲያዘዋውሩ፣ ሲሸጡ፣ ከመንግስትና ከተለያየ አቅጣጫ ጋር በሚያደርጉት ግንኙነት ሁሉ፣ የስነ ምግባር መመሪያ የስራቸው ማቀላጠፊያ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በስነ ምግባር መመሪያ የታነፁ አቅራቢ ይፈልጋሉ፡፡ የተበላሸ ጥሬ እቃ የሚያቀርቡላቸው፣ በዋጋ የሚያጭበረብሯቸው ፣ … በሂደት እየጠፉ ይሄዳሉ፡፡ እነዚህ የውጭ ኢንቨስተሮች ግብር እየከፈሉ፣ ሌሎች ግብር የማይከፍሉ የንግድ ሰዎች በገበያው ውስጥ ጤናማ ያልሆነ ግንኙነት እንዳይፈጥሩ ይረዳቸዋል፡፡ እዚህ አገር ኢንቨስት ያደረጉ ባለሀብቶች ኃላፊነት በጎደለው መንገድ የተመረተ ምርት ውጭ አገር ሲላክ እንደማይሸጥላቸው ያውቃሉ፡፡ ለምሳሌ የህፃናት የጉልበት ብዝበዛ፣ የአካባቢ ብክለት… ባለበት ሁኔታ የተዘጋጀ አበባም ሆነ ጨርቃ ጨርቅ፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች የአመራረት ስርዓት በሌለው መንገድ ሲመረት በዓለም አቀፍ ገበያ እንደማይሸጥላቸው ያውቃሉ፡፡ ስለዚህ ይዘው የመጡትን ገበያ አስተማማኝ በሆነ መሰረት ላይ ለማስቀመጥ የሥነ ምግባር መመሪያውን ይፈልጉታል ማለት ነው በማለት አብራርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የአገራችን የቢዝነስ ሰዎች የስነ ምግባር መመሪያ ካልተከተሉ ከውጭ አገር ባለሀብቶች ጋር በሽርክና ለመስራትና ለመወዳደር አይችሉም፡፡ ያለ ስነምግባር መመሪያ መስራት ትርፉ ውድቀት፣ በመመሪያ መስራት ለራስ ብልጽግና ለአገር ዕድገት ጠቃሚ መሆኑን ብዙ የቢዝነስ ሰዎች ስለተረዱና በአገር አቀፍ ደረጃ እውቅና ስለሚሰጣቸው መመሪያውን ተግባራዊ ለማድረግ ችግር እንደማይገጥማቸው የንግድ ም/ቤቱ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡

Read 2143 times