Sunday, 10 May 2015 15:19

ስደት እና “የስደታችን ትውስታ”

Written by  መሐመድ ነስሩ
Rate this item
(1 Vote)

    የሰው ልጅ በተለያዩ ፖለቲካዊና ማህበራዊ እንዲሁም ተፈጥሯዊ ችግሮች ከሀገር ሀገር ሊሰደድ ይችላል፡፡ የስደት መልኩ ውብ ሆኖ አያውቅም፡፡ ስደት በችግር ጊዜ መልከመልካም መስሎ የሚታይ መልከ ጥፉ ነው፡፡ ስደትን የራሱ ባልሆነ ተክለ ቁመና ማራኪ ሆኖ እንዲታይ የሚያደርገው የችግራችን ስፋትና ጥልቀት ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን ከ1960ዎቹ በፊት ጐልቶ የሚታይ የስደት ታሪክ ያልነበራቸው ህዝቦች ናቸው፡፡ ከ1960ዎቹ ወዲህ ግን የኢትዮጵያውያን ስደት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡ የሀምሳዎቹና የስልሳዎቹ እንዲሁም ሰባዎቹ ስደት ምክንያት ፖለቲካ ነበር፡፡
አሁንም በፖለቲካው ምክንያት ለስደት የተዳረጉ ዜጐች ቢኖሩም፤ የአብዛኛው ስደተኛ የስደት ምክንያት ግን ኑሮ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያኑን ችግርና እጦት ለስደት ዳርጓቸዋል፡፡
በተስፋዬ ዘርፉ የተፃፈው “የስደታችን ትውስታ” የተሰኘው መጽሐፍ ስደትን የሚያስቃኝ፣ በ184 ገፆች የተቀነበበ መጠነኛ ታሪክ ነው፡፡ ደራሲው ተስፋዬ ዘርፉ እና ጓደኞቹ ለስደት የተዳረጉት በፖለቲካ አመለካከታቸውና አቋማቸው ምክንያት ነው፡፡ ዛሬም በፖለቲካ ምክንያት የሚሰደዱ ለመኖራቸው የዓይን እማኝ ነኝ፡፡ ነገር ግን አሁን ጐልቶና ገኖ የሚታየው የስደት ዓይነት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ነው፡፡ ሰው በሀገሩ ላቡን እያንጠባጠበ አላልፍለት ሲለው፣ የሚበላውን አጥቶ በረሃብ አለንጋ ሲገረፍ፤ ሲራብ፣ ሲጠማ፣ ሲታረዝ፤ እስኪ እኔም ሂጄ የዕድሌን ልሞክር ብሎ ይሰደዳል፡፡ ይህ እውነት ነው፡፡ አሳዛኝ እውነት!
አብዛኛው የዘመኑ ወጣት ቁጭ ብሎ በረሃብና በችግር ከመጠቃትና ቁጭ ብሎ ከመሞት፣ በተስፋ ልቡን አብርቶ ወደ ነገ እግሩን አንስቶ፣ እንቅስቃሴ ላይ እያለ መሞት የመረጠ ይመስላል፡፡ ተቀምጦ ከማሸለብ ቆሞ መሄድ፣ ተኝቶ ከመሞትም በርትቶ በመሰደድ ህይወቱን ለመለወጥ የወሰነ መሆኑን በየጊዜው የምናያቸው ሁኔታዎችና እውነታዎች ይመሰክራሉ፡፡ ምርጫው ከሁለት አንድ ነው፡፡ ሞት ወይ ሽረት!
ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ፤ ከመጽሐፍ ጀርባ ላይ የሰፈሩትን አስተያየት፤ ሁሉም ሰው ቢያነብ መልካም ነውና እዚህ እጠቅሰዋለሁ፡-
“ስደት የሰው ልጅ በማህበር መደራጀት ከጀመረበት ጀምሮ ያልተለየው ዕጣ ፈንታ ነው፡፡ ምክንያቶቹ ተፈጥሯዊ ወይም ማህበረሰባዊ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ መጠኑ ሊበዛም ሊያንስም ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክም ይህንኑ አጠቃላይ ዓለም አቀፍ ገጽታ ከሞላ ጐደል ያንፀባርቃል፡፡ በተለይ የሃያኛው መቶ ዓመት አያሌ ኢትዮጵያዊያን በተለያየ ምክንያት ካገራቸው ለመሰደድ የተገደዱበት ዘመን ነበር፡፡”
የታሪክ ተመራማሪው ይህን ብቻ ብለው አያበቁም፤ ስለ መጽሐፉ በተለይ፤ ስለ ስደትም በአጠቃላይ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፡-
“አሁን ለህትመት የበቃው የተስፋዬ መጽሐፍ የዚህን ታሪክ አንድ ምዕራፍ ሥዕላዊ በሆነና ቀልብን በእጅጉ በሚስብ መንገድ ይተርካል፡፡ ወቅቱ የ1960ዎቹ ዓመታት የኢትዮጵያ ተማሪዎች የትግል ታሪክ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰበት፤ ከመንግሥት ጋር ያደርጉት የነበረው ፍልሚያ ጣራ የነካበት፤ በተለይ በታህሳሥ 1962 የተማሪዎች መሪ ጥላሁን ግዛው ከተገደለ በኋላ በተማሪዎች ንቅናቄ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ የነበራቸው ተማሪዎች ከፀጥታ ኃይሎች ወከባ ለማምለጥ የነበራቸው ምርጫ ስደት ነበር፡፡”
የድሮውን ስደት ካሁኑ ስደት ጋር ስናወዳድረው፣ የአሁኑ እጅግ አሳዛኝና የከፋ ሆኖ ይታያል፡፡ የፖለቲካ ተጋድሎ ማድረግ ህልው ከመሆን ከፍ ብሎ የሚገኝ፣ እንደ ሰው አንድ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከመድረስ ቀጥሎ የሚመጣ ነው፡፡
የሆድ ጥያቄ ቀላል አይደለም፡፡ አሁን ኢትዮጵያዊያን እየተሰደዱ ያሉት የሆድን ጥያቄ ለመመለስና ከድህነት ለማምለጥ ነው፡፡ ይህ ያፈጠጠ እውነት መሆኑ ቅስም ይሰብራል፣ ልብ ያደማል፣ ነፍስ ያቆስላል፡፡ ይህ የማይካድ ሀቅ ነው፡፡ ያፈጠጠ እውነት በመሆኑ ልንክደውም ሆነ ልናመልጠው አይቻለንም፡፡ ያለን ብቸኛው ምርጫ እውነቱን ፊት ለፊት መጋፈጥ ነው፡፡
ደራሲው ተስፋዬ ዘርፉ ነገሌ ቦረና የተወለደና ያደገ ሲሆን የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ነገሌ ቦረና እና ጅማ ከተማ ተከታትሎ፤ በበዕደማርያም የሚሰጠውን ትምህርት ቀስሞ፤ በ1960 ዓ.ም የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን መከታተል ችሎ እንደነበር ይገልፃል፡፡
በኃይለሥላሴ መንግስትና በተማሪዎች መሀል የተቃውሞና የእስር፤ የትችትና የሞት ክስተቶች ተከታትለው የተጓዙበት ነበር፤ ዘመኑ፡፡ ተስፋዬም ተማሪ በመሆኑ የመንግሥቱን ውድቀት የሚመኝ ተቃዋሚ ነበር፡፡ ምክንያቱም የዘመኑን ትኩሳት የሚጋራ ግለሰብ ነውና፡፡
የቀደመ ዘመን ስደትና የዚህ የኛ ዘመኑ ስደት ምክንያትና ውጤቱ የተለያየ ሊሲሆን ቢችልም፤ ሁለቱም ዘመኖች የሚጋሩት የራሳቸው የሆነ ተመሳሳይነት እንዳላቸው መረዳት ይቻላል፡፡ በቅርቡ በሊቢያ በምህረት የለሹ የአይኤስ ቡድን የታረዱት ሰላሳ ኢትዮጵያውያንና በርካታ ዜጐች በረሃ ለበረሃ እያቋረጡ ወደ አውሮፓ ለመሻገር የሚያደርጉት የስቃይ ጉዞ፤ አጀማመሩ ከነተስፋዬ ስደት ጋር ሊመሳሰል ይችላል፡፡
ተስፋዬ ለመሰደድ ከወሰነ በኋላ ያደረገውን የመጀመሪያ ዝግጅቱን ሲገልጽ እንዲህ ይላል፡-
“…በተለያዩ አካባቢዎች ወደሚኖሩ ዘመዶቼ ዘንድ በመሄድ በዘዴ ገንዘብ ለማሰባሰብ ሞከርኩ። ያገኘሁት ግን በቂ አልነበረም፡፡ ስለዚህ ለጉዞው ዝግጅት ያለኝ ጊዜ እያጠረ መሄዱን በመገንዘብ በሥራ ዓለም በነበርኩበት ጊዜ የገዛኋቸውን ዕቃዎች ከየነበሩበት ቦታ በማውጣት ጥቂት በቻ አስቀርቼ የነበሩኝን ልብሶች በሙሉ አሮጌ ተራ ወስጄ በተገኘው ዋጋ ሸጥኩ፡፡”
ይህ ከዛሬ አርባ አምስትና ሃምሳ ዓመት በፊት የተከወነ ነው፡፡ ነገር ግን በዛሬ የስደት ታሪካችን ውስጥም ጎልቶ የሚታይ ሃቅ ነው፡፡ ያላቸውን ንብረት ሸጠው ለህገወጥ ደላሎች ገንዘባቸውን የሚከሰክሱ ሞልተዋል፡፡ ለዚያውም በስንትና ስንት ልመናና ውጣ ውረድ በኋላ ያገኙትን ገንዘብ!
