Saturday, 30 May 2015 12:06

የጋዜጠኞቹ ልዩ ድራማ (ከዝዋይ መልስ!)

Written by  ምግባር ተካ
Rate this item
(5 votes)

 

 

 

መንደርደርያ 

ካስቴል ወይን ጠጅ ፋብሪካ ባለፈው ግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ የተቋቋመበትን 1ኛ ዓመቱን በማስመልከት፣ የወይን ፌስቲቫል በዝዋይ ከተማ በፋብሪካው ቅጥር ግቢ ውስጥ  አዘጋጅቶ ነበር፡፡ ድርጅቱ በዚህ ፌስቲቫል ላይ የውጭ አገር ዜጎች፣ የካስቴል ወይን አከፋፋዮች፣ የባር ባለቤቶች  እንዲሁም   ጋዜጠኞችን የጋበዘ ሲሆን የወይን አጠማመቁን ሂደት ካሳየ በኋላ ተጋባዦቹን ብሉልኝ ጠጡልኝ ይል ጀመር፡፡ ወይን ጠጅ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስና ካስቴል ቢራ በገፍ ቀርቧል፡፡ 

 ጋዜጠኞች ምሳ ከበላን በኋላ እንደየፍላጐታችን ከቢራውም ከወይኑም አንድ ሁለት አልን፡፡ ኧረ የምን አንድ ሁለት? ከዚያም በላይ ተጐነጨን፡፡ ገሚሱ ጋዜጠኛ አቅሙን አውቆ መጠጣቱን አቆመና፤ “አንሄድም እንዴ?” ማለት ተጀመረ፡፡ ገሚሱ ደግሞ በሞቅታ “ወደ ቤታችን አይደለም’ዴ የምንሄደው? ምን አስቸኮለን? እንጠጣ እንጂ” አለ፡፡ በመጨረሻ  9፡30 ላይ እንደምንም ተሰባስበን ከፋብሪካው ወጣን፡፡ በአውቶብሳችን ውስጥ 6 ሰዎች ሊፍት ጠይቀው አብረውን ተሳፍረው ነበር፡፡

ባለ 5 ገቢሩ ድራማ የሚጀምረው ከዝዋይ ከተማ ወጥተን፣ ወደ አዲስ አበባ እየተጓዝን ሳለ ነው፡፡

መቸት

ቦታው ፡- ከዝዋይ አዲስ አበባ                     መስመር ላይ

ሰዓት፡- 9፡45 ገደማ

ተዋናዮች፡- ጋዜጠኞችና ሊፍት ጠይቀው              የገቡ እንግዶች

ክፍል 1፣ ገቢር 1

ተዋናዮች፡- ጋዜጠኛና እንግዳ

በልካቸው የጠጡ ጋዜጠኞች ወንበር ይዘው ተቀምጠዋል፡፡ ሞቅ ያላቸው ደግሞ በመተላለፊያው ወዲያ ወዲህ እያሉ ጮክ ብለው ከጓደኞቻቸው ጋር ያወራሉ፡፡ አንድ ፎቶ ጋዜጠኛ ፊት አካባቢ ከተቀመጠ ጓደኛው ጋር ይጫወታል፡፡ ሊፍት ጠይቀው ከገቡት ሰዎች መካከል የፊት ረድፍ ወንበር ላይ የነበረው እንግዳ ተሳፋሪ፣ የወንበሩን መደገፊያ ይዞ ቆሞ፣ ፎቶ ጋዜጠኛውንና ጋዜጠኛ ጓደኛውን  ቁልቁል ያያቸዋል፡፡

