Wednesday, 11 March 2015 11:09

ፀሐይ

Written by  ትግስት ተፈራ
Rate this item
(0 votes)

(የአዲስ አድማስ 15ኛ ዓመት የአጭር ልብወለድ ውድድር አሸናፊ)

   በጠዋት መሥሪያ ቤት ስገባ ሰው ሁሉ የሆነ ነገር ሊነግረኝ ፈልጓል፤ የሆነ ነገር፡፡ ምን? ማወቅ አልቻልኩም፡፡ አለቃዬ ምን አዲስ ህግ አወጣ? ሰሞኑን ምን ተሳሳትኩ? ምን?  ለሳምንት ከከተማ ውጪ ነበርኩ፤ ግን በወጉ አስፈቅጃለሁ፤ ምን ሊሉኝ ይሆን? እየፈራሁ እነሱም እየፈሩኝ እንዲሁ የተለመደ የቃል ሰላምታ እየሰጠሁ ወደ ቢሮዬ ሽሽት …..
የአስተዳደር ቢሮውን አልፌ ፋይናንሶችን በርቀት ሰላም ብዬ፣ የቢሮዬን ቁልፍ ስጫን ሁሉ አንድ ነገር እየጠበቅሁ ነው፡፡ የሆነ ነገር ሹክ የሚሉኝ መሰለኝ፡፡ ገና ቁጭ እንዳልኩ ማርታ መጣች፡፡
 “አንቺ ዛሬ ምን ሆነሻል?” አለች፡፡ ምን ሆኛለሁ? እነሱ ገና ስመጣ ለምን ተያዩ?
“እ---ምንም-- ያው ታውቂ የለ-- ሰው ሰብሰብ ሲል አልወድም እኮ …” አልኩ፡፡
“እነሱማ ምንም ቢሆን ይመለከትሻል ብለው….”አለች፤ ያለ ሥራዋ ጠረጴዛዬ ላይ የተቀመጡትን የጽሕፈት መሣሪያዎች እያስተካከለች፡፡ ምንድን ነው እሚመለከተኝ?
“ማለት…”
“የዮኒን ነገር አልሰማሽም አይደል?” እጇ ከጠረጴዛው ላይ መንከላወሱን ሳያቆም አፍጥጣ እያየችኝ፡፡
“ምን ሆነ ዮኒ?”
 ዮናስ ባልደረባችን ነው፤ ራሱን ይኮፍሳል የሚል ስም ተሰጥቶት ብዙዎች ፊት እንደሚነሱት አውቃለሁ፡፡ አለቃችንም በተደጋጋሚ፤ “ለራስህ የሰጠኸውን ግምት አስተካክል፤ራስህን እንደ ፈላስፋ ታያለህ” ብሎታል፡፡ አባረረው እንዴ?
“ማስታወቂያ ሰሌዳው ላይ ስትገቢ ምንም አላነበብሽም?” ጠየቀችኝ፡፡
 “አላነበብኩም” አልኳት፤መባረሩን እርግጠኛ ሆኜ፡፡
“ዛሬ በምሳ ሰዓት ቤቱ እንሔዳለን፤እናቱ እኮ አረፉ” አለችና ፊቷን ቅጭም አደረገች፡፡ ስለ ሞት ሲነገር ፊት እንዲህ ቁጥር ማለት እንዳለበት አጥንታለች፡፡
“ሞቱ?” ሳላስበው ጮኽኩ፡፡ በአካል አላውቃቸውም። እረፍት ከመውጣቴ ከአንድ ሳምንት በፊት ምሳ ሰዓት ላይ እንደተለመደው “እናቴ ቡና አፍልታ ምሳ አቅርባ እየጠበቀችኝ ነው” ብሎ ሔዷል፤ ከሳምንት በፊት ለእናቱ አንድ አዲስ የወጣ የልቦለድ መፅሐፍ አንብቦላቸው እንዳለቀሱ ነግሮኛል፤ ከአንድ ሳምንት በፊት የከሰዓት ሥራ መግቢያ የሰዓት ፊርማ ተነስቶበት፣እናቱ የድሮ የልጅነት ትዝታቸውን ሲያወሩለት እንዳረፈደ ነግሮኛል፤ ከሳምንት በፊት…..
