Saturday, 06 June 2015 14:20

“የብራና ልጆች” አንደኛ ዓመት ልደት!

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(0 votes)

  አንደኛ ዓመት ልደት!
           
   “በክረምት በሚያገኙት ዝናብ መሬታቸውን እያረሱ በእርሻ የሚተዳደሩ የገጠር ነዋሪዎች! ዝናቡ ጊዜውን ጠብቆ ባለመምጣቱ ብቻ ሳይሆን ሰማዩም ደመና አለመቋጠሩን ሲረዱ ለፈጣሪያቸው እግዚኦታ ሊያቀርቡ ቀጠሮ ተይዞ፣ ሁሉም የአባወራ ቤተሰብ እንዲገኝ ጥሪ ተደረገ፡፡ የሰማ ላልሰማ እየነገረ በቀነ ቀጠሮው ዕለት ብዙ ሕዝብ በአደባባይ ተገኘ፡፡ የሃይማኖት አባቶች ምህላውን ሊያስጀምሩ ሲሉ፣ የጐበዝ አለቃው አንድ ሰው ከሩቅ ሲመጣ አይቶ ሥነ ስርዓቱ እንዲዘገይ አደረገ፡፡
“በሩቅ የታየው ሰው በእጁ ጥቁር ነገር ይዟል፡፡ እየቀረበ ሲመጣ የያዘው ነገር ብቻ ሳይሆን ወደ ምህላው አደባባይ እየመጣ ያለው ሰው በዕድሜውም ልጅ መሆኑ ታወቀ፡፡ ልጁ የያዘው ጥቁር ነገርም ዣንጥላ ነበር… ይህንን ተረት የንግግሬ መጀመሪያ ያደረኩት አንድ ነገር ለመጠየቅም ይሁን ለመጀመር ሲታሰብ፣ ጀማሪነትና ጠያቂነት የሚያስከትለውን ነገር ቀድሞ የመገመት አስፈላጊነትና የተፈለገው ነገር ሲገኝ የሚያመጣውን ጥቅምና ጉዳት ቀድሞ መገመት መቻል ውጤቱን በአዎንታ ለመቀበል ጥሩ ማሳያ ስለሆነ ነው፡፡”
ንግግራቸውን በተረት የጀመሩት የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙሴ ያዕቆብ ሲሆኑ ዕለቱ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ግንቦት 22 ነበር፡፡ ቦታው በብሔራዊ ሙዚየም ግቢ በሚገኘው ሉሲ ጋዜቦ ሬስቶራንት አዳራሽ ውስጥ ነው፡፡ ፕሮግራሙ ደግሞ
“የብራና ልጆች የቴሌቪዥን ፕሮግራም” የተመሠረተበትን አንደኛ ዓመት በዓል ተከብሯል፡፡ “የብራና ልጆች ፕሮግራም መተላለፍ ሲጀምር አንዴት ዘላቂ ማድረግ ይችሉ ይሆን የሚል ስጋት ነበረኝ፡፡ ፈጣሪ ምህላቸውን ሰምቶ፣ ዶፉን ቢያወርደውስ ብሎ አርቆ በማሰብ፣ ዣንጥላ ይዞ እንደመጣው ልጅ የብራና ልጆች ፕሮግራም አዘጋጆችም ሲጀምሩ ለቀጣይነቱም ስላሰቡበት አንደኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ለማክበር ችለዋል” በማለት ዶ/ር ሙሴ አድናቆታቸውን ገልፀዋል፡፡
