Saturday, 21 February 2015 13:09

አስራ አራት ጊዜ ምናብና ተመስጦ የደቀንለት መጽሐፍ

Written by  አብደላ ዕዝራ
Rate this item
(3 votes)

“ኩርቢት” ሲነበብ

    ድንቅና ኮስታራ ልቦለዶች ከሚጽፉ ጥቂት ደራስያን አንዱ ዓለማየሁ ገላጋይ ነው። “አጥብያ”፥ “ቅበላ” እና “የብርሃን ፈለጐች”  አያሌ ተደራሲያንን ቢያስደምሙም የሚመጥናቸው ሒሳዊ ንባብ ግን እንደ ተነፈጉ ናቸው። (ኧረ ለመሆኑ ከዘመነኛ -contemporary- ልቦለድ ደራሲያን የማን የፈጠራ ውጤት ለአጥጋቢ ባይሆንም፥ ለበቂ ሒሳዊ ጥናት የተጋለጠው? ያሰኛል።) በየሁለት ሳምንት ፍቃዱ አባይ ይመራውና ያስተባብረው የነበረ የሜይ ደይ መጽሐፍ ግምገማ በሩን መዝጋቱ ለሆነ የሒስ ቦግታ ንፍገትም ነው።
የአስራ አራት አጫጭር ልቦለዶች ስብስብ “ኩርቢት” በታተመበት ወቅት በኤፍ ኤም ሬድዮ ጣቢያዎች በቅብብሎሽ ቢነበብም ጥንካሬና ድክመቱን ጠቋሚ ሒስ የዳሰሰው አይመስለኝም። የመጽሐፉ ርዕስና የሽፋኑ ገፅ ምስል አንዳች የሚደብት፥ አዲስ አንባቢን የማያጓጓ መሆኑም ያብሰከስካል። አመዛኝ ገጾቹ እንደ ዝርግ ግጥም -prose poem- በዘይቤ በተኳሉ፥ ስሜትና እሳቦት በረቀቀባቸው ተናፋቂ መስመሮች ተወረዋል። የድርጊትና ግጭት እንቅስቃሴ መወሳሰብ ጥቂት ገፀባህሪያትን አይረሴ አድርጐ ለመቅረፅ አግዘውታል። በሁለት ገጽ ከጠበበው -ግን ያልተኮማተረ- “ዝግመተ ለውጥ” እስከ ሀያ ሰባት ገጾች በተፍታታው “ኩርቢት” ትረካ  ለአስራ አራት ርዕሶች አንባቢ ምናብና ተመስጦ ለግቷል። ዓለማየሁ ገላጋይ ለመጻሕፍቱ ርዕስና ሽፋን የእንዳለጌታ ከበደ ያክል ምነው በተጠበበበት ያሰኛል። ኩርቢት ማለት “ጋያ፥ ሲጋራ ማጨሻ” ስለሆነ እንደ ተምሣሌት -መጽሐፉን ካነበብን በኋላ - አንድምታዎች ይቀፈቅፋል እንጂ እንደ ሌጣ ርዕስ ስብስቡን አይመጥነውም።
“መጽሐፍ በሽፋኑ አይመዘንም” ቢባልም ሜዳ ላይ ወይም ከመደርደሪያ ሲሰጡ አንባቢን የሚማጠኑ ማራኪ ጥበባዊ ርዕስና ምስል ተድበስብሰው ከመዘለል ይተርፋሉ። ሽፋኑ ሲጠቃቅሰን ደባብሰነው ወደ ጀርባው ጽሑፍ -blurb- እናመራለን፤ ይዘቱን ገረፍ ገረፍ ለማድረግ ገፅ እናገላብጥ ይሆናል። የአንድ ሁለት ደቂቃ ትኩረት ከምናልባት -potential- መጽሐፍ ገዢ መንጠቅ በቂ ነው። ወሳኝ መለኪያ ግን የፈጠራ አቅሙ በጥሞና ለመነበብ የሚመስጠን ከሆነ ነው። እኔ በግሌ የሽፋኑ ጥበባዊ ውበት -ምትሀትም ይሆናል- ከወሰደኝ እያየሁት በሀሳብ ለመሰወር ብቻ እንኳን እገዘዋለሁ። ሰሞኑን ለርዕሱ ተናዳፊነትና ለምስሉ ጥልቀት የከፈልኩበት መጽሐፍ የደራሲው ስም ባይገለጥም፥ ርዕሱ “መጽሓፈ ቆንጥጥ” ሲሆን ምስሉን ለናንተ ማስረዳት ያዳግተኛል፤ ምናልባት ደራሲው ከነቢይ መኮንን የተዋሳቸው ስንኞች ይገልጡት ይሆናል። “ዋናው ማርጀት መቻል/ ከልጅነት ፍቅር፥ ካብሮ አደግ ህሊና፤/ ይበቃል ቀለሙ፥ ይበቃሃል ህልምህ፥ የአእምሮህ ወዘና።” [“የራስክን እሳት ሙቅ” ከሚለው የተቀነጨበ] ሽፋንም ጀርባም ሰንኮፍ ሳይሆኑ ከእምብርቱም ይመዘዛሉ። “ኩርቢት” ከተነበበ በኋላ ባዶና ገለልተኛ ሆነን አንቀጥልም። የተመሰቃቀለ የኑሮ ልምድና ገጠመኝ እውስጣችን ሰርገው ደከምከም ይለናል፤ አንድ ህይወት ሳይሆን በንባብ ተጨማሪ ስለተቋደስን ልቦናችን አይለዝብም። አሜሪካዊ ገጣሚ Joseph Brodsky እንዳለው፤“There are worse crimes than burning books. One of them is not-reading.” (መጽሐፍን በእሳት ከማጋየት የከፋ ወንጀል አለ፤ መጽሐፍ አለማንበባችን፥ ሳይገላለጥ ችላ መባሉ) (ከወንጀሎቹ አንዱ ነው።)
ደራሲው ለትረካው የመለመላቸው ገፀባህሪያት በአመዛኙ በሰከነ፥ በተደላደለ ህይወት አውድ ውስጥ ጊዜን እየላሱ እያሾፉ፣ እንቅልፍ የሚፈትጋቸው አይደሉም። እየተንሳፈፉ ሳይሆን፥ የእለት ጉርስን ፍለጋ በሆነ ጉዳይ ለመለብለብ ኑሮ እየጠለዛቸው፣ “እህታ” እውስጣቸው ተከማችቶ፥ መንገላታትን የተላመዱ ናቸው፤ ስቀው፥ ፎክረው፥ ተፈነካክተው፥ ተፋቅረው ... የተረፋቸውን ዕድሜ በመጠጥም ይሁን በጉስቁልና የሚልጉ ናቸው። ከኖሩትና ከቀሰሙት የኅላዌ ውጥንቅጥ ብዛት የአንድ ግለሰብ መሞት፥ የአያሌ ህይወቶች መክሰም ያክል ህልፈቱ ጥልቅ ነው። እንደ ባለፀጋ ነጠላ ልሙጥ ነፍስ ሳትሆን የታሹ ዥንጉርጉር ነፍሳት ከአንድ አካል ተወሽቀው አፈር ይበላቸዋል። አስራ ሶስት አጭር ልቦለዶቹን ለክፍል ሁለት ንባብ በማቆየት ዛሬ ትኩረቴ ወደ novella - ከአጭር የሰፋ፥ ከአብይ ያነሰ- መጠነኛ ልቦለድ ለመሆን ያደላውን፥ በሃያ ሰባት ገጾች ተደራሲን የሚያስደምም፣ ለስብስቡ ርዕስ የተሾመውን “ኩርቢት” ይሆናል።
ተራኪዋ የአስራ ሁለተኛ ፈተና ውጤት የምትጠብቅ፥ አስራ ስምንት አመት ሊሞላት የተቃረበች ኰረዳ ናት። ከህፃንነቷ ጀምሮ እቤታቸው ተከራይቶ ከነበረ ሠዓሊ -ብሩኬ የምትለው- ጋር የዕድሜዋን ትዝታ እያፍተለተለች፣ እውስጧ እየተብላላ አፍቅራው ድምፁ ጭምር ያነዝራታል።
... ከደቂቃ በፊት ደወለልኝ
“ጣዎሴ” አለኝ። ለምን እንዲህ ብሎ እንደሚጠራኝ ስጠይቀው፥ “የምታምር ወፍ ነሽ” ይለኛል።
“እ?” አልኩት
“የምናውቃቸው ደህና ናቸው?”
የምናውቃቸው ጀንበሯ፥ ዛፎቹ፥ የቀበና ወንዝና አሞራው ናቸው።
“ደህና” አልኩት።
ብሩኬ ስለአራቱ ሲያወራ ስለልጆቹ የተጨነቀ አባት ይመስላል።  [ገፅ 45-46]
ጣዎስ መዝገበ ቃላት ሲፈታው “ኦፈ ገነት፥ ጅራቱ የሚብለጨለጭ፥ አንገቱና ራሱ ሰማያዊ መልክ ያለው ተለቅ ያለና እጅግ የሚያምር ወፍ።” ይለዋል። የተራኪዋ ስም ቤተልሄም -መንፈሳዊ አንድምታ ቢቋጠርም- በጣዎሴ ተነጠቀ፤ ብሩክ ሠዓሊ በመሆኑ የግሉ ዕይታ እየመራው በተፈጥሮና በሰው ይመሰጣል። በዚህ የስልክ ጥሪ የተጀመረ ትረካ፣ ኮረዳዋ -ጣዎሴ- ከልጅነቷ ያጐነቀለውን እድሜዋን በብሩክ እንቅስቃሴ፥ ድርጊትና ንግግር እየመነዘረች ትተርካለች። በማግስቱ ደውሎ “ካንቺ ጋር ማውራት ያለብኝ ነገር አለ። ድብብቁ ቢበቃን ጥሩ ነው” ሲላት ከቀጠራት ካፌ እስክትደርስ ውስጧ ይታመሳል። ይህ በሃያ ሰባት ገጾች የተወሳሰበው ትረካ፣ በዛሬና በማግስቱ ሁለት የስልክ ጥሪዎች መካከል -መቼቱ- የኮረዳዋ የአመታት ትዝታና ኑሮ በምልሰትም በአስተውሎትም ተጥዶባታል። በሃያ አራት ሰአት ውስጥ የተቀነበበ እንቅስቃሴ አያሌ ሰበዞች ከትናንቶች ተመዘውበት የአምስት ገፀባህሪያት ህይወት የኖርነው ያክል ይኮሰኩሰናል።
ቀበና ተወልዳ የቦረቀች ኮረዳ እድገቷ በስዕል ቀለም፥ በብሩሽና በተወጠረ ሽራ እንዲሁም በብሩክ ዘይቤያዊ ገለጣዎች ስለተቦካ አካባቢዋንና ገጠመኞቿን ስትተርክ በገለልተኛ ቋንቋ ሳይሆን ግጥምን በሚያደናግዙ አረፍተ ነገሮች ናቸው። ዓለማየሁ ገላጋይ በተራኪዋ አንደበት የሰዓሊን ርዕዮት የሚያጐላ የረቀቀ ቅኔያዊ ቋንቋ ለማጥለል መካኑ ያስደምማል። ሠዓሊ ጥሩነህ  እሸቱ ወይም ገጣሚ-ሠዓሊ አገኘሁ አዳነ ይህን ልቦለድ አንብበውት፥ እንዴት ቃላት ቀለምና ንድፍ አፍልቀው ከምናባችን ሥዕል ሊወጥሩ መብቃታቸውን በተረጐሙልን ያሰኛል። ሁለቱን የጠቀስኳቸው ለሥዕልና ሥነጽሑፍ ጥምረት አስተውሎታቸው ጥልቅ መሆኑን ስለማውቅ ነው።
“ወቅቱ ክረምት ነበር። እናቴ በሯ ላይ በበርጩማ ተቀምጣለች። በረንዳው ላይ ስጫወት ቆይቼ ወደ ጓሮ ስዞር ብሩኬ የተወጠረ ሸራውን ማስደገፊያ የክፍሉ በር ላይ ገባ አድርጐ አቁሞት አየሁ። ትርጉም አልባ መስመሮች እየሞነጫጨረ ራቅ ቀረብ ይላል።
ራቅ ሲል የጣሪያው ጠፈጠፍ ጀርባው ላይ እየነጠረ የፈንዲሻ ቅርፅ ይሰራል። መስመሮቹ እንደ ወጨፎ ከቀኝ ወደ ግራ በሰያፍ የሚዘንቡ ነበሩ። መስመሮቹን ከማድመቅ ይልቅ ዳር ዳሩን ቱቢት በመሰለ ቀለም ሲያጀበጅብ መቆየቱ ትዕግሥት አስቆራጭ ቢሆንብኝም መከታተሌን ቀጠልኩ። ዳር ዳሩን የሚያንጃብበው ቀለም ለካስ ትርጉም ኖሮታል። ትንሽ አሎሎ ትልቅ አሎሎ ላይ የተቀመጠ መስሎ እየደመቀ የመጣው የሸራው መካከለኛ ክፍል በጥቂት መነካካት በተፈጠሩ መስመሮች ቁጭ ያለች ሴት ናት።
ገረመኝ። በመነካካቱ ቀጥሏል። ጥቂት መስመሮች ሲጨመሩበት ያቺ ቁጭ ያለች ሴት እናቴን መስላ አረፈችው። እጁን ትቼ የብሩኬን ፊት ለማየት ተመቻቸሁ። አንዴም ወደ እናቴ አይመለከትም። እእምሮው ውስጥ ከትቷት ጨርሷል። ከዛ እያወጣ ነበር የሚስላት።