ገና ብዙ ብዙ ጥያቄ ለማርታ ላቀርብላት ስል፣ ሔዋን በሩን በርግዳ ያፈነችው ሳቅ ፊቷን ወጥሮት ገባች፡፡
 “ዮናስ እኮ ዛሬ ሥራ ገባ” ብላ ሳቋን ለቀቀችው፡፡ የፊቷ ግት ረገበ፡፡ ማርታ በሳቁ አገዘቻት፡፡ ገና የመጀመሪያውን ሐዘን ከጉሮሮዬ ሳላወርደው፤ገና እየጮኽኩት እያለ  ሳቅ ይዘው መጡ፡፡
“ደህና አደራችሁ” በተከፈተው በር ዮናስ ገባ፡፡
የእነሱን ሳቅ የሰማ መስሎኝ ደንግጬ፤“ዮኒ አረፈድክሳ?” አልኩ፡፡ ምን ማለት ነው አረፈድክ ማለት? አላውቅም፡፡
“እ…ፂሜን እየተላጨሁ” አለ
ማርታና ሔዋን በሳቅ የተወጠረ ግታቸውን ይዘው፣ጥግ ፈልገው ከሌሎች ጋር ሳቅ ሊያልቡ ተሰወሩ፡፡ ሀዘን በጢም ውስጥ ብቻ ያደፍጥ ይመስል መላጨቱ እንደሚያስቃቸው ሳስብ በገንኩ፡፡ የእሱ የሀዘን ድምፅ ከሰላምታው ይጀምራል፡፡ “ደህና አደራችሁ” ሲል ድምፁ ውስጥ ሀዘኑ ታውቆኛል፡፡ ሁሉ ነገር እንደነበረ የማስመሰል ጥረት …. እሱ ግን ማስመሰል አያውቀውም ነበር፡፡
ቀና ብዬ ላየው አልደፈርኩም፡፡ ዝም ብዬ ሥራዬን ጀመርኩ፡፡ ዝም ብሎ ኮምፒውተሩን ከፈተ፡፡ ሁለታችንም የሒሳብ ባለሙያዎች ነን፡፡
ከሰዓታት በኋላ ሒሳብ ልክ አልመጣልኝ ሲል “……….” ብዬ ጠየቅሁት፡፡
“…….” ብሎ መለሰልኝ፡፡ ግን ልክ አልነበረም፡፡ እሱ ሒሳብ ተሳስቶ አያውቅም፡፡
ዮናስ እናቱ በሞቱ በሠልስቱ ሥራ ገባ፡፡ በየኮሪደሩ ተወራ፤
“ኸረ ምን አይነት አንጀት የሌለው ሰው ነው?”
“ሥልጣኔ ተብሎ ነው እንጂ….”
“የሆነ ልዩ ልሁን ባይ ነው-- ሲያስጠላ….”
“እና እንደ ደንቡ እናዋጣና ….” ስትል ገና አንዷ፤
“ኸረ ወደዛ ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ….አሉ” ተቀባብለው፤ለሀዘኑ ክብር እንደሌለውና እሱን ማስተዛዘንም ክብር እንደሚነካ ተወያዩ፡፡
ምንም ሳልለው ቀናት ተቆጠሩ፡፡ በጠዋት ቢሮ ይገባል፡፡ ከእኔ ጋር ሰው ቢኖርም ባይኖርም “ደህና አደራችሁ?” ይላል፤መልስ አይጠብቅም፡፡ መልስ አይፈልግም፡፡
የሰላምታ ልማድ የለውም፡፡ ይኼ የሰሞኑ ትህትና ከየት መጣ?
በዝምታ እየሰራን ግር ሲለኝ እጠይቀዋለሁ፤ ይመልሳል ግን ትክክል አይሆንም፡፡ ስለ እናቱ አንዳች አልጠየቅሁም፡፡ እነ ማርታ፣ ቤት መምጣት እንፈልጋለን ብለውት፣አያስፈልግም እንዳለ ሰምቻለሁ፡፡
ከሳምንታት በኋላ ድንገተኛ ዝናብ አባሮኝ፣ዋቢ ሸበሌ ሆቴል በር ላይ ከዝናብ ተጠለልኩ፡፡ ዝናቡ ድንገተኛ አይመስልም፤ ቀና ብዬ ሰማዩን አየሁ፡፡ ሰማይ ላይ የግራር ሥር የመሰለ ነገር ብልጭ ብሎ ይጠፋል፡፡ ጃንጥላ የያዙ ሴቶች ሳይቀሩ እየተሯሯጡ ጥግ ይይዛሉ፡፡ በቅፅበት አስፋልቱ ጭር ብሎ ጥግ ጥጉን የቆመው ሰው ቆፈን ያሳደደው ቆጥ ላይ የወጣ ዶሮ መሰለ፡፡ መኪኖች ሳይቀሩ ደመናው ያዘለውን ዝናብ ሽሽት ጥግ እየያዙ ቆሙ፡፡ በኃይል ዘነበ፡፡ ጎርፉ የመኪኖቹን ጎማ ለመሸፈን ብዙ ደቂቃ አልፈጀበትም፡፡ ዘመኑ 2007 መሆኑን ህንፃዎቹና መኪኖቹ ባይኖሩ ማወቅ የሚቻል አይመስልም፡፡ ያ የኖህ ዘመን….
