Wednesday, 11 March 2015 11:14

አድማስና እኛ

Written by  ነቢይ መኮንን -
Rate this item
(0 votes)

    አዲስ አድማስ ጥንስሱ የተጠነሰሰው፣ በተሟሸና በታጠነ ጋን ነው! ከፕሬስ ህጉ ጋር በተያያዘ የተነሱትን ጋዜጦች አስተውለን፣ የአንባውን አቅምና የወቅቱን አየር አጢነን፣ የሀገራችንን የዕድገት ደረጃ መዝነን፣ አዕምሮአችንን በወጉ አትብተን ስለተነሳን ነው በተሟሸ በታጠነ ጋን ነው የጠነሰስነው የምንለው!
መረጃ መስጠትና ማዝናናት ዋና ዓላማችን ነው Infotainment! ለምን? መረጃ አጥቷል ወይ ህዝቡ? አዎን አጥቷል! የሚያዝናናውስ ነገር አጥቷል ወይ? አዎ ነው መልሱ፡፡ መዝናኛው ግን መገለጢጥ (Unseasoned‚ untrimmed) መሆን የለበትም፣ አልን፡፡
እኔና አሰፋ ጎዳዬ (አሴ) ቀደም ብለን ብንተዋወቅም፣ በሥራ መንፈስ አልተሳሰብንም ነበር፡፡ ልብ ለልብ መግባባታችንን ግን በቅጡ አውቀናል፡፡ ከአንድ ኢ.ሲ.ኤ (ECA) ካለ ወዳጄ ጋር በተመካከርነው ሀሳብ መነሻነት አንድ የኮሙኒኬሽን የሽርካ ኩባንያ (Share Holders Company) ልናቋቁም አቅደን ሁላችንም ወደምናውቃቸው ወዳጆች እንሂድና አባላት እናሰባስብ ተባባልን፡፡ በዚህ መሰረት እኔ ከቅርብ ወዳጆቼ መካከል ወደ ሆነው ወደ አሰፋ ጎሳዬ ሄድኩኝ፡፡ ሀሳቡን ወዶታል፡፡ ግን እሱ በልቡ የያዘው ጉዳይ አለው፡፡
“የአክሲዮኑ አባል ለመሆንና ገንዘብ ለማዋጣት እችላለሁ፡፡ ያ ግን ውስጤ ያለውን ሀሳብ እንደማያዳክመው ተስፋ አደርጋለሁ” አለኝ፡፡
“ምንድን ነው ሀሳብህ? በግልፅ ንገረኝ?” አልኩት፡፡
“አንድ ጋዜጣ መፍጠር አለብን”
“ምን አይነት?”
“ለአንተ የሚመችህን ዓይነት”
“እንደዛ ከሆነ እኔ የማስበውን ልንገርህ” አልኩት፡፡ “Cultural revolution lags behind. Politics is the concentrated form of economics” የሚለውን ማርክሳዊ አካሄድ በኢትዮጵያ መንፈስ ሳስበው ገና ያላጸደቅነው፣ ያልሰለቅነው ብርቱ ሀሳብ ያለ ይመስለኛል፡፡ እንደ ሀገራችን ሁኔታና የዕድገት ደረጃ ከሆነ ለእኔ ዋናው ቁምነገር ባህል ነው - ቀዳሚ ነው! ባህላዊ ግንዛቤያችን በቅጡ ካልተውጠነጠነ ማናቸውንም ዓይነት ፖለቲካ ብንጭንበት ባዕድነቱ አይቀሬ ነው፡፡ በቀላሉ አይዋሃደንም፡፡ እንዲያውም በአንዳንድ አንፃር ከነአካቴው ዘይትና ውሃ ይሆናል፡፡ ባህልን ጉዳዬ ብለን ብናሰላ፡- አንደኛ/ የራሳችንን ስነልቦና የምናወጣበት መላ እናገኛለን፡፡ ሁለተኛ/ ባህላዊ እሴቶቻችንን ማሳያና ማጎልበቻ መላ እንፈጥራለን፡፡ ሶስተኛ/ በባህላዊ መንገድ የልባችን የምንለውን ፖለቲካዊ ጉዞ እንዳስሳለን፡፡ የራሳችንን ታላላቅ ሰዎች እናሳውቃለን፡፡ Guided democracy (መሪ የፈቀደው ዓይነት ዲሞክራሲ)ም ሆነ Tailored democracy (በልካችሁ እንስፋላችሁ የሚባል ዲሞክራሲ) እንደማይጠቅመን ማስረጃ እናቀርባለን፡፡ ውለን አድረንም የራሳችንን ልበ - ሙሉ ዲሞክራሲ (Full – fledged and focused to our advantage) የሚያሳይ ጋዜጣ ብቻ ሳይሆን የህዝብ ሀሳብ ማንሸራሸሪያ መድረክ እንፈጥራለን” አልኩት፡፡
“ዕውነት ነው፡፡ ማንም ሀሳቡን የሚያሰፍርበት ጋዜጣ ነው መሆን ያለበት!” አለኝ፡፡
“አዎ ግራም ይሁን ቀኝም የእኔ ነው ብሎ አምኖ ህዝቡ ፅሁፉን መላክ አለበት፡፡ የእኔ ነው ብሎ ማመንም አለበት”
“ስለዚህ ‹የእርሶና የቤተሰብዎ ጋዜጣ› ብለን ማስረዳት አለብን” አለኝ አሴ፡፡
“ምንም ወደኋላ የማልልበት ጉዳይ ነው፡፡ አሁን ያሉትን ጋዜጦች ግን ባህሪያቸውን ማወቅና የእኛን ጋዜጣ አካሄድ ማስተዋል ይገባናል”
“አንተ እንዴት ታያቸዋለህ?” አለኝ መልሶ፡፡
“አየህ ባሁኑ ጊዜ፤ በሁሉም ረገድ ፅንፍ ብቻ ነው ያለው፡፡ ወይ ነጭ ነው፡፡ ወይ ጥቁር ነው፡፡ እንጂ መካከል ላይ ላለው ህዝብ አልታሰበለትም፡፡ እንደ ሀገራችን ዕሙናዊ ዕውነታ ካየን፣ ከጥንቶቹ ፖለቲከኞች ማለትም ወይ ነጭ ወይ ጥቁር ይልቅ ግራጫው ክፍል (ፖለቲካ አይሻኝም አርፌ ስራዬን ልስራ የሚለው) ይበረክታል፡፡ ይሄንን ክፍል እንዴት እንድረሰው? ምን ዓይነት ጽሁፍ እናቅርብለት?”
አሴ ጉድ ያመጣው ይሄኔ ነው!
“ነቢይ” አለ “አየህ እኔ የጋዜጣ ህልም ያደረብኝ ዛሬ አይደለም፡፡ ድሮ ነው በጣም ድሮ! ደሞ ልብ አለኝ! እሰራዋለሁ!”
ዛሬ ሳስበው የዚያን ጊዜውን አሴ የሚከተለው ግጥሜ ይገልፀው ይመስለኛል፡-
 ነገን ትላንትና ያየ
ዐይን ያለው ሰው የት ይገኛል፣ ነገን ትላንትና ያየ፤
ከወዲሁ ራዕይ ያለው፣ መጪ ክፉ ደግ የለየ?
ቅጠልስ ሳይወድቅ ዕጣውን፣ የሚያውቅ አንጎል የቱ ይሆን?
ችግኝስ ሳይኮተኮት፣ ማደግና አለማደጉን -
ማወቅ የሚችል ማን ይሆን?
አገርስ ታምማ ስትተኛ፣ አሊያም ድና ስትነሳ
ማነው ትንቢቷ እሚገባው፣
ማነው ተረዳሁ እሚለው?
ረብ ያለው ትውልድ ማብቀሏን፣ እናታችን ፍም አውርሳ
በምጧ ልታሳድገን፣ ታርሳ ተምሳ ተክሳ፣
አህያ ወልዳ ማረፏን፣ በለሆሳስ ልታወሳ?!
የተረዳ ሰው ማነው?
አንዳንድ ጥበብ መነሻው፣ ማወቅን አለመፍራት ነው
አንዳንድ ጥበብ መሞቻው፣
አለማወቅን መድፈር ነው!
ማወቅና አለማወቅ፣ ዞሮ ገጠም ቀለበት ነው፤
በማወቅ ውስጥ አለማወቅ
ባለማወቅም ውስጥ ማወቅ
መኖሩን የምናጤነው፣ ድንቁርና ላይ ስንስቅ
ነውና ከዕንባችን ቀድመን፣ የሳቅን እሳት እንሙቅ!!
ያኔ ነው አገራችንን፣ የነገ መልኳን የምና‘ቅ!!
