Saturday, 21 February 2015 13:58

ማርያኖ ባሬቶ በእቅዶቻችን እንስራ ይላሉ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(3 votes)

ፖርቱጋላዊው ማሪያኖ ባሬቶ፤ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት በአገሪቱ የእግር ኳስ ታሪክ ከፍተኛው ደሞዝ የሚከፈላቸው ናቸው፡፡ በየወሩ ፌዴሬሽኑ ለአሰልጣኙ 18 ሺ ዶላር የተጣራ ደሞዝ ይከፍላቸዋል። በቅጥራቸው ወቅት የኢትዮጵያን ብሄራዊ ቡድን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፎካካሪነት እንዲኖረው የማብቃት  ሃላፊነት ተሰጥቷቸዋል። በህንዷ ግዛት ጎዋ ውስጥ በምትገኘው ሪባንዳር የተወለዱት ማርያኖ ባሬቶ አሁን 58ኛ ዓመታቸውን ይዘዋል፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት  አቦላ ከተባለና በፖርቹጊዝ ቋንቋ በድረገፅ ከሚሰራጭ ማጋዚን ጋር ቃለምልልስ ነበራቸው፡፡  የፖርቹጋል ስደተኞች በሚል መሪ ርእስ  አቦላ በሰራው ቃለምልልስ  በኢትዮጵያ ታላቅነት እና ምቹነት ቢማረኩም ማርያኖ ባሬቶ ፖርቱጋልን አልረሷትም ይላል፡፡ በቃለምልልሳቸው ኢትዮጵያውያን ስለፖርቱጋል አድናቆት እንዳላቸውና ባንድ ወቅት ስለነበረው የሁለቱ አገራት ታሪካዊ ግንኙነት መረዳታቸው እንዳስገረማቸው ሲናገሩ። ‹‹ ኢትዮጵያውያን ኩሩ ህዝቦች ናቸው፡፡ በቅኝ ባለመያዛቸው የሉዓላዊነት ክብር ይሰማቸዋል። ፖርቱጋል በኢትዮጵያ የነፃነት ታሪክ የነበራትን አስተዋፅኦ በማስታወስም ለውለታችን ያመሰግናሉ።›› ብለዋል፡፡ አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና የሆነች፤ በትልልቅ ሆቴሎች የደመቀች እና በግዙፍ የህንፃ ግንባታዎች እድገት ላይ ያለች ዘመናዊ ከተማ መሆኗን በቃለምልልሳቸው ያወጉት ማርያኖ ባሬቶ፤ ኢትዮጵያ በአዲስ አበባ የማትወሰን ብዙ ታሪክ እና ቅርሶች የሚጎበኙባት የቱሪዝም መስህብ እንደሆነችም ገልፀዋል፡፡ በማርያኖ ባሬቶ የሚመራው የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን በነገው እለት በድሬዳዋ ስታድዬም ከሱዳን አቻው ጋር ለኦል አፍሪካን ጌምስ ለማለፍ ወሳኝ ጨዋታ ያደርጋል። ባሬቶ ጨዋታውን ምክንያት በማድረግ ስለ ወጣት ቡድኑ፤ በኢትዮጵያ እግር ኳስ እንቅስቃሴ ስለታዘቧቸው አንዳንድ ሁኔታዎች እና ስለዋናው ብሄራዊ ቡድን ከስፖርት አድማስ የሚከተለውን ቃለምልልስ አድርገዋል፡፡

     በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት የሰሩባቸውን ወራት እንዴት ይገመግማሉ?
ምንም የተለወጠ ነገር የለም፡፡ ሃላፊነቱን ስረከብ ያቀረብኳቸው የስራ እቅዶች እንደነበሩ ታስታውሳለህ። በእነዚህ እቅዶች ተግባራዊነት ላይ ብዙ  አልተሰራም። ምናልባት የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ  ወደ አፈፃፀም ለመግባት የተለያዩ ጥናቶች እያደረገ ሊሆን ይችላል፡፡ የስራ እቅዶቹ  በሶስት የእግር ኳስ እድገት አቅጣጫዎች ላይ ያተኮሩ ነበሩ፡፡ በወጣቶች እግር ኳስ እድገት ላይ መሰረታዊ የሆኑ ስራዎች ማከናወን የመጀመርያ ነው፡፡ የስፖርት መሰረተልማቶችን እንዲጠናከሩ ማገዝ ሌላኛው ነው፡፡ ሶስተኛው ደግሞ የእግር ኳስ አሰልጣኞችን የብቃት ደረጃ ለማሳደግ ድጋፍ ማድረግ ናቸው፡፡  በመሰረተልማቱ  ዙርያ ዋናው ሃላፊነቱ የመንግስትና የፌደሬሽኑ ነው፡፡  እንደ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነቴ የምጠብቀው በመላው አገሪቱ ስፖርቱን ለማሰልጠን፤ ለማወዳደር እና ለማዘውተር የሚያስፈልጉ መሰረተ ልማቶች መስፋፋታቸውን ነው። በአገልግሎት አሰጣጣቸው ተግባራዊ መሆን ግን አለባቸው፡፡  በታዳጊ እና ወጣቶች እግር ኳስ እድገት ላይ ለመስራት የስፖርት መሰረተልማቶቹ አስፈላጊነት ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ የወደፊቱ የአገሪቱ እግር ኳስ ተስፋዎች በውድድር ፤ በስልጠና እና ስፖርቱን በማዘውተር በስፋት እንዲንቀሳቀሱ እድሎችን ይፈጥራሉ፡፡ ከመሰረተልማቱ ጎን ለጎን ግን ብቁ ስልጠና እና መነሳሳት የሚፈጥሩላቸው የእግር ኳስ ባለሙያዎች እና አሰልጣኞች ያስፈልጋሉ፡፡ ውድድሮችም መጠናከር ነበረባቸው፡ እነዚህን መሰረታዊ ተግባራት ለማከናወን በሚያስችሉ ሃሳቦች የበኩሌን ጥረቶች አድርጊያለሁ። በየክልሉ  በታዳጊ እና ወጣት ቡድኖች ውድድሮች እንዲጀመሩ የሞከርኩበትም ሁኔታ ነበር፡፡ ለምን ብትለኝ ውድድሮች ታዳጊዎችን በለጋ እድሜያቸው ፈልጎ ለመመልመል እና ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሳደግ ወሳኝ ናቸው፡፡ በተለያዩ ክልሎች የተለያዩ የታዳጊ ቡድኖችን ማደራጀትና በውድድሮች ማሳተፍ ይቻላል። ለምሳሌ በባህርዳር የሀ - 13፤ በትግራይ የሀ- 15፤ በጋምቤላ የሀ- 17 እንዲሁም በአዳማ የሀ- 19 ቡድኖችን የሚያሳትፉ ውድድሮች በአግባቡ በመምራት ማካሄድ ማለት ነው። በታዳጊዎች ደረጃ የሚከናወኑ ውድድሮች በጣም ጥቅም ይኖራቸዋል፡፡  ክለቦች የቡድኖቻቸውን ስብስብ ለማጠናከር እና ለማስፋት ውድድሮቹ ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራሉ፡፡
በወጣቶች የእግር ኳስ እድገት ላይ በነደፏቸው የስራ ሃሳቦች ተስፋ ሰጭ እንቅስቃሴዎች እየታዩ ናቸው?
ስራዬን በጀመርኩበት ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ክለቦች የወጣት እና ታዳጊ ቡድኖችን ትኩረት ሰጥተው በማዋቀር ብዙም እየሰሩ አልነበረም፡፡ ይህ ሁኔታም ክለቦች በቡድን ግንባታቸው መሰረታዊ ሂደቶችን በመከተል እድገት እንዳያሳዩ እንቅፋት ሆኖባቸው ቆይቷል፡፡ በብዙ ክለቦች ያሉ ተጨዋቾች እግር ኳስን ከ20 ዓመታቸው በኋላ መጀመራቸው  ወደ ፕሮፌሽናል ደረጃ የሚያድጉበትን እድል ያሳጥረዋል፡፡ በእርግጥ ባለፈው ብሄራዊ ቡድኑ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ የመጨረሻ ጨዋታዎቹን ሲያደርግ ያስገቧሃቸው ወጣት ተጨዋቾች የነበራቸው ብቃት ብዙ መነቃቃት ሊፈጥር ችሏል፡፡ ክለቦች በወጣቶች ላይ አተኩረው መስራት እንዲጀምሩ ያነሳሳበት ሁኔታ ነበር፡፡ እነዚያ ወጣት ተጨዋቾች አንዳርጋቸው፤ ናትናኤልና ዳዊት ነበሩ፡፡ ወደ ብሄራዊ ቡድን ስንቀላቅላቸው ከጅምሩ ብዙ ትችቶች ገጥመውናል፡፡ ወጣቶቹ ለብሄራዊ ቡድኑ በመሰለፍ ምርጥ ብቃታቸውን በማሳየታቸው ግን ሁኔታዎች ተቀይረዋል፡፡ ምክንያቱም ከዚያ በኋላ በተከታተልኳቸው ውድድሮች ክለቦች በየቡድኖቻቸው  የሚያሰልፏቸው ወጣት ተጨዋቾች ብዛት እንደጨመረ ስላስተዋልኩ ነው፡፡ በፊት በየክለቡ ከ23 ዓመት እድሜ በታች ያላቸው ተጨዋቾች ሁለት ወይም ሶስት ይሆኑ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን በትልልቅ ክለቦች ብዛታቸው ከ5 በላይ መሆን ጀምሯል፡፡ አሁን ለምሳሌ  በቅዱስ ጊዮርጊስ የቡድን ስብስብ ግማሹ እድሜያቸው ከ23 በታች  እንደሆነ መረጃው አለኝ፡፡ ብዙዎቹ ክለቦች አሰልጣኞቻቸው እና አስተዳደራቸው በወጣቶች መስራትን ማሳደጋቸው ለውጥ ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ያቀልለዋል፡፡ በእድሜያቸው የገፉ እና ልምድ ያላቸው ተጨዋቾች መጥፎ ናቸው ማለት አይደለም፡፡ ዋናው ነገር የብቃት እና የአቅም ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ በአጠቃላይ የኢትዮጵያን እግር ኳስ በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ እና የብሄራዊ ቡድኑን ዓለም አቀፍ ተፎካካሪነት ለማጠናከር  በወጣት እና ታዳጊዎች ላይ መስራት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡
የኢትዮጵያን እግር ኳስ ዓለም አቀፍ ተፎካካሪነት በተመለከተ ምን ታዝበዋል?
