Monday, 25 May 2015 08:52

ለጨርቆስ ነዋሪዎች አሁንም ሌላ ሃዘን!

Written by  ኤልሳቤጥ እቁባይ
Rate this item
(8 votes)

8 ተጨማሪ ወጣቶች በሜዲትራንያን ባህር ህይወታቸው ማለፉ ተረጋገጠ
በሰመጠችው ጀልባ እስካሁን 16 ኢትዮጵያውያን መሞታቸው ታውቋል
አንድ ወላጅ መርዶ ቢነገራቸውም የልጃቸውን መሞት አልተቀበሉም

   ባለፈው ወር 900 የሚደርሱ ስደተኞችን አሳፍራ፣ በሜዲትራኒያን ባህር ስትጓዝ  በነበረች ጀልባ ላይ በደረሰው የመስመጥ አደጋ ህይወታቸው ያለፈ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች መርዶ አሁንም የቀጠለ ሲሆን፤ 8 የጨርቆስ ወጣቶች መርዶ ለየቤተሰቦቻቸው ተነግሮ ሃዘን ተቀምጠዋል፡፡ አንድ ወላጅ  ግን “ልጄ አልሞተም” በሚል  መርዶውን አልተቀበሉትም፡፡
መላኩ እሬንሶ፣ ፋይዝ አብደላ፣ አብርሃም ንጉሴ፣ አቤል ሽብሩ፣ ኢስማኤል መሃመድ፣ ታዲዮስ ሙሉጌታ እና ፉአድ ዲኖ የተባሉት ወጣቶች ናቸው በሜዲትራንያን ባህር ህይወታቸው ማለፉ የተነገረው፡፡   
ባለፈው ጥቅምት ወር አምስት ሆነው ከአገር የወጡት  ብሩክ፣ አሸናፊ፣ መላኩ እሬንሶ፣ አብርሀም ንጉሴ እና ፋይዝ አብደላ የጨርቆስ ሰፈር አብሮ አደግ ጓደኛሞች ነበሩ፡፡ ወጣቶቹ  እስከ ሊቢያ በዘለቀው  የስደት ጉዞ አልተለያዩም ነበር፡፡ ወደ አውሮፓ የሚያደርጉትን የጀልባ ጉዞም በአንድ ላይ ለማድረግ ነበር ሃሳባቸው፡፡  ሆኖም ብሩክ እና አሸናፊ  ጀልባዋ ሞልታለች ተብለው ሳይሳፈሩ በመቅረታቸው  ከሦስቱ ጓደኞቻቸው ጋር ተለያዩ። ጣልያን ለመገናኘት ግን ሁሉም በየልባቸው ተስፋ ሰንቀው ነበር፡፡
መላኩ እሬንሶ፣ አብርሀም ንጉሴ እና ፋይዝ አብደላ የተሳፈሩባት የህገ-ወጥ ደላሎች ጀልባ ግን የሁሉንም ተስፋ አመከነችው፡፡ ጣልያን ከመድረሷ በፊት በመስጠሟ የሦስቱ ወጣት ኢትዮጵያውያን ህይወት ከእነ ህልሞቻቸው ሜዲትራኒያን ባህር ውስጥ ሰጥሞ ቀረ፡፡  
መላኩ እሬንሶ የ24 አመት ወጣት ሲሆን በአገር ውስጥ ገቢ ሚኒስቴር በሞተረኛነት ተቀጥሮ  ይሰራ ነበረ፡፡ የተሻለ ህይወት ፍለጋ ለስደት እንዳነሳሳው የሚናገረው ወንድሙ፤ቤተሰቦቹ ሃሳቡን እንዲቀይር ቢለምኑትም እምቢ ማለቱን ይገልጻል፡፡ ከአገር ከወጣ በኋላ ከቤተሰብ ጋር በስልክ ይገናኝ ነበር፡፡ ከፋሲካ በኋላ በዋለው ሐሙስ ስልክ ደውሎ “ነገ ወደ ጣልያን ልሳፈር ነው” ብሎ  መናገሩን ወንድሙ ጠቁሟል፡፡
ፋይዝ አብደላ ግንቦት 20 ሲመጣ 24 አመት እንደሚሞላው የገለጸው ወንድሙ፤ ከአገር ከመውጣቱ በፊት ሁለት ሆነው ለገሀር አካባቢ በመነፅር ስራ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ይደግፉ እንደነበር ተናግሯል፡፡  በባቡር መንገድ ግንባታው የተነሳ ከሚሰሩበት ቦታ እንዲነሱ መደረጉንና ንብረታቸው ተወርሶ መቅረቱን የገለጸው የሟች ወንድም፤ ፋይዝ በዚሁ ተስፋ በመቁረጥ ከአገር ለመውጣት መነሳቱን ተናግሯል፡፡  ሃሳቡን