Sunday, 10 May 2015 15:09

ኢህአዴግ፤ በኦሮምያ ክልል ህዝቡ ይመርጠኛል አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

“ህዝቡ ካልመረጠን ውሣኔውን በፀጋ እንቀበላለን”

በዘንድሮው ምርጫ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ በሁሉም የሚዲያ አማራጮች በመጠቀምና በየቦታው ፖስተሮችን በመለጠፍ እንዲሁም የቡና ጠጡ ስነሥርዓቶችን በማዘጋጀት ሠፊ የቅስቀሳ ስራ እያከናወነ ሲሆን አባላቱንና ደጋፊዎቹን በምርጫ ስነምግባር ዙሪያ ተከታታይ ስልጠና መስጠቱንም ይገልጻል፡፡ በመላ አገሪቱ ከ500 በላይ እጩዎች ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበው ኢህአዴግ፤ ዶ/ር መረራ ጉዲና ከፍተኛ ድጋፍና ተቀባይነት አግኝተንበታል ባሉት የኦሮሚያ ክልልም ሰፊ ቅስቀሳ እያደረገ መሆኑን የፓርቲው ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ደስታ ተስፋው ገልጸዋል፡፡ ህዝቡ እንደሚመርጠን እናምናለን ያሉት ሃላፊው፤ ህዝቡ ካልመረጠን ውሳኔውን በጸጋ እንቀበላለን ብለዋል፡፡   
ኢህአዴግ በምርጫ ቅስቀሳው እያከናወነ ስላለው ተግባራት በተለይም በኦሮሚያ ክልል ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ያለውን ፉክክር በተመለከተ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ የኢህአዴግ ጽ/ቤት ሃላፊ ከሆኑት አቶ ደስታ ተስፋው ጋር ተከታዩን ቃለምልልስ አድርጓል፡፡  