እናቴንና ስዕሉን እያስተያየሁ በመደነቄ ቀጠልኩ። [ገፅ 60]
ሥዕሉ ቀርቶ፥ በቅኔ መመሰጥ የሚቀናው ደራሲ፥ ገጣሚና ሐያሲ ደረጀ በላይነህ የ“ኩርቢት”ን ዝርግ ግጥሞች በተፈተነባቸው ያስመኛል። በአዲሱ “ብሌን” መጽሔት -ቅጽ 8- ረዳት ፕሮፌሰር ቴዎድሮስ ገብሬ [ገፅ 21]፤ “የሥዕልንና የሥነ ጽሑፍን ዝምድና በሌላ ጊዜ ራሱን በቻለ መጣጥፍ የምመለስበት ይመስለኛል” ባለው መሰረት “ኩርቢት”ን  እንዳማይዘነጋ ተስፋ አለኝ። ዘመነኛ የአማርኛ ደራሲያን --አዳም ረታ፥ ዓለማየሁ ገላጋይ፥ በዕውቀቱ ሥዩም ወዘተ-- በፈጠራ ውጤታቸው የልቦለድ እና የግጥምን ዘውጐች በማዋሀድ የተረኩም የተቀኙም ያክል ያስገርሙናል። በ“ኩርቢት” ትረካ እንኳን ብንወሰን ነፃ ግጥም -free verse- እና ዝርግ ግጥም -prose poem- ነቅሰን ማውጣት አያዳግትም። በልቦለዱ ትልምና ድርጊት ተቀዝፈን ስለምንሰምጥ እንጂ ተረጋግተን አንቀጾቹን እንደ ግጥም ብናጤናቸው፥ እንደ ስንኝ ከደረድራናቸው እንፈዛለን።
ዕድሜዋን በመንቀራፈፍ የምታራዝመውን ጀንበር
በትካዜ አያለሁ፥
እንዳማሩ መሞት የዘወትር ዕጣዋ መሆኑ፥
ይሄንን ሀዘን የሚያባብስ ህብረ ዜማ
ከወንዙ ከዛፉና ከነፋሱ ይንቆረቆራሉ።
የራሷ የሆነ ዘለሰኛነት አለው
አልቅሽ አልቅሽ አለኝ። [ገፅ 48]
እንዲህ ስንኞች ቁልቁል ቢጻፉ ነፃ ግጥም እንጂ ምን ሊባል? በውስጠ ምት -rhythm- የራሰው፥ ቤት ባለመድፋቱ እንደ ጥብቅ ግጥም አይሁን እንጂ ነፃ ግጥም ነው። ሰለሞን ደሬሳ --በዘበተ እልፊቱ-- “ስሜትና ቋንቋ ሲቸግርም ሃሳብና ቋንቋ የሚቋለፍበት አደራደር” ወለሎ ግጥም ነው እንዳለው አይነት።
ጀንበሯን የሚያያት እንደደረሰች ኮረዳ
........................
ቁልቁል የተደፋ የወርቅ ዝጉዳ መስላለች፥
የወጨጫ ተራራ እንደ ወለላ
ደርበብ ብሎ የሚወርደውን
ዝልግልግ ብርሃን፥
አፉን ከፍቶ ወደ ሆዱ ይልካል።
ከጩልሌው መንድፍደፍ ጋር
የዛፍ ፍሬዎች
የወርቅ እንባ እየመሰሉ


ፉ።
[ገፅ 47 ተመልሶ 46]
ብርሃኑ ገበየሁ ይህን ዘውግ በጥሞና አስረጅ እየጠቀሰ አጥንቶታል። [የአማርኛ ሥነግጥም፥ ገፅ 251-260] “... ገጣሚያን ቀንበር ከሆነባቸው ጥቂት የምጣኔ ህግጋትና የተወሰነ የቤት አመታት ስልቶች በመላቀቅ እምብዛም ለነባር ህጐች የማይገዛ፥ ገጣሚው የግሉን ምናብና ፈጠራ እንዲለማመድ እድል የሚሰጥ የግጥም ዘልማድ ... free verse (ነፃ ስንኝ) በመባል ይታወቃል።” ብሏል። ልቦለድ ውስጥ፥ በዐረፍተ ነገር ታግደው የታፈኑ ግጥሞች በንቁ አእምሮ ብንዳስሳቸው ውበታቸው በየገፁ ምናባችንን ያወረዙታል። የትረካውን አውታር ያድሱታል። ወደ አንቀፅነት ሲመለሱ የትረካውን ፍጥነት በማርገብ በመቼቱ እንድንጠልቅ እና ወጣቷ -ጣዎሴ- እንዴትና ለምን በሠዓሊ ብሩክ ፍቅር በዝግታ ተነድፋ፣ ታሪኩ ሲፈፀም የተከሰተውን ሌላ ሀቅ እስኪጐመዝዛት መሸሿን እናጤንላታለን እንጂ ግጥማዊ ዜማና ውስጣዊ ምት ብቻ ሆነው አይመክኑም። ዝርግ ግጥም -prose poem- እንደ አረፍተ ነገር ከጥግ እስከ ጥግ የሚወጠር ግን ዕምቅ፥ ዘይቤያዊና ውስጠ-ምቱ መሳጭ ነው። ዓለማየሁ ገላጋይ በዚህም ምናባችንን ይወርሰዋል።