ብዙ አያስታውቅበትም እንጂ በደንብ ጠጥቷል፡፡ ፎቶ ጋዜጠኛው ኮስመን ያለ ነው፡፡ እንግዳው መካከለኛ ቁመትና ሞላ የተደላደለ ሰውነት አለው፡፡ አንዳንድ ሰው መጠጥ ሲቀምስ እውነተኛ ማንነቱ ገሃድ ይወጣል፡፡ ድብድብ ያምረዋል፡፡ እንግዳው ተሳፋሪ፣ ፎቶ ጋዜጠኛውን ሲመለከት፤“ይቺን ጪባ አንዴ በቴስታ ብላት አትዘረጋትም” የሚል ስሜት ሳያድርበት አልቀረም፡፡ እናም ያለምንም ማስጠንቀቂያ ፎቶ ጋዜጠኛውን በቴስታ እንካ ቅመስ አለው፡፡ ተመቺው አፀፋውን ለመመለስ ተነሳ፤ነገር ግን አፍንጫው እየደማ ስለነበር ተመልሶ ጐንበስ አለ፡፡ሁኔታውን የታዘብን ሁሉ እንግዳው ተሳፋሪ ላይ ጮህንበት፡፡ የስድብ መዓት አወረድንበት፡፡ ቆመው ከነበሩት ጋዜጠኞች መካከል ጥቂቱ፤ “ምንም ሳያደርገው እንዴት ይመታዋል?” በማለት ሰውየውን ለመምታት ተጋብዘው ነበር፤ ሌሎች  መሃል ገብተው ገላገሉ፡፡በዚህ ሁሉ መሃል ሰውዬው አንዲት ቃል አልተነፈሰም፡፡ ከእኔ ፊት 2ኛ ወንበር ላይ የተቀመጠ ሌላ እንግዳ ደግሞ ለተማቺው ማገዝ ፈልጐ ሲቁነጠነጥ ነበር፡፡

እንግዳው አናደደኝና በቁጣ ስሜት፤ “ሊፍት ለምኖ ገብቶ ምንም ያላደረገውን ሰው እንዴት ይመታል? ባለጌ ነው!” አልኩ፡፡ ከሰውየው ጐን ተቀምጣ ስትጨነቅ የነበረችው ሴት፣

“አዎ! እሱስ፤ ምንም ሳያደርገው መማታቱ ጥፋተኛ ነው፡፡ ሰክሮ’ኮ ነው” አለች፡፡

ይኼኔ አገርግሮ የነበረው ሰውዬ  ተረጋጋ፣ ፀቡም በርዶ መኪና ተንቀሳቀሰ፡፡ 

ባለ አንድ ገቢር፣ ሁለት

ተዋናዮች፡- ጋዜጠኞችና እንግዳ

5 ደቂቃ እንኳ ሳንጓዝ ነው ሁለተኛው ጠብ የተጀመረው፡፡ አሁንም ያው የመጀመሪያው ተንኳሽ ነው ጸብ የጫረው፡፡ ሰውየው ድምጹን አጥፍቶ ከመቀመጫው በመነሳት በእኔ ትይዩ 3ኛ ረድፍ ላይ የተቀመጠ የፎቶ ጋዜጠኛውን የቅርብ ጓደኛ ቡጢ አሳረፈበት፡፡ ለጓደኛው አግዞ ለምን ሰደበኝ ይመስላል፡፡ ደግነቱ ሰውየው ከአንድ ጊዜ በላይ አይሰነዝርም፡፡

ቡጢ ያረፈበት ጋዜጠኛ የአፀፋ ምላሽ ሰንዝሯል፡፡ በቀድሞ ድርጊቱ ተናደው የነበሩ ጋዜጠኞችም መጠጥ ባደከመው ጉልበት ቸብ ቸብ አድርገው ሲገፈትሩት፣ ስካር አድክሞት ስለነበር ሚዛኑን መጠበቅ አቅቶት የመኪናው በር ላይ በጀርባው ተዘረጋ፡፡ ሁለቱ  ተመቺዎችና አንድ ጋዜጠኛ፤ አንድ ሁለቴ በእግራቸው መቱት፡፡ “ኡኡ! ለሦስት ደበደቡኝ” አለና ፀጥ አለ፡፡በዚህ ጊዜ ሌሎች ጋዜጠኞች በቃ! በቃ! በማለት ልጆቹን ተቆጡና፣ሰውዬውን በሳንሳ ተሸክመው ከመኪናው በማውረድ ንፋስ እንዲያገኝ መንገድ ዳር በደረቱ አስተኙት፡፡ ሰውየው ለ10 ደቂቃ ያህል ቢተኛም ሊነቃ አልቻለም፡፡ ሰዓቱ ደግሞ እየመሸ ነው፡፡ ያወረዱት ጋዜጠኞች ተሸክመው መኪና ውስጥ በማስገባት የመጀመሪያው ረድፍ  ወንበሮች ላይ አጋደሙት፡፡

ክፍል አንድ፣ ገቢር ሦስት

ተዋናዮች፡- ጋዜጠኞች ጋዜጠኛ

 ሞቅ ያለው ሌላ ጋዜጠኛ ምንም ያልቀመሰ ለመምሰል እየሞከረ፣የተፈጠረውን ነገር ረስተን እየተዝናናን እንሂድ በማለት፣ከኪሱ ገንዘብ አውጥቶ እያሳየ፣“እዚች ላይ ያላችሁን ጠብ አድርጉ” እያለ ከፊት ጀምሮ ወደ ኋላ ገንዘብ መሰብሰብ ጀመረ፡፡ ብዙዎች በሐሳቡ አልተስማሙም፡፡ ስሙን እየጠሩ “ተቀመጥ ተቀመጥ” እያሉ ቢጮኹም እሱ ግን ተቃውሞውን ከመጤፍ  አልቆጠረውም፡፡ 

