Saturday, 14 February 2015 15:50

በ2015 የአፍሪካ ክለቦች ውድድር ጊዮርጊስና ደደቢት ይሳተፋሉ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

በ2015 የአፍሪካ ክለቦች ውድድሮች ኢትዮጵያን የሚወክሉት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት የቅድመ ማጣርያ ተሳትፏቸውን ከሜዳቸው ውጭ በሚደርጓቸው ጨዋታዎች ይጀምራሉ፡፡ ከ2 ሳምንት በኋላ  የሁለቱም ክለቦች የመልስ ጨዋታዎች የሚደረጉት በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በክልል በሚገኘው የባህርዳር  ስታድዬም ይሆናል፡፡
ለ19ኛ ጊዜ በሚካሄደው የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ  የሚሳተፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ በቅድመ ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታው ከሜዳው ውጭ የሚገናኘው ከአልጄርያው ክለብ ኤኤምሲ ኤል ኦልማ ጋር ነው፡፡ በ1936 እኤአ የተመሰረተው የአልጄርያው ክለብ ኤል ኦልማ 25ሺ ተመልካች በሚያስተናግደው ስታድ ሜቮውድ ዙጋር የሚጫወት ይሆናል፡፡
ኤል ኦልማ በፈረንሳዊው ጁሊዬስ ስኮርሲ የሚሰለጥን ሲሆን በአፍሪካ ደረጃ ብዙ ልምድ የሌለው እና በ2008 የአልጄርያ ሊግ ሻምፒዮን የነበረ ነው፡፡በስፍራው የሚገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ የህዝብ ግንኙነት ክፍል እንደገለፀው በጨዋታው ላይ ቁጥራቸው በዛ ያሉ ወጣቶች እና ለአፍሪካ ሻምፒየንስ ሊግ እንግዳ የሆኑ ተጨዋቾች ለመጀመርያ ጊዜ የመሳተፍ እድል ማግኘታቸው አንድ ትልቅ እርምጃ ሆኗል፡፡ እነሱም  ሰልሃዲን ባርጌቾ፤አንዳርጋቸው ይላቅ፤ዘካርያስ ቱጂ፤ መሀሪ መና፤ዳዋ ሁጤሳን ናቸው፡፡ ከቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኤኤምሲ ኤል ኦልማ በደርሶ መልስ ጨዋታዎች የሚያሸንፈው በመጀመርያ ዙር ማጣርያ ሊገናኝ የሚችለው በቅድመ ማጣርያ የደርሶ መልስ ጨዋታ ከሴራልዮኑ ኢስት ኤንድ ላዮንስ ወይንም ከጋናው አሻንቲ ኮቶኮ አሸናፊ ነው፡፡
በሌላ በኩል ደደቢት  ለ12ኛ ጊዜ በሚካሄደው የአፍሪካ ክለቦች ኮንፌደሬሽን ካፕ ይሳተፋል፡፡ በቅድመ ማጣርያው የመጀመርያ ጨዋታ ዛሬ የሚገናኘው ከሲሸልሱ ክለብ ኮቴ ዴ ኦር ጋር ይሆናል፡፡ የሲሸልሱ ክለብ ኮቴ ዴ ኦር 2 ሺ ተመልካች የሚያስተናግድ ስታድዬም ያለው ሲሆን በ2014 በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ብቸኛውን የተሳትፎ ልምድ አስመዝግቧል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን በላከው መግለጫ ወደ ሲሺየልስ ካመራው የደደቢት እግር ኳስ ክለብ 29 የልኡካን ቡድን አባላት መካካል በቪዛ ምክንያት አራት የውጭ ሃገር ተጨዋቾች ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡  የሲሺየልስ ኢሚግሬሽን ባላስልጣን እ.አ.አ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ስራ ላይ ያዋለውንና በምእራብ አፍሪካ ሃገሮች ዜጎች ላይ ተፈጻሚ እንዲሆን የተደረገው ጥብቅ የጉዞ መመሪያ ባለመከበሩ ምክንያት ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ የተገደዱት የክለቡ ተጨዋቾች ሱሊማና አቡ፣ሞሃመድ አዳሙ፣ሳሙኤል ሳኑሚ እና ጋብርኤልአህመድ ሹኢብ ናቸው፡፡ ከደደቢት እና ከኮት ዴኦር  የደርሶ መልስ ጨዋታዎችን የሚያሸንፈው በመጀመርያ ዙር የኮንፌደሬሽን ካፕ ማጣርያ ከቡርኪናፋሶው አርሲ ቦቦ እና ከናይጄርያው ዋሪ ዎልቭስ አሸናፊ ጋር የሚገናኝ ይሆናል፡፡

Read 1446 times