የራሳቸውን ንብረት ሸጠው፤ ከዚህም ከዚያም ተበድረውና ተለቅተው ብቻ ሳይሆን የገበሬ አባታቸውን በሬና መሬት፤ የእናታቸውን ወርቅና ጌጥ ሸጠው የሚሰደዱ ጥቂት አይደሉም፡፡ ጥቂት አይደሉም ሳይሆን ብዙ ናቸው፡፡
*   *   *
ለመሰደድ ቁርጥ ውሳኔ ላይ የደረሱት ተስፋዬና ሁለቱ ጓደኞቹ በምዕራብ ኢትዮጵያ በመንዲ በኩል አድርገው ወደ ሱዳን ለመሻገር አውቶብስ ተሳፍረው ከአዲስ አበባ ተነሱ፡፡ እዚያው መኪና ውስጥ የተዋወቋቸው መምህራን (በኋላ ነጋዴዎች መሆናቸውን ተረድተዋል)፤ ራሳቸው ዘንድ ሊያሳርፏቸው እንደሚችሉና ከመንዲ ወደፈለጉበት እንዲሄዱ መንገድ እንደሚያመቻቹላቸው ቃል ከገቡላቸው በኋላ ለመንገድ አመልካቾች በሚል ገንዘብ ተቀበሏቸው፡፡ እነ ተስፋዬ በተባሉት ሰዓት፤ የተባሉበት ቦታ ላይ ሆነው መንገድ መሪዎቹ ከአሁን አሁን መጡ ብለው በጉጉት ሲጠብቁ፤ በፖሊስ ተከበቡ፡፡
የኤርትራ ነፃ አውጪ ተዋጊዎች ከመሆናቸውም በላይ ብዙ መሳሪያና ቦምብ በአህያ ጭነው ወደ ሱዳን ለመሻገር የተሰናዱ ወንበዴዎች ናቸው፤ በሚል ክስ እዛው መንዲ ለአንድ ወር ተኩል ያህል በእስር ከቆዩ በኋላ ተለቀው ወደ አዲስ አበባ የመልስ ጉዞ ለማድረግ በቁ፡፡ ወይም ተገደዱ፡፡
*   *   *
“የስደታችን ትውስታ” መጽሐፍ ባለታሪኮች በከሸፈው የመጀመሪያ ጉዟቸው ተስፋ ቆርጠው የዕለት በዕለት ህይወታቸውን መግፋት አልጀመሩም፡፡ በጐንደር፣ በሐቲት ሁመራ አድርገው ገዳሪፍ ከዚያም ወደ ካርቱም አቀኑ፡፡ ካርቱም እንደገቡም የፖለቲካ ጥገኝነት ለማግኘት አስበው ለፖሊስ እጃቸውን ሰጡ፡፡ ዕቅዳቸውን ግን እንዳሰቡት በቀላሉ አልተሳካም፡፡ ወደ አነስተኛና ጠባብ ክፍሎች ተወርውረው ተቆለፈባቸው፡፡
ተስፋዬ ሁኔታውን እንዲህ ይገልፀዋል፡-
“በዚያች ትናንሽ የግንብ ክፍሎች ውስጥ ለየብቻ ተቆልፎብን በቀን ሦስት ጊዜ ዳቦና ውኃ በበሩ ቀዳዳዎች እየተሰጠን በቀኑ ሙቀትና በሌሊቱ ቅዝቃዜ መሰቃየቱን ተያያዝነው፡፡ በሌሎቹ ትናንሽ ክፍሎች ውስጥም እንደኛው ያሉ እስረኞች ከሚደርስባቸው ስቃይ የተነሳ ያለማቋረጥ የሚያሰሙትን ጩኸትና ኃይለ ቃላት ግንቡ እያስተጋባው ስንሰማ፤ የሚፈጠርብን ጭንቀትና የመንፈስ መረበሽ አሰቃቂ ነበር፡፡”
ከካርቱም ወደ አምድሩማን ተወስደው ከአምስት ወራት በላይ በእስር ቆይተዋል፡፡ ከእስር ከተፈቱም በኋላ ለአስራ ሶስት ወራት ያህል ካርቱም፣ ሱዳን ቆይተው፤ ተስፋዬ ጊዜያዊ የግሪክ ቪዛ በማግኘቱ ምክንያት ወደዚያው እንደተጓዘ ይተርካል፡፡
*   *   *
