Saturday, 21 March 2015 10:29

ከበደች ተክለአብ አርአያ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ሰዓሊ፣ ቀራጺ፣ ገጣሚ፣ የዩኒቨርሲቲ መምህር
  የስነጥበብ ትምህርት መማር የጀመርኩት በአዲስ አበባ የስነጥበብ ትምህርት ቤት በ17 ዓመቴ ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር፣ በስነጥበብ ሙያ እተዳደራለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር፡፡ ስነጥበብን የመስራት ፍላጎት ብቻ ነው የነበረኝ፡፡ ህይወት ግን መንገዴን ወደ ስነጥበብ አቅጣጫ መራችው፡፡ በደርግ የአገዛዝ ዘመን በተካሄደው የተማሪዎች ንቅናቄ ተሳትፎ በማድረጌ መታደን ስጀምር፣ በጅቡቲ በኩል ለማምለጥ ሞከርኩ፡፡ ይሄም ሆኖ ግን በወቅቱ ሶማሊያና ኢትዮጵያ በድንበር ግጭት ውስጥ ስለነበሩ፣ ድንበር ላይ የነበሩ የሶማሊያ ወታደሮች በቁጥጥር ውስጥ አዋሉኝ፡፡ ቀጣዮቹን አስር አመታት ያሳለፍኩት በሶማሊያ እስር ቤቶችና የጉልበት ስራ ካምፖች ውስጥ ነበር፡፡ ህይወት ግን ለሁሉም ነገር ምክንያት ነበራት፡፡ “በገሃዱ አለም የምናስተናግዳቸው ሽንፈቶቻችን፣ በስነጥበቡ አለም ድሎቻችን ይሆናሉ፡፡ በስነ ውበት አይን ሲታይ፤ ችግሮቻችንን፣ ስቃዮቻችንንና ሽንፈቶቻችንን በመውደድና በእነሱ ከመማረር ይልቅ ወደ ስነጥበብ ስራነት በመቀየር፤ የኋላ ኋላ በቁጥጥራችን ውስጥ እናደርጋቸዋለን” በማለት ጽፋለች ሜልቪን ራደር። በእስር ቤት ያሳለፍኳቸው አመታት፣ ከተቀረው አለም የሰው ልጅ ጋር ትስስር ለመፍጠሬ ሰበብ ሆነውኛል፡፡ ለስነጥበብ ስራዎቼ የመነቃቃት ምንጭ የሆኑኝም እነዚያ የግዞት አመታት ናቸው፡፡
በአዲስ አበባ መርካቶ የሚባለው ሰፈር ውስጥ በ1950 ዓ.ም ነው የተወለድኩት፡፡ መጠነኛ ገቢ ያላቸው ወላጆቼ ካፈሯቸው አራት ልጆች፣ እኔ የመጨረሻዋ ነኝ፡፡ ዛሬም ድረስ የሚከተለኝን ትልቅ ተጽዕኖ ያሳደረችብኝ አሁን በህይወት የሌለችው እናቴ ናት፡፡ እናቴ መንፈሳዊውን አለም ከምድራዊው አለም ጋር በሚገርም ሁኔታ አጣጥማ ህይወቷን ስትመራ የኖረች፣ ፍጹም ሃይማኖተኛ፣ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ ነበረች፡፡ መደበኛ ትምህርት ባትከታተልም እጅግ ብሩህ አእምሮ ያላትና ለስነጽሁፍ ፍቅር የነበራት ሴት ነበረች። የማክሲም ጎርኪን መጽሃፍት አነብላት እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ከጎርኪ ስራዎች፣ ‘እናት’ ለሚለው ረጅም ልቦለድ የተለየ አድናቆት ነበራት፡፡ አማርኛ ማንበብና መጻፍ የቻለችው በራሷ ጥረት ነው፡፡ ለስነግጥም፣ በተለይ ደግሞ ለቅኔ እንዲሁም ለቲያትር የተለየ ፍቅር ነበራት፡፡ የስነጥበብ ስሜትም ነበራት። የራሷን የጥልፍ ዲዛይኖች ትሰራ ነበር፡፡ ለፍትህ መከበር ጠንካራ አመለካከት ያላት እናቴ፣ ከቁሳዊ ስኬቶች ይልቅ ለእሴቶች ራሳቸውን ከሚያስገዙ ጥቂት ሰዎች አንዷ ነበረች፡፡ በትምህርት አጥብቃ ታምናለች፡፡ አባቴ ወደ መቀሌ ከተማ ሄዶ መድሃኒት ቤት ሲከፍትና ፊቱን ወደ ንግድ ሲያዞር፣ እሷ ግን እኛን ልጆቿን ለማስተማር አዲስ አበባ መቅረትን ነው የመረጠችው፡፡ ከትምህርት ቤት ስንመለስ  ውሏችንንና የተማርነውን  ትጠይቀናለች፡፡ የቤት ስራችንን በአግባቡ እንድንሰራም ታበረታታናለች፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የእንግሊዝኛ መምህራን  መጽሃፍትን ሲያነቡልን በጽሞና አዳምጣቸው እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ይሄን የማደርገው ወደ ቤቴ ስመለስ ታሪኩን በአግባቡ ለእናቴ ለመተረክ ስል ነበር፡፡ እናቴ ሁሌም ከጎኔ ነበረች፡፡ በተደጋጋሚ ባጋጠሙኝ ፈታኝ የመከራ ጊዜያት ሁሉ በጽናት እንድቆም ትደግፈኝ ነበር፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ ስነጽሁፍ የመማር ሃሳብ  ነበረኝ፡፡ ንባብ ስወድ ለጉድ ነው፡፡ ግጥም ነፍሴ ነው፡፡ ቅኔ የመማር ከፍተኛ ፍላጎት ነበረኝ፡፡ ወደ ሰንበት ትምህርት ቤቶች እየሄድኩ ግዕዝ መማር የጀመርኩት ገና በልጅነቴ ነው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሆኜ በተቀሰቀሰው የተማሪዎች ንቅናቄ፣ በየጉራንጉሩ ግጥሞችን እየጻፉ መበተን ትልቅ የትግል ስልት ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ነው ግጥሞችን መጻፍ የጀመርኩት፡፡ እርግጥ የስዕል ስሜትም ነበረኝ፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ሆኜ፣ የሳይንስ ትምህርት ስዕሎችን መሳል እወድ ነበር፡፡ በስተመጨረሻም ስዕልና ቀለም ቅብ ይወዱ የነበሩት ወንድሜና አንድ ጓደኛዬ  ባሳደሩብኝ ተጽዕኖ፣ አስራ አንደኛ ክፍልን ተምሬ እንደጨረስኩ ስነጥበብ ለማጥናት ወስኜ፣ በ1968 ዓ.ም በአዲስ አበባ የስነጥበብ ትምህርት ቤት ገባሁ፡፡ ለአንድ አመት ከመንፈቅም ትምህርቴን ተከታተልኩ፡፡
በቀበሌና በወጣት ሊግ አማካይነት በተማሪዎች ንቅናቄ ንቁ ተሳትፎ ማድረጌን ቀጠልኩበት፡፡ ይሄም ሆኖ ግን ወታደራዊው መንግስት፤ የቀይ ሽብር ዘመቻን አውጆ ተማሪዎችን ከያሉበት እያደነ ማሰርና በጅምላ መጨፍጨፍ ሲጀምር፣ እኔም ለዚህ ክፉ ዕጣ ከታጩት ታዳኝ ተማሪዎች አንዷ መሆኔን አወቅሁት፡፡ ከተጋረጠብኝ አደጋ ማምለጥ ነበረብኝ፡፡ ለአንድ አመት ከመንፈቅ ያህል ከሌሎች አምስት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጋር አዲስ አበባ ውስጥ ተደብቀን ቆየን፡፡ በስተመጨረሻም ድንበር አቋርጠን ጅቡቲ ለመግባትና ጥገኝነት ለመጠየቅ በማሰብ፣ በ1971 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ወጣን፡፡ በድብቅ ድንበሩን ሊያሻግሩን ፈቃደኛ የሆኑ ነጋዴዎች ብናገኝም፣ ሙከራችን ግን እጅግ አደገኛ ነበር፡፡ አቋርጠነው ልናልፍ ባሰብነው ድንበር ላይ ኢትዮጵያና ሶማሊያ ጦርነት ገጥመው ነበር፡፡ ይህ መሆኑን ሳናውቅ ነው፣ በእግራችን ጉዞ የጀመርነውና የሶማሌ መደበኛ ጦርና  የሶማሊያ ነጻ አውጪ ግንባር ወታደሮች ሰፍረውበት ወደነበረው የጦር ካምፕ ሰተት ብለን የገባነው። በቁጥጥር ስር ውለን ወደ ሶማሊያ ተወስደን ታሰርን። በሁለቱ አገራት መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት ከሶስት አመታት ጦርነት በኋላ ቢጠናቀቅም፣ እኛ ግን ቀጣዮቹን አስር አመታት ያሳለፍናቸው በሶማሊያ እስር ቤቶችና የጉልበት ስራ ካምፖች ውስጥ ነው፡፡ በስተመጨረሻም በኢጋድ ስብሰባ ላይ በተደረገ ስምምነትና በአለማቀፉ የቀይመስቀል ድርጅት አግባቢነት ይመስለኛል፣ ሁለቱ አገራት የጦር እስረኞችን ለመልቀቅ ፈቃደኞች ሆኑ፡፡ እኛም በ1981 ዓ.ም ከእስር ተፈታን፡፡
እነዚያ በእስር ያሳለፍናቸው አመታት እጅግ አስቸጋሪ ነበሩ፡፡ ከእስር ቤቱ ቅጽር ውጪ ካለው አለም ጋር ምንም አይነት ግንኙነት አልነበረንም። ከጉሮሮ የማይወርድ ምግብ እየበላን፣ ንጽህና በጎደለው ማጎሪያ ውስጥ አስከፊ ሁኔታዎችን ተቋቁመን ውለን ማደር ነበረብን፡፡ ወባና በደም ኢንፌክሽን የሚፈጠረው ቺስቶሶሚያሲስ የተባለ በሽታ፣ ዘወትር ከእስር ቤቱ የማይጠፉ የተለመዱ የእስረኞች የስቃይ ምንጮች ነበሩ፡፡ ልንፈታ አንድ አመት ገደማ ሲቀረን፣ የኮሌራ ወረርሽኝ ሳይቀር ተከስቶ ነበር፡፡ እስር ቤት ውስጥ፣ ፍጹም ስለ ራሳቸው ግድ የሌላቸው አልያም ፍጹም አደገኛና ራስ ወዳድ ሰዎችን ልታገኚ ትችያለሽ፡፡ እኛ ጋ ሁለቱም አይነት ሰዎች ነበሩ፡፡ ፈጣሪ ከዚያ መከራ ያተረፈኝ ለእናቴ ብሎ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ እሷ ለኔ ከፈጣሪ የተሰጠችኝ ትልቅ ስጦታ ነበረች፡፡
 እንደ እስረኛ እርስ በርስ እንረዳዳ ነበር - በቁሳቁስ ሳይሆን መከራን አብሮ በመጋፈጥ። የጽሁፍ መሳሪያዎችን  ባገኘሁበት አጋጣሚ ሁሉ፣ በርካታ ግጥሞችን ጽፌያለሁ፡፡ የመድሃኒት ፓኮዎችንና የዱቄት ወተት ክርታሶችን እንደ ወረቀት እየተጠቀምን ነበር የምንጽፈው፡፡ እርግጥ በአማርኛ መጻፍ ክልክል ስለነበር፣ የጻፍኳቸውን ግጥሞች በየስርቻው እደብቅ ነበር፡፡ ብዙዎቹ ግጥሞቼ በአይጥና በድመት ተበልተዋል፣ በርካቶችም ጠፍተዋል፡፡ መጻፌ ከአእምሮ መቃወስ አድኖኛል። ቀስ በቀስ ትምህርት ቤት አቋቁመን ለእስረኞች ፊደላትን ማስቆጠርና ሌሎች ትምህርቶችን ማስተማር ጀመርን፡፡ ሳይንስ እና እንግሊዝኛን የመሳሰሉ ትምህርቶችን አስተምር ነበር፡፡ ትልቁ አስተዋጽኦዬ አማርኛ ማስተማር ሲሆን የተለያዩ ታሪኮችና ግጥሞችን እየጻፍኩ ለማስተማሪያነት እጠቀምባቸው ነበር፡፡ እኛ ከእስር ስንፈታ ማንበብና መጻፍ የማይችል እስረኛ አልነበረም። ትምህርቱም እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል አድጎ ነበር፡፡ መጽሃፍትን የምናገኘው አልፎ አልፎ ነው። በተለየ ሁኔታ የማስታውሳቸው፣ የፕሪሞ ሌቪን መጽሃፍትና የአሌክስ ሄሊን ‘ሩትስ’ የተሰኘ መጽሃፍ ነው፡፡ በሄሊ መጽሃፍ ውስጥ የተሳሉት የመስክ ሰራተኞች ህይወት፣ ከእኛ ህይወት ጋር በሚገርም ሁኔታ መመሳሰሉ ቀልቤን ማርኮት ነበር፡፡ ራሳችንን ዋጋ እንዳለው ሰብአዊ ፍጡር እንድናስብ ያገዙን  እነዚህ ነገሮች ናቸው፡፡
