Saturday, 13 June 2015 14:43

ህወሓቶች ከአሥሩ መስራቾች አንዱን እንዴት ዘነጓቸው?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 ከህወሓት ጋር ትግል የጀመሩ ብቸኛው የአማራ ተወላጅ ነበሩ
በ40ኛው የህወሓት በዓል ላይ ስማቸው አልተወሳም - ቤተሰቦች
አቶ አብጠው ታከለ ማናቸው? ከህወሓት  ጋር በምን ተገናኙ?

      ከህወሓት መስራቾች አንዱ እንደሆኑ የሚነገርላቸው የአማራ ተወላጁ አቶ አብጠው ታከለ (በበረሃ ስማቸው ሚካኤለ)፤ የትግል ታሪክ ተድበስብሶ መቅረቱን የሚናገሩት ቤተሰቦቻቸው፤ በጉባኤዎችም ሆነ በምስረታ በዓላት ላይ የእኚህን ታጋይ ስም የሚያነሳ አካል መጥፋቱ እንዳሳዘናቸው ለአዲስ አድማስ ገለጹ፡፡  
አቶ አብጠው የዛሬ 40 አመት ህወሓትን ከመሠረቱት 10 ታጋዮች አንዱ እንደሆኑ የህወሓት ጽ/ቤት አረጋግጧል የሚሉት ቤተሰቦች፤ እስካሁን ግን ይፋዊ የታሪክ እውቅና አልተሰጣቸውም ሲሉ ቅሬታቸውን ሰንዝረዋል፡፡ “ኢህአዴግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ በተካሄደ የትኛውም የህወሓት ጉባኤ ላይ አባታችን የተሣትፎ ግብዣ እንኳ ቀርቦለት አያውቅም” ያሉት የአቶ አብጠው ልጅ አቶ ካሣሁን አብጠው፤ አባታችን ካለፈ በኋላም ታሪክና ገድሉን ትውልድ እንዲያውቀው በሚያስችል መልኩ አለመነገሩ ቅር አሰኝቶናል” ይላሉ፡፡
ህወሐት 40ኛ ዓመት የልደት በአሉን ባከበረበት ወቅትም ሆነ ብአዴን 35ኛ ዓመት የምስረታ በአሉን ሲያከብር፣ ከትግሉ ጠንሳሾች አንዱ የነበሩት ታጋይ ሳይታወሱ መቅረታቸውን ልጃቸው ይናገራሉ፡፡ ይሄንኑ ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን እንዲሁም ለህወሓትና ብአዴን ከፍተኛ አመራሮች ለማስታወስ ልጃቸው አቶ ካሣሁን አብጠውና ባለቤታቸው ወ/ሮ አለም አፅብሃ ሰሞኑን ከሠሜን ጐንደር አዲስ አበባ ድረስ  ቢመጡም፣ የሚያነጋግራቸው አጥተው መመለሳቸውን ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡
ታጋይ አብጠው (ሚካኤለ)፤የህወሓት መስራች ከነበሩት 10 ግለሰቦች አንዱ መሆናቸውን የህወሓት ጽ/ቤት ማረጋገጡን ሚያዝያ 21 ቀን 2007 ዓ.ም ለብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽ/ቤት በፃፈው ደብዳቤ ያስታወቀ ሲሆን ታጋዩ ለትግሉ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ተገቢውን የታሪክ ቦታ እንዲያገኝ አስገንዝቦ፣ ለቤተሰቦቻቸውም ህወሓት አቅሙ በፈቀደ መጠን ክትትልና እንክብካቤ እንደሚያደርግ ገልጾ ነበር ይላሉ፡፡ “ግለሰቡ ደደቢት ከደረሱ 10 የህወሓት መስራቾች አንዱ ናቸው” ሲል ህውሓት በደብዳቤው ላይ ጠቁሟል፡፡  
“ሆኖም ለቤተሰቡ ቃል የተገባው እንክብካቤም ሆነ ለአባታችን ይሰጣል የተባለው ተገቢ የታሪክ ቦታና ይፋዊ እውቅና የውሃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል፤ ይህን ለማስታወስ አዲስ አበባ ድረስ ብንመጣም በሩን ከፍቶ የሚያነጋግረን አካል አጣን” ብለዋል ቤተሰቦቻቸው፡፡
አቶ አብጠው አሁን ለተገኘው ሠላም፣ ልማትና ዲሞክራሲ ጉልህ አሻራ ያስቀመጠ ታጋይ በመሆኑ ህወኃት ለእዚህ ታጋይ ከደብዳቤ ያለፈ ይፋ እውቅና እንዲሰጠው አበክረን እንጠይቃለን ብለዋል፡፡ ቤተሰቦቻቸው በአብዛኛው በግብርና የሚተዳደሩ እንደሆኑ በመጠቆምም እስካሁን ግን ለታጋይ ቤተሰቦች የሚደረገው ድጋፍና እንክብካቤ ጨርሶ ተደርጐላቸው እንደማያውቅ ገልጸዋል፡፡  
 አቶ አብጠው ታከለ ማን ናቸው?
