Saturday, 30 May 2015 12:42

እኛ፣ጥላሁን ገሠሠ እና የጋራ ሕይወታችን

Written by  አ.ተ
Rate this item
(9 votes)

 

 

 

                                                    አጭር ዳሰሳ

‹‹ትንፋሼ ተቀርጾ ይቀመጥ ማልቀሻ

ይህ ነው የሞትሁ’ለት የኔ ማስታወሻ››

 በእርግጥም የጥላሁን ገሠሠ ማስታወሻ ትንፋሹ እና ከ50 ዓመታት በላይ የነገሠበት ሕያው ድምጹ ነው፡፡ ዘከሪያ መሐመድ ደግሞ ‹የጥላሁን ማስታወሻ ትንፋሹ ብቻ አይደለም› ብሎ የአንጋፋውን ሙዚቀኛ ታሪክ በ432 ገጾች ቀንብቦ አስነብቦናል፡፡‹‹ጥላሁን ገሠሠ፡ የሕይወቱ ታሪክና ምሥጢር›› የተሰኘው መጽሐፍ የጥላሁን ገሠሠን ታሪክ እንደ ሙዚቀኛ እና እንደ ሰው አመዛዝኖና በግሩም ስነ ልቡናዊ ወደሮ አስተሳስሮ አቅርቦልናል፡፡ በዚህም የጥላሁንን ዕንባና ሳቅ፣ ድክመትና ብርታት፣ ዝምታና ጩኸት በሚገባ በማሳየት የሕይወት ታሪክ (ባዮግራፊ) ትርክተ-ገድል ብቻ ሳይሆን የባለታሪኩን ምሉዕ ስብዕና የማሳየት ጥልቅ ሥራ መሆኑን ለሌሎች ጸሐፍት ሳይቀር የሚበቃ ትምህርት ሰጥቷል፡፡

‹‹ስሜቱ ሲጨነቅ ባሳብ እያረረ

እራሱን በራሱ እያነጋገረ

ምስጢሩን በምስጢር ቀብሮ ያላኖረ

ኧረ ለመሆኑ ማነው ያልነበረ››

 ለዚህ መጽሐፍ መነሻ የሆነውንና ከ1934 ዓ.ም ጀምሮ በአቶ ፈይሣ ኃይሌ ሐሰና የተጻፈውን የቤተሰብ ታሪክ ማስታወሻ እንደመነሻ በመውሰድ ጸሐፊው እንደሚገልጸው፤ ጥላሁን ገሠሠ ከልጅነት ዕድሜው ጀምሮ በወላጆች የመተው አደጋ የተቀበለ፣ ወላጅ እናቱን በድንገተኛ አደጋ የማጣቱን መሪር ዕውነታ በልቡ ይዞ የኖረ፣ በልጅነት ሕይወቱ ጸሊም ጥላ ውስጥ እየኖረ በሙዚቃው ግን የሚሊዮኖችን ሕይወት ሲያፈካ የኖረ ግዙፍ ሰብዕና ያለው ምስጢራዊ ሰው ነበር፡፡

ዘፈን ለጥላሁን የእንጀራ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሕይወት ቁስል ማከሚያ መድኃኒት መሆኑንም በታሪኩ ውስጥ እናያለን፡፡ ምናልባትም ከብዙ አድናቂዎቹ በላይ በዘፈኖቹ ስሜቱ የሚነካው ጥላሁን ራሱ መሆኑን ስናነብ፣ ጥላሁንን እንደ አዲስ የማወቅ ስሜት ይሰማናል፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ትረካ ብቻ ሳይሆን ትንተናም ሰፊ ቦታ ተሰጥቶታል፡፡ ልጅነቱን፣ አስተዳደጉን እና ሙያዊ ሕይወቱን በስነ ልቦናዊ መነጽር እየፈተሽን፣ እንደዋዛ ካየነው እና ከሰማነው የጥላሁን ሰብዕና ውጪ በራሳችን ርትዕ ልቦና ዕውነቱን እንድንፈርድ ዕድሉ ተሰጥቶናል፡፡ ሰው ሰው በሚሸቱ ትርክቶቹ ጥላሁንን ሲዘፍን ብቻ ሳይሆን ሲያወራ፣ ሲጫወት፣ ሲፈራ፣ ሲተክዝ፣ ሲዝናና፣ ሲታመም እናየዋለን፡፡ ከመድረክ ጀርባ እንባውን እያዘራ ‹‹እኔ እዚህ ቆሜ እዘፍናለሁ፤ ይሄኔ የእናቴ ገዳይ አንድ ቦታ ቆሞ ይፏልላል›› የሚለውን መሪር ቃል ስናነብ የሙዚቀኛው ጥላሁንን ዝና ብቻ ሳይሆን፣ የሰውየው ጥላሁንን ስቃይ በሚገባ እንረዳለን፡፡