እንደተፈታሁ ወዲህ ወዲያ ሳልል በቀጥታ የመጣሁት ወደ አዲስ አበባ ነበር፡፡ ምክንያቱም ወንድሜ እኔን ፍለጋ አዲስ አበባ መምጣቱን ሰምቻለሁ፡፡ ወንድሜ ያንን ማድረጉ ለእኔም ሆነ ለእሱ አደገኛ ነበር፡፡ ከስድስት ወራት በኋላ ኢትዮጵያን ለቅቄ፣ መላው ቤተሰቦቼ ወደሚኖሩባት አሜሪካ አቀናሁ፡፡ ከረዥም ጊዜያት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ከእናቴ፣ ከወንድሜ፣ ከእህቴና ከቀሩት ቤተሰቦቼ ጋር ለመቀላቀል ቻልኩ። ለዓመታት ያቋረጥኩትን የስነጥበብ ትምህርት በመቀጠልም፣ በዋሽንግተን ዲሲው  ሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ በስነጥበብ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪዬን አገኘሁ፡፡ በሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን ስከታተል ግሩም  መምህራን  ገጥመውኛል፡፡ ሁለት ድንቅ መካሪ ዘካሪም  አግኝቻለሁ፡፡ የስነጥበብ መምህሬ እስክንድር ቦጎሲያንና የፊልም መምህሬ አብይ ፎርድን፡፡ ከእስክንድር ጋር በመሆን ‘ኔክሰስ’ የተሰኘ የሥነጥበብ ስራ ዋሽንግተን ዲሲ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የመስራት እድል አግኝቻለሁ፡፡
በስዕሎቼ ስሜቶቼን፣ ትዝታዎቼን እንዲሁም ጊዜና ቦታ ከሚገድባቸው ግላዊ ገጠመኞቼ፣ ዘመን እስከማይሽራቸው አለማቀፍ ጉዳዮች የተዘረጋውን ምናቤን መግለጽ ጀመርኩ፡፡ ራሴን በግላዊ ገጠመኞቼና ልምዶቼ ላይ ብቻ አልገደብኩም። ምናቤን ሰፋ በማድረግ ጦርነት፣ ስቃይና በስተመጨረሻም ፈውስን ወደመሳሰሉ አለማቀፍ ጉዳዮች ገባሁ፡፡ መጀመሪያ አካባቢ፣ በቀላሉ የሚለዩ የእይታ ተረኮችን በመጠቀም የግል ልምዶቼን በአለም ዙሪያ ከሚታዩ ተመሳሳይ ሁኔታዎች ጋር እያስተሳሰርኩ፣ ኤክስፕሬሽኒስት በተባለው የአሳሳል ዘዬ ነበር ስዕሎቼን የምሰራው። በመቀጠልም ከዚህ ቀደም እንደማደርገው ሁሉ ትኩረቴን በሰብዓዊ ጉዳዮች ላይ በማድረግ ከቀድሞዎቹ በበለጠ ምስል አልባ የሆኑ ወይም አብስትራክት ስዕሎችን መስራት ጀመርኩ፡፡ ከዚያም ቴክስቸር፣ ቀለምና ቅርጽን በመሳሰሉ የእይታ  መሰረታዊ ነገሮች በመጠቀም፣ ስሜትን የሚያጭሩ ሙሉ ለሙሉ ምስል አልባ ወይም አብስትራክት ስዕሎችን መሳል ቀጠልኩ፡፡ አሁን ብርን የመሳሰሉ ባህላዊ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን በመገጣጠም እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡ ብር በውስጡ ብርሃን ስለሚያሳልፍ እወደዋለሁ፡፡ ከሌሎች ቁሳቁሶች ጋር በመሸመን የተለያዩ ተደራራቢ ትርጉም ያላቸው መልዕክቶችን ማስተላለፍ መቻሌ ያስደስተኛል፡፡ ስዕሎችንና ቅርጻቅርጾችን ከስነግጥም፣ ሙዚቃና ስነጽሁፍ ጋር እያዋሃድኩ የራሴን ህብር እፈጥራለሁ፡፡ አንደኛው ጥበብ በሌላኛው እንዲሁም በእኔ ላይ መነሳሳትና ተጽዕኖ ይፈጥራል፡፡
ከሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ ከተመረቅኩበት ጊዜ ጀምሮ፣ በስቱዲዮ ስራዬን እየሰራሁ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የስነጥበብ ትምህርት አስተምር ነበር፡፡ በአሁኑ ሰዓት ጆርጂያ በሚገኘው ሳቫና የስነጥበብና የዲዛይን ኮሌጅ እያስተማርኩ እገኛለሁ፡፡ መምህር መሆኔን እወደዋለሁ፡፡ ምክንያቱም ራሴን ሙያው በየጊዜው ከሚደርስበት  ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ለማድረስ ስል፣ በስፋት እንዳነብና ጥናት እንዳደርግ ያስገድደኛል፡፡ ሌላው ሙያውን እንድወደው የሚያደርገኝ ነገር ደግሞ፣ ከዚህ በፊት ልምዱ ባልነበረኝ የስነጥበብ ጉዞዎች ላይ በተደጋጋሚ እንድሳተፍ ዕድል የፈጠረልኝ መሆኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ወይም በሌሎች የአፍሪካ አገራት ባስተምር ደስ ይለኛል፡፡ ምክንያቱም በሙያዬ  የማበረክተው አስተዋጽኦ በእነዚህ አገራት የተሻለ ተጽዕኖ ሊፈጥር ይችላል ብዬ አስባለሁ፡፡ አንድ ቀን የሙሉ ጊዜ የስቱዲዮ ሰዓሊ የምሆንበትና በጽሁፍ ስራ ላይ ብዙ ጊዜዬን ማሳለፍ የምችልበት ዕድል ይፈጠርልኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ስነጥበብ ለኔ ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ የምሰጠው ነገር ነው። ስነጥበብን የምኖርለት ሙያዬ ለማድረግ ችያለሁ ብዬ የማስበው በሁለት ምክንያት ነው፡፡ አንድም ስለ ቁሳዊ ስኬት ተጨንቄ አላውቅም፡፡ ሁለትም ሙያው የሚጠይቀውን ዲስፕሊን አክብሬና ሙሉ ትኩረቴን በእሱ ላይ አድርጌ ነው የኖርኩት፡፡
የዛሬ ዘመን ወጣት ሴቶች ትኩረት ሊሰጧቸው ይገባሉ የምላቸው ነገሮች አሉ፡፡ የመጀመሪያው ነገር አደጋዎችን ለመጋፈጥ ፈቃደኛ መሆን አለባቸው። ፈቃደኛ ካልሆኑ ምንም ነገር ሊያሳኩ አይችሉም። አደጋን መጋፈጥ በህብረተሰቡ ዘንድ ሰርጸው የኖሩና ቅቡል የሆኑ አመለካከቶችን መገዳደር ሊሆን ይችላል፡፡
ሴቶች ይህን ማድረጋቸው ህልማቸውን እውን ለማድረግ ያግዛቸዋል፡፡ ይሄም ሆኖ ግን፣ አደጋን መጋፈጥንና ከባህል  ልንማራቸው የምንችላቸውን ነገሮች ማክበራችንን በተመጣጠነ ሁኔታ ማስኬድ ይኖርብናል፡፡ ከሁሉም በላይ፣ ወጣት ሴቶች እውቀትን መሻት ብቻ ሳይሆን እውቀትን ፍለጋ ከተጉ፣ ግሩም የሚባሉ ነገሮችን ለማሳካት እንደሚችሉ አምናለሁ፡፡
(ሰዓሊና ገጣሚ ከበደች ተክለአብ የዛሬ 15 ዓመት አዲስ አድማስ መታተም ስትጀምር  የጋዜጣው እንግዶች ሆነው ከቀረቡት የጥበብ ባለሙያዎች መካከል ቀዳሚዋ ነበረች፡፡ ከላይ የቀረበውን ግለ ታሪክ የወሰድነው ባለፈው ጥቅምት ወር ለንባብ ከበቃውና የስኬታማ ኢትዮጵያውያንን ሴቶች ታሪኮች ከሚያስነብበው ተምሳሌት የተሰኘ መጽሐፍ ነው፡፡)

Read 2242 times