Monday, 23 February 2015 07:47

ቢሊዬነሩ

Written by  ድርሰት፡- ማክሲም ጎርኪ ትርጉም፡- ኢዮብ ካሣ
Rate this item
(13 votes)

        በብረታ ብረትና በነዳጅ ንግድ የነገሱ ባለጸጎች እንዲሁም ሌሎች የአሜሪካ ከበርቴዎች ሁሌም የምናብ አቅሜን በከፍተኛ ደረጃ ያነቃቁት ነበር፡፡ እነዚህ ተዝቆ የማያልቅ ገንዘብ ያላቸው ባለፀጎች፣ እንደ ሌሎች ሟች ፍጡራን ሊሆኑ እንደማይችሉ እርግጠኛ ነበርኩ፡፡  
እያንዳንዱ ሚሊዬነር (ለራሴ ሹክ አልኩት) ቢያንስ የራሱ ሶስት ሆድና 150 ጥርሶች አያጣም። ሚሊዬነር  ከማለዳው 12 ሰዓት አንስቶ እስከ ቀትር ሌሊት ድረስ ያለ እረፍት እንደሚያሻምድ አልተጠራጠርኩም፡፡ ምግቦቹ እጅግ ጣፋጭና ውድ እንደሚሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው! መቼም አመሻሽ ላይ በፈታኙ የማኘክ ሥራ መደካከሙ አይቀርም፡፡ ከመድከሙ ብዛትም (በምናቤ ሳልኩት) ቀን አጣጥሞ በጉሮሮው የላካቸውን  ምግቦች ይፈጩለት ዘንድ ለአሽከሮቹ ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡
መላወስ የተሳነው፣ ላብ ያጠመቀውና መተንፈስ ዳገት የሆነበት ሚሊዬነሩ፤ አሽከሮቹ ደጋግፈው አልጋው ላይ ያወጡትና እንቅልፉን ይለጥጣል፡፡ ያለበለዚያ በነጋታው ጠዋት 12 ሰዓት ላይ ዳግም የመብላት ሥራውን መወጣት አይችልም፡፡  
ለእንዲህ ያለው ሰው - የቱንም ያህል ስቃይ ቢያስከትልበትም - የሃብቱን ግማሽ ብቻ መጠቀም የሚሞከር አይደለም፡፡
ሃቁን ለመናገር እንዲህ ያለው ህይወት ቀፋፊ ነው፡፡ ግን ደግሞ አንድ ሰው ሚሊዬነር ከሆነ፣ ይቅርታ---ቢሊዬነር…ምን ምርጫ አለው? ከተራ ተርታው ሟች ብዙ እጥፍ የበለጠ ምግብ ካላሻመደ ቢሊዬነርነቱ ምኑ ላይ ነው ? ይሄ የታደለ ፍጡር፣ የወርቅ ካኔቴራና ሙታንታ እንደሚለብስ፣ በወርቅ ምስማሮች ያጌጠ ጫማ እንደሚጫማ፣ ጭንቅላቱ ላይ በባርኔጣ ምትክ የአልማዝ አክሊል እንደሚያጠልቅ …. በምናቤ ስየዋለሁ፡፡ ልብሱ እጅግ ውድ ከሆነ አጥላስ የተሰራ፣ ቢያንስ 50 ጫማ ርዝመት ያለውና በ300 የወርቅ አዝራሮች የተያያዘ ነው፡፡ በበዓላት ወቅትም ስድስት ውድ ጥንድ ሱሪዎችን ደራርቦ ለመልበስ መገደዱ አይቀርም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አለባበስ ጨርሶ ምቾት እንደሌለው አያጠያይቅም፡፡ ግን ደግሞ አንድ ሰው ያን ያህል ባለጸጋ ከሆነ፣ እንዴት እንደተቀረው ህዝብ ይለብሳል? የማይሞከር ነው!