የኢህአዴግ የምርጫ ቅስቀሳ እንዴት ነው? በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
አጠቃላይ ምርጫውን በሚመለከት እቅድ አውጥቶ በእቅዱ መሠረት እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ የተመደበለትን ነፃ የአየር ጊዜና የጋዜጣ አምድ በአግባቡ በመጠቀምም በስፋት በመቀስቀስ ላይ ነው የሚገኘው፡፡ ከተሰጠው የሚዲያ መድረክ ከ96 በመቶ በላይ እየተጠቀመ ነው ያለው፡፡ የፊት ለፊት ስብሰባዎችን በማድረግና ህዝቡን በመቅረብ ቅስቀሳዎች እያካሄደ ነው፡፡ በየአካባቢው የቡና ጠጡ ፕሮግራሞች  እየተዘጋጁ ህዝቡ በኢህአዴግ አፈፃፀሞች ላይ እየተወያየ የሚያነሣቸው ጉዳዮች ግልጽ እየተደረጉለት ነው፡፡ እስካሁን ባለው ሁኔታ በጣም ስኬታማ ቅስቀሳ ነው እያደረግን ያለነው፡፡ በቀሪዎቹ ጊዜያት ይበልጥ አጠናክረን የምንቀጥል ይሆናል፡፡
በኦሮሚያ ክልል “መድረክ” ከኢህአዴግ የተሻለ ተቀባይነት አግኝቻለሁ እያለ ነው፡፡ በክልሉ የኢህአዴግ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል? ዋነኛ ተፎካካሪ የሚለው ፓርቲስ የቱ ነው?
ኢህአዴግ እንደ ሌሎቹ ክልሎች ሁሉ በአጠቃላይ በቅስቀሳ እቅዱ መሠረት በክልሉ ቅስቀሳ እያደረገ ነው። ኦህዴድ በክልሉ ውጤታማ ቅስቀሳ በማካሄድ ላይ ነው ነው፡፡ መድረክ ወይም ዶ/ር መረራ የበላይነቱን ይዣለሁ ወይም ተቆጣጥሬያለሁ የሚሉት ተራ አሉባልታና ከጅምሩ አጠቃላይ የህዝቡን ትኩረት ለመቀየር የሚጠቀሙበት ዘዴ ነው፡፡ ለምሣሌ አንድ ያደረጉት ሠላማዊ ሠልፍ ነበር፡፡ በዚያ ሠልፍ ላይ ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ እድሜያቸው ለመምረጥ ያልደረሰ ልጆችን ጭምር ያሰባሰቡበት እንደነበር በሚዲያ ማንም ተከታትሎታል። ይሄን ወስዶ ሁሉንም ነገር ተቆጣጥሬዋለሁ የሚል ድምዳሜ ላይ መድረስ አይቻልም፡፡ የበላይ ሆኛለሁ የሚባለው ህዝቡ የሠጠው ድምጽ ከታየ በኋላ ነው፡፡ ህዝባችን በኦሮሚያም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ኢህአዴግ ያስመዘገባቸውን ስኬቶች እያደነቀ፣ ቀጣይነቱንም እንደሚፈልግ እያረጋገጠ ነው ያለው፡፡ አሁን ከጅምሩ የበላይነት ይዣለሁ የሚለው ስንቱን ህዝብ ያዘና ነው እንዲህ አይነት ድምዳሜ ላይ የደረሰው? ያ መራጭ ህዝብ ነው መጨረሻ ላይ የሚወስነው፡፡ ይሄ ካሁኑ ትኩረት ለመቀየር የሚደረግ ጩኸት ነው፡፡
ኢህአዴግ ስኬት ያስመዘገበ ፓርቲ ነው፡፡ ስራዎቹንና የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶቹን ነው እየገለፀ ያለው፡፡ ሁሉንም ነገር ተቆጣጥሬዋለሁ ብሎ አልደመደመም፡፡ ከዚህ ባሻገር መድረክ በተለይ በእነዚህ አካባቢዎች ህገወጥ ቅስቀሳ ያካሂዳል፡፡ የኢህአዴግ ምልክት ተቀይሯል፤ “እጅ” ሆኗል የሚል የማጭበርበር ቅስቀሳዎችን ያደርጋል፡፡ ለዚህ በቂ መረጃ አለን፡፡ የሆኖ ሆኖ ውድድር ስለሆነ ህዝብ የመጨረሻውን ውሣኔ መስጠት በሚችልበት መንገድ በኛ በኩል ቅስቀሳውን እያካሄድን ነው፡፡
እንደ ገዥም ሆነ ተወዳዳሪ ፓርቲ ሃላፊነታችንን በብቃት እየተወጣን ነው፤ በየአካባቢው ህገወጥ የሆኑ ቅስቀሳዎች አሉ፡፡ ለየአካባቢው የምርጫ ቦርድ ጽ/ቤትም እያመለከትን ነው የምንገኘው፡፡ ስነምግባሩን አክብረን በህጉ መሠረት በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ቅስቀሳችንን በስኬት እያከናወን ነው፡፡
ዶ/ር መረራ “ኢህአዴግ ምርጫውን ካላጭበረበረ አንሸነፍም” ብለዋል፡፡ ኢህአዴግ ምን ይላል?
በመጀመሪያ ደረጃ ኢህአዴግ ምርጫ ሊያጭበረብር የሚፈልግበት ምክንያትም ባህሪም የለውም፡፡  ይሄ  መጨረሻ ላይ የሚመጣን ሽንፈት ላለመቀበል የሚደረግ ቅድመ ድምዳሜ ነው፡፡ በውድድሩ ህዝባችን ይመርጠናል የሚል ሙሉ እምነት አለን፡፡ ብንሸነፍም በፀጋ እንቀበላለን። ይሄ ነው የኛ አቋም፡፡ ዶ/ር መረራ የያዙት፣ምንም ይሁን ምንም አሸናፊዎቹ እኛ ነን ብለው ቀድመው የመደምደም ጉዳይ ነው፡፡ ይሄ እንግዲህ ነገ በምርጫው ሽንፈት ቢገጥማቸው፣ ስለተጭበረበረ ነው በሚል የተለመደ አሉባልታ ለመንዛት ነው። ከዚህ ባለፈ ኢህአዴግ ሊያጭበረብር የሚችልበት ምንም መነሻ የለውም፡፡ ኢህአዴግ ተጨባጭ ለውጥ ያመጣ ለህዝብ የቆመ ድርጅት ነው፡፡ ህዝባችን በነፃነት ይመርጠናል ብለን ነው የምናስበው፡፡ ህዝቡ ካልመረጠን ደግሞ ውሣኔውን በፀጋ እንቀበላለን፡፡ ይሄ ኢህአዴግ መስዋዕትነት የከፈለበትና የታገለለት የዲሞክራሲ ውጤት ነው፡፡ ቀድሞ ድምዳሜ ማስያዝ ግን ሽንፈትን ላለመቀበል የሚደረግ እንቅስቃሴ አድርገን ነው የምንቆጥረው፡፡