ባለፈው ሰሞን በታዘብኩት ነገር ላስረዳህ እችላለሁ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት በአፍሪካ የክለብ ውድድሮች የነበራቸውን ተሳትፎ ማለት ነው፡፡ ሁለቱ ክለቦች የቅድመ ማጣርያ ጨዋታዎችን ከሜዳቸው ውጭ ሲጀምሩ ያስመዘገቡት ውጤት ገና ብዙ ስራዎች እንደሚቀሩ ተረድቻለሁ፡፡ ደደቢት የሲሸልሱን ክለብ ከሜዳ ውጭ ማሸነፉ ጥሩ ውጤት ቢሆንም የእኔን  ትኩረት የሳበው እንዴት በደካማ እግር ኳስ ውስጥ ያለ የሲሸልስ ክለብ በኢትዮጵያ አቻው ላይ ሁለት ግቦች  እንዴት ያስቆጥራል የሚለው ጥያቄ ነበር። ቅዱስ ጊዮርጊስም ቢሆን በአልጄርያ ሊግ አምስተኛ ደረጃ ካለ ክለብ ጋር ተጫውቶ በአንድ ጎል መሸነፉ እንደ ጠባብ የውጤት ልዩነት ቢወሰድም፤ ብዙ ግቦችን እንዳያስተናግድ ኡጋንዳዊው ግብ ጠባቂ በከፍተኛ ብቃት መታደጉን ማስተዋሌ የሚያሳስቡኝ የፉክክር ደረጃዎች ገና መሆናቸውን ተረድቼበታለሁ፡፡ ብዙ የቤት ስራዎች ይቀሩናል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ በአፍሪካ ደረጃ በሚደረጉ የማጣርያ ውድድሮች ገና እየተንገታገተ ይመስለኛል፡፡ ያለው የተፎካካሪነት አቅም አሁንም ብዙ ክፍተቶች ይስተዋሉበታል፡፡ በተለይ ከምእራብ እና ሰሜን አፍሪካ ክለቦች እና ብሄራዊ ቡድኖች ጋር ያለው ተፎካካሪነት በጣም ሰፊ ልዩነት እንዳለ ያመለክታል። ልዩነቱን ለማጥበብ በስፋት ትኩረት ማስፈለጉን የምመክረው ለዚህ ነው፡፡ ሁኔታዎችን ለመቀየር ብዙ መስራት እና ብዙ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል፡፡ ከተግባራዊ እንቅስቃሴዎች ይልቅ ወሬ በማብዛት ምንም ሊፈጠር የሚችል  ለውጥ የለም፡፡
ከተደጋጋሚ ውይይቶችና ምክክሮች ባሻገር ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማስፈለጉን እያሳሰቡ ነው?
አዎ፡፡ ከእግር ኳሱ ባለድርሻ አካላት ጋር በተለያዩ ጊዜያት መሰራት ስላለባቸው ተግባራት ብዙ ውይይት አድርገናል፡፡ በስፋት ተመካክረናል። ተስማምተን ለመስራትም ከወሰንን ብዙ ቆይተናል። ብዙ አውርተናል የምለው ለዚህ ነው፡፡ ከተደረጉ ውይይቶች ጎንለጎን ተግባራዊ ስራዎች ካልተከናወኑ ግን ችግሮች ይፈጠራሉ።  እንኳን የእግር ኳስ አስተዳደሩ ይቅርና ከመገናኛ ብዙሃናትም ጋር መከናወን በሚገባቸው ተግባራት ዙርያ የጋራ መግባባት ቢኖረንም የእቅዶችን አፈፃፀም ተከታትለው ግፊት ሲፈጥሩ አልተመለከትኩም፡፡ ውሳኔዎች ተግባራዊ ካልሆኑ ለምን ምክክርና ውይይት በብዛት ይደረጋል፡፡ ለወሬ ብቻ መሆን የለበትም፡፡
እንግዲህ የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን ነገ ወሳኝ ጨዋታውን ከሱዳን አቻው ጋር በድሬዳዋ ስታድዬም የሚያደርግ ይሆናል፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ይህን ስታድዬም የመረጠው በካፍ በተደረገው ፍተሻ ሙሉ ብቃት አሟልቶ በመገኘቱ እንደሆነ ገልጿል፡፡ የባህርዳር ስታድዬም ከጨዋታው በፊት የመጨረሻ መስፈርቶችን ባለማጠናቀቁ ግጥሚያውን ሊያስታናግድ አልቻለምም ተብሏል፡፡ በአጠቃላይ ግን ከሜዳ በተያያዘ አንዳንድ ችግሮች ያሉ ይመስለኛል፡፡ ምን አስተያየት ይሰጡኛል?