”እናቴ... እዚህ አያቶቼ ግቢ ውስጥ የኖረችው በመንፈስ ህልውና ነው ማለት እችላለሁ። ስትሄድ ኮቴዋ አይሰማም። ለዚህ ዓለም ሙቀትና ቅዝቃዜ ምንም አይነት ምላሽ ስትሰጥ አይታይም። አትስቅም፥ አታለቅስም። ሆዷ ተከፍቶ ስትበላና ስትጠጣ አጋጥሞኝ አያውቅም። ... የትኛውንም በደል እንደ ስፖንጅ መጥጦ የሚያስቀር ፊት ነበራት። መከፋትን ብቻ ሳይሆን መደሰትንም ፊቷ አስርጐ ያስቀር ነበር። ... አንድ ጠዋት ከቤት ወጥታ ጠፋች፤ ድምጿ ሳይሰማ ሰባት አመት ሆኗታል።
አንዳንድ ቀን በህልሜ ጥቂት ጥሬ በነጠላዋ ላይ ቋጥራ ጭው ባለ በረሃ ላይ ስትጓዝ አያታለሁ። መንፈስ ቅልቅል አካሄዷ አልተለወጠም። በሚንቀለቀለው በበረሃ ግልብልባት እየተንቀጠቀጠች እስክትጠፋ አያታለሁ።
 [ገፅ፥ 53/54/55]
ይህ ዝርግ ግጥም ዜማና ዘይቤ ብቻ ሳይሆን፥ ዕምቅነቱ ውስጣዊ ሰቆቃዋን ተጫጭና የምትስለመለም ነፍስ መግለጥ መቻሉ ነው። የተራኪዋ እናት -ስም የለሽ- እንደ ሰው ሳይሆን እንደ ተለጣፊ ጥላ -silhouette- ለመታወስ እንኳን ከሌላ ፍጡር የተረፈ ብርሃን ያስፈልጋታል። በሥዕልም በዕውንም ደራሲው እውስጧ የዘቀጠውን ሰቆቃ፥ በዝምታዋ የምታፍነው ሀዘን በተራኪዋ አንደበት ገለጠው እንጂ ውጫዊ ቁመናዋ አይታየንም። በጨለማ የምታደባ የሴት ቅርፅ ተክቶታል፤ መልኳ በሥነልቦናዊ መዘዟ ተደናገዘ። ልጇ የአራት አመት እድሜ እያላት ነበር ባሏ በመኪና አደጋ የሞተው። ብሩክ ስለ እናቷ በደል ሲያስረዳት ነው ጣዎሴ አይነጥላዋ የተገፈፈው።
“ለጐጆዋ እንዳለፋች፥ ለትዳሯ እንዳልማሰነች በስተመጨረሻ ሆዷን በጥወራ የምታሸንፍ፥ ፊት አይቶ ነዋሪ ተደረገች። የቁም እስረኛ ... አባትሽ ሁሉንም ሀብት በእናቱ ስም አድርጐ ነበር። ሲቀር ቀረ። ባዶ እጅና ልጅ። ላንቺ ስትል ስድስት ዓመት በነፃ ተገዛች።”  
ጤና፥ ጉልበት፥ ምናልባትም ውበት ሳያንሳት አባወራ በህይወት ሳለ ቤቱን ሲበድል ምን አኮማተራት? የብቸኛ ልጁ እናት ሆና እምነቱን ለምን ነፈጋት? ከሞተ ጀምሮ ያለኮሽታ፥ ተጠቅልሎ እንደ ተዘነጋ አልባሌ ጨርቅ ለህይወቷ ጣዕምና ትርጓሜ ሳትፍነከነክ ለምን በዝምታ ተሻረች? ዩፍታሄ ንጉሴ የተቀኘለት ዝምታ አይደለም። “ሲመታኝ ዝም ብል፥ ዝም ያልኩ መስሎታል / ሲታሰብ ነው እንጂ፥ ዝም ማለት የታል”  ልቡናዋን ያነተበ ዝምታ ነበር። እርግጥ ለልጇ የተጨነቀች ይመስላል። ለአመታት መንፈሷ ከተሰባበረ በኋላ ለመጥፋት ስትወስን ልጇን ታስመርጣታለች፤ ከእሷ ወይም ከአያቷ ለመኖር።
“ቤቲ” አለችኝ
“እ” አልኳት ጨዋታዬን ሳላቋርጥ
“ከእኔና ከእማማ ከማን ጋር ብትሆኚ ይሻልሻል?”