ታጋይ አብጠው ታከለ፤ ከእናታቸው ከእማሆይ ወለተ ስላሴ፣ ከአባታቸው አቶ ታከለ አመራ በሰሜን ጐንደር፣ አዲአርቃይ ወረዳ፣ ዛሬማ የምትባል ከተማ ተወለዱ፡፡ በወጣትነታቸው በግብርና እና በንግድ ስራ ላይ ሳሉ ነው ወ/ሮ አለም አፅብሃን ያገቡት፡፡ በዚህም ሳቢያ ለወ/ሮ አለም የስጋ ዘመድ ከነበሩት የህወሓት ዋነኛ መስራቾች ገሠሠ አየለ (ስሁል) እና ብርሃኔ አየለ ጋር የጋብቻ ዝምድና ተፈጠረ፡፡
 በ1965 እና 66 አካባቢ የትጥቅ ትግል ለማካሄድ እነ ገሠሠ አየለ ሲመክሩ፣ አቶ አብጠው አገር የመሰከረላቸው በረሃ አዋቂና ጀግና እንደነበሩ ያውቁ ነበር የሚሉት ልጃቸው፤ የካቲት 8 ቀን 1967 ዓ.ም እነ ገሠሠ አየለ (ስሁል) ደርግን ለመደምሰስ ያለው አማራጭ የትጥቅ ትግል መሆኑን ሲወስኑ ወደ አቶ አብጠው ዘንድ የትግል ጥሪ ያደርሳሉ፡፡ እሳቸውም ጥሪውን ወዲያው ተቀብለው፣ ያፈሩትን ንብረት ሜዳ ላይ በትነው፣ የወላጅ አባታቸውን የ40 ቀን ተዝካር እንኳ ሳያወጡ በቀጥታ ጉዞ ወደ ሽሬ ሆነ፡፡ ሽሬ ላይ ከአቶ ገሠሠ ጋር ስለ ትግሉ ጥንስስ ተወያዩ። እስከ የካቲት 10 ቀን 1967 ድረስም በጉዳዩ ላይ ሲመክሩ ቆዩ፡፡ የካቲት 11 ለትግል ወደ ደደቢት በረሃ ተጓዙ፡፡
በ1999 ዓ.ም ከትግሉ ጠንሳሾች አንዱ ለነበሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ስዩም መስፍን በፃፉት ደብዳቤ ላይም ለትግሉ ያበረከቱትን አስተዋፅኦ በዝርዝር በመግለፅ ሊያስታውሷቸው ሞክረዋል። እንዴት በረሃን መቋቋም እንደሚቻል ምክርና ማበረታቻ፣ በረሃ ላይ ቂጣ እንዴት ድንጋይ ላይ እንደሚጋገር፣  ወፍን ተከትሎ በመጓዝ የጫካ ማር እንዴት መብላት እንደሚቻል፣ አደን እንዴት እንደሚታደን ለትግል ጠንሳሾቹ ሥልጠና መስጠታቸውን በደብዳቤያቸው ያስታወሱት አቶ አብጠው፤ የትግል ጓደኞቻቸው በረሃብ ምክንያት በህይወትና ሞት መካከል በነበሩ ጊዜ የዱር እንስሳት እያደኑ ይመግቧቸው እንደነበር ያወሳሉ፡፡ በትግሉ ወቅት ለበራሪ ወረቀት ማባዣ ማሽን አስመጥተውም ለአገልግሎት እንዲውል ማድረጋቸውንም ይጠቅሣሉ፡፡
ሰኔ 10 ቀን 1967 ዓ.ም አቶ ገሠሠ አየለ፤ የአቶ አብጠውን ባለቤት ደርግ እንዳይገድልባቸው ሄደው ቦታ እንዲያስይዟቸው በነገሯቸው መሰረት፣ የደርግን ክትትልና ጫና ተቋቁመው፣ከባለቤታቸው ጋር ለመገናኘት ችለዋል፡፡ በቀጠሉት የትግል ዓመታትም፣ በደባርቅና በአካባቢው ያለውን የደርግ እንቅስቃሴ እያጠኑ ደደቢት ላሉት ታጋዮች መረጃ ያቀብሉ እንደነበር የሚናገሩት ቤተሰቦቻቸው፤ በስለላና በመረጃ ስራ ላይ ሳሉ በአንድ አውደ ውጊያ ላይ አንድ አይናቸውን እንዳጡም ይገልጻሉ፡፡ ከቁስላቸው ካገገሙ በኋላ በ1978 ዓ.ም ከህወሓት መስራች አንዱ የሆኑት አቶ አስገደ ገ/ሥላሴ፣ የዛሬማን ህዝብ ሰብስበው፤“አሁን ላለንበት ደረጃ ያደረሰን አቶ አብጠው ነው” በማለት የህወሓት መስራችነታቸውን ከመሰከሩላቸው በኋላ አንድ ክላሽ መሸለማቸውን ቤተሰባቸው ያስታውሳል፡፡  
