Monday, 11 May 2015 09:05

የገጣሚው ዕጣ ፈንታ! ሞት እና ብስራት

Written by  ሌሊሣ ግርማ
Rate this item
(17 votes)

     ስለ ገጣሚነቱ እርግጠኛ ነው፡፡ ገጣሚነትን ከፈጣሪ ያገኘው ፀጋ ነው፡፡ መታገል አስቦ አያውቅም፡፡
በተፈጥሮው ታድሏልና፡፡ ብዙ መጽሐፍት አሳትሟል፡፡ ለምን ስላሳተማቸው መጽሐፍት ሰው ሲወያይ እንደማይሰማ ግን አልገባውም። አምስት አመት ብቻ ነው ያለፈው፣ የመጨረሻውን መጽሐፉን ገበያ ላይ ካዋለ፡፡ እርግጠኛ ነው ስለገጣሚነቱ፡፡ እጣ ፈንታው ነው። እጣ ፈንታው ስሙ በወጣለት ቀን የፀደቀ
ስለመሆኑ እሱም ሆነ አባቱ ያውቃሉ፡፡ ግን መቼ እንደሆነ እርግጠኛ ባይሆንም አንድ ቀን የገጣሚዎች አውራ ተደርጐ የሚሰየምበት ቀን ይመጣል፡፡ አንዳንድ ጊዜ የኮከቡ ጥርሶች ከዘመን ጥርስ ጋር አልገጥም እንደሚል ይገባዋል፡፡ አልገጥም የሚለው ዘመኑ ነው፡፡ የዘመን ጥርስ ግን እጣ ፈንታን የመለወጥ አቅም የለውም።
ይታገለው ይሆናል፡፡ ግን በስተመጨረሻ አይሳካለትም፡፡ የዘመን ጥርስ ወረት ነው፡፡ ወረቱ ሲያልፍ ተሸራርፎ ይወድቃል፡፡ ያኔ የሚቀረው ገጣሚው እና ግጥሞቹ ብቻ ይሆናሉ፡፡ ይህ እምነቱ ነው፡፡ እምነት ብቻ ሳይሆን ለሱ የተፃፈለት እውነቱ ነው፡፡ እንደወትሮው ቀኑን ከዘመኑ ውስጥ መዞ እለት ብሎ ጠራው፡፡ ጠርቶት ከመኝታው ተነሳ፡፡ አድባሩ ከምትሰፍንበት ብቸኛ ስፍራ ነው ውሎው፡፡ ከአዳር በስተቀር ህይወቱ የተሳሰረችው ከዚህ የውሎው ስፍራ ነው፡፡ ስፍራዋ አራት ኪሎ ናት፡፡ አራት ኪሎ ጠዋት ወፍራም ቡናን ትመስላለች ለገጣሚው፡፡ የአራት ኪሎን ማለዳ በቡና ስኒ መስሎ ብዙ ግጥም ጽፏል፡፡ ቡናን አራት ኪሎ፣ አራት ኪሎን ደግሞ ቡና አድርጐ ያገጣጠመው ማነው? ተብሎ ከተጠየቀ መልሱን ማንም ያውቀዋል፡፡ ገጣሚው ነው፡፡ ገጣሚው በፃፋቸው ቅኔዎቹ የተነሳ በአራት ኪሎ በማለዳ ከቡና ውጭ ሲጠጣ የሚገኝ ለምልክት እንኳን አይገኝም፤ ተብሎ የተሞገሰበት ጊዜ ነበር፡፡ እየተሞገሰ ብዙ ከመቆየቱ የተነሳ በራሱ ምስል ስር ገጣሚው ራሱ ተንበርክኮ ኖረዋል፡፡ ጨጓራውን ቢልጠው እንኳን፣ ቡናው እና ስኒው ከድግግሞሽ ብዛት ጣዕማቸውን ማጣታቸው ቢታሰበው እንኳን የማለዳ ተግባሩን ለአንድም ቀን አዛንፎ አያውቅም፡፡
