Wednesday, 11 March 2015 11:12

አልቀርም መንኩሼ

Written by  የማነ ብርሃኔ
Rate this item
(0 votes)

(የአዲስ አድማስ 15ኛ ዓመት የግጥም ውድድር አሸናፊ)

አልቀርም መንኩሼ
ከዝምታሽ ገዳም
ጠርተሽኝ - ምናኔ፣
እንቢ ብዬ እንዳልቀር
ፈርቼ ኩነኔ፡፡
ብመጣም ዝምታ
ድርብ ተሸምኖ፣
ከገላሽ ላይ ውሏል
ካባ ጃኖሽ ሆኖ፡፡
መች አሰብኩ ለሆዴ
ብኖር ከገዳሙ፣
ሥራስሩን ምሰው
ፍሬ እየለቀሙ፣
ጥራጥሬ ቆልተው
… እየቆረጠሙ፣
ሰርክ እየማለዱ
በፀሎት በፆሙ፣
ሥጋን ወዲህ ጥለው
ነፍስን እያከሙ፡፡
መች ጠላሁ ለመኖር
ፅድቅን እያሰቡ፣
መንፈስ የሚያሸፍት
ሆነ እንጂ ድባቡ፡፡
ከዝምታሽ ገዳም
ዝምታሽ ጨምቶ፣
እርቃኑን ካልቀረ
ካባ-ጃኖ ትቶ፡፡
በሳቅ ካላፈካው
ድባቡን ለውጦ፤
ዝምታሽ ካልዋጠው
ዝምታን አላምጦ፡፡
ልውረድ ከመቀመቅ
ያብቃኝ ለኩነኔ፣
መንኩሶ ከመቅረት
ይሻለኛል ለኔ፡፡  

Read 1040 times