የካቲት 24 2007 ዓ.ም
አሴ ከዚህ በኋላ ነው ገና ጋዜጣው ሳይጀመር ከባሴ ሀብቴ ፅሁፍ ሲገዛ እንደነበር የነገረኝ፡፡ አልፎ ተርፎ የእንግሊዘኛ መጽሔት እየሰጠ ያስተረጉመው እንደነበረም አወኩኝ፡፡ ከእኔም ከዕለታት አንድ ቀን የገዛቸውን ጽሑፎች ለጋዜጣው እንደሚያውል ሚሥጥሩን ሹክ ያለኝ ይሄኔ ነው፡፡ አርቆ ማሰቡ ደስ አለኝ፡፡ አሰፋ ማለት ይሄ ነው!
ከጌታ መኰንን፣ ከበቀለ መኰንን፣ ከተፈሪ ዓለሙ፣ ከሰዓሊ መስፍን …ጋር ሆኖ Addis Art Week የሚባል ህፃናትን መንገድ ላይ ስዕል እንዲሰሩ የሚያደርግ ፕሮግራም ማቀዱን ሳውቅ ደግሞ የባሰውን ኢኮኖሚስቱ (ጉራጌው) አሰፋ፤ ጥበብ የገባው መሆኑን አየሁ፡፡ ይህ ሰው እንደሚገባኝ እሱንም እንደምገባው ያለጥርጥር አውቄያለሁ፡፡ ስለዚህ ጋዜጣ እናዘጋጅ ሲል ግርታ አልነበረብኝም፡፡ ከተለያዩ የቲ-ሩም ቆይታዎችና ብሔራዊ አካባቢ ካለው የአድማስ አድቨርታይዚንግ ቢሮ ፊት ለፊት ዘለዓለም ሬስቶራንት (በተለምዶ እንዳለ ቤት የምንለው ነው) ቆይታ በኋላ፤ ኦርማጋራዥ አጠገብ ወደ አሮጌው ቄራ ሲወጣ በስተግራ፤ የሚገኘው ሙሉጌታ ከበደ ኳስ ተጫዋቹ ቢራ ቤት ከፍቶበት የነበረ ቤት ውስጥ ነበረ የአዲስ አድማስ የመጀመሪያ ቢሮ የተከፈተው፡፡ ከአሴ ጋር እዚህም ጽሑፍ ማከማቸት (Back – log ማዘጋጀት የምንለው) ነበር ሥራችን፡፡
ማርቆስ ረታ፣ ብርሃኑ ንጉሤ፣ ተፈሪ መኰንን፣ ሰለሞን ገ/እግዚአብሔር፣ ሰለሞን ካሣ፣ አበበች ካሣ እና ከአዋሳ የመጣችው ፀሐፊያችን የውብዳር በቀለ ናቸው የሥራ ባልደረቦቻችን፡፡ እንዲያው ለወጉ የሥራ ባልደረባዎች እንባባላለን እንጂ ባልንጀራሞች ነን ብል ይቀላል፡፡ እኛ አርቲክል (ሐተታ) ስንፅፍ እንቆይና በሁለት ሶስት ቀን ውስጥ አሴ ይመጣና Where is my beef? ይለናል፡፡ ምሴን ስጡኝ! ምን አዘጋጃችሁልኝ፤ እጃችሁ ከምን? ማለቱ ነው፡፡ ይሄ እንግዲህ ያፋጥጠናል! ግን እየተግባባን እንደሆነ በበኩሌ ጥርጥር አልነበረኝም! ሌሎቹ ከእኔና ከአሴ በዕድሜ ያንሳሉ - ምናልባትም በፖለቲካ ልምድ! በእኔና በአሴ ዕምነት ነጭና ጥቁር ትተን ግራጫውን ንፍቀ ክበብ እንሸፍን የሚለው ሃሳብ ኒሻን ጋዜጣና ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ሲፅፉ ለነበሩት ለባልንጀራ ጋዜጠኞች ግር ማለቱ አይቀሬ ነበር - ዞሮ ዞሮ ግን የጋዜጦቹን አምዶች ስንከፋፈል ሁሉም የየፊናቸውን እንደማያጡ እኔ እርግጠኛ ነበርኩ፡፡