“ከሁለታችሁም ጋር” በግዴለሽነት
“አንዳችንን ምረጪ ብትባይስ?” ...
“እማማ ጋ”
እንደ ቀልድ የተፈተለከች ይቺ ቃል እንደ ጥይት ለዘልአለም የመለያያ ጦስ ትሆናለች ብዬ አልገመትኩም ነበር። አንድ ቀንም ሳትስቅ፥ ሳታለቅስ እንደ መንፈስ ግቢያችን ውስጥ ከወድያ ወዲህ ማለቷን ቀጠለች...
አንድ ጠዋት ከቤት ወጥታ ጠፋች፤ ድምጿ ሳይሰማ ሰባት አመት ሆኗታል። [ገፅ፥ 55-56]
ደራሲው ማንነቷን እውስጧ ቀበረው። ቅድመ ጋብቻ የነበራት ህይወት፥ ዛሬም ከሥጋ ዘመዶቿ ተገልላ መሸሸጓ፥ ይህ በብቸኝነት ተገፈታትራ ከአንድ ጥግ የመቆዘም ትዕግስት መነሻው ምንድነው? ገጿ እንደ ተሟጠጠ፣ እንደ ደረቀ ስለኖረች፣ ብሩክ የሳላት ወቅት ልጇ -ጣዎሴ- ምስሉን አይታ ደንግጣለች።
ሴቲቱ ቁርጥ እናቴን። ብቻ የስዕሏ እናቴ እያለቀሰች ነበር።
ሳይታወቀኝ “እንዴ?” ስል አንባረቅሁ።
ብሩኬ “ምነው?” እንደማለት ዞሮ አየኝ።
“ውሸት!” አልኩ
“ምኑ?”
“እናቴ አታለቅስም”
ብሩኬ ... ለራሱ የሚመስል ቃል ተናገረ። “ለቅሶዋን ልጅ አያየውም”
... ሮጨ ወደ ትልቁ ቤት ገብቼ እማማን ጠየቅኩ።
“እማማ እማማ ልጅ የማያየው ልቅሶ አለ?”
“ምን ትላለች ይቺ፥ ኋላ ልጅ የሚያየው ለቅሶ ነው ያለው?
ቀብር ጨዋታ መሰላት?” ... ወደ ጓዳ ገቡ።  [ገፅ 61]
በአያትና በተራኪዋ መካከል የተከሰተው አለመግባባት እንባ በ“ለቅሶ” መተካት የለኮሰው አንድምታ እስከ ቀብር በመፍሰሱ ነበር። ደራሲው የተራኪዋን እናት የህይወት ታሪክ በዝምታ ስለሸበበው ግቢ ውስጥ መኖሯ ከተንቀሳቃሽ ሬሳ ያልተለየ በመሆኑ ተምሳሌቱ ያንሰራራል። ሥዕል ሸራ ላይ ሲፀነስ፥ የተፈጥሮ ምትሀት ያለስስት ሲገለጥ የገፀባህሪያቱ ዳራና ታሪክ መኮማተር ለምን አስፈለገ? ተራኪዋ ሁሉን አወቅ ሳትሆን በቅርቧ ያለውን እንቅስቃሴ ብቻ ስለሚገለጥላት፥ ካልተነገራት በስተቀር የሌላውን ገመና የማወቅ አቅም ተንፍጓታል። ቢሆንም የብሩክን ገፅታ -ስለአፈቀረችውም ይሆናል- መግለጥ ከቻለች እራሷን፥ እናቷን ፥ አያቷን ... የገፃቸውን ውበት ይሁን አስቀያሚነት ማንፀር ለምን ተሳናት? ደራሲው ስለአልፈቀደ እንጂ ሌላ ምክንያት አይኖርም። ከአሁን እድሜዋ ጀምራ ወደ ኋላ  ወደ ፊት እየተመላለሰች ስትተርክ፣ የእድገቷን ሥነልቦናዊ ደረጃ በመጠበቅ ስለሆነ ደራሲው ተዋጥቶለታል። ድንቅና ተራ ደራሲን ከሚነጥላቸው ክህሎት አንዱ የልቦለድን ድርጊት የማጠንፈፍ ችሎታ ነው። ተራው ይተረትራል፤ ሁሉንም ይዘረግፋል። ብስሉ ይመርጣል፤ ከማንዛዛት ይልቅ ለጥቆማ ያደላል። ፈጠራውን