በመጀመርያ  ወጣት ቡድኑ እጅግ በጣም ወሳኝ የማጣርያ ግጥሚያ እንዳለበት  ሁሉም ባለድርሻ አካላት ያውቁ ነበር፡፡ ቡድኑ በማጣርያ ጉዞው ውጤታማ ከሆነ በአገሪቱ ያለውን የእግር ኳስ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያነቃቃ አስቀድሞ መረዳት ያስፈልግ ነበር፡፡ ግን የጨዋታው ወቅት እየተቃረበ እስኪመጣ ድረስ ትኩረት ተሰጥቶ ብዙ እየተሰራ አልነበረም፡፡  ወጣት ብሄራዊ ቡድኑ የመጀመርያ የማጣርያ ግጥሚያውን ከማድረጉ በፊት በነበረው የዝግጅት መርሐ ግብር ውጣውረዶች ነበሩ፡፡ በቂ የልምምድ ሜዳ አልነበረውም፡፡ ግጥሚያውን ስለሚያስተናግድበት ስታድዬም እንኳን በወቅቱ መረጃ ሊያገኝ አልቻለም፡፡ ለአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ለሁለቱ የባህርዳርና የድሬዳዋ ስታድዬሞች የብቃት ማረጋገጫ እንዲሰጣቸው ጥያቄ የቀረበው በመጨረሻዎቹ ሳምንታት ነው፡፡ ስታድዬም ጠፍቶ አይመስለኝም፡፡ ስራን በአግባቡ ካለማከናወን የተፈጠረ ይመስለኛል፡፡ አሁን ባለፈው ሰሞን ለዩኒቨርስቲዎች የስፖርት ፌስቲቫል  በክብር እንግድነት ተጋብዤ ወደ አዳማ ተጉዤ ነበር፡፡ የአዳማ ዩኒቨርስቲን ስታድዬም ስመለከት በጣም ነው የተገረምኩት፡፡ ስታድዬሙ ካለው የጥራት ደረጃ አንፃር ለምን ከካፍ የብቃት ማረጋገጫ እንዳልተጠየቀበት ሳስብ ግራ ተጋብቻለሁ፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ የአዳማ ዩኒቨርስቲ ስታድዬምን ለወጣት ቡድኑ የካምፕ ልምምድ መስርያ እንዲሆንና  ውድድሮችን እንዲያስተናግድበት ጥረት ማድረግ ነበረበት፡፡ በእርግጥ ይህ የአሰልጣኝነት ሃላፊነት አይደለም፡፡ ማንኛውም አሰልጣኝ የስራ ሃሳቦችን ያቀርባል፡፡ የእግር ኳስ አመራር ደግሞ መሰል ሁኔታዎችን በትኩረት በመስራት ለዋና አሰልጣኙ ተግባራት ምቹ ድጋፍ ለማበርከት መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል፡፡ በአጠቃላይ  የድሬዳዋ እና የባህርዳር ስታድዬሞች ከአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን የብቃት ማረጋገጫ እንዲኖራቸው ሲመለከት የአዳማ ዩኒቨርስቲ ስታድዬምን በዚህ ግምገማ ለማካተት ለምን ጥረት እንዳልተደረገ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ በአፍሪካ ደረጃ የምንወዳደር ከሆነ ለውድድሮች በቂ ዝግጅት የምናደርግባቸው ስታድዬሞች እና የልምምድ ሜዳዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቷቸው ሊሟሉ የሚገባቸው  ናቸው፡፡ በእግር ኳሱ ዙርያ ያሉ ሁሉ የድርሻቸውን ሃላፊነት ለመወጣት መትጋት አለባቸው።   የወጣት ቡድኑ ከሱዳን ጋር የሜዳውን አድቫንቴጅ ተጠቅሞ ለሚያደርገው ወሳኝ ጨዋታ በድሬዳዋ የሚገኘው ስታድዬም ብዙ ምቹ ላይሆን ይችላል፡፡  ከድሬዳዋ ስታድዬም ይልቅ ለወጣት ቡድኑ የሚመች የነበረው የባህርዳር ስታድዬም ይመስለኛል፡፡  የድሬዳዋ እና የባህርዳር ስታድዬሞች አህጉራዊ ውድድር ማስተናገድ እንዲችሉ ለካፍ የገባው ማመልከቻ መዘግየቱ ምርጫውን ያዛባው መስሎኛል፡፡ አስቀድሞ መስራት ለምን አልተቻለም፡፡ ለቡድኑ ውጤት የተሻለ ከነበረው የባህርዳሩ ስታድዬም ይልቅ የድሬዳዋው ለምን እንደተመረጠ ግልፅ ያልሆነልኝ ለዚህ ነው፡፡ በአፍሪካ የክለቦች ውድድር እየተሳተፉ ያሉት ቅዱስ ጊዮርጊስና ደደቢት የባህርዳሩን ስታድዬም  ምርጫቸው ማድረጋቸው እንደማስረጃ መመልከት ይቻላል፡፡ ባለኝ መረጃ መሰረት የድሬዳዋ ስታድዬም በጣም ሞቃታማ አየር አለበት፡፡ ሜዳውም ጥሩ እንዳልሆነ ተነግሮኛል። ስለዚህ የስታድዬም ምርጫው ለወጣት ቡድኑ ውጤታማነት እንቅፋት እንደሚሆን በተገቢው ወቅት አለመረዳት ምን ማለት ነው፡፡ የባህር ዳር ስታድየም ምቹ ሳር የተነጠፈበት እና ተስማሚ አየር ስለነበረው ለቡድኑ የሜዳ አድቫንቴጅ የተሻለ መሆኑን በመገንዘብ ለመስራት አለመቻሉ በጣም ግራ አጋብቶኛል፡፡ በሌላ በኩል እውነቱን ለመናገር የአዳማ ዩኒቨርስቲ ስታድዬም በክብር እንግድነት በተጋበዝኩበት የዩኒቨርስቲዎች የስፖርት ፌስቲቫል በተመለከትኩበት ወቅት በተሟላ መሰረተልማቱ ማርኮኛል፡፡ ብሄራዊ ቡድን በካምፕ አስቀምጬ ለማዘጋጀት ሃሳብ እንዳለኝ ስናገር ማንም ስለዚህ ስታድዬም የነገረኝ የለም፡፡ አሁን ወጣት ቡድኑን ከሱዳኑ ጨዋታ በፊት ልምምድ ሳሰራ የነበረው በንግድ ባንክ እና በመከላከያ የልምምድ ሜዳዎች ነበር። በእነዚህ ስፍራዎች ያደርገናቸው ዝግጅቶች የተሟሉ አልነበሩም፤ የአዳማ ዩኒቨርስቲ ስታድዬምን ብንጠቀም የተሻለ ነበር፡፡ ወደፊትም በዚህ በኩል ያሉ ሁኔታዎችን በፌደሬሽኑ በኩል ትኩረት ተሰጥቶባቸው  በተገቢው ጊዜ ተግባራዊ አገልግሎት እንዲሰጡ መደረግ አለበት። ከዚህ ጋር ተያይዞ ሊነሳ የሚችለው መሰረተልማቱ ካለ ተግባራዊ አገልግሎት የሚሰጥባቸው ሁኔታዎች መሰራት እንዳለባቸው የሚያመለክት ሁኔታ ነው። አዲስ አበባ ውስጥ ስለሚገኘው ብሄራዊ አካዳሚም መረጃ አለኝ፡፡ በዚያ አካዳሚ የልምምድ ሜዳ እና የካምፒንግ መሰረተልማት መኖሩን አውቃለሁ፡፡ ግን አካዳሚው ተመርቆ ስራ ከጀመረ ወዲህ ለብሄራዊ ቡድኖች የሚኖረው ድጋፍ ምንም እየተሰራበት አይደለም።  ወጣት እና ዋናው ብሄራዊ ቡድኖች በአገሪቱ ባሉት መሰረተልማቶች በአግባቡ የሚጠቀሙባቸው ሁኔታዎች የማይመቻቹት ለምንድነው ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ በነገራችን ላይ የድሬዳዋ ስታድዬም አለመመቸትን ያነሳሁት የወጣት ቡድኑ ውጤታማ ባይሆን እንደሰበብ ለመጥቀስ አይደለም። የምሰራው በየትኛውም ሁኔታ ተጫውቶ ለማሸነፍ የሚችል ቡድንን ነው፡፡ እንዲሁ ባለው መረጃ ተነስቶ የተሻለ ስታድዬም አለመመረጡ ትክክል ስላልመሰለኝ አስተያየት ለመስጠት ብዬ ነው፡፡  በየትኛ የእድሜ ደረጃ ያሉ ብሄራዊ ቡድኖች በሚካፈሉባቸው አህጉራዊ ውድድሮች ለውጤት የሚያግዙ ሁኔታዎችን መፍጠር የፌደሬሽኑ ሃላፊነት ነበር፡፡
የወጣት ቡድኑ የተጨዋቾች ስብስብ እና የፉክክር ደረጃን እንዴት ይገልፁታል? በካምፕ በሚደረግ ስልጠና መስራት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ አበይት እርምጃ መሆኑንም ይመክራሉ፡፡  ይህን አስመልክቶ ምን ማብራርያ ይሰጣሉ?
የወጣት ቡድኑ ለዋናው ብሄራዊ ቡድን የወደፊት ተስፋ መጠናከር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለው ነው፡፡
ሰሞኑን በዩኒቨርስቲዎች ውድድር ሻምፒዮን ከሆነው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቡድን የአቋም መፈተሻ አድርገን ነበር፡፡ 5ለ2 አሸንፈናል፡፡ በዚህ ጨዋታ በቡድን ስብስብ ውስጥ የተመለከትኳቸው ወጣቶች ለብሄራዊ ቡድኑ በቂ ተስፋ እንዳላቸው ተረድቻለሁ፡፡ ከውድድር ጎን ለጎን በዋናው ብሄራዊ ቡድን ግንባታ ወጣቶቹን በትኩረት በማሰራት ተተኪ ሆነው እንዲወጡ ሌሎች ስራዎችን ለማከናወን መነሻ የሚሆኑ ሁኔታዎችን ታዝቢያለሁ፡፡
አንድ ወሳኝ እርምጃ ልንግርህ፡፡ ይህ የወጣት ቡድን ባለው አቅም ተሰርቶበት ወደ ከፍተኛ የውጤት ደረጃ እንዲያቀና ዋናው ስራ የቡድን ስብስቡን ከአገር ውጭ በመውሰድ ለ3 እና አራት ወራት በሚቆይ እና በካምፕ በሚደረግ ስልጠና መስራት ያስፈልጋል፡፡ ወጣቶቹን ለምሳሌ ወደ አውሮፓ ወስዶ በካምፕ በማስቀመጥ በጥሩ መሰረተልማት፤ ብቃትን በሚያሳድጉ ስልጠናዎች እና የወዳጅነት ጨዋታዎች መገንባት የሚያስፈልግ ነው፡፡ እድገት የሚገኘው በከፍተኛ ትጋት በሚሰሩ ሁኔታዎች ነው፡፡ ለወጣቶቹ ይህ የካምፕ ዝግጅት እንደሚያስፈልጋቸው የሚገልፅ እቅዴን ካሳወቅኩ ቆይቻለሁ፡፡ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ እቅዶችን ለመተግበር አስቸጋሪ ነው መሰለኝ፡፡ በተደጋጋሚ እቅዶቹን በተመለከተ ያደርግኳቸው ጥረቶች በበጀት አቅም ማነስ ለማሳካት እንደሚቸግር ተረድቻለሁ፡፡ በእርግጥ ከወራት በፊት ዋናውን ብሄራዊ ቡድን ወደ ብራዚል በመውሰድ የካምፕ ዝግጅት እንዲያደርግ ያስቻልኩት የግል ጥረቴን ተጠቅሜ ነው፡፡ በቅርብ ከማውቃቸው የሙያ ባልደረቦቼ እና ወዳጆቼ የወጪ ድጋፍ በማድረጋቸው የካምፕ ዝግጅቱን ለመስራት ተችሏል። ከዚያ በኋላ  ግን ተመሳሳይ ስራዎችን ለማከናወን እቅድና ፍላጎት ቢኖርም የባልንጀሮቼን ድጋፍ በመጠየቅ ለማሳካት የምችል አይመስለኝም፡፡ በእርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ነባራዊ ሁኔታዎች አንፃር እግር ኳስ ቅድሚያ ትኩረት አግኝቶ በከፍተኛ የበጀት ድጋፍ እንዲሰራ ግፊት ማድረግ አስቤ አይደለም፡፡  ከስፖርቱ የሚቀድሙ አጣዳፊ የልማት ተግባራት ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጂ ከመንግስት ባሻገር በእግር ኳሱ ዙርያ ያሉት ባለድርሻ አካላት ፌደሬሽኑን በመደገፍ እና በማነቃቃት መስራት አለባቸው፡፡ በፌደሬሽኑ በኩልም የበጀት አቅምን የሚያሳድጉ ተግባራትን ለመስራት ጥረት ያስፈልጋል፡፡
