Saturday, 16 May 2015 11:11

የኃይሌ ጡረታ 23 ሁኔታዎች

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

ጡረታውን በ42ኛ ዓመቱ ቆረጠ ፤  27 ዓመታት ሮጠ
9 የወርቅ ሜዳልያዎች ተጎናፀፈ  ፤ 9 ማራቶኖች አሸነፈ
27 ሪከርዶች  ሰባበረ ፤ ከ100 በላይ አገራትን ዞረ
ከዓለም ሪከርዶች ከ5ሺ ሜትር 25.25 ሰከንዶች፤ከ10ሺ 13.80 ሰከንዶችና ከማራቶን 46 ሰከንዶችን ቀነሰ
በሽልማት ከ3.5 ሚሊዮን ዶላር በላይ አፈሰ
       ግሩም ሠይፉ
   ታላቁ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ባለፈው ሳምንት እውነተኛውን ጡረታ ካወጀ በኋላ በርካታ መገናኛ ብዙሃናትና ማህበራዊ  ድረገፆች በሰጡት ሽፋን የስፖርቱ ዓለም አበይት መነጋገርያ ሆኖ አልፏል፡፡ ኃይሌ ጡረታውን ያወጀው በግሬት ማንችስተር ራን በመሳተፍ ውድድሩን በ16ኛ ደረጃ ካጠናቀቀ በኋላ ነበር፡፡ ከፕሮፌሽናል የአትሌቲክስ ውድድሮች በጡረታ መገለሉን በይፋ ሲያስታውቅ ‹‹ ጡረታ የወጣሁት ከውድድሮች ተሳትፎ ነው፡፡ ሩጫ ግን መቼም አላቆምም፡፡ ሩጫን ማቆም አይቻልም፡፡ ህይወት እኮ ነው፡፡›› በማለት ለቢቢሲ ቃሉን ሰጥቷል፡፡ ለረጅም ጊዜ አብረውት የሰሩት ሆላንዳዊው ማናጀር ጆስ ሄርማንስ በመጀመርያ አስተያየታቸው አንድ ውድድር ይቀረዋል በማለት አትሌቱ የሩጫ ዘመኔ አበቃ ማለቱን አልቀበልም ብለው ነበር፡፡ በማግስቱ ግን በይፋ በስፖርት ማኔጅመንት ተቋማቸው ግሎባል ስፖርት ኮሚኒኬሽን ኦፊሴላዊ ድረገፅ መግለጫ በማውጣት የኃይሌን በጡረታ መሰናበት በይፋ አረጋግጠዋል፡፡ ‹‹ሁሉንም ደጋፊዎች አመሰግናለሁ፤ ተፎካካሪዎቼን ዋናው ስፖንሰሬን አዲዳስ ላደረጉልኝ ድጋፍ እና ለሰሩት ውለታ ሁሉ አመሰግናለሁ፡፡ 23 አስደናቂ ዓመታትን በዓለም አትሌቲክስ ፕሮፌሽናል ውድድሮች ቆይቻለሁ። በስፖርቱ የሚኖረኝን አስተዋፅኦ መቀጠል እፈልጋለሁ፡፡ የሩጫ አምባሳደር ሆኜ በመላው ዓለም ስፖርቱን ማስተዋወቅ እፈልጋለሁ›› ሲል የተናገረው ኃይሌ፤ ‹‹ያለፈውን ሁሉ ሳስብ ሁሉም ምርጥ ልምዶች ነበሩ፡፡ ስለአገሬ ማሰብ እፈልጋለሁ፤ ጥሩ ለውጥ ለኢትዮጵያ ማምጣት እሻለሁ፡፡›› ብሏል፡፡
የዱባይ ማራቶን አዘጋጆች የሶስት ጊዜያት አሸናፊያቸው ጡረታ ሲወጣ ምስጋና እና አድናቆታቸውን በማቅረብ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በሶስቱ የዱባይ ማራቶን ድሎች እስከ 2 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት ያገኘው በውድድሩ አምባሳደርነት የዱባይ ማራቶንን ታዋቂ አድርጎታል ያሉት የውድድሩ አዘጋጆች፤ የሃይሌ ተሳትፎ  ዓለም አቀፍ ደረጃ ውስጥ ከቶናል በሚል  አምባሳደራችንና ጓደኛችን ሲሉም አሞካሽተውታል። ጡረታ ከወጣ ዓመታት ያስቆጠረውና አሁን በዓለም አቀፍ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አባል ሆኖ የሚያገለግለው ኬንያዊው ፖል ቴርጋት በበኩሉ ፤ እንኳን ለጡረታ አበቃህ ካለ በኋላ ወደ ስፖርቱ አመራር እንዲገባ ጥሪ አቅርቦለታል፡፡ ኃይሌ ታላቅ ሰው እንደሆነ የተናገረው ፖል ቴርጋት ስፖርቱን እንዴት ለመገንባት እንደሚቻል ወጣቶችን በአርዓያነት ያስተማረ እና ያነሳሳ ብሎም አመስግኖታል፡፡ በኢትዮጵያ፤ በአፍሪካ በመላው ዓለም እና በስፖርት እና በሌሎች መስኮች የአመራርነት ሚናውን መቀጠል ይገባዋል በሚልም ምክሩን ለግሶታል፡፡ ኃይሌ ከአትሌቲክስ ስፖርት በጡረታ ከተገለለ በኋላ በኢንቨስትመንቱ ላይ ያተኩራልም በሚል ተዘግቧል፡፡ በሪልስቴት ፕሮጀክቶች፣ በ4 ሆቴሎች፣ በቡና ግብርና፣ በማዕድን ቁፈራና በሃዩንዳይ ወኪልነት ከ1600 በላይ ሰራተኞችን በማስተዳደር መሥራቱን ይቀጥላል፡፡