ዕቅዱ የሰመረለት አይመስልም፡፡ እኔ ጋ እስኪደርስ ራሱ ካወጣውና ሊፍት ጠይቃ የገባችው ሴት ከሰጠችው ገንዘብ በቀር ምንም አልያዘም፡፡ “የለኝም” ሲባል ዝም ብሎ ነው አልፎ የሚሄደው፡፡ እኔም ፈቃደኛ አለመሆኔን ሲያይ አልፎኝ በመሄድ፣መሃል ላይ እጅብ ብለው ወደቆሙት ሞቅ ያላቸው ጋዜጠኞች ሄደ፡፡ ከመቼው ከኋላ ጠብ እንደተነሳ እግዜር ይወቀው፡፡ ገንዘብ ሲጠይቅ የነበረው ጋዜጠኛ በቴስታ ከተመታው ፎቶ ጋዜጠኛ ጋር የስድብ ጥይት መወራወር ጀመሩ፡፡ ለዱላ ሲገባበዙ መሃል ገብተው ገላገሏቸው፡፡ አንደኛው ለገላጋይ እያስቸገረ፤ “እናትህ ---፤ አንት የሻዒቢያ ተላላኪ” ሲል ተሳደበ፡፡የጋዜጠኞቹ ሁኔታ ከቁጥጥሩ ውጭ የሆነበት የመኪናው ሾፌር፣ በሌላ አውቶቡስ ለተሳፈረው አስተባባሪያች ደውሎ የሆነውን ነገረው፡፡ ጠቡ በገላጋዮቹ በርዶ ጉዞ ጀመርን፡፡ ጥቂት እንደተጓዝን የፊት ረድፍ ወንበር ላይ የተጋደመው ሰካራም ቀና እንኳ ሳይል አስመለሰው፡፡ሦስቱ ፀቦች የተነሱት ከዝዋይ ተነስተን መቂ እስክንደርስ ነበር፡፡ ሰክሮ የተኛው ሰውዬ አልነቃ ስላለ ምናልባት አሞት ይሆናል በሚል መቂ ስንደርስ፣ ወደ ሐኪም ቤት ወሰድነው፡፡ የክሊኒኩ ሠራተኞች ሁኔታው ሲነገራቸው ለመተባበር ፈቃደኛ ሆኑና መኪናው ድረስ መጥተው፣ ሰውዬውን ከመረመሩት በኋላ ከስካር በስተቀር ምንም ችግር እንደሌለበት ነገሩን፡፡

ክፍል አንድ፤ ገቢር አራት

ተዋናዮች፡- የሚዲያ ኃላፊና ሊፍት ጠይቃ የገባች ወጣት 

ከክሊኒኩ እንደተመለስን መኪናችን ለጥቂት ጊዜ ቆም ብሎ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ሊፍት ጠይቀው ከገቡት ሰዎች መካከል መጨረሻ ወንበር ላይ የነበረችው ወጣት በተፈጠረው ነገር መናደዷን ገምቻለሁ፡፡ በዚያ ላይ የሚዲያ ኃላፊው አጠገቧ ቆሞ ይነዘንዛታል፡፡ ጠበሳ መሆኑ ነው፡፡ ቢቸግራት ከመኪናው ለመውረድ ተነሳች፡፡ ሃላፊው ይባስ ብሎ ማለፊያ መንገድ ዘጋባት፡፡ “አሳልፈኝ እንጂ” ስትል ጮኸች፡፡ ዞር ብዬ አየሁ፡፡ መንገድ የዘጋባት የማውቀው ጋዜጠኛ መሆኑን ሳይ፣ ስሙን ጠርቼ “አሳልፋት እንጂ” አልኩ፡፡ ዞር ብሎ አይቶኝ ምንም አላደረኳትም’ኮ በሚል ከበሬታ ፈገግ እያለ “እህቴ’ኮ ናት” አለኝ፡፡ “እህትህም ብትሆን ልለፍ ስትል አሳልፋት” አልኩትና መንገዱን ለቀቀላት፡፡ ትልቅ ሻንጣዋን አብሯት ከነበረው ልጅ ጋር ይዛ ለመውረድ ወደ በሩ ሄደች፡፡ በሩ ጋ  ደግሞ ሌላ ችግር ገጠማት፡፡