ጋዜጣችን፤ የፊት ገፁ የዜና፣ ሁለተኛ ገጽ - የት እንሂድ፣ ሦስተኛ ገፅ የሰሞኑ አጀንዳ፣ አራተኛ ገፅ - ርዕሰ አንቀፅና መልዕክቶቻችሁ፣ አምስተኛ ገፅ - ነፃ አስተያየት፣ ስድስተኛ ገፅ - ምን ይሻላል? (ሳይኮሎጂ) ሰባተኛ ገፅ - ባህል፣ ስምንተኛ - ሥራ፣ ዘጠነኛ - ትምህርት፣ አሥረኛ - ንግድና ኢኮኖሚ፣ አሥራ አንደኛ - ሳይንስና ቴክኖሎጂ፡፡ አሥራ ሁለተኛው - ዋናው ጤና፣ አሥራ ሶስት - ጥበብ ገፅ፣ ሃያ - ስፖርት አድማስ፡፡ ከእነዚህ አምዶች ብዛት የምንረዳው ምን ያህል ለጋሥ አምዶችን ይዘን እንደተነሳን ሲሆን፤ ለመስሪያቤታችን ብረት መዝጊያ ናቸው ከምንላቸው ቋሚ ሰራተኞቻችን ሌላ፤ እንደ ባሴ ሀብቴ፣ አዶኒስ፣ ስብሃት ገ/አግዚአብሔር፣ ኤፍሬም እንዳለ፣ ተሾመ ገ/ሥላሴ፣ ደራሲ መስፍን ሀ/ማርያም፣ አብደላ ዕዝራ፣ ሰአቸ፣ ጌታቸው አበራ፣ ዶ/ር ሱራፌል ከበደ፣ አልአዛር ኬ፣ ዮሐንስ ሰ.፣ አብዱልመሊክ፣ አሰፋ ጫቦ፣ ሰለሞን በቀለ (ስፖርት)፣ በቀለ መኰንን፣ አየለ እሸቱ፣ እንዳለጌታ ከበደ፣ በዕውቀቱ ስዩም፣ መሀመድ ኢድሪስ፣ ህሊና ተፈራ፣ እቱ ገረመው፣ እዝራ እጅጉ፣ ተፈሪ ዓለሙ፣ ብርሃኑ ገበየሁ፣ ዳዊት ፀጋዬ፣ ዳደ ደስታ፣ ከበደች ተ/አብ፣ አሸናፊ ዘደቡብ፣ ዳንኤል በላቸው፣ ላምሮት፣ ገነት ግርማ፣ ዶ/ር ሚካኤል ታምሩ፣ ዶ/ር የሺጥላ…ፀዳለ-ጥበብ…ከበደ ደበሌ፣ ቢልቄሣ፣ ሰለሞን ዋሲሁን፣ እመቤት አብዲሣ ወዘተ…ያሉ ድንቅ ፀሐፊዎች ነበሩ ጽሑፍ የሚያዋጡልን፡፡ እኛን እኛ ያደረጉን እኒህ ሁሉ ነበሩ፡፡ በብርቱው እናመሰግናቸዋለን፡፡
ሴንትራ ሸዋ ሆቴል ፊት ለፊት ባለው ቢሮአችን ነበር የጋዜጣ ህትመት ሥራን ሀ ብለን የጀመርነው፡፡ ርኩቻውን፣ ግድፈቱን፣ ማምሸቱን፣ ማንጋቱን ከሞላ ጐደል ሠራተኛው ሁሉ ተጋርቷል፡፡ በአሴ በኩል የምናውቃቸው ጓደኞች ሳይቀሩ አብረውን አምጠዋል፡፡ እጅግ እናመሰግናቸዋል፡፡ እንደ ሰዓሊና ገጣሚ መስፍን ሀብተማርያም ያሉትን የአዕምሮ ሀብቶች መዘንጋት አይቻልም፡፡ እንደ አብርሃም ረታ (ዲቸራ ቀንዶ) ያሉትን ባለሰፊ ምናብ ፀሐፊ ምኔም መርሳት አይቻልም፡፡
አዲስ አድማስ አዲስ ጠላ ለመጥመቅ የተሰባሰቡ አዕምሮዎች ውጤት ነው፡፡ ባህላዊና ጥበባዊ እሴቶችን ለማበልፀግ የተጣረበት ነው፡፡ ወጣት ገጣሚያንን ለማብቃት የአዕምሮ ቀለም አፍስሰናል፡፡ አንድም በመረጃ አቅርቦት፣ አንድም በማዝናናት ብፅዓት፣ የማንበብ ባህል እንዲያድግ የበኩላችንን አዋጥተናል፡፡ የእኛ ጋዜጣ የመቻቻል መናኸሪያ ነው፡፡ ኃላፊነት የሚሰማው ሥነጽሑፍ የመሆን ትጋታችን የተሳካ ይመስለናል፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን አሁንም በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ጋዜጣ ነውና ፀሐፊዎች ናቸው ጉልበታችን፡፡ አንባቢያችን ነው ኃይላችን! የአዲስ አድማስ ዓላማ ዛሬም ኢንፎቴይመንት ነው! እንደሁልጊዜው፤ ስላነበባችሁን ከልብ እናመሰግናለን!!

Read 1656 times