ኃይሌ ገብረስላሴ በአትሌቲክስ ስፖርት የምንግዜም ምርጥ አትሌት መሆኑን በርካታ ዘገባዎች፣ የስፖርቱ ኤክስፕርቶች እና የሚዲያ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ እየገለፁ ታሪኩን በማስታወስ፤ የአትሌቲክስ ገድሎቹን በምስልና በአሃዝ አስደግፈው በመጠቃቀስ እና የስንብት ምስጋና በማቅረብ ዘክረውታል፡፡  አትሌት ኃይሌ  ለ27 አመታት በቆየበት የሩጫ ስፖርት ከመካከለኛ ርቀት 800 ሜትር አንስቶ፤ በረጅም ርቀት የ10ሺ እና 5ሺ ሜትር የትራክ እና የቤት ውስጥ ውድድሮች፤ ከ1 ማይል እስከ 10 ማይል በሚወስዱ ሩጫዎች፡ ከ10 እስከ 25 ኪሎሜትር በሚለኩ የጎዳና ላይ ሩጫዎች እና በማራቶን እና በግማሽ ማራቶን ውድድሮች በአጠቃላይ እስከ 26 በሚደርሱ የሩጫ ውድድር ዓይነቶች በመወዳደር እና አስደናቂ ውጤት በማግኘት በታሪክ መዝገብ ስሙን ያሰፈረ ነው፡፡
ስፖርት አድማስ በኃይሌ ጡረታ መታሰቢያነት በዓለም አትሌቲክስ ያለፈባቸውን የሩጫ ዘመናት ከዚህ በታች በቀረቡት 23 ሁኔታዎች እንዲህ ያስታውሳል፡፡
1. ኃይሌና የቀለበሰው ጡረታ
ከ5 ዓመታት በፊት ለተሳትፎ ብቻ 400ሺ ዶላር ተከፍሎት በተወዳደርበት የኒውዮርክ ማራቶን በጉልበቱ ላይ በገጠመው ጉዳት ውድድሩን አቋርጦ ለመውጣት ግድ ሆኖበት ነበር፡፡ በወቅቱ ሰጥቶት በነበረው መግለጫ እንባ በተናነቀው ስሜት ውድድር በቃኝ ሲል ተናገረ፡፡ ከሳምንት በኋላ ግን ይህን ጡረታውን ቀልብሶታል፡፡ ወደ ውድድር ተመልሶም በአትሌቲክሱ ዓለም ስሙ እየተነሳ እንደቀጠለ  አይዘነጋም፡፡
2. ኃይሌና እድሜው
ከሳምንት በፊት ከፕሮፌሽናል የአትሌቲክስ ውድድር ጡረታ ሲወጣ 42ኛ ዓመቱን እንደያዘ ተገልፆ ነበር፡፡ ጎን ለጎን እድሜው ስለመጭበርበሩ ተነስቷል፡፡ ባንድ ወቅት በእድሜው ዙርያ ተጠይቆ ‹‹እድሜ ቁጥር ነው፤ ሩጫ ስወዳደር የ20 ዓመት ሰው መሆኔ ነው የሚሰማኝ› ብሎ ነበረ፡፡  ከ5 ዓመታት በፊት በኒውዮርክ ማራቶን ሲወዳደር  በጉልበቱ ላይ ባጋጠመው ጉዳት አቋርጦ ሲወጣና ሩጫን በቃኝ ብሎ በተሰናበተበት ወቅት እድሜው ማነጋገሩ አልቀረም፡፡ በተለይ “ሌትስ ራን” እና “ራኒንግኮምፒውቴተርስ” የተባሉ  ድረገፆች  እውነተኛ እድሜው ስንት ነው በሚል ጠያቂ ርእስ ትንታኔ ሰርተዋል፡፡ ራኒንግ ኮምፒውቴተርስ ታላቁ ሯጭ ፓስፖርት ላይ የሰፈረ እድሜው በ5 ዓመት ሳያንስ እንደማይቀር ለማመልከት ሞክሮ ነበር፡፡ በ2007ና በ2008 እኤአ ላይ በበርሊን ማራቶኖች የዓለም ማራቶን ሪከርድን ለሁለት ጊዜ ሰብሮ ሲያሻሽል ኃይሌ በ34 እና በ35 አመቱ መሆኑ ግን አሉባልታውን ያፋለሰ እውነታ ነበር፡፡ ትክክለኛው እድሜ 39 እና 40 ሆኖ ሪከርዶቹን ካስመዘገበ  ምን ያህል ምርጥ ብቃት ያለው እንደሚያመለክት ጠቅሰው የተከራከሩለት ባለሙያዎች ነበሩ፡፡ በአብዛኛዎቹ የስፖርት አይነቶች ምርጥ ስፖርተኞች የሚቆዩበት አማካይ የእድሜ ጣርያ ከ38 እስከ 40 ነበር፡፡
2. ኃይሌና ምርጥ ሰዓቶቹ
በ1500 ሜትር 3፡ 33.73
በ1 ማይል 3፡ 52.39
በ3ሺ ሜትር 7፡25.09
በ 2 ማይል 8፡ 01.08
በ5ሺ ሜትር 12፡39.36
በ10ሺ ሜትር 26፡22.75
በማራቶን 2፡03፡59
3. ኃይሌና ሜዳልያዎቹ
በዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድር መድረኮች 9 የወርቅ ሜዳልያዎች አሉት፡፡ በኦሎምፒክ በ10ሺ ሜትር ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎች ሲያገኝ  በ1996 አትላንታ እና በ2000 እኤአ በሲድኒ ኦሎምፒኮች ነበር፡፡ በዓለም ሻምፒዮና ደግሞ 4 የወርቅ፤ 2 የብር እና 1 የነሐስ ሜዳልያዎች ሰብስቧል። 4 የወርቅ ሜዳልያዎች ያገኛቸው በ10ሺ ሜትር ሲሆን በ1993 ስቱትጋርት፤ በ1995 ጉተንበርግ፤ በ1997 አቴንስ እና በ1999 እ.ኤ.አ ሲቪያ በተካሄዱበት ወቅት ነው፡፡ በተጨማሪ በ10ሺ ሜትር በ2003 ፓሪስ ላይ የብር እንዲሁም  በ2001 ኤድመንትን ላይ የነሐስ እና በ5ሺ ሜትር በ1993 እ.ኤ.አ ስቱትጋርት ላይ የብር ሜዳልያዎችንም አግኝቷል፡፡  በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይም በ3ሺ ሜትር 4  የወርቅ ሜዳልያዎችም ሲኖሩት በ1997 ፓሪስ፤ በ1999 ማቤሺ እና በ2003 እኤአ በበርሚንግሃም የተረከባቸው ነበሩ፡፡
በ1500 ሜ 1 የወርቅ  ሜዳልያም በ1999 ማቤሺ ላይም ተጎናፅፏል፡፡ በአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ5ሺ እና 10ሺ ሜትር 1 የብር እና 1 የነሐስ ሜዳልያዎች በ1993 ደቡብ አፍሪካ ደርባን ላይ ሲወስድ፤ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና 1 የነሐስ ሜዳልያ በ1994 እኤአ ቡዳፔስት ላይ ማጥለቁ ከዋና የሜዳልያ ስኬቶቹ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
4. ኃይሌና ማራቶን
በ15 ዓለም አቀፍ ማራቶኖች ተወዳድሮ፤ በ9  አሸንፏል፡፡ የበርሊን ማራቶንን ለ4 ጊዜያትና የዱባይ ማራቶንን ለ3 ጊዜያት በማሸነፍ ብቸኛው አትሌት ነው፡፡
በ2002 በለንደን 3ኛ፤ በ2005 በአምስተርዳም 1ኛ ፤ በ2006 በለንደን 9ኛ ፤ በ2006 በበርሊን 1ኛ እንዲሁ በፉካካ 1ኛ ፤ በ2007 በለንደን አቋርጦ ወጣ ግን በበርሊን 1ኛ ወጥቶ የመጀመርያውን የዓለም ማራቶን ሪከርዱን በ2 ሰዓት ከ04 ደቂቃዎች ከ26 ሰከንዶች አስመዘገበ፤ በ2008 በዱባይ 1ኛ ወጥቶ በድጋሚ በበርሊን 1ኛ ሆኖ ሲያሸንፍ ሁለተኛውን የዓለም ማራቶን ሪከርድ በ2 ሰዓት ከ03 ደቂቃዎች ከ59 ሰከንዶች አስመዘገበ፤ በ2009 በዱባይ 1ኛ፤ በ2010 በዱባይ 1ኛ ሆኖ በኒውዮርክ አቋርጦ ወጣ፤ በ2011 በበርሊን ማራቶን አቋርጦ ወጣ፡፡
በ2012 በቶኪዮ 4ኛ ሆነና በፉካካ ማራቶን አቋርጦ ወጣ፡፡
5. ኃይሌና የመጀመርያዎቹ
ለመጀመርያ ጊዜ በዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ጉልህ ውጤት ያስመዘገበው በ1992 እኤአ ላይ በዓለም ታዳጊዎች ሻምፒዮና በ5ሺ እና 10ሺ ሜትር ውድድሮች ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎች እንዲሁም በተመሳሳይ የውድድር ዘመን በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና በወጣቶች ምድብ ያገኛቸው የብር ሜዳልያዎቹ ናቸው፡፡
የመጀመርያው የዓለም ሪከርዱን በ1994 እኤአ ላይ በ5ሺ ሜትር ሲያስመዘገበው በሆነ ጊዜ በ12፡56.96 ሲሆን በ10ሺ ሜትር ደግሞ የመጀመርያውን ሪከርድ በ1995 እኤአ ላይ በሆላንድ ሄንግሎ አስቀድሞ የነበረውን ሰዓት በ9 ሰከንዶች በማሻሻል በ26፡43.53 አስመዝግቧል፡፡ የመጀመርያው ውድድሩ በ16 ዓመቱ አገሩ ላይ የሮጠው  ማራቶን ሲሆን ያስመዘገበው ጊዜ 2 ሰዓት ከ42 ደቂቃዎች ነበር፡፡