‹‹እምነት ተስፋ አለኝታዬ

ቀኝ ክንዴ መመኪያዬ

ዝና ክብሬ መጠሪያዬ

ያገሬ ሕዝብ ገበናዬ››

ጥላሁን ገሠሠን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ውጪ ማየትና መረዳት ፈጽሞ የሚቻል አይሆንም፡፡ የጥላሁንን ታሪክ የማውሳት ሥራም ይህን የ50 ዓመት ቁርኝት ከሁለቱም ወገን አጉልቶ ማሳየት እንዳለበት ዘከሪያ በቅጡ የተረዳ ይመስላል፡፡ መጽሐፉ በሦስት መንግሥታት ውስጥ የነበረውን ሕዝባችንን ኪናዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ታሪክ በጥላሁን ሕይወት ውስጥ በቅጡ ያስቃኘናል፡፡ ከዚህ ባለፈም የጥላሁንን ዜማዎች በየዘመኑ ከነበሩት ሁነቶችና ዕውነታዎች ጋር እያዛነቁ የኢትዮጵያን ሕዝብና የጥላሁንን ጥልቅ ትስስር የሚያወሱ ምዕራፎች በመጽሐፉ ውስጥ ተካትተዋል፡፡ ‹‹ሒሳብ ተከፍሏል››፣ ‹‹በዘፈን አንደኛ››፣ ‹‹ፍቅር ከሽፍታ ሲያስጥል››፣ ‹‹የመወደድ ፀጋ እና ፈተና››፣ ‹‹ሕዝብ ልጁን በፍቅር አከመ›› የሚሉት ተረኮች በጥላሁን ሕይወት ውስጥ እያንዳንዳችን የነበረንን ስፍራ በግልጽ ያሳያሉ፡፡ የሕይወት ታሪክን ጥሩ ከሚያስብሉት መስፈሪያዎች አንዱ፣ አንባቢው ራሱን በባለታሪኩ ሕይወት ውስጥ እንዲያይ ማስቻሉም ነውና እነዚህን ትረካዎች ስናነብ፣ በየዘመናቱ ውስጥ ያሳለፍነውን የራሳችንን ሕይወት እናስታውሳለን፡፡ ምናልባትም የጥላሁን ሕይወት የሁላችንም ሕይወት ማጀቢያ ሙዚቃ እንደሆነ እናያለን፡፡ በዕንባው ውስጥ ዕንባችን፣ በሳቁ ውስጥ ሳቃችን ታትሟልና፡፡