ከዚህ ሌላ ከስነ ምግባር ውጪ የሆኑ በመድረክ በኩል የሚፈፀሙ ድርጊቶች እንዳሉ እየታዘብን ነው፡፡ በአጠቃላይ የምርጫ ቦርድ እያየ ያስተካክላል የሚል እምነት ነው ያለን፡፡ ምርጫን ቀድሞ አሸንፌያለሁ ማለት በሚገባ ሊጤን የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ ምርጫው ሊጭበረበር አይችልም፡፡ ምክንያቱም ከድምጽ መስጫው እለት ጀምሮ የእያንዳንዱ ተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ በምርጫ ጣቢያው  ይገኛል፡፡ ይታዘባል፡፡ የሚቆጠረውና ይፋ የሚደረገውም እነዚህ አካላት ባሉበት ነው፡፡ የምርጫ ሂደቱ ለማጭበርበር እድል የሚሰጥም አይደለም፡፡
የኢህአዴግ አባላትና ደጋፊዎች በመድረክ  አባላት ላይ ድብደባ፣ እስርና  ወከባዎችን እየፈፀሙ ነው የሚል ስሞታ ይሰነዘራል --- በዚህ ጉዳይ ላይስ ኢህአዴግ ምን ይላል?
ኢህአዴግ መላ አባሉና አመራሩ ስልጠና ሰጥቶ ነው ወደ ስራ የገባው፡፡ በየጊዜውም አፈፃፀሙን ይከታተላል፣ ይቆጣጠራል፡፡ ያጠፋ ካለም የእርምት እርምጃ ይወስዳል። በዚህ መንገድ እየተሠራ አሁን ስኬታማ ነገር ነው ያለው። ነገር ግን ተቃዋሚዎች ይሄን ተጨባጭነት የሌለው ስሞታ ያቀርባሉ፡፡ ሲጣራ ግን ምንም ነገር አይገኝበትም፡፡ ስለዚህ ይሄም ለመወዳደር ምቹ ሁኔታ አላገኘንም ብሎ በምርጫው ሂደት ላይ ጥላሸት ለመቀባት የሚደረግ ጥረት ነው፡፡ ተጨባጭ ማስረጃ ካለ በምርጫ ቦርድም ለኢህአዴግም ማቅረብ ይቻላል፡፡ ለምሣሌ በጋራ ምክር ቤቶች የሚቀርቡ ስሞታዎች አሉ፡፡ ሲጣሩ እንደውም ጥፋቱ የተቃዋሚዎች ሆኖ ነው የሚገኘው፡፡ መድረክ በተለይ ኦፌኮ እኛ ላይ ነው ወከባ እያደረሰ ያለው፡፡ የኛን አባላት የማሸማቀቅ፣ ለአባላቶቻችን የተለያየ ስያሜ በመስጠት ስራቸውን እንዳይሠሩ እንቅፋት የመሆን ነገር እየታየ ነው፡፡
በኛ በኩል ግን አልፎ አልፎ በታችኛው መዋቅር የሚፈጠሩ ችግሮችን ተከታትለን ፈትተናል፡፡ ይሄ በዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ  ሊያጋጥም የሚችል ነው፡፡ መሠረታዊ ችግር አይደለም፤ እኛም የማስተካከያ እርምጃ እየወሰድን ነው፡፡ አንዳንድ ቦታ ጥፋት የፈፀሙትን እስከ ማባረር የደረሰ እርምጃ ተወስዷል፡፡ ይሄ ባለበት ሁኔታ የሚነሱት ስሞታዎች ተጨባጭነት የላቸውም። እናንተ ጋዜጠኞችም የሚባለውን ሁሉ እውነት ነው ብላችሁ የምትወስዱ ከሆነ ትክክል አይደለም፡፡ ቅሬታ የሚያነሱበት ቦታ ድረስ ሄዳችሁ ማረጋገጥ አለባችሁ፡፡ ይሄ ከሆነ እውነታው ይረጋገጣል፡፡ በኛ በኩል ካለፉት ምርጫዎች በተሻለ ለዲሞክራሲያዊ ምርጫ ተዘጋጅተን ነው ወደ ሂደቱ የገባነው፡፡
በአጠቃላይ ስለቀጣዩ የምርጫው ሂደት ምን ይላሉ?
አገራችን አሁን ያለችበትን የልማት፣ የሠላምና የዲሞክራሲ ደረጃ ሁላችንም እንገነዘባለን፡፡ ሁላችንም ተጠቃሚ የምንሆነው ይሄ ሂደት ሲቀጥል ነው፡፡ ተቃዋሚዎች ቅስቀሳ እያካሄዱና ከህዝብ ዘንድ እየደረሱ ነው፡፡ የኛ አባሎችም በየደረጃው የጀመሩትን የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡ ዋናው የምርጫው ባለቤት የሆነው ህዝብ፣ የሚፈልገውን ፓርቲ በመምረጥ መብቱን ማረጋገጥ አለበት፡፡ ሚዲያውም ከስሜታዊ ዘገባዎች ወጥቶ፣ በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርቶ የምርጫው ሂደት የተቃና እንዲሆን መስራት ይኖርበታል፡፡ የምርጫው ሂደት ዲሞክራሲያችንን ከነበረበት ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያደርስ እንደሚሆን እምነቴ ነው፡፡

Read 2564 times