6. ኃይሌና ሪከርዶች
በዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ውድድሮች በተለይ ከ1999 እስከ 2009 እኤአ ባሉት 19 የውድድር ዘመናት በረጅም  ርቀት ከፍተኛ የበላይነት ነበረው፡፡ በዋናዎቹ የአትሌቲክስ መድረኮች እና በዓለም ሻምፒዮናዎች በ15 ውድድሮች ተሳትፎ 11 ውድድሮችን ያሸነፈ ምርጥ አትሌትም ነው፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ባሳለፋቸው 23 የሩጫ ዘመናት  27 ሪከርዶች እና ምርጥ ፈጣን ሰዓቶችን አስመዝግቧል፡፡ ከ27ቱ በአይኤኤኤፍ የፀደቁለት 20 የዓለም ሪከርዶች ናቸው፡፡ ከእነሱ ውስጥ 61 የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሪከርዶች  ናቸው፡፡ ብዙዎቹን ሪከርዶች በተለይ በ10ሺ እና በ5ሺ ሜትር ውድድሮች ያስመዘገበው በ22 ዓመቱ ነበር፡፡  ሪከርዶቹን ያስመዘገበው ደግሞ በ17 የተለያዩ የአትሌቲክስ የውድድር አይነቶች ሲሆን በ2000 እና 3000 የቤት ውስጥ አትሌቲክስ፤ በ5ሺ ሜትር የቤት ውስጥ አትሌቲክስና በትራክ ፤ በ2 ማይል የቤት ውስጥ እና ትራክ፤ በ10ሺ ሜትር በትራክ፤ በማራቶን፤ በጎዳናላይ ሩጫዎች በ10 ኪሎሜትር፤ በ15 ኪሎሜ፤ በ20 ኪሎሜ፤ በ25 ኪሎሜትር በ10 ማይልና በግማሽ ማራቶን ውድድሮች ናቸው፡፡
በዓለም አትሌቲክስ በ5ሺ ሜትር በወንዶች በአይኤኤኤፍ እውቅና ያገኘው የመጀመርያው ኦፊሴላዊ ሪከርድ በ1912 እኤአ ሃነስ ኮልሄማን በተባለ ፊንላንዳዊ 14 ደቂቃዎች ከ36.6 ሰከንዶች በሆነ ጊዜ  የተመዘገበው ሲሆን   በ2004 እኤአ ሪከርዱ በኢትዮጵያዊው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በ12 ደቂቃዎች ከ37.35 ሴከንዶች እስኪያዝ ድረስ ድረስ 35 ሪከርዶች  ፀድቀዋል፡፡  የተቀነሱት 2 ደቂቃዎች ከ99.25 ሰከንዶች ናቸው። ኃይሌ ገብረስላሴ ለ4 ጊዜያት በ5ሺ ሜትር ሪከርድ ነበረው፡፡  የመጀመርያው 5ሺ ሪከርድ በ1994 በሆላንድ ሄንግሎ በ12 ደቂቃዎች ከ56.96 ሴከንዶች ሲሆን ከነበረው ክብረወሰን ያሻሻለው 1 .53 ሰከንዶች ነበር፡፡ ሁለተኛ ሪከርዱን  በ1995 እኤአ በስዊዘርላንድ ዙሪክ በ12 ደቂቃዎች ከ44.39 ሰከንዶች ሲያስመዘግብ 10.91 ሰከንዶች  ቀነሰ፡፡ ይህ ሪከርዱ  ለሁለት ዓመት ቆየና በ2.43 ሰከንዶች  በ1997 በስዊዘርላንድ ዙሪክ አወረደው፡፡ እንዲሁም 4ኛውን ሪከርድ በ1998 በፊንላንድ ሄልስንኪ በ0.38 ሰከንዶች በማሻሻል በ12 ደቂቃዎች ከ39.74 ሰከንዶች አስመዘገበ፡፡ በአራቱ ሪከርዶች ከ5ሺ ሜትር የዓለም ሪከርድ ጊዜ 25.25 ሰከንዶችን አራግፏል፡፡
በ10ሺ ሜትር ውድድር በወንዶች ምድብ በአይኤኤኤፍ እውቅና አግኝቶ ለመጀመርያ ጊዜ የፀደቀው የ10ሺ ሜትር ሪከርድ በ1912 ፈረንሳዩ ጂን ቡዊን የተመዘገበው 30 ደቂቃዎች ከ58.8 ሰከንዶች ነው፡፡ በ2005 እኤአ ላይ ኢትዮጵያዊው ቀነኒሳ በቀለ በ26 ደቂቃዎች ከ17.53 ሰከንዶች በሆነ ጊዜ የመጨረሻውንን ክብረወሰን አስመዝግቦ ላለፉት 10 ዓመታት ተቆጣጥሮት ቆይቷል፡፡ በሪከርዱ ሂደት በ3 ደቂቃ ከ61.37 ሰከንዶች ተፈጥኗል፡፡