በሚያዝያ ወር 1985 ዓ.ም በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ ከደረሰበት በስለት የመወጋት አደጋ ጋር በተገናኘ፣ ጥላሁን በሕይወት ሳለ ‹‹ሆድ ይፍጀው›› ከማለት በቀር በአንደበቱ የተናገረውን ሌላ ቃል ሳንሰማ 22 ዓመታት አልፈዋል፡፡ ድርጊቱን ማን ነው የፈፀመው የሚለው ጥያቄ ዛሬም ድረስ የብዙዎች ጥያቄ እንደሆነ አለ፡፡ ጥላሁን ገሠሠ፡ የሕይወቱ ታሪክና ምሥጢር  በተሰኘው በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ግን፣ ጥላሁን ከዚያ አደጋ ጋር በተገናኘ ለመጀመርያ ጊዜ ከ“ሆድ ይፍጀው” የተለየ ምላሽ የሰጠበትን አጋጣሚ እናነባለን፡፡ በወንጀል ነክ ጉዳይ ላይ ይፋዊ መግለጫ የመስጠት መብትም ሆነ ሥልጣን እንደሌለው የተረዳው የመጽሐፉ ደራሲ፣ በጽሑፍ ጥበብ አጥር ተከልሎ አዲስ መረጃ ይፋ አድርጓል፡፡ በአንድ ወንጀል‑ነክ ጉዳይ ላይ ከመጽሐፍ ደራሲ ይፋዊ መግለጫ የመጠበቅ የዋህነት ካልጋረደን በቀር፣ በጉዳዩ ላይ በጥላሁን አንደበት የተባለው ተብሏል፡፡

‹‹አንዳንድ ሰው አለ ብዙ ‘ማይናገር

በተግባር የሚያሳይ ሰርቶ ቁም ነገር››

 ብዙ ሠርተው ያልተወራላቸው፣ የሚገባቸውን ዕውቅናና ምስጋና ያላገኙ አያሌ ሰዎች በየሙያ ውስጥ አሉ፡፡ ሙዚቃ ደግሞ ከሌሎች ሙያዎች በተለየ የሕብረት ሥራ ነውና፣ ከጥላሁን ንግሥና ጀርባ ያሉ እና የነበሩ የሙያ አጋሮቹ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በሥራዎቹ ላይ ካሳረፉት አሻራ አኳያ በወጉ ተወስተዋል፡፡ በተለይም ከወርቃማው የሙዚቃ ዘመን ፈርጦች ጀርባ ሆነው በግጥምና ዜማ ድርሠት፣ እንዲሁም በቅንብር የተሳተፉ አንጋፋ ባለውለታዎችን ዘከሪያ አስታውሷቸዋል፡፡ ‹‹የሙያ አባቶችና አጋሮች›› በሚለው ምዕራፍ፤ ኢዩኤል ዮሐንስ፣ አፈወርቅ ዮሐንስ፣ ሣህሌ ደጋጎ፣ ተዘራ ኃይለሚካኤል፣ ገዛኸኝ ደስታ፣ ግርማይ ሐድጎ፣ ሠይፉ ኃይለማርያም፣ አቡበከር አሸኪ፣ አየለ ማሞ፣ ሰሎሞን ተሰማ፣ ፋንታ አንተአለኸኝ፣ ተስፋዬ ለሜሳ፣ ክፍለየሱስ አበበ እና ሌሎችም የጥላሁን የሙያ አጋሮች ከነሥራዎቻቸው ተወስተዋል፡፡

የተወሰኑ የጥላሁን ገሠሠ ዜማዎች ታሪካዊ ዳራ መጠቀሱም ዜማዎቹን እንደ አዲስ በአዲስ ዐውድ እንድናጣጥማቸው ያደርጋል፡፡ የጥላሁን የአማኑኤል ሆስፒታል ቆይታና ‹‹አንቺ ጤና ሆነሽ፤ እኔ ጤና እያጣሁ›› የሚለውን ዜማ ‘ትስስር’፣ ‹‹እሩቅ ምሥራቅ ሳለሁ››ን እና የኮርያ ዘማቹን ደራሲ ገዛኸኝ ደስታ ታሪክ፣ የመጀመሪያ ባለቤቱን እና ‹‹ትዳር ያስጠላሽ በልጅነት›› ዜማን ቁርኝት የሚዳስሱት ትረካዎች ለዚህ በአብነት ይጠቀሳሉ፡፡

