Monday, 09 March 2015 12:13

በአዲስ አድማስ ዋዜማ

Written by  ሰዓሊ በቀለ መኮንን (ረዳት ፕሮፌሰር)
Rate this item
(0 votes)

ሁሉም ነገር የሆነበት ጊዜ ወደ ሁዋላ እየራቀ ሲሔድ ለዛሬ ሕልም መምሰሉ አይቀርም።  ጥቂት ቆይቶ ደግሞ ግማሽ ጐኑን ተረት ይበላዋል። ለእንደኛ አይነቱ ፅፎ ማስቀመጥ ብዙ  ለማይሆንለትማ ጭራሽ በመረሳት ጎርፍ  የሚጠረግበት አጋጣሚ ጥቂት አይደለም።
እንዲህ ሥራውን አክብሮ መሰረቱን አሳምሮ ቀና እንዳለ፣ አስራ አምስት አመታትን አስቆጥሮ ዛሬ የደረሰው የአዲስ አድማስ ጋዜጣ፤ የዛሬ አስራ አምስት አመት  ረዥም ጉዞ የማይታክተው ቁምነገረኛ ጋዜጣ ጀምረን  እስቲ ሳናቋርጥ ማሳተም ያቅተንም እንደሆን፣ ሞክረን አቅማችንን ካላየን ምን ዋጋ አለው ? በሚል ወኔ  ባለቤቱ  አሴ - አሰፋ ጎሳዬ መውጣት መውረድ ከጀመረ ሰንበትበት ብሎ ነበር። ታዲያ ምንም እንኳ አብዝቶ የሚገናኘውም የሚመክረው ከቆየ የስራም የሐሳብም ባልደረባው ከጌታ መኮንን ጋር ቢሆንም በተለይ ከስራ በሁዋላ አመሻሽ ላይ በዋዛውም በቁም ነገሩም ከሚቀላቀሉት መካከል   እኔም አንዱ ነበርኩ።
 ከዚያ ቀደም ብሎ  አምስት ስድስት ዓመት በፊት ገደማ  “አዲስ አርት ፌስቲቫል” የተሰኘውን በሐገሪቱ የመጀመሪያውን  ሳምንት ሙሉ የተካሔደ ዙሪያ መለስ የስነ-ጥበብ ፌስቲቫል ለማዘጋጀት ጌታ መኮንን አሰባስቦ ካስተዋወቀን ምርጥ ሰዎች አንዱ ነበር- አሴ ። እርሱ ሰዓሊ ወይ ገጣሚ ባልሆነበት ሌሎች ታውቀው እነርሱው  በሚጠቀሙበት የሳምንት ሙሉ ትልቅ ክብረ-በዓል በአዲስ አበባ ይካሔድ ዘንድ የከሰረው የገንዘብ መጠን፣ ያባከነው የጊዜ ብዛት፣ የወጣ የወረደበት ቦታ፣ የተለማመጠው የለመነው የሰው ብዛት፣ በዚያም ያገኘውን የመንፈስ ደስታ አሁንም ድረስ ሳስበው   ካለማቸውና  ካከናወናቸው ተግባራቱ ሁሉ
 የታዘብኩት በርግጥ ሰውና ሐገሩ  መለወጥ ካማራቸው የምር መለወጫ መንገዱ ይኸው መሆኑን ነው
ርዕይ ፣ ዛሬ እንደ ብይ መጫወቻ ሳይሆን ርዕይ ከተባለ በበኩሌ የአሴ አይነት ርዕይ ያለተጨማሪ ማብራሪያ ምን እያሉ ምን ማድረግ እንደሆነ ያኔም አሁንም በቀላሉ ይገባኛል። አዲስ አርት ፌስቲቫል እስከ ዛሬ ያልደበበዘዘውን አሻራ ጥሎ እንዲያልፍ ከጌታ መኮንን ጋር ሁሉን ካደረጉ  በሁዋላ፣ አሴ በአንድ ወይ በሌላ መልክ ቋሚ የሆነ የእውቀት ወይም የጠቅላላ መረጃ መድረክ መፍጠር ወይም ከዚያም በላይ “ትልቅ የሆነ ነገር ላገራችን በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ እንችላለን ? ” ዓይነት ነገር የሁልጊዜ ጥያቄና ጨዋታው ነበር። ለራሱ
ስራ ፈጥሮ ብዙ ብዙ መንገዶችን በብዙ ሌሎች መስመሮች በኩል ደጋግሞ  እንደሞከረ
