Saturday, 30 May 2015 12:56

በአፍሪካ የሆቴል ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ 10 ነጥቦች

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

 

 

 

የአፍሪካ የሆቴል ኢንዱስትሪ መሪዎች በየዓመቱ በሚያደርጉት ቋሚ “አፍሪካ ሆቴል ኢንቨስትመንት ፎረም” (ኤኤችአይአፍ) ተገናኝተው

በአፍሪካ፣ ሆቴሎችን ማሳደግና ማስፋፋት በሚቻልባቸው ነጥቦች ላይ ተመካክረዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትስስር (Chain) ያላቸው፣

በርካታ እውቀትና ልምድ ያካበቱ ከፍተኛ የሆቴል ሥራ አስፈጻሚዎች፣ ዋና ዋና የዓለማችን የሆቴል ኢንቨስተሮችና በዘርፉ የላቀ እውቀት

ያላቸው በርካታ አማካሪ ባለሙያዎች በጉባኤው ተሳትፈው፣ በአፍሪካ ሆቴሎችን ለማስፋፋት አስፈላጊ ናቸው ያሏቸውን ነጥቦች

ተናግረዋል፡፡ የፎረሙ አዘጋጅ “ቤንች ኢቨንት” (Bench Event) የጉባኤው ተሳታፊዎች ቅድሚያ ሊሰጧቸው ይገባል ብለው የወሰኗቸውን

10 ነ ጥቦች - የረዥም ጊ ዜ እ ቅድ፣ ፋ ይናንስ፣ ዕ ድገት (ልማት)፣ ሕዝብ እ ና ልማት በ ማለት በ አምስት ክ ፍሎች አ ጠቃሎ አ ቅርቧቸዋል፡፡

 ሀ) የረዥም ጊዜ እቅድ

የአፍሪካ መንግሥታት፣ የአገራቸውን ሰፊ የቆዳ ሽፋን ያካለለ የረዥም ጊዜ ዕድገት (ልማት) ስትራቴጂ መንደፍ አለባቸው፡፡ ይህን ሲያደርጉ፣ በአገሪቷ ውስጥ አዲስ የተሠራ ወይም ማስፋፊያ የተደረገለት ሆቴል ያለበትን ደረጃ በከፍተኛ እርግጠኝነት ማወቅ ያስችላቸዋል፡፡ ይህም በተወሰነ አካባቢ ብቻ የሚደረገውን የኢንቨስትመንት ክምችት ስጋት በማስቀረት በመላ አገሪቱ የተመጣጠነ ልማትና ዕድገት እንዲኖር ያስችላል፡፡

በመሠረተ ልማት ላይ ኢንቨስት ማድረግ፡- የአፍሪካ መንግሥታት በራሳቸው ተነሳሽነት “መዳረሻ እሆናለሁ” ብለው ሩቅ በማለም፣ በመሠረተ ልማት (በመንገድ፣ ስልክ፣ ኢንተርኔት፣ ውሃ፣ መብራት፣..) ላይ ኢንቨስት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ መሠረተ - ልማት ሲያሟሉ፣ በራዕያቸው የተገረሙና የተደነቁ ቱሪስቶችን፣ የቢዝነስ ሰዎችንና ኢንቨስተሮችን መሳብ ይችላሉ፡፡ በጣም ጠቃሚ ከሆነው የትራንስፖርት መሠረተ ልማት አንዱ የአውሮፕላን ማረፊያ (ኤርፖርት) ነው፡፡ በዚህ ረገድ፣ በአንጐላ፣ በኬንያ፣ በናይጄሪያ፣ በሩዋንዳና ሴኔጋል (ኮትዲቯር) አዳዲስ አውሮፕላን ማረፊያዎች እየተሠሩ ነው፡፡

ለ) ፋይናንስ

ለፋይናንስ ችግር (እጥረት) ወደ ውጪ ተመልከቱ፡- የአፍሪካ መንግሥታትና ኢንተርፕርነሮች፣ ለሚያስፈልጋቸው የገንዘብ እጥረት መፍትሔ እንዲሆናቸው ወደ ውጭ አገር መመልከት ወይም በአገር ውስጥ በፕሮጀክታቸው አካባቢ ያሉ ኢንቨስተሮችን መቃኘት ይኖርባቸዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ብዙ ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች፣ ከሌሎች አገሮች ጋር በንፅፅር ሲመለከቱ ብዙ የአፍሪካ አገሮች እያሳዩ ባሉት ከፍተኛ ዕድገት እየተሳቡ ናቸው፡፡

በአፍሪካ ኢንቨስት ያደርጋሉ ተብለው የሚጠበቁት፣ ጥሩ የአየር ትራንስፖርት ትስስር ካላቸው መካከለኛ ምሥራቅ አገሮችና በአኅጉሩ የተስፋፋ ቢዝነስ ካላት ቻይና ነው፡፡

ሆቴሎችን በንብረትነት (Asset) ማየት፡- በተለምዶ ሆቴሎች በራሳቸው እንደ ንብረት አይታዩም ነበር፡፡ አሁን ግን ሁኔታዎች እየተቀየሩ ነው፡፡ የሆቴል ባለቤት መሆን፣ በረዥም ጊዜ አገር የቱሪስት ወይም የቢዝነስ መዳረሻ ስትሆን እኔም ውጤታማ እሆናለሁ ብሎ በረዥሙ ማሰብ ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ኢኮኖሚው ደካማ (ቀዝቃዛ) በሆነበት ዓመት ከተገኘው ትርፍ ላይ እንደገና ኢንቨስት ማድረግ ለታክስ የሚከፈለውን ገንዘብ በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ (ማዳን) ነው፡፡