የቢሊዬነር ኪስ በጣም ሰፊና ጥልቅ እንደሚሆን ገምቼአለሁ፡፡ እዚያ ትልቅ ኪስ ውስጥ ለአንድ ቤተክርስቲያን ወይም ለሙሉ የሴኔት አባላት የሚሆን ክፍል በቀላሉ ማግኘት አያዳግትም፡፡ የዚህ ዓይነቱ ሰው ቦርጭ፣ ርዝመቱንና ስፋቱን ልገምተው ያልቻልኩት የአንድ መርከብ አካል (ቦዲ) እንደሚያህል አስቤአለሁ፡፡ የሰውነቱን መጠን በተመለከተ ግን ጥርት ያለ ምስል መከሰት አልቻልኩም፡፡ ሆኖም ለብሶት የሚተኛው የአልጋ ልብስ ከጥቂት መቶ ስኩዌር ሜትሮች እንደማያንስ ገምቻለሁ፡፡ ትምባሆ የሚያኝክ ከሆነ ምርጡን ብቻ እንደሚያኝክ አልተጠራጠርኩም። አንዴ ወደ አፉ የሚልከውም ሁለት ፓውንድ የሚመዝን  ትምባሆ ነው፡፡ እርግጥ ነው ገንዘብ መውጣቱ አይቀርም!
በሚገርም ሁኔታ የዚህን መንዲስ የሚያህል ሰውዬ ጭንቅላት በተመለከተ ለራሴ ግልጽ ያለ ምስል መፍጠር አልቻልኩም፡፡ ለዚህ ከማንኛም ነገር ውስጥ ገንዘብ ጨምቆ ለማውጣት ከተዘጋጁ ግዙፍ ጡንቻዎችና አጥንቶች ለተበጀ ፍጡር፣ ጭንቅላት እምብዛም አስፈላጊ መስሎ አልታየኝም፡፡
ከእነዚህ አስደማሚ ፍጡራን አንዱን ፊት ለፊት ስጋፈጠውና ቢሊዬነርም እንደ ሌላው ሁሉ የሰው ልጅ መሆኑን አምኜ ስቀበል የሚፈጠርብኝን መደነቅ--- ማን ሊገምተው ይችላል!
የእጅ መደገፍያ ባለው ወንበር ላይ በምቾት ተለጥጦ የተቀመጠ ረዥም፣ ጨምዳዳ ፊት፣በፀሃይ የጠቆረ ጅማታም እጁ ዓይን በማይሞላ ሰውነቱ ላይ የተነባበረ ሽማግሌ ተመለከትኩኝ፡፡ የፊቱ ለንቋሳ ቆዳ ሙልጭ ተደርጎ ተላጭቷል፡፡ ሊወድቅ የደረሰው የታችኛው ከንፈሩ፣ በቅጡ የተዋቀሩ መንጋጋዎቹን የሸፈኑለት ሲሆን የወርቅ ጥርሶቹን አጋልጠውታል፡፡ ጠፍጣፋ፣ ቀጭንና ኩበት የሚመስለው የላይኛው ከንፈሩ፤ ሲናገር እንኳ አይንቀሳቀስም፡፡ ግንባር የለሽ ፈዛዛ ዓይኖች፤ምልጥ ያለ ጭንቅላት ነው ያለው፡፡
አለባበሱ ከተራው ሟች ፍጡር ምንም የተለየ ነገር የለውም፡፡ ቀለበት አድርጓል፤ ሰዓት አስሯል። ከጥርሶቹ ውጭ ወርቅ የለውም፡፡ እሱም ቢሆን ግማሽ ፓውንድ እንኳን አይሞላም፡፡ መላ ገፅታው ሲታይ፣ በአውሮፓ የአንድ መሳፍንት ቤተሰብ አዛውንት አገልጋይን ያስታውሳል፡፡  
እኔን በተቀበለኝ ክፍል ውስጥ ምንም የተለየ የምቾትና የቅንጦት ነገር አይታይም፡፡ የቤት ቁሳቁሶቹ ጠንካራ መሆናቸውን ከመግለጽ ውጭ ሌላ ሊባል የሚችል ነገር የለም፡፡ “ምናልባት ዝሆኖች ወደዚህ ቤት ያዘወትሩ ይሆናል” የቤቱን ግዙፍና በርካታ ቁሳቁሶች ስመለከት ያለ ውዴታዬ ያሰላሰልኩት ሃሳብ ነበር፡፡
“አንተ ነህ ቢሊዬነሩ?” ጠየቅሁት፤ ዓይኔን ማመን ስላቃተኝ፡፡
“እንዴታ! መጠርጠሩስ?” ጭንቅላቱን በአሳማኝ ሁኔታ እየነቀነቀ  መለሰልኝ፡፡
“እሺ፤ ቁርስ ላይ ስንት ኪሎ ስጋ ትጨርሳለህ?”