ይህን ወጣት ቡድን ውጤታማ ማድረግ ካስፈለገ፤ ዋናው ብሄራዊ ቡድን ያለውን የፉክክር አቅም ለማስቀጠል የባለድርሻ አካላት ትኩረት እና ርብርብ ያስፈልጋል፡፡
የወጣት ቡድን ወደ አውሮፓ ወይም በሌላ አህጉር ወስዶ በካምፕ ዝግጅት ለማድረግ እና ተጨዋቾቹን በሚቀጥሉት ሶስት እና አራት አመታት የብሄራዊ ቡድኑ የውጤት ተስፋ እንዲሆኑ ለማስቻል የሚጠይቀውን በጀት ለማሟላት ስፖንሰሮች የማይገኙት ለምንድነው ብሎ ማጥናት ተገቢ ነው፡፡ አሁን ያለው ዋና ብሄራዊ ቡድን 70 በመቶ የሚሆነውን የተጨዋቾች ስብስብ ሊገነባ የታቀደው ከዚህ ወጣት ቡድን እንደሆነ መገንዘብ ይኖርብናል፡፡
በወጣት ቡድኑ ውስጥ እድሜያቸው ከ21 አመት በታች የሚሆኑ ተጨዋቾች በብዛት አሉ። እነ አንዳርጋቸው፤ ናትናኤል፤ ዳዊት፤ ዳንኤል፤ አብዱልከሪም፤ታሪኩ የወደፊት ተስፋዎች ናቸው። እነሱን አሳድጎ ለመቀጠል ግን ዘላቂ የሆኑ ስራዎች ያስፈልጋሉ፡፡ እነዚህ ተጨዋቾች በአፍሪካ ደረጃ ከፍተኛ የፉክክር ብቃት ይዘው ማደግ አለባቸው። ከመካከላቸው ወደ አውሮፓ ለመሻገር የሚችሉትን ለዚያ ደረጃ የሚያበቃ ስራ በማከናወን መደገፍ ያስፈልጋል፡፡ አንዳንዶቹ ወጣቶች ከወዲሁ በቂ ልምድ እያካበቱ ናቸው፡፡ የምታስታውስ ከሆነ አንዳንድ ወጣት ተጨዋቾችን ወደ ብሄራዊ ቡድን ባሳደግኩበት ወቅት በ3 ጨዋታ አራት ነጥብ ሰብስበን ነበር፤ አንጋፋ እና ልምድ ያላቸው ግን ምንም ነጥብ አልነበራቸውም፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ እና በቻን ውድድር ተሳትፎ በነበረው ዋና ብሄራዊ ቡድን ጎል ማግባት የተቻለው  አንድ ብቻ ነው፡፡ ቡድኑ ወጣት ተጨዋቾች ገብተውበት በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ከትልልቅ ቡድኖች ጋር ሲጫወት ግን ስድስት ጎሎች ተመዝግበዋል፡፡ እነዚህ አሃዛዊ መረጃዎች በወጣት ተጨዋቾች ሊኖር የሚችለውን ውጤታማነት የሚያሳዩ ይመስለኛል፡፡ እነዚህ ወጣት ተጨዋቾች በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚካሄዱ ጠንካራ ውድድሮች ልምድ እንዲያገኙ እየተደረገ እና በበቂ ስልጠና እና ልምምድ እየሰሩ እንዲያድጉ መንቀሳቀስ ከተቻለ ወደ የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ያለው ተስፋን ማሳካት ይቻላል፡፡ከአገር ውጭ በካምፕ ዝግጅት ተተኪ ትውልድን ማፍራት በብዙ አፍሪካ አገራት ውጤታማነቱ ታይቷል፡፡ በኮትዲቯር፤ በካሜሮንና በብዙዎቹ የምእራብ አፍሪካ ያሉ ብሄራዊ ቡድኖች የየአገሮቻቸው ክለቦች  ከተለያዩ የአውሮፓ ክለቦች ጋር ተቀናጅተው በመስራታቸው ተጠናክረዋል፡፡ ታዳጊዎች ከ17 አመት በታች እድሜ ይዘው በአውሮፓ ደረጃ በካምፕ ዝግጅት እንዲሰሩ ይደረጋል፡፡ በዚህም የተገኙ ውጤቶችን መገንዘብ ለማንም አዲስ ነገር መሆን የለበትም፡፡ ብዙዎቹ የምእራብ እና የሰሜን አፍሪካ አገራት እግር ኳሳቸውን ይህን በመሰለ አቅጣጫ በመምራት ሲሰሩ በርካታ ዓመታት አልፈዋል፡፡ በኢትዮጵያ ይህን ተመክሮ ለመተግበር ምንም አይነት እርምጃዎች እንደመነሻ  አለመስራታቸው የሚያስገርም ነው፡፡ በምእራብ አፍሪካ ያሉ ክለቦች ታዳጊዎቻቸውን ወደ አውሮፓ ትልልቅ አካዳሚዎች በመላክ እድገታቸውን በማቀላጠፍ ብቻ አይደለም የሚሰሩት፤  በየአገሮቻቸው ያሉ አካዳሚዎችን የስልጠና  ደረጃ በፕሮፌሽናሊዝም መዋቅር ለማሳደግ ከአውሮፓ ብቁ አሰልጣኞችን በማስመጣት ሁሉ ይሰራሉ፡፡ እነዚህን አቅጣጫዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ለማስፋፋት መሰራት አለበት፡፡
ለመሆኑ ዋናው ብሄራዊ ቡድን ያለበት ወቅታዊ ሁኔታ ምን ይመስላል?