‹‹ . . . የጥንቱ ትዝ አለኝ››

የኢትዮጵያ የሙዚቃ ፈርጥ የሆነውን የጥላሁንን ታሪክ ማስታወስ የግማሽ ምዕተ ዓመት የኢትዮጵያን የሙዚቃ ታሪክ ማስታወስ ነው፡፡ ዘከሪያ ግን ከዚህም አልፎ ከዘመናዊ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ጅማሮ ተነስቶ በሀገሪቱ ውስጥ የተስተዋሉትን ወሳኝ ሙዚቃዊ ለውጦች እና ክስተቶች ለመዳሰስ ሞክሯል፡፡ ከእነዚህ ክስተቶች ውስጥ አንዱ የሆነውን ጥላሁንንም ለሙዚቃው ያበረከተውን አስተዋጽኦና ሙያዊ ውርስ፣ ድክ ድክ ይል ለነበረው ዘመናዊ ሙዚቃ ያመጣውን በረከት፣ በሙዚቃው ሥራ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ተጠቃሚነት እና መብት ለማስከበር ያደረገውን ጥረት፣ በሙዚቃው ታሪካዊ ዐውድ ውስጥ አሳይቷል፡፡ ዘመናዊ የኢትዮጵያ ሙዚቃ፣ የሐገር ፍቅር ማኅበር፣ የክብር ዘበኛ እና የጥላሁን ገሠሠ ወርቃማ ዘመናት በስፋት ተዳስሰዋል፡፡ ጥላሁን ከተለያዩ የሀገራችን ኦርኬስትራዎች እና ባንዶች ጋር የነበሩትን ቆይታዎች እና በምሽት ክበባት ሲዘፍን የነበረባቸውን ጊዜያት በተቻለ መጠን ለመዳሰስ ሞክሯል፡፡

እነዚህ የመጽሐፉ ክፍሎች፣ ከዝክረ ጥላሁን ባለፈ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ታሪክ በአጭሩ ለማወቅ ለሚሻ አንባቢ ጥሩ መረጃዎችን ይዘዋል፡፡ ሙዚቃችን እንደ ክብር ዘበኛ እና ፖሊስ ኦርኬስትራ ተቋማዊ አደረጃጀት በነበረው ወቅት የነበረውን ጥራት፣ በሂደት የታዩት በጎ እና ዕኩይ ለውጦች በሙዚቃችን ጥራት ላይ ያሳረፉትን አሻራ በጥላሁን የሙዚቃ ካሴቶች አማካይነት ለመጠቆም መሞከሩ የሚመሰገን ነው፡፡

‹‹አካም ነጉማ ፈዩማ

ሂሪያ ሂንቀቡ ኮቡማ››

 እኒህን የኦሮምኛ ስንኞች ‹‹ብቻዬን ነኝ እኔ›› በሚለው በጥላሁን በራሱ ዜማ እንተርጉማቸው፡፡ ‹ብቻዬን ነኝ አጋርም የለኝ› የሚለው ጥላሁን፤ አብዛኛውን ሕይወቱን እንዲህ ባለ አጋር መሻት ውስጥ አሳልፏል፤ ይለናል ጸሐፊው፡፡ የዚህን ግላዊ፣ ስነ ልቦናዊና ስነ አዕምሯዊ ምክንያት ለማብራራት የሚሞክረው ጸሐፊው፤የጋብቻ ሕይወትን  በሚተርከው ክፍል የጥላሁንን ባለቤቶች እና ልጆች፣ የትዳር ሕይወቱን ምስቅልቅሎች፣ እንዲሁም ‹‹ታሞ ከመማቀቅ፣ አስቀድሞ መጠንቀቅ›› ይሉት አባባል ከማይገዛው ባህርይው በመነጨ ቸልተኝነት ሳቢያ  የደረሰበትን ጉዳት ይተርካል፡፡ በመጨረሻዎቹ የሕይወት ዘመናቱ ያጋጠሙትን ችግሮች ስናነብ የቀደመ ሰብዕናውና ግዝፈቱ፣ ክብሩና ሞገሱ እየታሰበን ማዘናችን አይቀርም፡፡ በአንድ ወቅት [እ.ኤ.አ በ2008] ጥላሁን ገሠሠ አሜሪካ ውስጥ በተሽከርካሪ ወንበር ላይ ተቀምጦ፣ በገረጣ ፊቱ እና በደከመ ድምጹ የግዱን በሚያዜምበት ሰአት፣ የሙያ አጋሩ ማህሙድ አህመድ ሊያግዘው ወደ መድረክ ሲመጣ የነበረውን ደማቅና ጥልቅ ሕዝባዊ ስሜት የሚያስታውሱ ትረካዎችን በያዘው በዚህ ክፍል የጥላሁን ሕይወት ድምድማት ይበጅለታል፡፡