መፃሕፍትን፣ ፀሐፊያንንና ንባብን ማዕከል አድርጐ በኢቢኤስ ቴሌቪዥን የሚተላለፈው “የብራና ልጆች” ፕሮግራም፤ ሥዕልና ሙዚቃን ከርዕሰ ጉዳዩ ጋር በማቅረብ፤ የጥበብን ሕብራዊነትና ተደጋጋፊነትን በተግባር እያሳየ ይገኛል፡፡ በበዓሉ ላይ በአሸናፊ ቻምበር ኦርኬስትራ የታጀቡ ግጥሞች ተነበዋል፡፡ ወጐችና ከመፃሕፍት የተመረጡ አንቀፆችም ቀርበዋል፡፡
በምሽቱ ዝግጅት ለየት ያሉ ትኩረት የሚስቡ ሥነ ስርዓቶችም ነበሩ፡፡ “አያ ቶኔ ቶር” በሚል ርዕስ የቀረበው ሙዚቃዊ ተውኔት አንዱ ነው፡፡ “እናት ኢትዮጵያ” ብዙ ጊዜ በሴት ገፀ ባሕሪ ስትወከል እንመለከታለን፡፡ “አያ ቶኔ ቶር” ጥንታዊ የኢትዮጵያን ዕውቀት ወክሎ ቀርቧል፡፡ ገፀ ባሕሪው “እየጠፋሁ ነው፣ በመዘረፍ አደጋ ውስጥ ነኝ፣ የመረሳት ችግር ገጥሞኛል፣ አድኑኝ!” በሚል ላቀረበው ጥሪ፤ በአንድ ትውልድ ውስጥ ያሉና በወጣቶች የተወከሉ ሦስት የተለያዩ አካላት፤ በጥሪው ዙሪያ ተሟግተዋል፡፡
የታክሲ ሹፌሮች፣ ረዳቶች፣ የጐዳና ተዳዳሪዎች መሰሎቻቸውን የወከሉት ወጣቶች፤ ሠርቶ መኖርና ተደስቶ ውሎ ለማደር ላይ ትኩረት ቢያደርጉም፤ በልዩነት የሚነታረኩ ትውልዶች ወደ ጋራ ጉዳይ እንዲመጡ፣ የተበታተኑ እንዲሰባሰቡ፣ የተሻለው እውነት እንዲያሸንፍ… ፍላጐታቸውን ከማሳየታቸውም በላይ መታገዝ ካለበት ጋር በአጋርነት ሲቆሙ ታይቷል፡፡
ሁለተኛው ቡድን በፌስ ቡክ (facebook)  ትውልድ የተወከሉት ናቸው፡፡ “ፎቶግራፍሽ ያምራል”፣ “አንተም ታምራለህ”፣ “ዓይኖችሽ ውብ ናቸው”፣ “ያንተም” የሚሉትን ለመፃፃፍ የአማርኛ ቋንቋ ፊደላት በዝተዋልና መቀነስ አለባቸው ብለው ያምናሉ፡፡ ፊደላቱ ብቻ ሳይሆኑ የሥማችንም መጠሪያ ማጠር አለበት በሚል ከሁለት ፊደል ያልበለጠ (ያውም የእንግሊዝኛ) መጠሪያ ለራሳቸው የሰጡ ናቸው፡፡ ስማቸው ትርጉም፣ መልዕክትና ክብር ኖረው አልኖረው የሚያስጨንቃቸው አይደሉም፡፡
በወጣቶች የተወከለው ሦስተኛው ቡድን፤ “አይን” የሚለው ቃል በዓይኑ “ዓ” መፃፍ አለበት ብሎ ሽንጡን ገትሮ የሚከራከር ነው፡፡ ቃላት የበዙበት ስያሜ ያለምክንያት አልተሰጠም ብለው ያምናሉ። ምክንያታቸውንም ያቀርባሉ፡፡ ያወቁትንም ሌላው ዘንድ እንዲደርስ ይጥራሉ፡፡ የብራና ሰነድና መፃሕፍት መጥፋት፣ መሰረቅና መቃጠል ዜና ሲሰሙ መርዶ እንደተነገራቸው ያዝናሉ፡፡
በአንድ ዘመን፣ በአንድ በአገርና ትውልድ ውስጥ፤ የተገኙት ወጣቶች ስለ ጥንታዊ የአገር ጥበብ ያላቸው ዕውቀትና መረዳት በሦስት የተለያዩ ገፀባህርያት (ቡድኖች) ወክሎ የሚያሳየው ሙዚቃዊ ተውኔት የሚያበቃው “አያ ቶኔ ቶር”ን የሚደግፉ ወጣቶች ቁጥር መበርከቱን በማሳየት ነው፡፡