መቼት ውስጥ ለማንቀሳቀስ ወሳኝ ሁነቶች፥ ግጭት፥ ምልልስ ... ይመርጣል። በ“ኩርቢት” ዓለማየሁ ገላጋይ ለመግለጥ የሚያዳግት ጥቃቅን ሁነቶች ሳይፈታተኑት፥ የገፀባህሪያቱን ህይወት -- በተለይም የተራኪዋ እናት እና ብሩክ ከግቢው ውጭ -- አልተከተላቸውም። ሁሉን አወቅ ተራኪ አለመጠቀሙ በኮረዳዋ ዕጣ ፈንታ እንድንደመም፥ ሌሎች ብርሃን ሳይሻሟት ከአእምሯችን እንድታደራ ስለወሰነ ከሆነ ሰምሮለታል።
አንዲት ሴት መበደሏን እንጠረጥራለን እንጂ እንደ መንፈስ -ghost- ለመኖር ደፍጥጦ ያጐበጣት ሀይል፥ ወኔና ተስፋ የሰለባትን ምክንያት ማወቅ ተስኖናል። የባሏ መሞትና ባዶ እጇን መቅረቷ ከመንፈራገጥ፥ አዲስ ህይወት ከመጀመርና በራሷና በሌሎች ጉዳይ ከመሞገት አያግዱዋትም። ልክ በስብስቡ ሌላ አጭር ልቦለድ የተቀረፁት የቦኖ እናት፤ ድህነት ሳይሰብራቸው ለእለት ጉርስ መነፈግ ሳይሰጉ ከሃብታም ጐረቤት ጋር ይላተማሉ።
“እታለማሁ መሃን በመሆናቸውና ለሰፈርተኛው የቦኖ ውኃ በማስቀዳታቸው ነው `የቦኖ እናት` የሚል ቅጥል ስም የወጣላቸው። እታለማሁ በቅጽል ስማቸው አይከፉም። እንዲያውም አንዳንዴ `እኔ የቦኖ እናት` እያሉ በራሳቸው ያሾፋሉ። ”የተራኪዋ እናት እጦት ወይም ልጄን ማን ያሳድጋታል የመሰለ ስጋት ሳይሆን ሌላ ጥልቅ ድብቅ ምክንያት ይኖራታል፤ ሰው የሚያደርጋትን ባህሪያት አወላልቃ የሰው ጥላ ለመሆን ያበቃት -dehumanized-። ሰባት አመት ከፍቅርና ወሲባዊ ፍላጐት ተገልላ በዝምታ መታፈኗም በደል ነው። የጣዎሴ ወንድ አያት የቤት አዛዥነት ስልጣናቸውን በባለቤታቸው ተቀምተዋል።
“እንደማንኛውም የአውሬ ማህበር በሰው ልጆችም ዘንድ እናት ልጆቿ እስኪያድጉ በልምምጥ ትኖርና ሲደርሱላት የበላይነቷን ትቆናጠጣለች” የትንባሆአቸውን ኩርቢት ከመማግ በስተቀር በስተእርጅና ምንም አልተረፋቸውም፤ ተሸንፈዋል። ደራሲው ሴት ስትበደል ብቻ ሳይሆን ወንድም ሲገፈተር ቀረፃቸው።
ተራኪዋ በሠዓሊ ብርኩ የልጅነት ትዝታዋ፥ በቡሩሹና ንግግሩ ውበትን ጥበብን ለማጣጣም መብቃቷ፥ ቀስ በቀስ በጥልቅ አፍላ ፍቅር እንድትወረር አደረጋት። ስልክ ደውሎ “ካንቺ ጋር ማውራት ያለብኝ ነገር አለ። ድብብቁ ቢበቃን ጥሩ ነው”  ሲላት ፍቅሩን የሚገልጥላት መስሏት ተቅበጠበጠች፥ በኑሮ ለመፍካት አለመች። ሰአቱ ደርሶ ተገናኙ፤ የደካከመው ቢመስልም አዲስ ወደ ተከራየው ቤት ይወስዳታል። እናቷን በጠፋች በአመቱ አፈላልጐ ከእሷ ጋር ትዳር መስርቶ ሁለት ልጆች ወልዷል።
ለጥቂት ደቂቃ የማደርገው ጠፋኝ። ...