ክፍል አንድ፤ ገቢር አምስት

ተዋናዮች፡- ሌላ ፎቶ ጋዜጠኛና ወጣቷ እንግዳ

ግራና ቀኝ ባሉት የመጀመሪያ ረድፍ ወንበሮች ላይ በቴስታ ተማቺው ሰካራም ተጋድሟል፡፡ አጠገቡ ጥቂት ጋዜጠኞች ቆመዋል፡፡ አንደኛው ሌላ ፎቶ ጋዜጠኛ ነው፡፡ ወጣቷ ሰካራሙን ተራምዳ ለማለፍ ስትል ፎቶ ጋዜጠኛው ፊቷ ተገተረባት፡፡ ሊግባባት ፈልጎ ነበር፡፡ ወጣቷ በንዴት ብው! አለችና “አሳልፈኝ!” በማለት እንደገና ጮኸች፡፡ የጋዜጠኛውን ስም ስለማውቅ ጠርቼ፤ “አሳልፋት እንጂ” አልኩት፡፡

 ፎቶ ጋዜጠኛውም ፈገግ እያለ፤ “ምንም አላረኳትም’ኮ ሻንጣሽን ላሳልፍልሽ ነው ያልኳት” አለኝ፡፡ “ራሷ ታሳልፍ ተዋት” አልኩትና መንገዱን ለቀቀላት፡፡

ወጣቷ በንዴት ጦፋ ስለነበረ፣ ሻንጣዋን ካሳለፈች በኋላ፤“ስቱፒድ!” ብላ ሰድባው ወረደች፡፡ ፎቶ ጋዜጠኛውም እንዴት ትሰድበኛለች ብሎ በመጦፍ፣ ወጥቶ ሊደበድባት ሲጋበዝ፣ ውጭ የነበሩ ጋዜጠኞች ያዙት፡፡

                         ****** ******

መጠጥ በጣም መጥፎ ጠላትና አደገኛ አሳሳች ነው፡፡ ከልክ እንዳያልፍ ተቆጣጥረው በጥንቃቄ ካልጠጡ፣ በተገላቢጦሽ የሰዎችን አዕምሮ ይቆጣጠርና ተገዢው ያደርጋቸዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ይሉኝታ ይጠፋል፣ ማኀበራዊ ሕጐችና ደንቦች ይጣሳሉ፡፡ ሰው ምን ይለኛል? የሚል ስጋት ይጠፋና ጤነኛ ሆነው የማያደርጉትን ለመፈጸም ይገፋፋሉ፡፡

የሚዲያ ሃላፊው ጋዜጠኛ፤ ስለሴቶች መብት መከበር፣ ስለሴቶች እኩልነት፣ ሴት ልጅ ከፍላጐቷ ውጭ ምንም ዓይነት ፆታዊ ትንኮሳ (አቢዩዝ) ሊደረግባት እንደማይገባ ብዙ ጊዜ በሚዲያው እንደተናገረና እንዳስተማረ እገምታለሁ፡፡ ከመጠጥ በኋላ ግን ሁሉ ነገር ተረሳ፡፡  ሾፌሩ የደወለላት አስተባባሪያችን መኪናውን አስቁሞ፤ “ምነው እንደዚህ ሆናችሁ? አፈርኩባችሁ!” አለን፡፡ ያኔ አብዛኞቹ ጋዜጠኞች ስካሩ የበረደላቸው ቢሆንም ጥቂት ያልበረደላቸው የሚያደርጉት ነገር አስጠልቶኝ ነበር፡፡ ስለዚህ ከመኪናው ወርጄ “አፈርኩባችሁ” ያለን አስተባባሪያችን ወደነበረበት አውቶቡስ ለምኜ ገባሁ፡፡

ሁኔታው ያላማራቸው ጥቂት ጋዜጠኞች የመጀመሪያው ፀብ እንደተጀመረ ከኛ መኪና ላይ ወርደው በትራንስፖርት መመለሳቸውን፣ የሰከረው ሰውዬ ነቅቶ ምንም ሳይናገር ዝም ብሎ መቀመጡን፣ ሳሪስ ሲደርስም ጋዜጠኞቹን “ክፉ አይንካችሁ” ብሎ መውረዱን በማግስቱ ሰማሁ፡፡

 

 

 

 

Read 2612 times