ከዕለቱ ዝግጅት በሁለተኛነት ትኩረት ሳቢ የነበረው የሙዚቃ ግጥም ፀሐፊው ገጣሚ ሙሉጌታ ተስፋዬ የተዘከረበት ሁኔታ ነው፡፡ ለብዙ ድምፃዊያን የዘፈን ግጥሞች እንደሰጠ የተነገረለት ገጣሚው፤ “የባለቅኔ ምህላ” በሚል ርዕስ “በስንዱ አበባ አሳታሚ” ከታተመው መድበል የተመረጠ ግጥም ቀርቦለታል፡፡
ሦስተኛውና በምሽቱ ከቀረቡት ፕሮግራሞች ሁሉ ታላቅ የነበረው ደግሞ የደራሲ፣ ሐያሲና ወግ ፀሐፊው መስፍን ሀብተማርያም “የቡና ቤት ሥዕሎች” መጽሐፍ ታትሞ ለአንባቢያን መቅረቡ መበሰሩ ነው፡፡ “የብራና ልጆች” የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጆች መጽሐፉ ዳግመኛ  ስለታተመበት ዓላማና ምክንያት ሲገልጹ፡-
“የብራና ልጆች አንደኛ ዓመት ክብረ በዓልን ስናከብር በየዓመቱ አንድ ደራሲን በተለየ ሁኔታ ማክበርና ማመስገን ስለምንችልበት ሁኔታ መክረንበት ውሳኔ ላይ ደረስን። የዘንድሮ ተመስጋኛችን ሁለገቡ የብዕር ሰው መስፍን ሀብተማርያም ሆነ፡፡ የውጭ አገር ትምህርቱን አጠናቆ በመጣ ማግስት ያገኘውን ዕውቀት ለወገኖቹ ሊያካፍል ጽፎ ያሳተመው መጽሐፍ ዓይነቱ በምን ክፍል ይመደብ? መጠሪያ ስያሜውስ ምን ይባል? በሚል ከመነሻውም የብዙ የዘርፉ ምሁራንን ትኩረት ስቧል፡፡ በወግ ምንነትና ጀማሪነት ዙሪያ ዛሬም አነጋጋሪ ሀሳቦች እየቀረቡ ነው፡፡ የዚህን ባለውለታ ደራሲ መጽሐፍ አሳትመን በመሸጥ፤ ገቢውን ለቤተሰቡ ሰጥተን ማመስገን በመፈለጋችን ነው “የቡና ቤት ሥዕሎች” መጽሐፉን ያሳተምንለት። የብዙ አካላት እገዛና ትብብር መሻታችን እውን እንዲሆን ረድቶናል” ብለዋል፡፡ በመጪው ሐምሌ 7 ከዚህ ዓለም በሞት ከተለየ አንድ ዓመት የሚሞላው ደራሲና ወግ ፀሐፊ መስፍን ሀብተማርያም፤ “የብራና ልጆች” ያሳተሙለት መጽሐፉ በተመረቀበት ሥነ ሥርዓት ላይ ደራሲ አፈወርቅ በቀለ ባደረጉት ንግግር፤ “ሁልጊዜ እንደምለው ወጣቱ ትውልድ በግጥም፣ በሥዕል፣ በድርሰት…ትንታግ ነው፡፡ በሁሉም ዘርፍ ትንታግ ሆኖም ይቀጥላል፡፡ የብራና ልጆችን ጥረትና ዓላማ ለማገዝ፣ በነፃ የተሰጠኝን “የቡና ቤት ሥዕሎች” መፅሐፍ ዋጋውን እጥፍ አድርጌ በመክፈል፣ ተባባሪያችሁ መሆኔን አረጋግጣለሁ” በማለት 50 ብር ለሚያወጣው መጽሐፍ አንድ መቶ ብር ከፍለዋል፡፡  

Read 1941 times