 አስታውሳለሁ። ሁሉንም የገንዘብ ትርፍ አጥቶባቸው ሳይሆን እርሱ “ሐገር” ፣ “ ወገን” ከሚለው ኅብረተሰብ ጋር አብሮ ከማደግ ፣ አውቆ ከማደግ ጋር በልቡ ያለውን ሕልም አልፈታ ስላለው ብቻ ነው ጥሎ ሌላ ለመጀመር የሚደክመው ። ይህ አይነቱ የአስተሳሰብ ሐብት ዛሬ አሰፋ ካለፈ በሁዋላ በኖርናቸው ጥቂት አመታት ውስጥ በብርሃን ፍጥነት  አሽቆልቁሎ፣ የከፋ ኪሳራ ውስጥ እንደምንገኝ አጥብቄ አምናለሁ። ከዚያ አንፃር ከተመዘንን፣ ስንቶቻችንና ማንኛችን ሞተን፣ ማንኛችን ደግሞ  የኗሪነት ቆጠራ እንደሚመለከተን አላውቅም።
ከብዙ ማውጣትና ማውረድ፣ ከብዙ ምክርና ማሰላሰል በሁዋላ  ያ የመረጃ መድረክ ጋዜጣ ቢሆን እንደሚያስኬድ ከዚያም ቀስ በቀስ የኢትዮጵያን ስነ-ጥበብ ሊያግዝ የሚችል አቅም የሚኖረው ተቋም ራሱ ይፈጥራል ተብሎ ጋዜጣው ይቅደም የሚል ውሳኔ ላይ ተደረሰ። ሁልጊዜም አሰፋ በስነ-ጥበብ ውበትና ጉልበት ላይ እምነት ነበረው። በዙሪያው በነበርነው የሙያው ሰዎች ተፅዕኖ አይመስለኝም። ዋናው ምክንያት ከገዛ ስልጣኔው የመነጨ እንደሆነ እኔ ጥርጣሬ የለኝም ። ስልጣኔው ስል  መማሩ ብቻ ማለቴ  አይደለም ። በመማርብቻ መሰልጠን እንደማይገኝ ከብዙ ምሁራኖቻችን ስለምናስተውል። ይልቁንም  አሰፋ ሲበዛ አንባቢ ፣ ምን  እንደሚያነብም የሚያውቅ ፣ በጥልቅና በፍጥነት ማንበብ የሚችልበት፣ የሚያነበው ለባላጋራ ማጥቂያ ወይም ያደባባይ  መኮፈሻ  ሳይሆን በቃ ለዕለት ተለት የአይምሮ ምግቡ  እየሰፈረ የሚመገበው ነው። ከዚያ የሚገኘውን ጉልበት እንዴት  ለሕይወት ጥያቄዎች መልስ መፈለጊያነት  እንደሚተረጉመውም አሳምሮ ያውቅበታል። እንኳን ከመፅሀፍ ከጉዋደኛ የሰማውን በራሱ እውቀትና ባካባቢው አቅምና ቋንቋ  አዋዝቶ  ያወርደዋል እንጂ አንዱንም  በደረቁ  ቃል በቃል ደግሞት አያውቅም። ለዚህ አይነቱ ሰብዕና   ስነ- ጥበብን ማወቅም ሆነ ማድነቅ፣ ማክበርም ሆነ መደገፍ እንግዳም ትርፍ ነገርም አይሆንም ።
አንድ ቀን ምሽት ጋዜጣው ሊታተም በጣም ጥቂት ቀናት ሲቀሩት፣ እነ አሰፋ በርከት ብለው ከሚያወኩበት ቦታ ስልክ ካንዳቸው ዘንድ ይደወልልኛል። ጌታ ይመስለኛል ደዋዩ። “አሁን ርዕሱ ላይ ደርሰናል። አሁን ሁላችንም  የወደድነውንና ጥሩ የመሰለንን ርዕስ እየሰነዘርን  ነው። ለምሳሌ  አዲስ ….. “ ብሎ ሳይጨርስ ካፉ ቀልቤ …” በቃ እንግዲህ  ጀመራችሁ ገብረ-ማርያም ሲባል ወልደማርያም ማለት ደስ አይልም …አዲስ ዘመን እዚያ ጋ ስለሚታተም እዚህ  ጋ የግድ አዲስ -ዓለም ፣ አዲስ-ማተብ እያልን መቀጠል አያምርብንም--”
እያልኩ  ትንሽ ተሞጣሞጥኩ። በስብሰባም ይሁን በሻይ ጨዋታ ላይ፣ ነገራችን  ሁሌም
 ከድርቀት የነፃ ነበር። “በመሰረቱ-- በዋናነት---በአዋጭነት ….” ብሎ ንግግርን ፊት ሰጥተነው አናውቅም።
በዚያ ምሽት ካልዘነጋሁ እነ ነቢይ፣ እነመስፍን እና ሌሎችም አብረው የነበሩት ሁሉ ብዙ ቀልዶችና ሐሳቦች ሰነዘሩ ።ግፋ ቢል ሁለት ቀናት ፈጀ መሰለኝ ፣ ወዲያው የመጀመሪያዋ አዲስ አድማስ ታትማ ወጥታ፣ ሁላችን በጣም ተደሰትን ። ያኔ ያሽሟጠጥኩባት “አዲስ”  እነሆ  ከዚያም በሁዋላ  ስንትና ስንት  አዲሶችን ፈለፈለች ። አዲስ ነገር ። አዲስ ጉዳይ …..እና ሌሎችንም።

Read 1364 times