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ የታተመው መጽሐፍ፤ ደራሲ ተስፋዬ ዘርፉ ቀድመውት ግሪክ ገብተው ከነበሩ ወዳጆቹ ጋር ተገናኝቶ፤ ለአጭር ጊዜ ስራ አግኝቶ፤ በፕሪየስ ከተማ ለተወሰነ ጊዜ ከቆዩ በኋላ ህገወጥ መሆናቸው ታውቆ ፖሊስ እየፈለጋቸው የመሆኑ ዜና ሲደርሳቸው ከፕሪየስ ወደ አቴንስ ተጓዙ፡፡ ተጉዘውም ወደ ጀርመን ከሚሄዱ አሜሪካውያን ጋር በመቀላቀል ከዩጐዝላቪያ ድንበር ደረሱ፡፡ እዚያም ጥቂት ከቆዩ በኋላ ለቀናት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡ በኋላ ግን ነፃ መሆናቸው ተነገራቸው፡፡ ከዚያም በዩጐዝላቪያ ፖሊሶች ትብብርና መሪነት ከጣሊያን ድንበር ደርሰው የእውር ድንብራቸውን እየተጓዙ ወደ ጣሊያን ገቡ፡፡
ተስፋዬ ከሦስት ዓመት ከመንፈቅ በስቃይና በትግል የተሞላ ቆይታ በኋላ ወደ ዴንማርክ የመሄድ ዕድል አግኝቶ እስካሁን የሚኖርባት ሀገር ዜጋ ለመሆን እንደበቃ ማራኪ በሆነ ቋንቋና ትረካ የስደት ህይወቱን አብራርቷል፡፡ ወይም አውስቷል፡፡
*   *   *
ስደት የመከራ ቋት መሆኑ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶች ግን ይህንንም እያወቁ ከመሰደድ ሊታቀቡ ወይም ሊገቱ አልቻሉም፡፡ እርግጥ ነው፤ ከፊት የተደቀነውን መከራና ስቃይ እያወቁ እራሳቸውን ወደ እሳቱ የሚጥሉ የመኖራቸውን ያህል፤ በወሬ ተደልለውና በደላሎች ተጭበርብረው የሚሄዱም አሉ፡፡
እውነቱን ለመናገር አሁን የሚታየው የስደት ሁኔታ መንግሥትን ከመተቸት የሚያድነው አይደለም፡፡ በሀገሪቱ የተንሰራፋው አድሎአዊ አሰራርና የተስፋፋው የስራ አጥነት ችግር ስር መስደዱ፤ እንዲሁም ስራ ለመያዝ የፓርቲ አባል መሆን እንደ መስፈርት መወሰዱ ወጣቶችን ጥርሱን አሹሎ ለሚጠብቃቸው የስደት አጋዘን ቀለብ አድርጓቸዋል፡፡
በዚሁ “የስደታችን ትውስታ” በተሰኘው መጽሐፍ መግቢያ ላይ የደራሲው ወዳጅና የስደት ውጣ ውረዱ ተካፋይ የነበሩት ዶ/ር ሙሐመድ ሐሰን ያሉትን በመጥቀስ ነገራችንን እንቋጨው፡፡ ዶክተሩ እንዲህ አሉ፡-
“(እኔና ደራሲው) ስደት መበረታታት አለበት የሚል ግንዛቤ የለንም፡፡ ይሁን እንጂ የሀገራችን ህዝቦች በአገኙት አጋጣሚ በየአቅጣጫው እንደሚሰደዱ የሩቅና የተረሳው ብቻ ሳይሆን በቅርቡ በዜጐቻችን ላይ እየደረሰ ያለው ችግር በቂ ማስረጃ ነው፡፡ ታዲያ ይህ የማያልቀው የስደት ሰቆቃ ማብቂያው መቼ ይሆን…?”
ይህ የሁላችንም ጥያቄ ነው!

Read 3662 times