ኃይሌ ለ2 ጊዜያት ሪከርድ በማሻሻል ሚና ነበረው። የመጀመርያው የ10ሺ ሜትር ሪከርድ በ1995 በሆላንድ ሄንግሎ የተመዘገበው 26 ደቂቃዎች ከ46.53 ሰከንዶች ሲሆን አስቀድሞ የነበረውን ሪከርድ በ8.70 ሰከንዶቸ ያሻሻለ ነበር። ሁለተኛውን ሪከርዱን አሁንም በሆላንዷ ሄንግሎ ከተማ በ1998 ሲያስመዘግብ 26 ደቂቃዎች ከ22.75 ሰከንዶች ሲሆን አስቀድሞ ከነበረው ሪከርድ 5.10 ሰከንዶች ፈጥኖ ስለገባ ነበር፡፡ በሁለቱ የ10ሺ ሜትር ሬከርዶች ከ5ሺ ሜትር የዓለም ሪከርድ ጊዜ 25.25 ሰከንዶች ከ10ሺ የሰዓት ክብረወሰን 13.80 ሰከንዶችን ቀንሷል፡፡
ከበላይነህ ዴንሳሞ በኋላ የዓለም ማራቶን ሪከርድ ክብረወሰን ወደ ኢትዮጵያ የተመለሰው ከ19 ዓመታት በኋላ ነበር፡፡ በ2007 እኤአ ላይ በበርሊን ማራቶን 2 ሰዓት ከ04 ደቂቃዎች ከ26 ሰኮንዶች   በሆነ ጊዜ ባሸነፈው ኃይሌ ገብረስላሴ አማካኝነት ነበር፡፡ በ2008 እኤአ ላይ ኃይሌ ይህን ክብረወሰኑን በድጋሚ ሲያሻሽል 2 ሰዓት ከ03 ደቂቃዎች ከ59 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ ርቀቱን በመሸፈን ነበር፡፡ ይሄው ሰዓት አሁንም የኢትዮጵያ ሪከርድ ነው፡፡ በዚሁ ሁለተኛ የማራቶን  ሪከርዱ ኃይሌ ገብረስላሴ ርቀቱን ከ2 ሰዓት 4 ደቂቃዎች በታች በመግባት የመጀመርያ አትሌት ሲሆን በክብረወሰኑ ባለቤትነት ለ5 ዓመታት ቆይቷል፡፡
በማራቶን በ2003 እኤአ በፖልቴርጋት ተይዞ የነበረውን 2 ሰዓት ከ04 ደቂቃዎች ከ55 ሰከንዶች ሪከርድ በ2007 ሲሰብር በ19 ሰከንዶች በመቀነስ እንዲሁም በ2008 እኤአ ላይ የራሱን ሰዓት በ27 ሰከንዶች በማሻሻል  በአጠቃላይ በሁለቱ ማራቶን ሪከርዶቹ የርቀቱን ክብረወሰን በ46 ሰከንዶች አፍጥኖታል፡፡
በሩጫ ዘመኑ ካስመዘገባቸው በአይኤኤኤፍ የፀደቁለት  20 የዓለም ሪከርዶች ጡረታውን ሲወጣ  ያልተሰበሩ ሁለት ዓለም አቀፍ ሪከርዶች አሉት፡፡ በ20 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በ2007 እኤአ በቼክ ኦስትራቫ 56 ደቂቃዎች ከ25.98 ሰከንዶች  እንዲሁም በ1 ሰዓት ሩጫ አሁንም በ2007 እኤአ 21285 ሜትሮች ርቀትን በመሸፈን የተዘገቡት ናቸው፡፡
ሌሎች ልዩ ሪከርዶችም በስሙ ይገኛሉ፡፡ በ2008 እኤአ ላይ በበርሊን ማራቶን በ35 ዓመት እድሜው አስመዝግቦት የነበረው የማራቶን ሪከርድ 2 ሰዓት ከ03 ደቂቃዎች ከ59 ሰኮንዶች በአንጋፋ ሯጮች ምድብ አሁንም በክብረወሰንነት የያዘው ነው፡፡ እድሜያቸው ከ40 በላይ በሆኑ አትሌቶች 3 ማስተርስ ሬከርዶችም አሉት፡፡ በ10 ኪሎሜትር 28 ደቂቃዎች፤ በ10 ማይሎች 47 ደቂቃዎች እንዲሁም በግማሽ ማራቶን 1 ሰዓት ከ01 ደቂቃ ኮ9 ሰከንዶች በሆኑ ጊዜዎች የተመዘገቡ ናቸው፡፡
7. ኃይሌና ደረጃዎቹ
በ22 ዓመታት የሩጫ ዘመኑ ከ27 በላይ  ሪከርዶችን ማስመዝገብ የቻለው ኃይሌ  በምንጊዜም የውጤት ደረጃዎች  ከመጀመርያዎቹ አስር አትሌቶች ተርታ ይሰለፋል፡፡ በ10ሺ ሜትር የምንገዜም ፈጣን ሰዓቶች ደረጃ እሰከ 10 ባለው ደረጃ ሶስት ፈጣን ሰዓቶች ያሉት ኃይሌ በዚሁ ደረጃ ላይ በ1998 የ10ሺ ሜትር ርቀትን በ26 ደቂቃ ከ22.75 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ የሸፈነበት ጊዜ በሶስተኛ ደረጃ የተመዘገበለት ነው፡፡ በ5ሺ ሜትር ውድድር ደግሞ በምንግዜም ፈጣን ሰዓት እስከ 10 ባለው ደረጃ ሶስት ፈጣን ሰዓቶችን ያስመዘገበው አትሌቱ በ1998 እኤአ ላይ ርቀቱን በ12 ደቂቃ ከ39.36 ሰኮንዶች የጨረሰበት ጊዜው ሁለተኛ ደረጃ የተሰጠው ነው፡፡ በማራቶን የምንግዜም ፈጣን ሰዓት ደረጃ ላይ በ2007 እኤአ ላይ 2 ሰዓት ከ04 ደቂቃ ከ26 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ ያስመዘገበው ሰዓት በ9ኛ ደረጃ እንዲሁም በ2008 እኤአ ላይ 2 ሰዓት ከ03 ደቂቃ ከ59 ሰኮንዶች የሆነው ጊዜ በ5ኛ ደረጃ ተመዘግበውለታል፡፡