ቡናን መጥላት ግጥሞቹን እንደመጥላት ነው፡፡ አራት ኪሎን ማዘውተር ማቆም ከአድባሯ ጋር መፍታት ነው ብሎ ያምናል፡፡ አዳዲስ እይታ መፍጠር እንደሚጠበቅበት አይክድም፡፡ ግን በፊት ከጠጣው የቡና አተላ ላይ የሃሳብ ቅራሪ እንዴት ማፈንገጥ እንደሚችል እርግጠኛ አይደለም። የተለመደው ካፌ ውስጥ የተለመደው ቦታ ተቀምጦ የተለመደውን የቡና ሲኒ እየጠበቀ በተለመደው መንገድ እግሩን አጣመረ፡፡ ከማጣመሩ በማስከተል ሲጋራውን ለኮሰ፡፡ ሁሉም ተግባሩ የተያያዙ ናቸው፡፡ ከዚሁ የተግባር ሰንሰለት ውስጥ አምስት የግጥም ደቡሎች ፈልቀዋል። የትኛው ግጥም ከየትኛው መድበል ውስጥ እንደወጣ የሚያውቁ ብዙ ተከታዮች እንዳሉት የሚያውቀው እሱ ነው፡፡ እውቀቱን ተጠራጥሮ አያውቅም፡፡ ለመጠራጠር የሚያበቃ ምክንያት ገጥሞት አያውቅም፡፡ ግን የዘመኑ ጥርሶች እንደዚህ አይነት ለጥርጣሬ የሚያተጉ ፍጡራንን ትውልድ ብላ እያመጣች መሆኑን አልፎ አልፎ ይጠረጥራል፡፡ በአለፈው አንድ ወጣት (ውርጋጥ) ከእሱ ጐን ተቀምጦ የእሱን ግጥም በሌላ ገጣሚ ስም ሲቀኝ ሰምቶት በገላጋይ ነው ከጠብ የተረፈው፡፡ ሁለተኛ እንዳይለምደው አሳፍሮ ያንን ወጣት ሸኘው፡፡ የሱን ስም ከተቀኘው ግጥም መነጣጠል የብልግና መጀመሪያ መሆኑ ገብቶታል፡፡
ስምን ከግጥም መነጣጠል ሃይማኖትን ከሀገር ከመነጣጠል፣ ማተብን ከአንገት በጥሶ ከመጣል የተለየ አይደለም፡፡ ስሙ እጣ ፈንታው ነው፡፡ ግጥሙ ደግሞ የእጣ ፈንታው ግብ ነው፡፡ እጣ ፈንታ ያለ ግብ ምንም እርባና የለውም፡፡ “አንድ” ከተባለ “ሁለት” መከተሉ አይቀርም። በአራት ኪሎ ላይ እሱ ጐን የተቀመጠው ጐረምሳ የሰራውን ስህተት በሌላ ሰፈር በዚያው ቅጽበት ሌላ ወጣት እየሰራው እንደሆነ ያውቃል፡፡ ማወቁ ለመጀመሪያ ጊዜ ስጋት ፈጠረበት፡፡ እስካሁን በሰራቸው ግጥሞች አንድን ትውልድ ሳይሆን አንድን
ሺ ትውልድን ገዝቶ ማቆየት እንደሚችል ነበር የሚያስበው፡፡ እጣ ፈንታውም የተፃፈው እንደዚያው ተብሎ ስለሆነ ጥርጣሬ ኖሮት አያውቅም ነበር፡፡ ጥርጣሬም አንድ ብሎ ከተጀመረ ሁለት እና ሦስት ሆኖ ራሱን ያበዛል፡፡ ገጣሚው ስለራሱ ቅንጣትም ጥርጣሬ ተሰምቶት ባያውቅም በዙሪያው ያሉት ሰዎች ላይ ተፈጥሮ ከሆነ መመርመር እንዳበት አሰበ፡፡ ሲጋራውን እያጨሰ…ጓደኞቹን መጠበቅ ጀመረ። ቡናውን በሙሉ ጥሞና ለማጣጣም መንፈሱን ሰበሰበ። ግን ምንም አዲስ ነገር የለውም፡፡ ወንበሮቹን…አስተናጋጆቹን አይኑን ጨመቅ እና በልጠጥ እያደረገ ታዘባቸው፡፡ ምንም አዲስ ነገር የላቸውም፡፡ ገጥሞ ጨርሷቸዋል፡፡ ሰዎቹን ሴቶቹን ከአራት ኪሎ ሆኖ የሚታየውን ሰማይ፣ ከአራት ኪሎ የሚታየውን አምላክ…ገነት እና ገሀነም ከአራት ኪሎ
