Saturday, 25 April 2015 10:38

“እንዳስጨነቋቸው መጠን እንዲሁ በዙ፣ እጅግም ጸኑ” ዘጸ1፡12

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ቅድስት ቤተክርስቲያን በሊቢያ ለተሰውት ወንድሞቻችን በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃ በቀኖናዋ የምትሰጠውን ስያሜና ክብር ስንጠባበቅ ነበር። ባለፈው ማክሰኞ ማታ ቤተ ክርስቲያኗ በEBC በሰጠችው መግለጫ፤ “ስለ ሃይማኖት የተጋደሉ መስተጋድላን” ብላቸዋለች።
በዘመናችን የሰማዕትነት ወግ ያሳዩንን የሃይማኖት ጀግኖች፤ ሠዓሊና የግራፊክስ ባለሙያ ወንድማችን ዘሪሁን ገ/ወልድ፤ በኢትዮጵያዊ የአሳሳል ዘዬ “በከመ ተወክፎሙ እግዚእነ ለሰማዕታተ ሊቢያ ዘተመትሩ በእንተ ስሙ” (ስለስሙ የተገደሉትን የሊቢያ ሰማዕታት ጌታችን እንደተቀበላቸው) የሚያሳይ ስዕል አዘጋጅቶልናል፡፡ ከቁጭታችን የተነሳ አሰቃቂ የሆነውን የሰማዕታቱን ቪዲዮና ፎቶዎች ፖስት ከማድረግ ይልቅ ይህንን ምስል መጠቀም እንችላለን። በደም የታጠቡት ምስሎች መሰራጨታቸው ለገዳዮቹ የፈለጉትን የማስታወቂያ ሥራ የሚሰራ ሲሆን ለሰማዕታቱ ቤተሰቦችና የቅርብ ወዳጆች ግን ከፍተኛ ሰቀቀን መሆኑን ልብ ልንል ይገባል። ሰሞኑን ሁለቱ ሰማዕታት ከኤርትራ ናቸው የሚል ዜና ተሰምቷል፡፡ ከኤርትራ ቀርቶ ከየትም ቢሆኑ ቤተክርስቲያን ምስክርነታቸውን እንጂ ፓስፖርታቸውን አትመለከትም፡፡ ቤተክርስቲያን በስንክሳር አምነው ሳይጠመቁ ለሰማዕትነት የበቁና በደማቸው የተጠመቁ ብዙ ሰማዕታት አሏት፡፡
የሰማዕታቱ ደምና መከራ ቅድስት ቤተክርስቲያናችንን ወደ መንፈሳዊ ተጋድሎ ዘመንዋ የሚመልሳትና አንድ የሚያደርጋት ይሁንልን፡፡ ከሃይማኖት የወጡ በምግባርም ያፈነገጡ፣ እረኛን በማጣት የተበተኑ ምእመናን የቤተ ክርስቲያን ልጆችንም የሰማዕታቱን ደም ምክንያት አድርጐ ወደ በረቱ ይመልስልን!
ተመስገን ዘገየ (አዲስ አበባ)

Read 1528 times