ሐ. ዕድገት (ልማት)

የዕድገት ሂደትን ማፋጠን፣ ኢንቨስተሩ አንድን ንብረት ለመግዛት ውል ከተፈራረመ በኋላ ወዲያውኑ ቢዝነሱን ከጀመረ በንግዱ ወይም በሥራው የበለጠ ስኬታማ የመሆን ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ በ7 ዓመት (Time zone of 7 years) ቢዝነሴን (ሆቴሌን) እዚህ ደረጃ አደርሳለሁ ማለት አይታወቅም፡፡ በአንፃሩ ግን በሰንሰለት የተሳሰሩ ሆቴሎች ከምንም (Scratch) ተነስተው በወራት ፍጥነት ከፍተኛ ደረጃ የሚደርሱበትን የኮንስትራክሽን ሞጁል ውጤት ለማግኘት እየተመራመሩ ነው፡፡

የአየር መስመር መክፈት፡- አንዲት አገር የበለፀገች የቱሪስት ወይም የቢዝነስ መዳረሻ ለመሆን የአየር መስመር በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ በኢኮኖሚ የበለጠ ለመበልፀግ የአየር ትራንስፖርት ዋነኛው አንቀሳቃሽ ኃይል መሆኑን በርካታ ጥናቶች አመልክተዋል፡፡ ስለዚህ የበለጠ የአየር ትስስር መፍጠር ያስፈልጋል፡፡

መ. ሕዝብ

ከአገር ውስጥ ኢንቨስተሮች ጋር ማስተሳሰር፡- ብዙ የውጭ ኢንቨስተሮች ጠንካራ ወይም ሁነኛ ሸሪክ ካላገኙ በአፍሪካ አዲስ ኢንቨስትመንት መጀመር አይፈልጉም፡፡ ስለዚህ፤ እነዚህን ሁለት ወገኖች ማስተሳሰር ቅድሚያ የሚሰጠው ስትራቴጂ መሆን አለበት፡፡

ኢንዱስትሪዎችን ማቀራረብ፡- አዲስ ሆቴል ለማቋቋም የሚያነሳሱ ውይይትን መፍጠር የሚችሉ ዝግጅቶችን መደገፍ ያስፈልጋል፡፡ እንዲሁም ጠቃሚ የሆኑ አዳዲስ ሰዎችን በማስተዋወቅ አነስ ያለ እውቀትና ልምድ ያላቸው ኢንቨስተሮች ስለሁሉም የስራ ሂደቶች እንዲያውቁ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ረ. ባህል

ፖለቲካው የተረጋጋ መሆኑን ማስተዋወቅ፡- ለአንድ አገር እንግዳ ተቀባይነትና (ለኢንቨስትመንት ምቹነትና ለኢንዱስትሪው ሰላም)  

የተረጋጋ ፖለቲካ እጅግ ወሳኝ ናቸው፡፡ በሰሜን አፍሪካ አገሮች የተከሰተው ዓይነት የፖለቲካ ብጥብጥ (ያለመረጋጋት) በአገሮቹ ሊካሄዱ የነበሩ የሆቴል ኢንቨስትመንቶች እንዲዘገዩ አድርጓል፡፡  እውነተኛ ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮች ገንዘባቸውን ማፍሰስ የሚፈልጉት የተረጋጋ ሰላምና ፖለቲካ ባለበት አገር ነው፡፡ ስለዚህ የአፍሪካ መንግሥታት በአገራቸው የተረጋጋ ፖለቲካ እንዲኖር ከልብ መጣር አለባቸው፡፡

10. የሚታመንባችሁ ሆኑ (እምነት ፍጠሩ)

ያለመታደል ሆኖ በአንዳንድ የአፍሪካ ክፍሎች ዕቃዎች እንደሚጠፉና የተገባ ቃል እንደማይከበር በጣም ብዙ ታሪኮች ይነገራሉ፡፡

ይህ ነገር ሁሉንም የቢዝነስ ሰዎች እንዲሰጉ ያደርጋቸዋል፡፡ መታመንን ለመፍጠርና ለመገንባት የሚደረገው ሂደት፣ እንደ ፈታኝ የባህል ለውጥ ስለሚቆጠር፣ እጅግ የላቀ ጥንካሬና ትግል ይጠይቃል፡፡

ስለዚህ በቆራጥነት መሥራት አማራጭ የሌለው ነገር ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ከውይይቱ የተገኙ አስተያየቶችና ሌሎች ተመሳሳይ ጉዳዮች ከሴፕቴምበር 30 እስከ ኦክቶበር 1 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ በሚደረገው ዓለም አቀፍ የኤኤችአይኤፍ ጉባኤ ቀርበው በሚኒስትሮች፣ በከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ከደህንነት (ከሆስፒታሊቲ) ኢንዱስትሪ በመጡ ተሳታፊዎች ጠንካራ ውይይት እንደሚደረግባቸው ይጠበቃል፡፡

 

 

 

 

 

Read 1824 times