አንፃር ሁሉም ተብለዋል፡፡ የተባለው ደግሞ በእሱ ብቻ ሊባል የሚችል ነው፡፡ የሚሻሻል ነገር የለውም፡፡ እርግጠኛ ነው፡፡ ታዲያ ግጥሙ ያለ እሱ ስም መንቀሳቀስ የጀመረው ምን ሆኖ ነው፡፡ ጓደኞቹ ተንጠባጥበው እንደሚመጡ ያውቃል፡፡ ከበውት እንደሚቀመጡ እና ሙሽራ እንደሚያደርጉትም ያውቃል፡፡ ትላንት የተደረገው ዛሬም ይደገማል፡፡ ዘመናት የእሱን ዝና ሊነኩት አይችሉም፡፡ ከጓደኞቹ መሃል አንደኛው መጣ፡፡ በእጁ አዲስ መጽሐፍ ይዟል፡፡ የግጥም መጽሐፍ ነው፡፡ ከእሱ መጽሐፍ ውጭ አዲስ የግጥም መጽሐፍ ውይይት ሊደረግ መሆኑ ነው፡፡ በውይይቱ ሁሉ ጐልቶ የሚወጣው ሁሌም አንድ እውነት ነው፡፡ የእሱን የመጀመሪያ ግጥም የሚያክል ገጣሚ መጥቶ አያውቅም፡፡ የሱን የግጥም መጽሐፍ የሚያክሉ ግጥሞች በሀገሪቷ ታሪክ ተጽፈው አያውቁም። አምስቱ መጽሐፍት ደግሞ ለዘለአለም በግጥም ዙፋን ላይ ቋሚ ሆነው ነግሰዋል፡፡ የእሱን አሻራ ለመምሰል የሚሞክሩ እንጂ በአሻራቸው አሻራውን ለመብለጥ የሚንደፋደፉ ሁሉ ከውድድሩ
ቀድመው ተሸንፈዋል፡፡ ሁለተኛው ቡናውን አዘዘ፡፡ ጓደኛው በሌላው ነገር ሊሽቀዳደመው ባይችልም በቡና ሲኒ ማንሳት ግን ለመግዳደር ይሞክራል፡፡ ገጣሚው ዘና ብሎ ሁለተኛ ሲጋራ ለኮሰ፡፡ የግጥም ስሜት መፈጠር የሚጀምረው ከሁለተኛው ሲኒ በኋላ ነው፤ በተደጋጋሚ እንዳየው፡፡ ስሜቱ ሲፈጠር በወረቀት ላይ አውጥቶ ይጫጭራል፡፡ የጫረውን አጥፎ ኪሱ ይከታል፡፡ ከዛ ያሰላስላል፡፡ ቡና ይደግማል። በዙሪያው ደቀ መዝሙሮቹ ያለ አንዳች ህውሰት ትንፋሻቸውን ውጠው ይጠብቃሉ፡፡ የፈጀውን ያህል ጊዜ ቢፈጅ በፀጥታ ይጠብቁታል፡፡
የቡና ሰንሰለት፣ በድራፍት ሰንሰለት ለመተካት የመጀመሪያው ትዕዛዝ በገጣሚው ሲሰጥ ስራ መጠናቀቁን ማብሰሩ እንደሆነ ያውቃሉ፡፡ በዙሪያው ያሉት እንደ ንብ እዝዝዝ ማለት ይጀምራሉ፡፡ ገጣሚው ሁሌ ተጋባዥ ነው። ፀሐይ ነው፤ ብርሐኑን እንደማያልቅ አድርጐ፣ ለዘመናት እንዳይደበዝዝ አድርጐ ሰጥቷል፡፡ ስለ
