Monday, 02 March 2015 08:47

የህብረት ሥራ ማህበራት ኤግዚቢሽን ባዛርና ሲምፖዚየም ሊካሄድነው

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(0 votes)

ሁለተኛው አገር አቀፍ የህብረት ሥራ ማህበራት ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚየም - 2007 በመጪው ሳምንት እንደሚካሄድ የፌዴራል ህብረት ስራ ኤጀንጀሲ አስታወቀ፡፡
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ክቢር አቶ ኡስማን ሱሩር፣ ሰሞኑን በጽ/ቤታቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ ኤግዚቢሽንና ባዛሩ “የህብረት ስራ ማህበራት ስኬቶችን በማስፋፋት ህዳሴያችንን እናፋጥናለን” በሚል መሪ ቃል ከየካቲት 26 እስከ 30 በኤግዚቢሽን ማዕከል እንደሚካሄድ ገልፀዋል፡፡
ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡና በተለያዩ ዘርፎች የተሳተፉ 240 የህብረት ስራ ማህበራት፣ ዩኒየኖችና ፌዴሬሽኖች ምርትና አገልግሎታቸውን በማቅረብ ከሸማቹ ህብረተሰብ ጋር በቀጥታ በመገናኘት የገበያ ትስስር እንደሚፈጥሩ የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፣ እርስ በርስ አንዱ የሌላውን ምርት ወይም አገልግሎት በመግዛት የገበያ እድልና የልምድ ልውውጥ ይፈጥራሉ ብለዋል፡፡
በአምራቾችና በሸማቾች መካከል ጠንካራ የገበያ ትስስር ሲፈጠር ህብረተሰቡ ለህብረት ሥራ ማህበራት ያለው አመለካከት ይለወጣል ያሉት አቶ ኡስማን፣ በርካታ የማህበረሰቡ አካላት ከሚገናኙባቸው እንደዩኒቨርሲቲ፣ ማረሚያ ቤቶችና ሆስፒታሎች ያሉ ተቋማት ምርትና አገልግሎታቸውን በማቅረብ ያስተዋውቃሉ የገበያም ትስስርም ይፈጥራሉ ብለዋል፡፡
በግብርና ምርት የተሰማሩ ማህበራት በኤግዚቢሽኑ ላይ ቡና፣ ሰሊጥ፣ … ያቀርባሉ፡፡ ወደ አግሮ ፕሮሰሲንግ የተሸጋገሩ ብዙ የህብረት ስራ ማህበራት ስላሉ፣ በምርታቸው ላይ እሴት ጨምረው፣ ለምሳሌ ዛላ በርበሬ ከመሸጥ ቅመም ጨምረው በማስፈጨት ለሱፐር ማርኬቶች የሚያቀርቡ፣ ጥሬውን ገብስ ከማቅረብ፣ ወደ ቆሎ፣ ወደ በሶ፣ ወደ ጩኮ፣ … ቀይረው ለሱፐር ማርኬቶች የሚያቀርቡና ኤክስፖርት የሚያደርጉ ማህበራት ስላሉ፣ ኤግዚቢሽኑን ሲመለከቱ በህብረተሰቡ ውስጥ ያለው ብዥታ ይቀይራል የሚል እምነት እንዳለ ገልፀዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በኤግዚቢሽኑ ዋዜማ የካቲት 25 ቀን ከ700 በላይ ሰዎች የሚሳተፉበት የፓናል ውይይት በተባበሩት መንግስታት ስብሰባ አዳራሽ (ኢሲኤ) እንደሚካሄድ ጠቅሰው፣ የአገራችንን የህብረት ስራና ዓለም አቀፍ የህብረት ስራ እንቅስቃሴን መነሻ ያደረጉ የመልካም ተሞክሮ ጥናታዊ ተሞክሮ ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል ብለዋል ዋና ዳይሬክተሮ አቶ ኡስማን ሱሩር፡፡

Read 1331 times