በዚህ መሀል አንድ ሰው ከሩቅ እጁን ኪሱ ከትቶ፣ አስፋልቱን እየተንቀባረረበት ጎርፉን እየለጋ ይመጣል፡፡
“አያችሁ ያንን እብድ--- ለእሱ ፀሐይ ወጥቷል” አለ አንዱ፤ ወንድ መሆኑን በድምፁ ብቻ አወቅሁ እንጂ በብዙ ዝናብ ፈሪ ሰው ተከልሎ አልታየኝም፡፡ ጭር ባለው አስፋልት ዝናብና አንድ ሰው ብቻ ነበሩ፡፡ ሰውየው እየቀረበ ሲመጣ አለባበሱ ሙሉ ነው፡፡ ፀጉሩ አናቱ ላይ ሰጥሟል፡፡ ፊት ለፊቱ መንገዱን እያየ እጁን ከኪሱ ሳያወጣ ይጓዛል…. እየተንቀባረረ…. ዝናቡን በካልቾ እየለጋ…… እያንቦጫረቀ…..
አልፎኝ ከሄደ በኋላ “ዮኒ” ብዬ ጮኽኩ፡፡ አልሰማኝም፡፡
“ዮኒ” ሮጥኩና ወደ ውሃው ገባሁ፡፡
ከኋላዬ ብዙ ሳቅ ነበረ፡፡
“ዮኒ…..ዮኒ…..” እያለከለኩ አስፋልቱን የሸፈነው ጎርፍ ውስጥ በቁሜ እየዋኘሁ፣ ነጭ ረጅም ቀሚሴ ከኋላዬ እየተንሳፈፈ ደረስኩበትና እጁን ያዝኩት፡፡ “ዮኒ…” ፈገግ ያልኩ ይመስለኛል፡፡
“እ--” ለአፍታ ቆም አለና አይቶኝ ትርጉም የሌለው ሳቁን ሳቀ፡፡ ድሮም ድንገት ይስቃል፤ሳቁ ልምድ እንጂ ስንቅ አይመስለኝም ነበር፡፡ መንገዱን ቀጠለ፡፡ እጁን እንደያዝኩ ተከተልኩት፡፡ ኖህ ፈርቶ ረጅም አመት ደክሞ የሰራው መርከብ አላስፈለገንም፡፡ በጎርፉ በቁማችን እየዋኘን ወደ ፊት አልን፡፡
በዝምታ ጥቂት እንደተጓዝን፤ “ቁርስ ግን በልተሃል?” አልኩት፤የምለው ጠፍቶኝ እንጂ ቁርስ እንደማይወድ አውቃለሁ፡፡  
“እንደ ዛሬም በልቼ አላውቅ” ሲል የሚያሾፍ መሰለኝ፡
“ፀሐይ ከሞተች ጀምሮ ቁርስ ሳልበላ ወጥቼ አላውቅም ” ሲል ግር አለኝ፡፡
“እንዴ -- ድሮ ማዘር ስለማይሰጡህ ነበር ማትበላው?” አልኩ፤ለቅሶ ሳልደርሰው፣ ቁጭ ብዬ ሳላዋየው ደፍሬ ስለ እናቱ ሳወራ ለምን እንዳልከበደኝ አላውቅም፡፡  
“እሷ ቁርስ እንደማልወድ ታውቃለች”
“እና አሁን ወደድክ?”