”እህትና ወንድምሽ ናቸው”
ወደ እናቴ ዞሬ አየኋት። ስር ስር ይስለከለክ የነበረ እንባዋ መንጭቶ በአፍላ ግፊት እየተንዶለዶለ ነበር። አንዳች ነገር ውስጤ ከተሸሸገበት እየፈካና እየጐላ ሲመጣ ይታወቀኝ ነበር።
ትዝታዬን ተዘረፍኩ፥ ጀንበሬን ተዘረፍኩ፥ ልጅነቴን ተዘረፍኩ፥ ፍ-ፍ-ፍቅሬን ተዘረፍኩ። ...
ባዶ ሆኛለሁ። የብሩኬ ድምፅ ከውስጤ ገመገም ጋር እየተጋጨ ያስተጋባል። ገደል ለገድል ይሽሎከሎካል። ማልቀስ ተሳነኝ፤ ማልቀስ ተጐዳህ የማለት ቅብጠት ነው። ከእንግዲህ እንዳላለቅስ አውቃለሁ። መሣቅም ተደሰትኩ የማለት ቅብጠት ነው። ከእንግዲህ እንዳልስቅ አውቃለሁ። አያቴ ሲሞት የእርሱን ኩርቢት እወርሳለሁ።
    [ገፅ 71]
እንደ ሀቅ ካሳደጉት ቅዠት --ያውም የፍቅር ጥልቀት የዋጠው-- ድንገት መባነን ያጥበረብራል። Milan Kundira ስለ ጥሬነት ወይም የልምድ ማነስ -inexperience- አንድ ልቦለዱን ሲያጤን የተናገረው ጣዎሴን ይገልጣታል። ... inexperience (is) a quality of the human condition. We are born one time only, we can never start a new life equipped with the experience we have gained from a previous one. We leave childhood without knowing what youth is, ... even when we enter old age, we do not know what it is we are heading for. The old are innocent childern of their old age. [The Art of the Novel]. ጥሬነት የሰው ባህሪ ነው። አንድ ጊዜ ብቻ ስለምንወለድ ካለፈ የህይወታችን ልምድ እውስጣችን ያደረ ስንቅ ስለሌለን ልጅነት፥ ወጣትነት ብሎም እርጅናን መኖር የምንጀምረው ለእያንዳንዱ የዕድሜ ኩራባ የዋህ ሆነን ነው። ሌላው በቅድሚያ ቢነግረን እንኳን እስከ አልተዘፈዘፍንበት ድረስ ያደፈጠ ጥሬነት ጉድ ያደርገናል። ለዚህም ነው ጣዎሴ የተሰወረችው እናት መገኘት፥ የሁለት ህፃናት እህት መሆኗን መገንዘብ፥ እነዚህ ጣፋጭና ህይወት-አዳሽ ሁነቶች አልካሱዋትም፤ በደስታ አዲስ ህይወት መበርገድ ሲገባት በመደናገር ዋዠቀች። ከልቧ ለአመታት የተላወሰውን የ`ብሩኬን` ፍቅር መነጠቅ ለጋ ዕድሜዋና ውስን ገጠመኟ የማይቋቋሙት የግልብጥ እውነታ ሆነ። ለወንድ አያቷ ሽንፈት ተምሣሌት የሆነውን ኩርቢት በመውረስ፥ የቀራትን ዕድሜ እንደ ትንባሆ እየማገች ተስፋዋን በጢስ ለማባከን ወሰነች። ደግነቱ ወጣትነት ተደፍጥጦ የሚቀር ሳይሆን ዳግም የመነቃቃት -resilience- ቁልፍ ባህርዩ ነውና ታንሰራራለች። ዓለማየሁ ገላጋይ አብይ ልቦለዱን “የብርሃን ፈለጐች” ሲቋጭ ዋናው ገፀባህሪ ከሞጆ አዲስ አበባ ሲመለስ “ንፁህ” የሚላትን ጣዎሴን ፍለጋ ቀበና ድረስ መቅበዝበዙን ጦቅሞናል። ሁለቱን ሌላ ጠነን ያለ ልቦለድ የመሰለ ኑሮ መረቡን ዘርግቶ ሊያጠምዳቸው አድብቷል። ለ“ኩርቢት” ስብስብ የተሾመው አጭር ልቦለድ አዟዙረው ቢመሰጡበት ያስደምማል። ሂሳዊ ዳሰሳ የማይፈታቸው አስራ ሶስት ርዕሶች ከምናብና ጥሞና ለመላወስ አድፍጠዋል፤ በክፍል ሁለት ይነበባሉ።

Read 2988 times