8. ኃይሌና አዲዳስ
የመጀመርያው የመሮጫ ጫማው በ1989 እኤአ ላይ የሮጠበት የአዲዳስ ምርት ነበር፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከታላቁ ዓለም አቀፍ የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያ ጋር ትስስሩን ቀጥሏል፡፡ በ1992 እኤአ ላይ ከአዲዳስ ኩባንያ ጋር የስፖንሰርሺፕ ስምምነት ፈፀመ፡፡ በዚያው ዓመት በዓለም ወጣቶች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ተሳትፎ በ5ሺ እና በ10ሺ ሜትር ድርብ ድል ሊያስመዘግብ በቅቷል፡፡ በ1996 እኤአ በአትላንታ ኦሎምፒክ ላይ ደግሞ የመጀመርያውን የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ ሲያጠልቅ የሮጠበት ጫማ አዲዳስ በልዩ ሁኔታ ያመረተው “ዘ ስፔሻል”  ነበር፡፡ በ2007 እኤአ ላይ ደግሞ በበርሊን ማራቶን ተወዳድሮ የራሱን የመጀመርያ የማራቶን የዓለም ሪከርድ ሲያስመዝግብ የሮጠበት የአዲዳስ ምርት የሆነውና “ዘ ፕሮፕሌት” የተባለው የመሮጫ ጫማ ሆኗል፡፡ በ2008 እኤአ ላይ ለራሱ ሁለተኛውን የዓለም ሪከርድ በማራቶን በዚያው በርሊን ላይ ሲያስመዝግብ ደግሞ በአዲዳስ የተሰራለት “ነፍጠኛ” የተባለ የመሮጫ ጫማ  ነበር፡፡
ከዓለም አቀፉ የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያ ጋር ለ26 ዓመታት በዘለቀበት ትስስር ከፍተኛው ምእራፍ የሆነው በ2013 እኤአ ላይ ከአዲዳስ ዓለም አቀፍ ብራንድ አምባሳደሮች አንዱ ለመሆን ሲበቃ ነበር፡፡  ስለ ስፖርት ማርኬቲንግ እና ስፖንሰርሺፕ በአውሮፓ ውስጥ በተፃፈ አንድ መፅሃፍ ላይ በተገኘ መረጃ መሰረት ኃይሌ ገብረስላሴን በስፖንሰርሺፕ ውል ለማስፈረም አዲዳስ እና ናይኪ ከባድ ትንቅንቅ ውስጥ ገብተው እንደነበር ተወስቶ፤ አዲዳስ ለአምስት አመት ውል በ2.5 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ ሰጥቶት እንዳሸነፈ ተገልጿል፡፡
9. ኃይሌና ስፖንሰርሺፕ
ዋና ስፖንሰሮች፤ አዲዳስ እና ፓወር ባር ናቸው፡፡ ፓወር ባር የተሰኘው ሃይለ ሰጭ ውሃን  ከ1998 እኤአ ጀምሮ እንደሚጠቀም ከኩባንያው ድረገፅ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡በስፖርት መጠጥ አቅራቢነት ከ20 ዓመታት በላይ ልምድ ባለው ኩባንያ የሚመረተው ፓወር ባር ቫይታሚን፤ መእድናት እና ካርቦሃይድሬት ያለው  ነው፡፡
ከሁለት ዓመታት በፊት ደግሞ ኃይሌ በዓለም አቀፍ ደረጃ አነጋጋሪ የነበረበትን የስፖንሰርሺፕ ውል ከስኮትላንዱ እውቅ ውስኪ ጋር ፈፅሞ ነበር፡፡ አትሌቱ በወቅቱ ስፖርተኛ ሆኖ መጠጥ በማስተዋወቁ ተወቅሷል፡፡ በውስኪ ብራንድ አምባሳደርነት 100ሺ ዶላር እንደተከፈለው በወቅቱ ተዘግቦ ነበር፡፡
10. ኃይሌና የገንዘብ ሽልማት
በዓለም አቀፉ የጎዳና ላይ ሩጫዎች ስታስቲክስ እና ውጤት አሰባሳቢ ተቋም በተሰራ ስሌት የምንግዜም ከፍተኛ የሽልማት ገንዘብ ያገኙ አትሌቶች ደረጃን ይመራል፡፡ ይህን ዓለም አቀፍ ደረጃ  በወንዶች ምድብ  የሚመራው በ52 የተለያዩ ጊዜያት በሰበሰበው 3 ሚሊዮን 546ሺ 674.80 ዶላር ( በኢትዮጵያ ብር 69 ሚሊዬን 511ሺ አካባቢ” ነው፡፡   የጎዳና ላይ ሩጫዎች የስታትስቲክስ ባለሙያዎች ዓለም አቀፍ ማህበር