‹‹በአካል ሳይፈተን በአካል ሳይነካ

የማን ምንነቱ ግብሩ ሳይለካ

እርግጥ በተፈጥሮ በወል ስም ይጠራል

በቁም ነገር መድረክ ሰው ከሰው ይለያል››

 የዚህ ዘፈን ግጥም ደራሲ ሻምበል ክፍሌ አቦቸር እንዳሉት፤ በእርግጥም ‹‹ሰው ከሰው ይለያል››፡፡ ጥላሁን ገሠሠም ከብዙዎቹ ዘመነኞቹና መሰሎቹ በብዙው ይለያል፡፡ ግማሽ ምዕተ ዓመት የፈሰሰ የድምጽ ማዕበል፣ በተግባር የተፈተነ ሀገር ወዳድነት እና ጥልቅ የሙያ ክብር በእርግጥም ጥላሁንን የተለየ ሰውና የተለየ ሙያተኛ ያደርጉታል፡፡

ቀደም ብዬ እንደጠቀስሁት፣ ይህን ዳጎስ ያለ መጽሐፍ ያበረክትልን ዘንድ ደራሲ ዘከሪያ መሐመድን የቀሰቀሱት፣ ከ1934 አንስቶ የቤተሰባቸውን እና የጥላሁንንም የልጅነት ታሪክ በጽሑፍ ከትበው ያኖሩት አቶ ፈይሣ ኃይሌ ናቸው፡፡ እኒህ ሰው የሙዚቃውን ንጉሥ ታሪክ በእናቱ ወገን፣ ከሰባተኛ ቅድመ‑አያቱ ጀምሮ በዝርዝር ጽፈው ከማኖራቸውም ባሻገር፣ ጥላሁንን /ገና የአንድ ዓመት ሕጻን ሳለ/ እና የቅርብ ቤተሰቦቹንም ፎቶግራፍ በማንሳት ለትውልድ አኑረዋል፡፡ ነገር ግን አቶ ፈይሣ በጽሑፍ ያኖሩት የጥላሁን የልጅነት ሕይወትን የሚመለከት ጥሬ ሐቅ ብቻውን ስለ ሙዚቃው ንጉሥ ሰብዕና ብዙ ላይነግረን ይችል ነበር፡፡ የአቶ ፈይሣ ኃይሌን የቤተሰብ ታሪክ ማስታወሻዎች በጥንቃቄ በማንበብና በመመርመር፣ የጥላሁንን የጉልምስና፣ በተለይም የትዳር ሕይወቱን፣ ምስቅልቅሎሽ ምሥጢር ከቤተሰብ ታሪክ ማሥታወሻዎቹ ውስጥ የመዘዘ እና በጥልቀት የተነተነልን ደራሲው ነው፡፡ ጥላሁን ገሠሠ፡ የሕይወቱ ታሪክና ምሥጢር የተሰኘውን መጽሐፍ የወለደው ደራሲው በዚህ ረገድ ያደረገው የግል ጥረት ነው፡፡ በዚህ ጥረቱም የዚህን ልዩ ሰው አስደማሚ ታሪክ ልዩና ውብ በሆነ አቀራረብ ስለከተበልን ለዘከሪያ መሐመድ በእውነት ምስጋና ይገባዋል፡፡ 

 

 

 

Read 7748 times