ሌላው ነገር ከዛ በኋላ አያገባውም፡፡ ስለ መብል እና መጠጥ እሱ ማሰብ አይፈልግም፡፡ ሃሳብ ሊሆንባቸው የሚገባ መፍትሔ ያብጁ፡፡ ደግሞም እስከ አሁን አበጅተው ቆይተዋል፡፡ ዛሬ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ እየፃፈ ሲንሾካሹኩ ሰማቸው፡፡ እንዳናጠቡት ለማስገንዘብ አንድ ሁለቴ በአይኑ ገሰፃቸው፡፡ እየተቀባበሉ የመጀመሪያው በግ ይዞ የመጣውን መጽሐፍ ያነባሉ፡፡ እያነበቡ እንደነበር በተመስጦው ውስጥም ሆኖ ያውቃል፡፡ በጐቹ ሌላ እረኛ ሊኖራቸው በፍፁም እንደማይችል ያውቃል፡፡ የግጥም ተራ አስከባሪ እሱ ብቻ
ነው። ጉልበቱን አስመስክሯል፡፡ እስከወዲያኛው፡፡ ምን እንደሆነ ጉዳዩን ጠየቃቸው፡፡ የመጽሐፉን ገጽ ገለጥ ገለጥ አድርገው አንድ ስንኝ አነበቡለት፡፡ ድገሙልኝ አላቸው፤ ደገሙለት፡፡ በእዝነ ህሊናው ወደ ራሱ አምስት የግጥም መጽሐፍ ሄዶ የተሰረቀ ሃሳብ መሆኑን ለማወቅ መረመረ፡፡ ደግሞ አስነበበ፡፡ ደግሞ መረመረ፡፡
እንደዛ አይነት ግጥም በእርግጥም ከእሱ ውስጥ ወጥቶ አያውቅም፡፡ መረጋጋት አቃተው፤ ግራ ተጋባ፡፡ ልክ እግዚአብሔር በመንበሩ ላይ ከእነ ሁሉን ቻይ፣ ሁሉን አዋቂ ማንነቱ ጋር ተረጋግቶ ባለበት ጽበት…መላዕክቶቹ ስለ ሌላ እሱ ሰምቶ ስለማያውቀው ሌላ ከእሱ በላይ ሃያል ስለሆነ አዲስ መጤ እግዚአብሔር የነገሩት መሰለው፡፡ ሊረዳ አልቻለም፡፡ ከእሱ ውጭ ሌላ እሱ ሊኖር አይችልም፡፡ ከእሱ ውጭ ሌላ (ወጣት) እሱ ከየት መጣ? መጽሐፉን ተቀብሎ አገላበጠ፡፡ ከማገላበጥ በኋላ አደብ ገዝቶ አነበበው፡፡ በእያንዳንዱ ገፅ…ይህ ያልታወቀ ገጣሚ ከኋላው ሲሮጥ እንደነበር እንኳን ሳያየው ድንገት ፈትለክ ብሎ የዘላለምን የፍፃሜ መስመር ከእሱ ቀድሞ ሲገባ ተመለከተ፡፡ የመጀመሪያው ገጽ ላይ ያለው ግጥም ከእሱ የመጨረሻ ግጥም ይበልጣል፡፡ የዚህ አዲስ ገጣሚ አንድ የመጀመሪያ መድበል የእሱን አምስት መድበሎች እንደ በግ ሲያግዳቸው በምናቡ ተሳለበት፡፡ የተሳለበትን ግን ግጥም አድርጐ የመፃፍ አንጀት አልነበረውም፡፡ ጽፎ መብለጥ ከሚችላቸው ከዘወትር መጠኖቹ ውጭ ነው፡፡ በአፉ መጽሐፉ እንደማይረባ ለመናገር ቢፈለግም ነሱፍ አልታዘዝ አለው፡፡ ነፍሱ የተሰጣትን እጣ ፈንታ መሸከም ሳትችል ለዝምታ አሳልፋ ገጣሚውን ስትሰጠው ያስተዋለበት ቅጽበት ይሄ ብቻ ነበር፡፡ የእሱን መጽሐፍት በግ አድርጐ የሚያግድ መጹሐፍ፣ ከፈጣሪ የመጣ ሊሆን እንደማይችል