ለቤተሰብ ሲገልጽ ሌላ አማራጭ እንዲፈልግ የተነገረው ቢሆንም እሱ በጄ አላለም፡፡  “ሳልነግራችሁ ከምሄድ ቢያንስ እወቁትና ፀልዩልኝ ብዬ ነው” አለና ከጓደኞቹ ጋር ተያይዞ ሄደ ብሏል- ወንድሙ፡፡ “ፋይዝ ለጉዞው ብዙ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ እንኳ አያውቅም ነበር፤ ቤተሰቡም የገንዘብ አቅም ስለሌለው ሊቢያ ከገቡ በኋላ ጓደኞቹ ወደ አውሮፓ ሲሻገሩ እሱ ከወር በላይ ገንዘብ እስኪያገኝ መጠበቅ ነበረበት” ያለው ወንድሙ፤ በሊቢያ ቆይታውም እጅግ የከፋ መከራ ማሳለፉን ነግሮናል ብሏል፡፡
ወጣት አብርሀም ንጉሴ፤ የእነ መላኩ እና ፋይዝ አብሮ አደግ ጓደኛ ሲሆን እሱ ከአገር ከወጣ በኋላ ቤተሰቦቹ መኖሪያቸውን ወደ ካራቆሬ ቀይረዋል። በሊቢያ በአይኤስ አሸባሪ ቡድን የተፈፀመው ግድያ ከተሰማ በኋላ ደላሎች ከኢትዮጵያ የሚደወል ስልክ እንደማያነሱ የሚናገረው የመላኩ ወንድም፤ ባህሬን በምትገኝ እህታቸው አማካኝነት ወደ ደላላ በመደወል ባደረጉት ማጣራትና ጀልባዋ ሞልታለች ተብለው ከጉዞው በቀሩት የሰፈሮቻቸው ልጆች አማካኝነት ባገኙት መረጃ፤ መላኩ፣ አብርሀም እና ፋይዝ በአደጋው ህይወታቸው እንዳለፈ ለማወቅ እንደቻሉ ተናግሯል፡፡
አቤል ሽብሩ ሌላው ህልሙንና ህይወቱን የሜዲትራኒያን ባህር ውጦ ያስቀረበት የ25 አመት ወጣት ነው፡፡ አገር ውስጥ ሳለ እየተሯሯጠ የኤሌክትሪክ ስራዎችን ይሰራ እንደነበር የገለጸው ወንድሙ፤ ወደ ውጭ ለመሄድ ማሰቡን ለቤተሰብ ሲናገር ሃሳቡን ለማስቀየር ብዙ ቢጣርም ልቡ ክፉኛ ተነሳስቶ ስለነበር ከጉዞው ለማስቀረት አለመቻሉን ተናግሯል፡፡ ከአገር የወጣው ከስድስት የሰፈሩ ልጆች ጋር ቢሆንም አብዛኞቹ ከመተማ ሲመለሱ፣ እሱ አልመለስም ብሎ መንገዱን ቀጠለ፡፡ ከቤተሰቡም ጋር በስልክ ይገናኝ ነበር፡፡ የስደት ጉዞው እጅግ ከባድ መሆኑን ይነግራቸው እንደነበር የሚያስረዳው ወንድሙ፤ አብረውት ከወጡት የሰፈሩ ልጆች ጋር ቢለያይም ሱዳን ላይ ከሌሎች የጨርቆስ ልጆች ጋር መገናኘቱን ነግሮኝ ነበር ብሏል፡፡ አቤል ጀልባዋ ላይ ሲሳፈር ሞልቷል ተብለው ከተመለሱት ልጆች ለአንዱ፣ የቤተሰቡን አድራሻ በመስጠት “የሆነ ችግር ከተፈጠረ ንገርልኝ” ሲል አደራ ሰጥቶት ነበር። አደጋው ከተከሰተ በኋላ መርዶውን ለቤተሰቡ የተናገረውም ይኸው አደራውን የተቀበለው ልጅ እንደሆነ የሟች ወንድም ይገልጻል፡፡
ኢስማኤል መሀመድ የ19 አመት ወጣት ሲሆን እሱም ልክ እንደ ሌሎቹ የስደት ጉዞ ማሰቡን ሲገልጽ፣ ሃሳቡን ለማስቀየር ብዙ ተለምኖ እንደነበር ቤተሰቦቹ ተናግረዋል፡፡  ሆኖም የተሻለ ነገን በማለም ህይወቱን ለማሻሻል በሃሳቡ ጸና፡፡ ግን ምን ያደርጋል --- ያሰበበት ከመድረሱ በፊት የሜዲትራኒያን ባህር ህይወቱን ነጠቀው፡፡ ከአገር ከወጣ በኋላ ስልክ እየደወለ፣ ገንዘብ ሲያስፈልገው ይልኩለት እንደነበር የተናገሩት አባቱ፤ከእሱ ጋር አብረው ሊቢያ የገቡ ነገር ግን ጀልባዋ በመሙላቷ ሳይሳፈሩ የቀሩ የሰፈሩ ልጆች በሰጠመችው