እንግዲህ በሚቀጥለው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ እንዲኖረን ከፈለግን ተገቢውን ትኩረት ሰጥተን ለመስራት እና በቂ ዝግጅቶች የማከናወኑ ተግባራት አሁኑኑ መጀመር ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ የእኔም ትኩረት ከወጣት ቡድኑ በኋላ ብሄራዊ ቡድኑ በመሰብሰብ ለአፍሪካ ዋንጫ እና ለሌሎች ውድድሮች በቂ እና የተሟላ ዝግጅት እንዲያደርግ መስራት ነው፡፡ አሁን በወጣት እና በዋናው ብሄራዊ ቡድን የያዝኳቸው ተጨዋቾቹ በተለይ ወጣቶቹ በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በወዳጅነት እና በነጥብ ጨዋታዎች የ5 እና የ6 ጨዋታዎች ልምድ መያዛቸው ትልቅ አቅም መሆኑን እረዳለሁ፡፡ ይሁንና በዋና ብሄራዊ ቡድኑ የተጨዋቾች ስብስብ ክፍተቶች መኖራቸውን እያስተዋልኩ ነው። እነዚህ ክፍተቶች  አጀማመሩን ፈታኝ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ለዋናው ብሄራዊ ቡድን 53 ተጨዋቾች በመምረጥ ዝግጅት ለመጀመር ጥሪ ያደረግኩት ከሁለት እና ሶስት ሳምንት በፊት ነው፡፡ የሚገርምህ ከእነዚህ ተጨዋቾች ያገኘሁት አጥቂዎች ሁለት ብቻ ናቸው። ይባስ ብሎ በቀኝ ተመላላሽ እና በመሃል ተከላካይ መስመር ሙሉ ብቃት ያላቸው ተጨዋቾችን ለማግኘት አልተቻለም፡፡ በብዙዎች ክለቦች የአማካይ ስፍራ አንድ የውጭ አገር ተጨዋች ወሳኝ ሆኖ መሰለፉም በዚህ የጨዋታ መስመር ወሳኝ ተጨዋች የማግኘቱን ሁኔታ አጥብቦታል፡፡  በፕሪሚዬር ሊጉ የሚወዳደሩ ክለቦች ከላይ በተዘረዘሩት ወሳኝ የጨዋታ ቦታዎች  ኢትዮጵያውያን ተጨዋቾችን ከማሰለፍ ይልቅ የውጭ ተጨዋቾችን በመቅጠር የሚሰሩበትን አቅጣጫ በስፋት መተግበራቸው እያሳሰበኝ ነው፡፡ በየክለቡ በአጥቂ፤ በቀኝ ተመላላሽ እና በመሃል ተከላካይ መስመር በቋሚ ተሰላፊነት የሚጫወቱት የውጭ አገር ዜጎች ናቸው፡፡ ይህ አካሄድ ብሄራዊ ቡድኑን እንዳያዳክመው አስግቶኛል፡፡ ክለቦች ከውጭ ተጨዋቾች ይልቅ ከወጣት ቡድኖቻቸው እና ከዝቅተኛ የውድድር ደረጃ ከሚገኙ ክለቦች ተተኪዎችን በመፈለግ ቡድኖቻቸውን ለማጠናከር መስራት ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ ይህን እያደረጉ ባለመሆናቸው  የብሄራዊ ቡድኑን መጠናከር ያስተጓጎሉ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል፡፡
ተስፋ ያደረግኩት በግብ ጠባቂ በኩል ብቻ ነው። ከሃዋሳ ያገኘነው ወጣት ግብ ጠባቂ ክብረአብ ማስረጃ የሚሆን ነው፡፡ ይህ ወጣት ክለቡ በጥሎ ማለፍ ጨዋታ ላገኘው ስኬት በብቸኝነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነበረው፡፡ በሁሉም የጨዋታ ስፍራዎች እንደዚህ አይነት ተጨዋቾች በብዛት ከየክለቡ የሚወጡበት የቡድን መዋቅር መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ በግብ ጠባቂ በኩል የመረጥናቸው ሌሎች ሶስት ተጨዋቾችም የወደፊቱን የብሄራዊ ቡድን ተስፋ ያለመለሙ ናቸው። ይሁንና እነዚህን ወጣት ግብ ጠባቂዎችም ለተሻለ ደረጃ ለማብቃት በሚሰሩ ተግባራትም የተወሰነ ክፍተት አለ፡፡ በተገቢው የእድገት ሂደት እንዲቀጥሉ ደረጃውን የጠበቀ አሰልጣኝ እና የዝግጅት ሁኔታ እንዲፈጠርላቸው እየተናገርኩ ነው፡፡ በስልጠና ያሉ ሁኔታዎች ካልተለወጡ በቀር በእነዚህ ወጣት ግብጠባቂዎች ላይ የያዝናቸው ተስፋዎች አለአግባብ ሊመክኑ ይችላሉ፡፡  እነዚህን አይነት ወጣት ተጨዋቾች ቅድም በጠቀስኩልህ በባህር ማዶ በሚሰራ ሰፋ ያለ የካምፕ ዝግጅት ማሰልጠንና ብቃታቸውን ማሻሻል ወሳኝ እርምጃ ይሆናል፡፡
ዋናው ብሄራዊ ቡድን ከፊቱ ለሚጠብቁት አህጉራዊ የማጣርያ ውድድሮች ተጨዋቾች ተጠርተው እንደነገሩ ዝግጅቱን ከጀመረ 15 ቀናት ይሆኑታል። የተጠሩ ተጨዋቾችን ቶሎ የማግኘት ሁኔታ ግን አሁንም አንዳንድ ችግሮች ይታዩበታል፡፡  አሁን ለምሳሌ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት በአፍሪካ ደረጃ ባላቸው የቅድመማጣርያ ተሳትፏቸው ለብሄራዊ ቡድን የምንፈልጋቸውን ተጨዋቾች በቶሎ ስለማይሰጡን ከወዲሁ ወደ ቡድኑ በመቀላቀል ለመስራት አለመቻሉ የፈጠረብን መስተጓጎል አለ፡፡ ብዙ ልምምድ ያልሰሩ ተጨዋቾችን በወቅቱ ሳናገኝ የሰሩ ልጆችን በመቀነስ የመተካት ሁኔታ በእኔ አሰራር ሊኖር አይችልም፡፡
ከትልልቅ ክለቦች ብቻ ሳይሆን በብሄራዊ ሊግ ደረጃ እና በክልሎች ከሚገኙ ቡድኖች ተጨዋቾችን ወደየብሄራዊ ቡድን በመጥራት በተከተሉት አሰራር ተደንቀዋል፡፡ ስለእነዚህ ውሳኔዎች ምን ይነግሩናል?