ለራሱ አስረዳ፡፡ “ይሄ አዲስ መጽሐፍ የተፃፈው በራሱ በሰይጣን እጅ ነው” ብሎ ለመጽናናት ድራፍት አዘዘ፡፡ ድራፍቱን እንደ ጭንቀት ማውራረጃ  ከዚህ ቀደም ተገልግሎበት አያውቅም፡፡ ግጥምን ለማዋለድ የሚያምጠው ምጥ እና ጭንቀት ለማስወገድ የሚማጥ ምጥ ለየቅል ናቸው፡፡ “አዳም ከገነት ሲባረር” በሚል ከዚህ ቀደም ጽፎት በአህዛቡም ተመስክሮለት የነበረውን ግጥም ምንም ስለፃፈው ነገር ሳይገባው መቀኘቱን ድንገት ተረዳው፡፡ አዳም ከገነት ሲባረር የተሰማው ስሜት፣ ገጣሚው ከተሰማው የመበለጥ ስሜት ጋር ብቻ ነው ሊወራረስ የሚችለው፡፡ አዳም ከገነት ሲባረር ባይተዋር ነው የሆነው። የፈጣሪ ልጅ የነበረ ሰው የፈጣሪ ጠላት ሆነ፡፡ በገነት ያሻውን በልቶ…ያሻውን ተኝቶ የሚያልም ሰው ወደ ምድር ሲጣል ሊሰማው የሚችለው ባይተዋርነት ብቻ ነው፡፡ የፈጣሪ ባለሟል የነበረው ገጣሚ ድንገት ብኩርናውን እንደተነጠቀ ገባው፡፡  
ይሄ አዲስ ገጣሚ ሰይጣን ነው ቢልም፣ ሰይጣን የጥበብ ፈጠራ መስራት እንደማይችል ያውቃል፡፡ ጥበብ የሚመጣው ከፈጣሪ ውክልና ብቻ ነው፡፡ ከገነት ተባርረው አዳም መሆኑ ድንገት ተገለጠለት፡፡ ፈጣሪ አዳምን የተካው በአንድያ ልጁ ክርስቶስ ነው፡፡ ከአራት ኪሎ ገነት ውስጥ ፈጣሪ አስቀምጦት አምስት የግጥም መድበል የሚሞሉ ስንኞችን ፃፈው በሌላ ከሱ በበለጠ ሊተካው ነበር ለካ፡፡ አዳም የዕጸ በለስ ፍሬዋን አትብላ ተብሎ የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ በመተላለፉ ነው ከገነት የተባረረው፡፡ ገጣሚው ምን አጥፍቶ ከቀድሞ አማናዊ ዙፋኑ እንደተገፈተረ ሊገለጽለት አልቻለም፡፡ ሄዋን አይደለችም ያሳሳተችው፡፡ የሴት ዘርን ላለመቅረብ ሁልጊዜ ጥንቁቅ ነው፡፡ ጥንቁቅ አዳምን ሆኖ ነው የኖረው፡፡ ጥበብን ብቻ ከፈጣሪ ወደ ሰው ለማስተላለፍ ነፍሱን ጠብቆ፣ ስብን አቅልጦ ሳይመቸው የኖረ ነው፡፡ ታዲያ ፈጣሪ እሱኑ ባለሟል አድርጎ ለምን ሳያስቀጥለው ቀረ? ለምን ሌላ እረኛ በእሱ በጎች ላይ ሾመበት? ከዛ በኋላ ያሉት ቀናት እንደ ቀድሞው ሊሆኑለት አልቻሉም፡፡ እየተንጠባጠቡ በዙሪያው ይሰበሰቡ የነበሩት ወዳጆቹ… እየፈሰሱ ሟምተው ተሰወሩ። የተሰወሩት የት ነው? ብሎ ትንሽ ካጠያየቀ በኋላ የማይቀረውን እውነት ሰምቶ ጥርጣሬውን አረጋገጠ፡፡ በጎች ሁሌ እረኛ ይፈልጋሉ፡፡ ጠንካራው እረኛ የበለጠ በግ ይሰበስባል፡፡ ደካማው ደግሞ የበለጠ በግ መሰብሰብ አቅቶት ይበትናል፡፡ ደካማ መሆኑን መቀበል አቃተው፡፡ አባቱ ከፈጣሪ ተማክሮ ያወጣለት የእጣ ፈንታው ማህተም ተከተበበት ስም ሳይለው ትንቢቱ እንዴት እንደተለወጠ ሊገባው አልገባውም፡፡ የዘመን ጥርሶቹ እንዴት የሱን የብርሃን ስም አና የእጣ ፈንታውን ኮከብ … ልክ እንደ ወረቀት ቀዳዳው እንደጣሉ ማወቅ አልቻለም፡፡ እጣ ፈንታው እሱን ጥሎ ወደ ሌላ ሄዶበታል። መክሊቱ ተሰርቋ፤ በዚህ ወጣት፡፡ የወጣቱን ስም
መረመረው፡፡ ትዕቢት እንጂ የትንቢት ቅንጣት በውስጡ የማይተረጎም ስም ነው፡፡ የተጠየፈውን መፅሐፍ ገዝቶ በራሱ እልፍኝ በድብቅ መረመረው፡፡ በመረመረው ቁጥር እየገዘፈ ስለሚመጣ ምርምሩን ገታው፡፡ ምርምሩን ከቀጠለ የራሱን መጽሐፍ ለአዲሱ ገጣሚ እንደ እጅ መንሻ በማበርከት በግ መሆኑን የመግለጽ ፍላጎት እንደሚጠናወተው ታውቆታል፡፡ ወደ አራት ኪሎ መሄዱን አላቆመም፡፡ አድባሩ ሰፈር መቀየሯን ቢያውቅም ሊከተላት ካልቻለ … ድሮ ከትማ በነበረበት ተቀምጦ ስጋና ደሟ ሳይሆን ጥላዋን ቢያመልክ እና ቢማፀን ስለሚሻለው ነው፡፡ ቡና መጠጣት ባይፈልግም ቡና ግን ሱስ ሆኖ እንዲፈልጋት የማስገደድ ደረጃ ደርሳለች፡፡ ድራፍትም በእሱ ሳይሆን በእሷ ቁጥጥር ስር ስለመሆኑ ማረጋገጫዋን በብርጭቆ ብዛት ደርድራ አስቆጠራለች፡፡ ደከመው አዳምን፤ ደከመው፡፡ በብርታቱቲ ዘመን ተሰምቶት የማያውቀው የሴት አስፈላጊነት ለመጀመሪያ ጊዜ ተሰማው፡፡ ሄዋን ድሮ እንደሚያስባት እንዳልሆነች የታወቀው እንደ ድሮው ማሰብ ሲያቆም መሆኑ ደንቆታል፡፡ ሄዋን ድካምን አምጪ ነበረች በገጣሚነቱ ብርታት ዘመን፡፡ የእግዜር አንደኛ ምርጫ በሆነበት ዘመን፡፡ ከምርጫ ወደ ምርጫ ሲወርድ የሄዋንም ምንነት አዲስ ትርጉም ቀየረ፡፡ ሄዋን ለአዳም ገነት
በነበረበት ቆይታ የስህተት ምንጩ ነበረች፡፡ ከገነት ከተባረረ በኋላ ግን ሄዋን ለአዳም ድካሙን የምታበረታ ምርኩዙ ሆነች፡፡ ለካ በብርታቱ ዘመን በኤደን ገነት እግዜር አንፀባራቂ ነጭ መስታወት በነበረ ጊዜ ሄዋን ያላሳሳተችው አዳም ነበር ገጣሚው፡፡ ሄዋን ያላሳሳተችው አዳም ከገነት አይባረርም ማለት አይደለም ለካ፡፡ ለካ መባረሩ በጣም ወረደ አይቀርለትም፡፡ ለካ እጣ ፈንታው አዳምነት ነው። ለካ አዳምነት ከገነት መባረሩ ከኃጢያቱ ጋር ተያይዞ የተፈረደበት አይደለም፡፡ ከመጀመሪውም አዳም በመሆኑ የተፃፈለት እጣ ፈንታው እንጂ፡፡ ገጣሚው አዘነ፡፡ ደከመው፡፡ የሚያስለቅስ ግጥም ይጽፍ ነበር እንጂ ለካ በውን ከተወለደ ጀምሮ