ጀልባ ላይ መሳፈሩን አረጋግጠውልኛል ብለዋል፡፡ የኢስማኤል ታናሽ ወንድምም ባለፈው ጥር ወር የመጀመሪያ ሴሚስተር ፈተና ተፈትኖ ውጤት እንኳን ሳይቀበል በተመሳሳይ መንገድ ከአገር መውጣቱንና  አሁን ጣሊያን መግባቱን እንደሰሙ አባት ተናግረዋል፡፡ ኢስማኤል ድንገት ከአደጋው  ተርፎ ይሆናል በሚል ተስፋ በጣሊያን የስደተኞች ካምፕ ውስጥ ባሉ ልጆች አማካኝነት ያፈላለጉት ቢሆንም ሊገኝ እንዳልቻለ የሟች አባት ተናግረዋል፡፡
በሮያል ፎም የስፖንጅ ፍራሽ ፋብሪካ ውስጥ በሞተረኛነት ይሰራ የነበረው ታዲዮስ ሙሉጌታ፤ የ22 አመት ወጣት ሲሆን  ከአገር የወጣው ባለፈው መጋቢት ወር ነው፡፡ የሱዳን ቪዛውን ካስመታ በኋላ ለእናቱ ሲነግራቸው አይሆንም በማለታቸው ለአንድ ወር ያህል አኩርፏቸው ነበር፡፡ “እዚህ የፈለከውን ነገር ላድርግልህ፤አትሂድ” ቢሉትም  አሻፈረኝ በማለቱ ቤተሰቦቹ  አልቅሰው እንደሸኙት ይናገራሉ።
ከፋሲካ በኋላ ባለው ሰኞ ቤተሰቡ ጋ ስልክ ደውሎ “ልንነሳ ነው” ብሏቸው ነበር፡፡ የጠየቀውን ብር ከላኩለት በኋላ ሐሙስ ቀን ለመጨረሻ ጊዜ ደውሎላቸው “ውሀው በጣም ሞልቷል፤ ፖሊሶችም አሉ፤ እንዴት እንደምንሆን አላውቅም” ሲል  ስጋቱን ገልጾላቸው እንደነበር ቤተሰቦቹ ይናገራሉ፡፡ ቅዳሜ ዕለት ደግሞ ደላላ ለአባቱ ደውሎ፤ “እንኳን ደስ ያላችሁ፤ ልጃችሁ ጣሊያን ገባ” ይላቸዋል፡፡ ልጁ ጣሊያን ገባ ቢባልም ድምፁን ስላጠፋ መልሰው ደላላው ጋር ቢደውሉም ስልክ አያነሳም፡፡
ይሄኔ በጭንቀት የተወጠረው ቤተሰብ፤ ሱዳን ያለችው ሴት ደላላ ጋር ይደውላል፡፡ ከደላላዋ የሰሙት ዜና ግን አስደንጋጭ ነበር፡፡ “ሊቢያ ያለው ደላላ መርከቧ የሁለት ሰአት መንገድ ሲቀራት ነው ጣልያን ገብቷል ብሎ የነገራችሁ፤ ይሄ በአገር የመጣ ነው፤ እሱን ጨምሮ ሌሎች የጨርቆስ ልጆችም ህይወት አልፏል” ስትል አረዳቻቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ  አሁን ጣሊያን የገቡ የሰፈር ልጆች፣ ታዲዮስ በዛች በሰጠመች ጀልባ ላይ ተሳፍሮ እንደነበር ስላረጋገጡልን ሀዘን ተቀምጠናል ብለዋል የሟች አጎት፡፡
የፉአድ ዲኖ ቤተሰቦችም ልጃቸው በአደጋው እንደሞተ ተነግሯቸው ሀዘን የተቀመጡ ቢሆንም በህይወት ሊኖር ይችላል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የልጃቸው መርዶ የተነገራቸው አንዲት እናት ግን ማረጋገጫ ባይኖራቸውም “ልጄ አልሞተም” በሚል ሀዘን አለመቀመጣቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ባለፈው ወር በሜዲትራንያን ባህር 900 የሚደርሱ  ስደተኞችን ከአቅሟ በላይ ጭና ስትጓዝ በነበረች ጀልባ ላይ በደረሰው የመስጠም አደጋ የተረፉት ሰዎች 30 አይሞሉም፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት በዚሁ አደጋ 8 የአባኮራ ሰፈር ወጣቶች ህይወታቸውን እንዳጡ መዘገባችን ይታወሳል፡፡

Read 3994 times