Saturday, 14 February 2015 15:42

“ብሌን” መጽሄት ከ15 ዓመት በኋላ ለንባብ በቃች

Written by 
Rate this item
(2 votes)

የጥናት ጽሁፎችን አደባባይ ለማውጣት ትኩረት ተሰጥቷል

 የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር ከተቋቋመ ከ30 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በነሐሴ ወር 1982 ዓ.ም ለንባብ የበቃችው “ብሌን” የሥነፅሁፍ መፅሔት ፤ ከ15 ዓመት የህትመት መቋረጥ በኋላ ሰሞኑን ታትማ ዳግም ለአንባብያን ቀረበች፡፡
የደራስያን ማህበር 50ኛ ዓመት ክብረበዓልን ምክንያት በማድረግ በሰኔ 2003 ዓ.ም የ“ብሌን” መፅሔት ልዩ ዕትም (ቁ.7) ለንባብ መብቃቱ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ መደበኛው የመፅሄቷ ዕትም ለዓመታት ሳይታተም ቀርቷል፡፡ ከማህበሩ የ30 ዓመት ጉዞ በኋላ መጽሄቷ ብቅ ስትል ለኢትዮጵያ ሥነፅሁፍ ዕድገት እንደ አንድ ብስራት ቆጥረን ነበር ያሉት የአሁኗ የ“ብሌን” ዕትም አርታኢዎች፤ መፅሔቷ “ቅፅ 1፣ ቁጥር 1” መባሏ ቢያንስ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ዕትም በየዓመቱ ይታተማል የሚል ተስፋን የሚያመላክት ቢሆንም በማህበሩ የ24 ዓመት ታሪክ ውስጥ ከ7 የበለጠ የ“ብሌን” እትም ሊታተም አልቻለም ብለዋል፡፡
ለመፅሄቷ መቋረጥ ተጠያቂው ሁላችንም ነን በማለትም አርታኢዎቹ ኋላፊነቱን ለሁሉም አከፋፍለዋል፡፡ “… በመጀመሪያ ደረጃ የኢደማን አመራር ይዘው የነበሩትን ሁሉ የሚመለከት ቢሆንም የችግሩ አድማስ ግን ሁላችንንም የሚያካትትና ሁላችንንም በተለያየ የኃላፊነት ደረጃ የሚያስጠይቅ ነው፡፡” ሲሉም አስረድተዋል፡፡
አዲሱ የደራስያን ማህበር ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙሴ ያዕቆብ መፅሄቷ ላይ ባሰፈሩት መልዕክት፤ የጠንካራ ተሳታፊዎች እጦት፣ የህትመት በጀትና የደጋፊ ወገን እጥረት መፅሄቷ ወቅቷን ጠብቃ እንዳትወጣ ዋነኛ ተግዳሮቶቿ እንደነበሩ ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ የመፅሔቷ ዕትም ትኩረት የተደረገው በምርምር አምባው ተወስነው የነበሩ የጥናት ውጤቶችን ወደ “ብሌን” መድረክ በማምጣት አደባባይ ማውጣት ላይ ሲሆን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከተደረጉ ጥናቶች ውስጥ ሶስቱ (የስንቅነሽ አጣለ፣ የቴዎድሮስ ገብሬና የአራጌ ይመር) ተመርጠው እንደቀረቡ ተገልጿል፡፡
“የዚህ ዓይነቱ ሙከራ ወደፊት ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ብሌን በምርምርና በፈጠራ፣ በሂስና በንድፈ ሃሳብ መካከል ድልድይ ሆና እንድታገለግል ምኞታችን ነው” ብለዋል፤ አርታኢዎቹ፡፡
በ108 ገፆች የተቀነበበችው “ብሌን” መፅሄት፤ ከጥናትና ምርምር ፅሁፎች በተጨማሪ አጭር ልቦለድና ግጥሞችን ያካተተች ሲሆን በ50 ብር ለገበያ ቀርባለች፡፡ መፅሄቷ በዓመት ሁለት ጊዜ እየታተመች ለአንባቢያን እንደምትደርስም ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 2988 times