“እኔ ጠዋት ስጋ አልበላም” ያልጠበቅሁት መልስ ሰጠኝ “ቁራጭ ብርቱካን፣ አንዲት እንቁላል፣ ትንሽዬ ስኒ ሻይ፣  ይሄው ነው …”
“ጥሩ” እንደገና ጀመርኩ፤ በከፊል ሳልረጋጋ “እንዳትዋሸኝ፤ ሃቁን ንገረኝ፡፡ በቀን ስንት ጊዜ ትበላለህ?”
“ሁለቴ” አለኝ ተረጋግቶ  “ቁርስና እራት ካገኘሁ በቂዬ ነው፡፡ ቀትር ላይ ሾርባ፣ ጥቂት ዶሮ ወይም ዓሳ፣ አትክልቶችና ፍራፍሬ፣ ከዚያ አንድ ስኒ ቡና፣ ሲጋራ …”
መገረሜ በፍጥነት እየጨመረ መጣ፡፡ ትንፋሽ ወሰድኩና ጥያቄዬን ቀጠልኩ፡-
“ያልከው እውነት ከሆነ፣ በገንዘብህ ምን ታደርግበታለህ?”
“ተጨማሪ ገንዘብ እሰራበታለሁ!”
“ምን ሊያደርግልህ?”
“የበለጠ ብዙ ገንዘብ ለማግኘት!”
“እኮ ምን ሊያደርግልህ?” ደግሜ ጠየቅሁት፡፡
እጆቹን በመቀመጫው መደገፍያ ላይ በማድረግ ወደ እኔ አስግጎ፣ በገጹ ላይ የጉጉት ስሜት እየታየበት፤  
“ነካ ሳያደርግህ አይቀርም?” አለኝ፡፡
“አንተስ?” አልኩት …
ሽማግሌው ጭንቅላቱን ዘመም አደረገና፤ በወርቅ ጥርሶቹ በስሱ አፏጭቶ፤
“ካንተ ዓይነት ዝርያዎች ውስጥ የተዋወቅሁት የመጀመሪያው የሰው ልጅ አንተ ነህ” አለኝ፡፡
ከዚያም ጭንቅላቱን ወደ ኋላ አስደግፎ ለተወሰነ ጊዜ ተመለከተኝ  - በዝምታና በጥንቃቄ በመመርመር፡፡
“ሥራህ ምንድነው?” እንደገና ጀመርኩ፡፡
“ገንዘብ መስራት” በአጭሩ መለሰልኝ፡፡
“አሃ--ሃሰተኛ ገንዘብ ነዋ የምትሰራው!” በደስታ ስሜት ጮኬ ተናገርኩ፤ በመጨረሻ የእንቆቅልሹን ፍቺ ያገኘሁት ስለመሰለኝ፡፡ ቢሊዬነሩን ግን ስሜት ፈነቀለው፡፡ መላ ሰውነቱ ተንቀጠቀጠ፡፡ ዓይኖቹ እንደ ጉድ ተንከባለሉ፡፡
“ተሰምቶ የማይታወቅ ነገር ነው!” አለ፤ ስሜቱ ሲረጋጋ፡፡ ከዚያ ጉንጮቹን ወጠራቸው ፤ ለምን እንደሆነ ባላውቅም፡፡   
ጥቂት አሰብኩና ተከታዩን ጥያቄ አከልኩለት፤
“ገንዘብ የምትሰራው እንዴት ነው?”
“በጣም ቀላል ነው፡፡ የባቡር ሃዲድ መስመሮች አሉኝ፣ ገበሬዎች ጠቃሚ ምርቶች ያመርታሉ፤ እኔ ለገበያ አቀርባቸዋለሁ፡፡ ገበሬው እንዳይራብና የበለጠ ማምረት እንዲችል ምን ያህል ገንዘብ ልተውለት እንደሚገባ በትክክል አሰላለሁ። የቀረውን እንደ ትራንስፖርት ክፍያ ለራሴ አስቀምጣለሁ፡፡ ይሄ ለእኔ  በጣም ቀላል ነው!”
“እና ገበሬዎቹ በዚህ ይረካሉ?”
“ሁሉም ይረካሉ ብዬ አላምንም” አለ፤በገራገር ጨቅላነት “ግን ደግሞ ሰዎች ምን ብትሰጣቸው አይረኩም ይባላል፡፡ ሁልጊዜ በቃኝ የማያውቁ  ለየት ያሉ ሰዎች  አሉ…”

Read 6066 times