“እሷ እያለች እኮ ‘ማልበላው ለምሳ ስመለስ፣ ቡና አቀራርባ ቁርስ አዘጋጅታ እንደምትጠብቀኝ ስለማውቅ ነው፡፡ አሁን ቁርሴን ባልበላ ድጋሚ ምግብ ለማግኜቴ ምን ዋስትና አለኝ?” አለኝና ያን የማልወደውን ሳቅ ሳቀ፡፡
“እ… ከባድ ነው” አልኩ፤ኪሱ የወሸቀውን ክንዱን እንደያዝኩ፣ጎርፍ እያጀበን ቀሚሴን እያንሳፈፍኩ እንሄዳለን፡፡
“ከባድ ብቻ ?” መልሶ ጠየቀኝ፡፡
“ፀሐይን ለዘላለም እንደማላገኛት እርግጠኛ መሆን ከባድ ብቻ?” አለ
“አንተ እኮ ቶሎ ሥራ መግባት የለብህም ነበር፤ፈቃድ ወስደህ ትንሽ ጊዜ ብታርፍ--” በዚያውም ከሰው ትችት ባድነው ብዬ የሰነዘርኩት ሃሳብ ነው፡፡
“ምን ላድርግ ቤት መዋል አልቻልኩም፤ ሰዎች የእናቱን ሀዘን ሳይጨርስ በሰልስቱ ቢሮ ገባ ይላሉ፤እኔ እኮ ግን እስካሁን ቢሮ የለሁም ” አንዴ ብቻ ከደረት ተነስታ ሳቅ መስላ የምትወጣ ጩኸቱን አሰማ፡፡
“እሳቸው ሲሞቱ አንተ የት ነበርክ?”
“ቢሮ… ቢሮ ነበርኩ” አለ ችኩል ብሎ
“ተደውሎልህ ነዋ?”
“ጎረቤቶቻችን ደውለው-- ና --- ፀሐይ አሟታል አሉኝ፤ ደንግጬ ወዲያው ወጣሁ…አንዳንዴ ልቤ ላይ ወጋኝ ብላ ጥቂት አረፍ ስትልበት ይለቃታል፡፡ ባሰባት ማለት ነው? እያልኩ ሰፈራችን ያለ ጤና ጣቢያ ስበር ደረስኩ፡፡ የሰፈሬ ልጆች እዚያው አካባቢው ዮኒ ሰላም ነው ብለው አክብረው ሰላም ሲሉኝ መደንገጥ ጀመርኩ፤ እንዲህ ተከባብረን አናውቅማ…ወደ ጤና ጣቢያው ስገባልሽ፣ እነ ወ/ሮ ትብለፅ ሁሉ ነጠላቸውን አዘቅዝቀው አደግድገው ….” የያዝኩት እጁ የተንቀጠቀጠ መሰለኝ፡፡
“ምንድን ነው ፀሐይ የታለች-- የታለች እናቴ-- እያልኩ በኃይል ጮኽኩ፤ ቁጭ በል ቁጭ በል እያሉ ብዙ እጆች ሊያንበረክኩኝ ይጥራሉ፡፡ እኔ ዝም ብዬ የታለች ፀሐይ-- የታለች-- ስል አንዷ ጎረቤታችን ሞታለች ዮናስ ቻል አድርገው አለች፡፡ እንዲህ ማለቷን ከሰማሁ በኋላም የታለች  ፀሐይ፤ የታለች እላለሁ ዝም ብዬ” አለና ያን እርጉም ሳቁን ሳቀ፡፡
ዝም አልኩት፡፡
“ከዛ ወጥቼ ሮጥኩ”
“ወዴት?”
“እንጃ ግን ከጤና ጣቢያው ግቢ ዝም ብዬ እየሮጥኩ ወጣሁ….እነዛ መንገድ ላይ በአክብሮት ሰላም ያሉኝ አብሮ አደግ ጓደኞቼ ከየት እንደመጡ እንጃ ያዙኝ” እጁ በኃይል ተንቀጠቀጠ፡፡ የእኔ እንባ ከዝናቡ ጋር ፊቴን ያጥበዋል። እሱ እያለቀሰ ያውራኝ እንዲሁ ያውራኝ መለየት አልቻልኩም፡፡
“እናቴን እንደ ወንድ ልጅ ጋቢ ተከናንቤ-- ፊቴን አጥቁሬ-- ሰው እየተከተልኩ አይደለም የሸኘኋት-- ሰውነቴ ሁሉ ውሃ እስኪመስለኝ ድረስ አልቅሻለሁ፡፡ እንባዬ ለአፍታ እንኳን ለዘላለም የሚቆም አልመሰለኝም ነበር-- እሁድ ሰውነቴ ድቅቅ ብሎ እንቅልፍ እንቅልፍ ሲለኝ ዋለ፤ ሰኞ በጠዋት ሰዎች መ‘ተው አሟት ነበር? ብለው መላልሰው ሲጠይቁኝ --- ምን ላድርግ? ብድግ ብዬ ቢሮ ሄድኩ” አለና ዝም አለ፡፡
‘አይዞህ ሞት በሁሉም አለ፤ ዋናው በህመም አለመሰቃየታቸው ነው፣ እኛ ሁላችንስ ወደዚያው አይደለን …’ ልለው አሰብኩና ተውኩት፤ ሁሉም ቃላት አጉል እኔን ያደክሙኛል እንጂ እሱን አያፅናኑትም፡፡ ዝም እንዳልኩ እሱ ቀጠለ፡፡
“እሷ እያለች የማታውቀው ነገር ሁሉ ላይ አሁን የሚያገባት ይመስለኛል፤ አሁን ይኼ ዝናብ እሷ ስለሌለች ሆን ብሎ የሚመታኝ ይመስለኛል፡፡ ሰማዩ ብልጭ ሲል ሆን ብሎ እሷ ስለሌለች ሊያስደነግጠኝ የፈለገ ይመስለኛል፡፡ እሷ ከሞተች ጀምሮ እንኳን የቤቱ የሆቴል ቤቱ የምግብ ጣዕም የተለወጠ ይመስለኛል… እሷ እኮ ግን ያን ሆቴል ጨርሶ በእግሯ ረግጣው አታውቅም” ብሎ ያችን ሙት ሳቁን ሳቀ፡፡
“ሞት እንዲህ ከባድ ይሆናል ብዬ አስቤ አላውቅም፡ ለእናቴ እንዲህ ሳላደርግላት፣ እንዲህ ሳልሆንላት የምለው ነገር ኖሮ አይደለም በጣም ያዘንኩ፤ ግን በቃ ናፍቆቷን አልቻልኩትም፤ በጣም በጣም ትናፍቀኛለች… እናቴ በተለይ ምሳ ሰዓት ላይ ቡና አፍልታ ስትጠብቀኝ ጎረቤት እንኳን አትጠራም ነበረ፡፡ ለእነሱ ሆን ብላ ጠዋት ጠዋት ቡና ታፈላለች፡፡ ለምን እንደሆን ታውቂያለሽ? እኔ እና እሷ ብቻ ስንሆን ደስ ይላታል፡፡ ልጅነቷን ታወራኛለች፣ ልጅነቴን ታወራኛለች፣ አንዳንዴ ደግሞ መፅሐፍ አነብላታለሁ … ቀብር ወይ ሌላ አስገዳጅ ነገር ካልገጠማት እናቴ በህይወቷ የማስታስተጓጉለው ቀጠሮ ምሳ ሰዓት ከእኔ ጋር ማሳለፍን ነው፡፡ ፀሐዬ እኮ ምንም ደብቃኝ አታውቅም ነበረ፡፡
አየሽ ያን ቀን እንደምትሞት አለማወቋ እንዴት እንደሚያስጠላ? ብታውቅ እኮ ቁርሴን በግድ ታበላኝ ነበር፤ ሌሊቱን ሳንተኛ የጀመርኩላትን መፅሐፍ እጨርስላት ነበር፣ቡናውን በጠዋት ተነስተን እንጠጣ ነበር…” አለና አሁንም ሳቀ፡፡
ሄደን ሄደን ጦር ኃይሎች ደርሰናል፡፡ ዝናቡ አባርቶ ልስልስ ያለች የማትጠገብ ፀሐይ ወጣች፡፡ እጁን ለቅቄ ንክር ልብሴን  መጭመቅ ያዝኩ፡፡
“አየሻት ፀሐዩዋን--ጭፍግግ ያለውን ሰማይ እንዴት በፈገግታ እንዳጥለቀለቀችው አየሽ…” ቀና ብዬ ሰማዩን እንዳይ ወተወተኝ፡፡
ረጅም መንገድ ሲያለቅሱ የነበሩ ዓይኖቼ ፀሐዩን መቋቋም ስላልቻሉ እንዳንጋጠጥኩ ጨፈንኳቸው፡፡
“አየሽ የኔ ፀሐይም-- የኔን በሥራ -- በኑሮ የደከመ ልብ ምሳ ሰዓት ላይ እንዲህ ነበር ወገግ የምታደርገው” ሲል አይኔን እንደጨፈንኩ የእሱን ፀሐይ አየሁ፡፡

Read 1419 times