አንድም ዘለላ እንባ አልቅሶ አያውቅም፡፡ አሁን አለቀሰ፡፡ ቀጣይ እጣ ፈንታው ከምሳሌያዊው አዳምም የከፋ መሆኑ ነው ያስለቀሰው፡፡ በገነት ሊኖር ተመኝቶ ከጎን አጥንቱ ያላሰራት ሄዋን ከተባረረ በኋላም ተከትላው አትመጣም ለካ፡፡ ድካሙን የምትደግፍ አፍቃሪ … ከገነት ከተባረረ በኋላ አልገኝ አለች፡፡ ግጥሙን ይወዱ የነበሩ ሴቶችም ገጣሚውን ለካ ወደው ያልቀረቡት በእጣ ፈንታው ምክንያት ነው፡፡ በድል አድራጊነቱ ዘመን አራት ኪሎ ያራቃቸው ሴች፣ በውድቀቱ አራት ኪሎ ላይ ሊደግፉት አልቻሉም። ከቡና፣ ድራፍት ከጂን የተረፈ ገንዘብ እያጠራቀመ ወደ ጨለማው ሰፈር አርቴፊሻል ሄዋን ፍለጋ መግባት ጀመረ። ከጊዜያት በኋላ አደስ የተመረጠው፣ ከእሱ የበለጠው እረኛ … በብዙ በጎቹ ተከቦ ወደ እሱ ካፌ መጣ፡፡ የመጣው ሊተዋወቀው እንደሆነ ነገረው፡፡ እሱ ባይዋጥለትም እንደሚያደንቀውም አረጋገጠለት፡፡ አኳኋኑ ሁሉ እንደክርስቶስ ሆነበት፡፡ በጣም ከፍ ያለ ሆኖ ሳለም ዝቅ ያሉትን ሁሉ ያከብራል፡፡ ከፍ ያሉ ስለመሆናቸውም ይነግራቸዋል፡፡ ለእሱም ነገረው፡፡ በእሱ አንደበት ሲነግረው ከቁጥጥሩ ውጭ አመነው፡፡ ድካሙን የሚያበረታ ንግግር ሰጠው “ያንተ አይነት ገጣሚ ስራ መቼም አይዘነጋም፡፡ ቢዘነጋ እንኳን ወደፊት ተመልሶ ገና መሆኑ አይቀርም” አለው አዲሱ እረኛ፡፡ እውነተኛው ገጣሚ፡፡ እውነተኛው ገጣሚ የተናገረውን የተስፋ ቃል፣ አዳም በምሳሌያዊ ጆሮው ነው ያደመጠው፡፡ ምሳሌያዊ ጆሮው የወጣቱን ገጣሚ ንግግር “ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ” ብሎ ነው የተረጎመለት፡፡ የልጅ ልጆቹ ታሪክ ሲያጠኑ… የሱን ግጥም እንደው አንዴ እንኳን አንስተው በትምህርት ቤት ውስጥ ከተማሩበት ትንቢቱ ተሳካ ማለት ነው፡፡ ሊድን የሚችለው እንደዛ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ በተረፈ ግን እውነተኛ ገጣሚ ሲወለድ የሱንም ሞት እግረ መንገዱን አብስሯል፡፡ የአዳም ሀጢአት በክርስቶስ ትንሳኤ ፀድቷል፡፡   

Read 5140 times