የአንድ አገር ብሄራዊ ቡድን እኮ ለሁሉም በሩ ክፍት መሆን ያለበት ነው፡፡ በትግራይ፤ በጋምቤላ እና በሌሎች ክልሎች ያሉ የስፖርቱ አመራሮችን በየክልሎቻቸው ያሉ ምርጥ ተጨዋቾችን በመለየት እንዲያሳውቁኝ በደብደቤ ጠየቅኩ፡፡ እነሱም ላቀረብኩት ጥያቄ ሙሉ እምነት ስላደረባቸው ምርጥ ተጨዋቾች ያሏቸውን 7 ወጣቶችን አሳወቁ፡፡ እነዚህ ልጆች ከብሄራዊ ቡድኑ የመጀመርያ ስብስብ ጋር ተቀላቅለው በመስራት አስደናቂ ተሞክሮ አገኙ፡፡ ከሰባቱ ወጣት ተጨዋቾችም ሁለት ልጆች ባሳዩት አሳማኝ ብቃት በብሄራዊ ቡድኑ እንዲቆዩ ወስኛለሁ፡፡ ከትግራይ እና ከጋምቤላ ክልሎች የመጡት ናቸው፡፡ ዋና ብሄራዊ ቡድኑ እስከሚያደርገው የመጀመርያው የማጣርያ ጨዋታ ይዥያቸው ለመቆየት ወስኛለሁ፡፡ ወጣቶች ተገቢው እድል ተፈጥሮላቸው የበለጠ እንዲያድጉ ያስፈልጋል፡፡ አሁን ለምሳሌ  ከጋምቤላ ክልል ያገኘሁት ወጣት የአጥቂ መስመር ተሰላፊ በጣም ጥሩ ችሎታ አለው፡፡ የትግራዩም ልጅ በተከላካይ መስመር ላለው ክፍተት አፋጣኝ መፍትሄ እንደሆነ ተገንዝቢያለሁ፡፡ ከወላይታ፤ ከአርባምንጭ እና ከሙገር የመጡት ወጣት ተጨዋቾችም ላይ እምነት አለኝ፡፡ በወጣት ተጨዋቾች ምልመላ ከትልልቅ ክለቦች ባሻገር በሁለተኛ ደረጃ ካሉ ክለቦች እና የክልል ቡድኖች ጋር ግንኙነት በመፍጠር የምተገብራቸው ስራዎች የምፈልገውን መልዕክት አንፀባርቀዋል፡፡ በየትኛውም የአገሪቱ ክልሎች ያሉ ታዳጊ እና ወጣት ተጨዋቾች በብቃታቸው አሳማኝ ከሆኑ እና የማደግ ፍላጎት ካላቸው የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ትኩረት ሰጥቶ ሊመርጣቸው እንደሚችል መረዳታቸው ለማስተላለፍ የፈለግኩት መልዕክት ይመስለኛል፡፡ በዩኒቨርስቲዎች የስፖርት ፌስቲቫል በቀረብልኝ የክብር እንግድነት ግብዣ ተገኝቼ በነበረበት ወቅትም ተመሳሳይ መነቃቃት ለመፍጠር ሞክሪያለሁ፡፡ በዩኒቨርስቲዎቹ ቡድኖች አንዳንዶቹ ለብሄራዊ ቡድን የመጫወት ብቃት እንዳላቸው የተናገርኩት ማለት ነው፡፡ የአመራረጥ መስፈርቴ ለሁሉም ወጣቶች እድል እንደሚሰጥ ለማመልከት  ነው፡፡ በእርግጥ በዩኒቨርስቲው ቡድኖች የተመለከትኳቸው ልጆች ለብሄራዊ ቡድን እንዲደርሱ የሚያልፉት የእድገት ምእራፍ አለ፡፡ በመጀመርያ በክለብ መያዝ አለባቸው፡፡ ለዚህም ነው ክለቦች በእንደዚህ አይነት ውድድሮች አዳዲስ እና ወጣት ተጨዋቾችን ለመመልመል ትኩረት እንዲሰጡ እና እንዲሰሩ ያነሳሳሁት፡፡



Read 3386 times