አቶ አብጠው ከትግል በኋላም በአካባቢያቸው ከፀረ-ሠላም ኃይሎች ጋር ሲዋጉ እድሜያቸውን እንዳሳለፉ የሚገልፁት ቤተሰቦቻቸው፤“አባታችን ባይማርም ለሰው ልጅ ሰብአዊ መብቶች መከበር አጥብቆ የሚቆረቆር ሰው ስለነበር፣ በማህበረሰቡ ዘንድ አንቱታንና ከበሬታን ተጎናጽፏል፤በትግል አጋሮቹ መዘንጋቱና ስሙን እንኳ የሚጠቅስ አካል መጥፋቱ ግን በእጅጉ አሳዝኖናል” ሲሉ ቅሬታቸውን ገልፀዋል፡፡
ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ በኋላ በ1993 ዓ.ም ለህክምና ወደ አዲስ አበባ መጥተው፣ በአቶ ስዩም መስፍን አማካኝነት ጦር ኃይሎች ሆስፒታል ለ3 ወራት ተኝተው ከታከሙ በኋላ “አንተ ወታደር አይደለህም” ተብለው ከሆስፒታል እንዲወጡ በመደረጋቸው፣ ወደ ትውልድ ቀዬአቸው መመለሳቸውን ልጃቸው ያስታውሳሉ፡፡ ከዚያ በኋላም ቢሆን ወደ አዲስ አበባና መቀሌ በመመላለስ፣ የታጋይነታቸውና የህወሓት መስራችነታቸው ጉዳይ እውቅና አግኝቶ፣ እንደ ማንኛውም ታጋይ ድጋፍና እንክብካቤ እንዲደረግላቸው በተደጋጋሚ ከመጠየቅ ወደ ኋላ ባይሉም ሰሚ ጆሮ አለማግኘታቸውን ቤተሰቦቻቸው ያስረዳሉ፡፡
በ1999 ዓ.ም በከፍተኛ የአንጀት ህመም መሰቃየታቸውንና ተገቢውን ህክምና ሊያገኙ ባለመቻላቸው ወደ ዋልድባ ገዳም ገብተው የመነኮሱ ሲሆን ከአንድ አመት በኋላም ህይወታቸው ማለፉን ልጃቸው ገልጸዋል፡፡  በህወሓት በኩል ለአንድ ጀግና ታጋይ የሚደረገው ክብር ሁሉ ቢነፈጋቸውም ከ1ሺህ በላይ የሚሆን የአካባቢው ህዝብ በራሱ ተነሳሽነት፣ በክብር ባንዲራ ወጥቶላቸው፣ በታላቅ ሥነ ሥርዓት በመነኮሱበት የዋልድባ ገዳም እንደቀበሯቸው ቤተሰቦቻቸው ይናገራሉ፡፡           
የህወሓት አንጋፋ ታጋይና አመራር የነበሩት አቶ ገብሩ አስራት ስለታጋይ አብጠው ተጠይቀው፤ግለሰቡን በአካል ባያውቋቸውም ከህወሓት መስራቾች አንዱ መሆናቸውን እንደሚያውቁ ገልፀው፣ከህወሓት ጠንሳሽ አቶ ገሠሠ አየለ (ስሁል) ጋርም ዝምድና እንዳላቸው አውቃለሁ ብለዋል፡፡
 ህወሓት ታሪክ ለሰሩ የቀደሙ ታጋዮች ተገቢውን ክብር የማይሰጠው፣ ግለሰቦችን እንደ አገልግሎት እቃ ብቻ ስለሚመለከት ነው የሚሉት አቶ ገብሩ፤ አንድ ሰው ከእነሱ በሃሳብ ከተለየ ያበረከተው አስተዋፅኦ ሁሉ ገደል ይገባና በጠላትነት ይፈረጃል ይላሉ፡፡ የግለሰቡን ታሪካዊ ገድልም ለማስታወስ አይሹም ብለዋል- አንጋፋው የህወሓት ታጋይ አቶ ገብሩ፡፡ “እኔም ሆንኩ የሃሳብ ልዩነት ፈጥረን ከህወሓት የወጣን ሰዎች፣ እስከ ትግሉ ፍፃሜ ድረስም ሆነ ከዚያ በኋላ ለኢትዮጵያ ህዝብ ብዙ ታግለናል” ያሉት አቶ ገብሩ፤ ከህወሓት በሃሳብ ስንለይ ግን በአንድ ድምፅ እንደ ጠላትና ከሃዲ ተደርገን ነው የተፈረጅነው፡፡ ምናልባት አቶ አብጠው (ሚካኤል) ጉዳይም ተመሳሳይ ሊሆን ይችላል፤ ሲሉ ግምታቸውን ተናግረዋል፡፡                        
ነሐሴ 1 ቀን 2002 ዓ.ም በወጣው የአዲስ አድማስ ዕትም፣ “ከህወሓት መስራቾች አንዱ በመነኮሱበት ገዳም አረፉ” በሚል ርዕስ የታጋይ አብጠው ታከለን ዜና ዕረፍት መዘገባችን  ይታወሳል፡፡                 

Read 6245 times