(ARRS/ Associations of Road racing statisticians)  በድረገፁ ይፋ እንዳደረገው  በ1 የውድድር ዘመን ከፍተኛውን የሽልማት ገንዘብ በመከፈልም  አንደኛ ነው፡፡ በ2002 እኤአ ባገኘው 1 ሚሊዮን76ሺ 890 ዶላር ስለተቀበለ ነው፡፡
11. ኃይሌና ፎርብስ
ታዋቂው የቢዝነስ ጥናት አድራጊ ሚዲያ ፎርብስ በ2015 እኤአ ላይ ከአፍሪካ ተጽእኖ ፈጣሪ 40 እውቅ ሰዎች አንዱ ይፋ አድርጎታል ፡፡ በዚሁ የአፍሪካ ተጽእኖ ፈጣሪ ዝነኞች ደረጃ ኃይሌ አስረኛ ነው፡፡ ከእሱ ብልጫ የነበራቸው፡ ታዋቂው ናይጄርያዊ ደራሲ ቺንዋ አቼቤ፤ ሴኔጋላዊው ድምፃዊ ዩ ሱንዱር፤ አይቮራዊው ዲድዬ ድሮግባ፤ ትውልዱ ከሴኔጋል የሆነው ዓለም አቀፍ ድምፃዊ ኤኮን፤ ዋሌ ሶዬንካ እና ሌሎቹ የምእራብ አፍሪካ ሙዚቀኞች ሳሊፍ ኪዬታ፤ ሬሚ ኩቲ እና ቲያሚኒ ዲያሜቴ ናቸው፡፡
12.    ኃይሌና መፅሃፍት
በታላቁ አትሌት ዙርያ  ኢትዮጵያ ውስጥ የተፃፈ ዳጎስ ያለ መፅሃፍ ባይኖርም ጉልህ ተጠቃሽ የሚሆነው የጥበብ ውጤት በህይወት ታሪኩ ዙርያ የተሰራው እና ፅናት ወይም ‹‹ኢንዱራንስ፤ ዘ ስቶሪ ኦፍ ዘ ግሬተስት ዲስታንስ ራነር ኢን ሂስትሪ›› የተባለው ፊልም ነው፡፡ በሌሎች የዓለም ክፍሎች ግን ቢያንስ አምስት እውቅ መፅሃፍት የሩጫ ዘመን ስኬቱንና ህይወት ታሪኩን በመንተራስ ለንባብ በቅተዋል፡፡ “ዘ ግሬተስት፡ ዘ ሃይሌ ገብረስላሴ ስቶረሪ” የሚባለው መፅሃፍ በራሱ ሃይሌ ገብረስላሴ እና በጂም ዴኒሰን የተፃፈ ነው፡፡ ሁለተኛው መፅሃፍ ደግሞ “ኃይሌ ገብረስላሴ ዘ ግሬተስት ራነር ኦፍ ኦል ታይም” በሚል ርእስ በክላውስ ዊዴት የተፃፈው ነው፡፡ ሶስተኛው በጀርመንኛ ቋንቋ የተፃፈውና ስለልምምድ ፕሮግራሙ እና የውድድር ብቃቱ “ላውሪን ዊዝ ሃይሌ ገብረስላሴ፤ ዳትሬኒንግ ፕሮግራም” በሚል ርእስ አበበ በተባለ ግለሰብ፤ በቀድሞ አሰልጣኙ ወልደመስቀል ኮስትሬ እና በራሱ በኃይሌ ገብረስላሴ ትብብር የተዘጋጀው  ነው፡፡ ይህ መፅሃፍ ያገለገለው እንኳን በአማዞን ድረገፅ እስከ 723 ዶላር ዋጋ አለው፡፡ አራተኛው መፅሃፍ  በታዋቂው ጃፓናዊ የአትሌቲክስ ፎቶግራፈር ጂሮ ሞቺዙኪ ‹ኃይሌ ገብረስላሴ ኤምፐረር ኦፍ ሎንግ ዲስታንስ› በሚል ርእስ በተለያዩ ፎቶዎች ታጅቦ የቀረበ ነው፡፡ አምስተኛው መፅሃፍ ደግሞ “ኃይሌ ገብረስላሴ፤ አፍሪካ ሌጀንድ ሲርዬስ” በሚል በኤልዛቤት ቴብላ የተዘጋጀው ነው፡፡
13. ኃይሌና የክብር ሽልማት
በኦሎምፒኳ ከተማ ሉዛን ውስጥ  86 ዓመታት እድሜ ያለው በ‹ዘ አሶሴሽን ኢንተርናሲዮናሌ ዴላ ፕሬስ ስፖርትስ›  ልዩ ክብር ሽልማት ተሰጥቶታል፡፡ ሽልማቱ AIPS Power of Sport Award  ተብሎ የሚጠራ ሲሆን በየዓመቱ በስፖርቱ ዓለምን፤ አገርንና ማህበረሰብን  የለውጡ አስተዋፅኦ ላበረከቱ  የሚሰጥ ልዩ የክብር ነው፡፡  ሽልማቱ በአትሌት ምስል የተዘጋጀ የቅርፅ ስራ ሲሆን ተሰርቶ የተዘጋጀው በቻይናው የኦሎምፒክ ምርቶች አምራች እና አከፋፋይ ኩባንያ ሆናቭ ነው፡፡  ለዚህ ክብር ለመመረጥ የበቃው በአትሌቲክስ ስፖርት ለረጅም ጊዜ በከፍተኛ ውጤት በመቆየቱ፤ በስፖርቱ ያለው ተወዳጅነት በአገሩ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም በመሆኑ፤ በጂ4ኤስ ታዳጊዎች ፕሮግራም 14 ወጣት አትሌቶች በ2012 የለንደን ኦሎምፒክ ተሳትፎ እንዲያገኙ በፈጠረው መነቃቃት እና በሰጠው ድጋፍ፤ በፀረ ኤድስ ዘመቻ ለአመታት ባበረከተው አስተዋጽኦ፤ በአፍሪካ ትልቁ የሆነውና  የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር በመመስረትና በዚሁ ስር የሚካሄዱ ውድድሮችን በተለያዩ የተባበሩት መንግስታት እና የበጎ አድራጎት ተቋማት ብሄራዊ መልዕክቶች እንዲታጀብ በማድረግ በፈፀመው ተግባር እውቅና በማግኘቱ ነው፡፡   በስፔን ትልቅ ክብር የሚሰጠውን‹ፕሪንስ ኦስተሪዬስ አዋርድስ ፎር ስፖርትስ› በስፖርት የሰው ልጅን የላቀ ብቃት እና ችሎታ ያሳደገ አትሌት በመባል ከስፔን ንጉሳውያን ቤተሰብ እጅ ተቀብሏል፡፡  በወቅቱ ይህን ሽልማት የወሰደው ከፍተኛ ፉክክር ከታዋቂው ኳስ ተጨዋች ራውል ጎንዛለዝ ጋር በማድረግ ነበር፡፡ ‹ፕሪንስ ኦስተሪዬስ አዋርድስ ፎር ስፖርትስ›   የተባለው የክብር ሽልማት በጆኖ ሚር የተባለ ቀራፂ የተሰራ ቅርፅ፤50ሺዩሮ፤ ዲፕሎማና የሽልማቱ አዘጋጅ ፋውንዴሽን አርማ የተቀረፀበት ስጦታን የሚያካትት ነው፡፡ በዓለም አቀፉ የጎዳና ላይ ሩጫዎች ማህበር በ2006፤2007 እና 2008 እኤአ የዓለም ምርጥ አትሌት ተብሎ ተሸልሟል፡፡
14. ኃይሌና ፖለቲካ
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ለመግባት ፍላጎት እንዳለውና ፕሬዝዳንት ለመሆን  እንደሚፈልግ በበርካታ ዘገባዎች ተጠቅሷል፡፡  ፖለቲካን የፈለገው የብዙ ወገኑን ጥቅም ለማስጠበቅ እንደሆነ ለአሶስዬትድ ፕሬስ ባንድ ወቅት የገለፀ ሲሆን ህዝብን የበለጠ የሚረዳበት እድል ስለሚሻ መሆኑን ተናግሯል፡፡ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ የፓርላማ ተመራጭ ሆኖ ለመወዳደር እቅድ አለው፡፡ የአገር ሽማግሌ ሆኖም ያገለግላል እንዳለው እና ወደ አገሪቱ ፖለቲካ የመግባት ፍላጎት እንዳለውም በርካታ የዓለም ሚዲያዎች ባሰራጩት መረጃ ገልፀዋል፡፡  በ2017 ፓርላማ ለመግባት በግል ተወዳዳሪነት ምርጫ እንደሚገባ እና አገሪቱ በእድገት ወደፊት እንድትራመድ የመርዳት ፍላጎት አለኝ ማለቱ ተዘግቧል፡፡
14. ኃይሌና ቅፅል ስሞቹ
ዘ ኤምፐረር፤ ሊትል ኤምፐረር፤ ዘ ግሬት ጋቢ፤ ዘ ኤጅለስ ራነር፤ ኤማን ፍሮም አናዘር ፕላኔት እና የምንግዜም የረጅም ርቀት ምርጥ ሯጭ የሚሉ ስሞችን አትርፏል፡፡
15. ኃይሌና ልምምዱ
ስለሚሰራው ልምምድ እና ተያያዥ መርሃግብሮች ከየትኛውም የዓለም አትሌት በተለየ ግልፅ መሆኑ ይነገራል፡፡ በሳምንት እስከ 190 ኪሎሜትር ይሮጣል፡፡ በሳምንት እስከ 13 የልምምድ መርሃግብሮች አሉት፡፡  3 መርሃግብሮች ፍጥነቱን ይሰራባቸዋል፡፡
16. ባለፉት 25 ዓመታት በመላው ዓለም ከአትሌቲክስ ውድድር በተያያዘ፤ በስራ እና ጉብኝት 17. ከ100 አገራት በላይ ተጉዟል፡፡
18. የሚወደው የሩጫ አይነት 10ሺ ሜትር ውድድርን ነው።
19. ከባድ ተፎካካሪዬ የሚለው ፖል ቴርጋት ነው፡፡
20. ከአውሮፓ አትሌቶች ለፓውላ ራድክሊፍ ልባዊ አድናቆት አለው፡፡
21. ምሩፅ ይፍጠርን ተምሳሌት ያደርጋል፡፡ በሞስኮ ኦሎምፒክ በረጅም ርቀት ባገኛቸው ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎች ወደ ሩጫ ለመግባት ምክንያት ሆኖኛል፡፡
22. በሲድኒ ኦሎምፒክ ከፖል ቴርጋት ያደረገው ፉክክር ምርጡ ውድድሩ ነው፡፡ በ2007 የለንደን ማራቶን ውድድር አቋርጦ ለመውጣት መገደዱ መጥፎ የውድድር ትዝታው ነው፡፡
23. ሃይሌጋብር በሚል የሚሰራጨው የአትሌቱ የቲውተር ማስታወሻ እስከ 140ሺ ለአድናቂዎች ሲከታተሉት እሱም በዚህ ማህበራዊ ድረገፅ ከ800 በላይ አጫጭር ፅሁፎችን ማስተላለፉን ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 3178 times